giziew.org

እንኳን ደህና መጡ

መጽሔት የማሳተምና የማስቀጠል ዓላማው ከውስጣቸው ያልወጣው ጥቂት የቀድሞው ፓሮሲያ መጽሔት አዘጋጆች ሥራውን እንደገና ዐቀዱ …

ታሪክ

ጊዜው መጽሔት ከዚህ በፊት ፓሮሲያ ይባል የነበረው መጽሔት ቀጣይ ነው። ፓሮሲያ መታተም የጀመረው በታህሣሥ ወር 1989 ዓም በፍልውሃ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን በሚገኝ አንድ ክፍል ውስጥ በወጣቶች አነሳሽነት ነበር። በወቅቱ የማተሚያ ቤት ወጪን መሸፈን ባለመቻሉ የመጽሔቱ ረቂቅ ከተተየበ በኋላ በስቴንስል እያንዳንዱን ገጽ በማተም ነበር ሥራው የጀመረው። በቀጣይ ገጾችን እየቆረጡ ማዘጋጀትና በስቴፕለር ሁለት ቦታ በመምታት ሥራ ውስጥ ሁሉ የተሳተፉት በፈቃደኝነት የተሠማሩ ወጣቶች ነበሩ። ሥራው እጅግ አድካሚና በርካታ ቀናት የወሰደ፤ ቀንም ማታም ተሠርቶ የተጠናቀቀ ነበር። ወቅቱ የገና በዓል የሚከበርበት እንደመሆኑ የመጀመሪያው ዕትም ገዢ ርዕስ “… የሰላም አለቃ” የሚል ሲሆን መጽሔቱም ለምዕመናን በነጻ ነበር የታደለው።

 

በዚያን ዘመን በመጽሔት ደረጃ የሚታተምና ለሕዝብ የሚሥራጭ ጽሁፍ ባለመኖሩ ወጣቶች ይህንን ሃሳብ ለመተግበር በርካታ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። የተለያዩ የመጽሔት ሥራ ለመተግበር የተካሄዱ ውጥኖችም ነበሩ። አንዳንዶቹ እስከ ምሥረታ ድረስ ሄደው ሲጨናገፉ ሌሎች ደግሞ ገና ከእንጭጩ ተቀጭተዋል።

መጽሔት የማተም ሥራውን ፈታኝና አስቸጋሪ ያደረገው የገንዘብ ዕጦት ብቻ አልነበረም። ጽሁፍ ማሰባሰብ፣ ተከታታይ ጽሁፍ የሚጽፉ ዓምደኞችና መደበኛ መጣጥፎችን የሚያዘጋጁ ጸሐፍት አለማግኘት፣ ቢገኙም በሚፈለገው የጊዜ ገደብ ጽሁፎቻቸውን አለማድረስ፣ ጽሁፎችን ለማቀናበርና የመጽሔቱን ቅርጽ ለማስያዝ ብቃት ያለው ባለሙያ እንደሚፈለገው አለመኖር፣ የነበሩትም ከጊዜ መጣበብ የተነሳ ሥራውን በተፈለገበት ፍጥነት ለማጠናቀቅ አለመቻል፣ ለኅትመት የሚወጣውን ወጪ ለመተካት የሚያስችል የተቀናጀ የስርጭት ሥርዓት አለመዘርጋት፣ ሥራው በተቀጣሪ ሳይሆን በፈቃዳቸው በተነሳሱ ወጣቶች መሠራቱ፣ ጥቂቶቹ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው።

 

እነዚህን ሁሉ ተግዳሮቶች በመጋፈጥ ፓሮሲያ መጽሔት ከተጀመረበት የA5 መጠን በማደግ ወደ ሙሉ መጽሔት (A4) አድጋ ነበር። በቀጣይም የወረቀቱን ጥራት የላቀ እንዲሆን በማሰብ መጠኑ ወደ ዱሮው ተመለሰ። በአዲስ መልክ መታተም የጀመረው መጽሔት በቀላሉ በኪስ ውስጥ የሚገባና በላብ ሽፋኑ እንዳይበላሽ ተደርጎ በጥራት የሚታተም ነበር። የሽፋኑ ባለቀለም መሆን፣ የውስጥ ዲዛይኑ፣ በአጠቃላይ ጥራቱ በላቀ ሁኔታ ተጠብቆ ለዓመታት በዚህ ሁኔታ ሲታተም ቆይቷል።

ሆኖም ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የመጽሔቱ ኅትመት በመሃል ተቋረጠ። እንደገና ለማስጀመር የተካሄዱ ሙከራዎችም ሳይሳኩ ቀረ። መጽሔቷ የማትመለስ እስኪመስል ከዕይታ ጠፋች። በዚህ ወቅት ነበር የመጽሔቷን ስም የያዘ ሌላ አገልግሎት የተጀመረው። ይህም አገልግሎት የፓሮሲያ መጽሔት ስም ከዓላማው ጋር የሚሄድ ሆኖ ስላገኘው አገልግሎቱን በዚያው ሰየመው። “ፓሮሲያ” የሚለው ቃል የግሪክ (የፅርዕ) ሲሆን ቀለል ያለው ትርጉሙ “ጌታ ዳግም ይመጣል” የሚል ነው።

 

መጽሔት የማሳተምና የማስቀጠል ዓላማው ከውስጣቸው ያልወጣው ጥቂት የቀድሞው ፓሮሲያ መጽሔት አዘጋጆች ሥራውን እንደገና ዐቀዱ፤ ወቅቱም ሰኔ 2010ዓም ነበር። በውይይቱ ላይ ዋናው አጀንዳ ሆኖ የቀረበው “ፓሮሲያ ለምን ከሸፈች?” የሚል ግምገማ ማካሄድ ነበር፡፡ በወቅቱም ከሁሉም ተግዳሮቶች ልቆ በዋንኛነት የወጣው ወጪው ጉዳይ ነበር። ምክንያቱም ማተሚያ ቤቶቹ ለማተም ከሚያወጡት በትንሹ ከዕጥፍ በላይ ያተርፋሉ። እዚያ ወጪ ላይ ትርፍ አስቦ፣ ሸጦ፣ መጽሔቱን ማስቀጠል የማይታሰብ እንደሆነ ለመረዳት ተቻለ። ስለዚህ የራሳችን ማተሚያ ቤት ሳይኖረን ወደ መጽሔት ኅትመት ድጋሚ መግባት ለተመሳሳይ ኪሣራ የሚዳርግ እንደሆነ ውሳኔ ተደረሰበት።

ማተሚያ ቤቱን ለመመሥረት የሚያስፈልጉ ወጪዎችን አስመልክቶ የተደረገው ጥናት ያመላከተው ነገር የመነሻ ወጪው እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ነው። በመሆኑም ይህንን ለማሳካት ከምንም ተነስቶ ማተሚያ ቤት ለመመሥረት ገንዘብ ማሰባሰቡ ለሰሚው አሳማኝ ያልሆነና አድካሚ አካሄድ ሆኖ ስለተገኘ መጽሔት በማተም ሥራ ውስጥ መግባትና በተጓዳኝ ማተሚያ ቤቱን መመሥረት እንዲሠራበት እንደ አማራጭ ቀርቦ ተወሰነ።

ከዚህ ውሳኔ በኋላ ፈታኙ ጉዳይ የመጽሔቱ ስም ማን ይሁን የሚል ነበር። ፓሮሲያ በሕዝቡ ዘንድ የሠረጸና የሚታወቅ በመሆኑ በዚያው እንቀጥል የሚለው አንዱ ሃሳብ ነበር። ሌላው ደግሞ ፓሮሲያ አሁን ሌላ አገልግሎት በመሆኑ ከዚያ ጋር ስሙ ይወዛገባል፣ ስለዚህ በአዲስ ስም መጀመር ነው ያለበት የሚል ነበር። ሁለተኛው ሃሳብ አሳማኝ ሆኖ በመገኘቱ ስም ማሰባሰብ ተጀመረ። ከተሰበሰቡት 22 ስሞች “ጊዜው” የሚለው የላቀ ብልጫ በማግኘቱ ከመስከረም 2010 ዓም ጀምሮ ጊዜው መጽሔት መታተም ጀመረ።

የጌታችንና የመድኃኒታችን ክርስቶስ የምድር አገልግሎት ወደመጠናቀቂያው ሲቃረብ ደቀመዛሙርት ወደ እርሱ ቀርበው ስለ ዳግም ምፅዓቱና ስለ ፍጻሜ ዓለም ጠይቀውት ነበር። መድኃኒዓለምም ሁኔታውን በዝርዝር ካስረዳቸው በኋላ የምፅዓቱን ቀንና ሰዓት ማንም እንደማያውቅ በመንገር ይህንን እንዲያደርጉ አሳሰባቸው፤ “ስለዚህ ጊዜው መቼ እንደሚሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፣ ጸልዩም” (ማርቆስ 13፡33)።

ይህንን የጌታ ቃል መሠረት በማድረግ እና የዘመኑን ፍጻሜ በመረዳት የመጽሔታችንን ስም “ጊዜው” በማለት ሰይመን ለንባብ መብቃት ችላለች። ለዚህ ሁሉ ስብሃት ለአብ፤ ስብሃት ለወልድ፤ ስብሃት ለመንፈስ ቅዱስ ይሁን! አሜን!

የጊዜው መጽሔት ቅርጽ

ጊዜው መጽሔት በአገር ውስጥና በውጪ የምትሰራጭ ሲሆን በውስጧ ስምንት መደበኛ ዓምዶችን ያካተተች ነች። እነዚህም፤

የጥሞና መልዕክት አጠር ያለ፤ አንባቢያን በጸጥታና በርጋታ ሊያሰላስሉበት የሚገባ ተከታታይነት ያለው መልዕክት የሚቀርብበት፤

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፤ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕስ ወይም ክፍል ለጥናት በመውሰድ በተከታታይ ጥልቅ ትንታኔ የሚሰጥበት፤

ለጤናችን፤ “ሰውነታችን የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ” የመሆኑ ምስጢርና ከዚያ ጋር በተያያዘ አኗኗራችንና ጤና አጠባበቃችን ከአምልኳችን ጋር እየተመጋገበ የሚሄድ መሆኑ የሚዳሰስበት፤

“አንባቢው ያስተውል” ጌታ ክርስቶስ ዳግም የመምጣቱን ሁኔታ ሲያስረዳ ምልክቶቹን በምናይበት ጊዜ “አንባቢው ያስተውል” እንዳለው፤ “ጊዜው” መድረሱን የሚያመለክቱ፤ የትንቢት ፍጻሜዎችንና የዘመኑን ሁኔታ የሚያገናዝቡ የዜና ዘገባዎች የሚቀርቡበት፤

ቤተሰብ፤ በኤድን ገነት በእግዚአብሔር የተመሠረቱት ሁለት ተቋማት ሰንበትና ቤተሰብ ከመሆናቸው አኳያ የቤተሰብ አመሠራረትና አመራር ከመንፈሣዊ ህይወታችን ጋር ያለው ቁርኝት የሚዳሰስበትና ትንታኔ የሚሰጥበት፤

ይህ ነው ታሪኬ፤ ሰዎች እንዴት ክርስቶስን ወደማወቅ ሕይወት እንደመጡ፣ ሕይወታቸው እንዴት እንደተለወጠ፣ እግዚአብሔርን ለመከተል ውሳኔ ሲያደርጉ ከጠላት የመጣባቸው ጥቃት ምን እንደነበርና እንዴት እንደተቋቋሙት፤ እስካሁን በእምነት የመቆየታቸውን ምሥጢር ምን እንደሆነ የሚቀርብበት፤

የመዳን ታሪክ በሰማይ የተጀመረው ታላቁ ውዝግብ እንዴት ወደ ምድር እንደደረሰና የሰውን ልጅ ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳስገባው፤ እንዲሁም ይህ ውዝግብ በምን መልኩ እንደሚጠናቀቅ በተከታታይ የሚተነተንበት፤

ጥያቄና መልስ፤ ከዝግጅታችን ተሳታፊዎች የሚደርሱንን ማንኛውንም መንፈሣዊ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሙከራ የምናደርግበት ዓምድ ነው። ያሏችሁን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች በአድራሻችን ላኩልን፤ እናስተናግዳለን።

ከዚህ ሌላ በመደበኛ ዕትም የማይወጡ ጉዳዮች ሲኖሩ ዓምዶቹ በሙሉ ቀርተው በልዩ ዕትም የሚዳሰሱ ይሆናል።

ስለዚህ ጊዜው መጽሔትን በዚህ መልኩ በማቀናበር ለንባብ አድርሰናልና ይህችን መጽሔት ለሕይወታችን መታደሻ ያድርግልን።

መልካም ንባብ።

ጊዜው መጽሔት አዘጋጆች!