giziew.org

አሜሪካ በትንቢት

ሌላም አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፥ የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ ሁለት ቀንዶችም ነበሩት ...
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

በቅርቡ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ሰው ሰራሽ አስተውሎን ወይም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም የሰው ልጅ ከእንስሳት ጋር መነጋገር እንደሚችል ነው። ይህ ማለት ግን በቅርቡ የሰው ልጅ ከበሬ ጋር ቁጭ ብሎ ስለ ዓለም ሰላም፣ ስለ ኑሮ ውድነት፣ ስለ መካከለኛው ምስራቅ ጦርነት፣ ወዘተ ይነጋገራል ማለት አይደለም።

በዘመናት ሁሉ ከእንስሳት ጋር ቅርርብ ያላቸውና አርቢዎች የጋማ፣ የቤት እንስሳና ከብቶቻቸውን ሲያናገሩና ስሜታቸውን ለመረዳት ሲሞክሩ የኖሩ ቢሆንም ዘመናዊው ሳይንስ ግን የሰው ሰራሽ አስተውሎን በመጠቀም፣ የእንስሳትን የተለያዩ ድምጾች በማቀነባበር እንስሳቱ  በሚያወጡት ድምጽ ምን ለማለት ፈልገው እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል ነው የሚለው።

መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ስለሚናገሩ አውሬዎች በተለይ በራዕይ መጽሐፍ ጠቅሶ እናነባለን። እነዚህ እንስሳት አፋቸውን ከፍተው በሚናገሩበት ጊዜ ከማንነታቸው ወይም ተገማች ከሆነው ባሕርያቸው ውጪ የሆነ ነገር ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።

ለምሳሌ በራዕይ 13 ሁለት አውሬዎችን ይጠቅስና በተለይ ሁለተኛውን አውሬ በተመለከተ ዮሐንስ ሲናገር በግ ይመስላል ካለ በኋላ ፍጹም ባልተጠበቀ ሁኔታ “እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር” ይላል (ራዕይ 13፡11)።

ለመሆኑ ይህ አውሬ ማነው? እንደ ዘንዶ መናገሩስ ምንን ነው የሚያመለክተው? እነዚህን ጥያቄዎች ከመመለሳችን በፊት ግን በመጽሐፍ ቅዱስ የትንቢት ምሳሌ አፈታት መሠረት “አውሬ” ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ የግድ ይላል። ከዚያ ሲቀጥል ሌሎቹንም እንዲሁ በመተንተን እግዚአብሔር እንድናውቅ የፈለገውን መልዕክት መረዳት አለብን።

በሌሎች ጉዳዮች ተይዘን ለተወሰኑ ጊዜያት ተቋርጦ የነበረው መጽሔታችን በዚህኛው ዕትሙ ከላይ የጠቀስናቸውን ጉዳዮች የሚያብራራ ይሆናል። “አሜሪካ፡ እንደ ዘንዶ የሚናገር በግ” የሚል ርዕስ በሰጠነው በዚህ ዕትማችን አሜሪካ በትንቢት እና በአፈጻጸሙ ላይ ያላትን ተሣትፎ እናብራራለን። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ዓምዳችን በስፋት የተዳሰሰ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ በጥያቄና መልስ ዓምዳችን ይህንኑ “አሜሪካ በእርግጥ በትንቢት የተጠቀሰች አገር ናት?” በሚል መሪ ርዕስ በርካታ ጥያቄዎችን እያነሳን መልሶችን ሰጥተናል። አንባቢው ያስተውል በሚለው ዓምድ ሥር “እንደ ዘንዶ” በሚል መነሻ ሃሳብና ርዕስ ከገዢው ርዕስ ጋር የተያያዘ አጠር ያለ መረጃ ተቀናብሯል።

“የሥጋ ደዌ ያልበገረው ፍቅር” በሚል ርዕስ የተወዳጁን ዶ/ር ሮናልድ ኬዘንን ታሪክ አቅርበናል። ዶ/ር ኬዘን ከሕክምና ሙያ ባሻገር ልዩ የሙዚቃ መክሊት የነበረውና ይህንኑ መክሊቱን በተለይ በፍልውሃ ቤተክርስቲያን ብዙዎች የሚያስታውሱት በመሆኑ ይህ ነው ታሪኬ ዓምድ ይህንን ታላቅ የአገርና የቤተክርስቲያን ባለውለታ ይዘክራል።

በቤተሰብ ዓምድ ደግሞ “የትዳር ሥንክሳር” በሚል ርዕስ ስለ ትዳርና አብረውት ስለሚመጡ ተግዳሮቶች እጥር ምጥን ያለች ጥልቅና ትምህርት ሰጪ ጽሑፍ ቀርቧል።

በኤድን ገነት የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን ያሳተውና ዓለምን ሁሉ ለውድቀት የዳረገው “የቀደመው እባብ፣ ዲያቢሎስ ሰይጣን” ማንነት የመዳን ታሪክ ዓምዳችን በስፋት ተንትኖታል።

በዚህ መደበኛ ዕትማችን ከተለመዱት ዓምዶች መካከል የጥሞና ጊዜ ዓምድ በዚህ ዕትም እንደማይኖር ስንገልጽ ለአንባቢዎቻችን በቅድሚያ ይቅርታ እየጠየቅን ነው።

ይህችን መጽሔት ካነበቡ በኋላ ጥያቄ ወይም ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲደረግበት የሚፈልጉት ጉዳይ ካለ በአድራሻችን በአንዱ ሊያገኙን ይችላሉ።

መልካም ንባብ!

አዘጋጆቹ


የቅርብ ጽሁፎች

በ Facebook ይከተሉን

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *