ትንቢቱ የተነገረው ከ500 ዓመት በፊት ነበር፤ እንዲህ የሚለው “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” (ዘካርያስ 9፡9)። ሆኖም ይህ “ደስ ይበልሽ” ተብሎ የተተነበየ የደስታ፣ የሆሳዕና መዝሙር በልቅሶ ተቀየረ!
ጌታችንና መድኃኒታችን የማርታና የማርያምን ወንድም አልዓዛርን ከሞት ባስነሳባት ጊዜ የሁሉም ትኩረት ከበፊቱ በበለጠ በእርሱ ላይ ሆነ። የካህናት አለቆችና ጸረ-መድኃኒዓለም የነበሩት ሁሉ በሽብር ተሞሉ፤ አልዓዛር ከሞተ ከአራት ቀን በኋላ እንዴት ሊነሳ ቻለ? ምን ዓይነት ኃይል ቢኖረው ነው ይህንን ማድረግ የቻለው? ይህንን መደበቅና ማስተባበል አንችልም፤ እርምጃ መውሰድ አለብን፤ አልዓዛርን መግደል አለብን፤ አልዓዛርንም ብቻ ሳይሆን ራሱን ክርስቶስን ማስወገድ አለብን በማለት ተማከሩ (ዮሐ. 11፡53፤ 12፡10)።
ጌታችን ክርስቶስ አልዓዛርን ከሞት ካስነሳ በኋላ ከቢታኒያ ወደ ኤፍሬም ከተማ ሔደ፤ ከዚያም ፋሲካ ከመሆኑ ከስድስት ቀን በፊት ወደ ቢታኒያ ተመልሶ መጣ። በዚያም የእራት ግብዣ በተደረገለት ጊዜ ማርያም “እጅግ የከበረ የጥሩ ናርዶስ ሽቱ ንጥር ወስዳ የኢየሱስን እግር ቀባች፤ በጠጕርዋም እግሩን አበሰች፤ ቤቱም ከናርዶስ ሽቱ ሞላ” (ዮሐንስ 12፡3)። በሁኔታው ያልተደሰተው ይሁዳ ሽቶው ተሸጦ ለድሆች መርጃ መዋል ነበረበት የሚል ተቃውሞ አቀረበ። ጌታችን ሲመልስም “ድሆችስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም አለ” (ዮሐ. 12፡8)።

በማግስቱ ግን የመሲሕን በዳዊት ዙፋን መቀመጥ የሚያበስር ከ500 ዓመታት በፊት የተተነበየ ትንቢት የሚፈጸምበት አንድ ታላቅ ትዕይንተ ሕዝብ ተካሄደ። እጅግ በርካታ ሕዝብ በአልዓዛር መነሳት ወሬውን ሰምቶ እየተደነቀ የነበረ ሲሆን ከዚያም ሌላ የፋሲካ በዓል ሊከበር ጥቂት ቀናት ስለቀሩት የሕዝቡ ቁጥር ከመጠን በላይ ነበር። ብዙ ጊዜ ራሱን በመደበቅ አገልግሎቱን ይፈጽም የነበረው ጌታችንና መድኃኒታችን አሁን ግን አንድ ያልተጠበቀ ትዕይንት እንዲሆን ፈቀደ።
“በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ ወደ እርስዋም ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፥ ፈትታችሁም አምጡት” በማለት ጌታችን ለደቀመዛሙርቱ ትዕዛዝ ሰጠ (ሉቃስ 19፡30)። ውርንጫዋ መጥታ እንደተቀመጠባት የአካባቢው ድባብ ተቀየረ። ብርና ወርቅ ሁሉ የእርሱ የሆነው የፍጥረተዓለም ገዢ፣ ወደዚህ ምድር ሲመጣ በከብቶች ግርግም ተወለደ፤ “የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ በሺህ ተራራዎች ያሉ እንስሶችም የእኔ ናቸውና” ያለው የነገሥታት ንጉሥ፣ በዳዊት ዙፋን ንግሥናን ሲቀበል በተውሶ በተገኘች አንዲት ውርንጫ ላይ ተቀመጠ (መዝ. 50፡10)።
እስከዚህ ቀን ድረስ በእግሩ በየቦታው ሲጓዝ የነበረው ጌታ አሁን ግን ሌላ መጓጓዣ ተጠቀመ፤ ውርንጫዋን በመምራት ፊት አውራሪው ደግሞ አልዓዛር ነበር። በሁኔታው ደቀመዛሙርት ተደንቀዋል። ነገርግን ሰዎች በመሰባሰብ ደስታቸውን መግለጽ ሲጀምሩ ትዕይንቱ እየተቀየረ መጣ። ወዲያውም የሕዝቡ ቁጥር እየጨመረ ብቻ ሳይሆን ሁኔታውም ሌላ መልክ ያዘ። እጅግ በርካታ ሰዎች ልብሳቸውን፣ የዛፍ ቅጠሎችን እና የዘንባባ ዝንጣፊን መንገዱ ላይ እያነጠፉ በዝማሬና በዕልልታ እንዲህ እያሉ ተከተሉት፤ “ሆሣዕና ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር ወንጉሦሙ ለእስራኤል”።
የመቶ ዓመታት ትንቢትን በዓይናቸው ሲፈጸም ስላዩ ነበር “ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው” በማለት የጮኹት። ተስፋ የተደረገበት መሢሕ፣ በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጠው ጌታ፣ ከሮም ቀንበር እስራኤልን ነጻ የሚያወጣው ታዳጊ፣ ኢየሩሳሌምን መቀመጫው አድርጎ በዳዊት ዙፋን ላይ የሚነግሠው የተባረከው የእስራኤል ንጉሥ። “በጌታ ስም የምትመጣ የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት፤ ሆሣዕና በአርያም” በማለት አስጮኻቸው (ማር. 11፡10)።
ከዚህ ስብስብ ውስጥ አልዓዛርን ከሙታን ሲያስነሳው ዓይተው የመሰከሩ ነበሩ፤ ዝናውንም በየአገሩ የበተኑ፣ ያንንም ሰምተው ስብስቡን የተቀላቀሉ በዚህ ትዕይንተ ሕዝብ ውስጥ ነበሩ። ከአጋንንት ኃይል ነጻ ያወጣቸው በትዕይንቱ ውስጥ ነበሩ፤ ከእነርሱም ሌላ የዓይን ብርሃናቸው የተመለሰላቸው፤ ጆሯቸው የተከፈተላቸው፤ የታሠረው ምላሳቸው የተፈታላቸው፤ ለዓመታት ሽባ ሆነው አሁን ግን እንደልባቸው መንቀሳቀስ የተቻላቸው፤ በማኅበራዊ ፈቀቅታ እና በኳራንቲን ተጽዕኖ “እርኩስ ነኝ” እያሉ ከሁሉ ተለይተው የዳዊት ልጅ አንጽቷቸው ወደ ሕዝብ የተቀላቀሉ፤ መጽናናትን የተቀበሉ መበለቶችና ወላጅ አልባዎች፤ ኃጢአታቸው የተሰረየላቸው፤ ከመናቅ ወደ ክብር፤ ከሐዘን ወደ ሐሴት፤ ከውርደት ወደ ከፍታ፤ ከሞት ወደ ሕይወት የመጡና ሌሎችም እጅግ በርካታ ሰዎች ነበሩ።
እነዚህ ማንም መካድ በማይችልበት መንገድ የጌታችንን አዳኝነትና ኃያልነት የሚመሰክሩ ሆነው በቦታው መገኘታቸው ብዙዎችን እንዲያምኑ ሲያደርጋቸው፤ በፍርሃት ያራዳቸውና ሌላ ሤራ እንዲወጥኑ ያደረጋቸውም ነበሩ። አንዳንድ የጨነቃቸው ፈሪሣውያን ግን “መምህር ሆይ፥ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው” ሲሉት ጌታም “እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ አላቸው” (ሉቃስ 19፡ 39፣40)። ይህንን ትዕይንትና የሕዝብ ማዕበል በዘመኑ በነበረ ዓድማ በታኝም ሆነ ሌላ ኃይል መቋቋም እንደማይችሉ የተረዱ ግን ዕልልታውን ወደ ሐዘን ለመቀየር ቆርጠው ተነሱ።

ጉዞው በየመንገዱ በርካታዎችን እየጨመረ ወደ ኢየሩሳሌም ሲቀጥል የካህናት አለቆችና ፈሪሣውያን በፍጥነት ወደ ውሳኔ የሚያደርሳቸውን ሤራ ማዋቀር ጀመሩ። “አንድ ስንኳ ልታደርጉ እንዳይቻላችሁ ታያላችሁን? እነሆ፥ ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል ተባባሉ” (ዮሐ. 12፡19)። በወቅቱ በነበራቸው ማኅበራዊ መስተጋብር ጉዳዩ በፍጥነት የአይሁድ ሸንጎ አባላት ዘንድ እንዲደርስ ተደረገ። አልዓዛርን ከሞት በማስነሳቱ አልዓዛርንም ጌታችንንም ለመግደል የተወጠነው ሤራ ተግባራዊ መሆን እንዳለበት መመሪያ ተላለፈ።
የትዕይንቱ ማብቂያ ወደሆነው የኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ ሲደርስ ሁኔታዎች መቀየር ጀመሩ። በዕልልታና በዝማሬ የተከተለው ሕዝብ ፈጽሞ ያልጠበቀውን ነገር ከጌታችን ፊት ላይ ተመለከተ። ኢየሩሳሌም ንጉሧን ለመቀበል ዝግጅት ብቻ ሳይሆን ፍላጎትም አልነበራትም። ወደ ኢየሩሣሌም “ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት” (ሉቃስ 19፡41)። ያለቀሰው በፊቱ ቀራንዮ ስለታየው፤ ወይም የሚደርስበት ስቃይና መከራ አስጨንቆት አልነበረም።
ያለቀሰው “እንዲህ እያለ” ነበር፦ “ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል። ወራት ይመጣብሻልና፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና” (ሉቃስ 19፡42 – 44)።
የመጎብኘቷ ዘመን እንዲመጣ እጅግ ብዙዎች ተመኝተዋል፤ ቃትተዋል፤ አልቅሰዋል። ኢየሩሳሌም ግን በአምላኳ ላይ ማመጿን አላቆመችም፤ እንዲያውም ለበርካታ ዓመታት ይህንን አቃልላ ስትመለከት ኖራለች። ኃጢአቷ ከፍቶ “ፈረሶቻቸውም ከነብር ይልቅ ፈጣን፤ ከማታም ተኵላ ይልቅ ጨካኝ፤ ለመብልም እንደሚቸኵል ንስር” የሆኑት ባቢሎናውያን ከሩቅ መጥተው ከተማዋንና ቤተመቅደሱን ከማፍረሳቸው በፊት ነቢያት እያለቀሱ የተናገሩላትን ትንቢት ናቀች (ዕንባቆም 1፡8)። ይልቁንም ነቢያቶቿን ገደለች፤ አሳደደች። በባቢሎን ከፈረሰች በኋላ እንደገና እንድትሠራ እጅግ በርካታዎች ለፍተዋል፤ እነዘሩባቤልና ዕዝራ መከራ አይተዋል፤ እነ ነህምያ አልቅሰዋል።

አሁን ደግሞ ለምህረት የተዘረጋውን እጁን አልቀበልም ስላለችው ከተማ ጌታችን አለቀሰ፤ ዓመጸኝነቷ የሚያመጣባትን ውድመት አይቶ አለቀሰ፤ ዕብሪተኛነቷ የሚያስከትልባትን ጥፋት አሻግሮ ተመልክቶ አለቀሰ፤ የእግዚአብሔርን ልጅ፤ የዓለምን መድኃኒት አልቀበልም በማለቷ አለቀሰ፤ ከዚህ ሌላ አንዳችም መዳኛ እንደሌላት ዓይቶ አለቀሰ፤ ሆሣዕና በለቅሶ ተቀየረ!
ዓመጸኛዋ ኢየሩሳሌም ጌታዋን ሰቀለች፤ ቀጥላም ጻድቁን እስጢፋኖስን ወገረች፤ ሃዋሪያትን አሳደደች፤ በግፍ ላይ ግፍን አከማቸች፤ ፈውስ እስከማይገኝላት ድረስ ፈጣሪዋን ካደች፤ ምህረትን ናቀች። ዓመታትን ጠብቆ የተናቀው ምህረት ፍትሕን ወለደ። ኢየሩሣሌም በአረመኔው ሮም ወደመች፤ መቅደሱም ዓመድ ሆነ።
በሰሙነ ሕማማት፣ በስቅለትና በፋሲካ የጌታችንና የመድኃኒታችንን መሐሪነት ስናስብ ሆሳዕና ልንል እንችላለን፤ ተገቢም ነው። ነገርግን ሆሳዕናው ወደ ልቅሶ የሚቀየርበት ጊዜ ደርሶ ይሆን? ትኩረት ሰጥተን እናስብ። የእግዚአብሔር ምህረት ሁልጊዜ ያለገደብ የሚቀጥል አድርገን በመገመት አቅልለን እንዳናየው የሆሳዕና ትዕይንት ያስተምረናል። ምህረት የሚያበቃበት ጊዜ ይመጣል። ፍትሕ ቦታውን የሚወስድበት ቀን አለ። ጻድቅ ፈራጅ የሆነው አምላካችን ለዓለማችን፣ ለአገራችን፣ ለከተማችን፣ ለሕዝባችን፣ ለራሳችን እንደ ኢየሩሳሌም ሳያለቅስልን ምህረቱን አሁን እንቀበልና በመንገዱ እንሂድ።
“እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ” (ዮሐ. 12፡32)። ጌታችንና መድኃኒታችን አሁንም ወደ እርሱ ሊስበን ይፈልጋል፤ ይጥራል። በፍቅር ውስጥ ማስገደድ ስለሌለ ፈጽሞ አያስገድድም። ሆሳዕና ወደ ለቅሶ ሳይቀየር የምህረት ጥሪውን እንስማ፤ ንሰሃ እንግባ፤ ለእርሱም እንታዘዝ።
ጥበበሥላሴ መንግሥቱ










