ከተቋቋመ ወደ 160 ዓመታት ያሳለፈውና ከሚያመርታቸው ምርቶች መካከል የሕጻናት ዱቄት ወተት አንዱ የሆነው ኔስል የተባለው ኩባንያ በአንድ ወቅት የሚዲያ ትኩረት የሳበ ክስ ቀርቦበት ነበር። ይኸውም የሚያመርተውን የሕጻናት ወተት ወደ 3ኛው ዓለም አገራት እንደ ነርስ በለበሱ የሽያጭ ባለሙያዎች እንዲሰራጭ በማድረግ ሕጻናትን ለከፋ አደጋ አጋልጧል የሚል ነው። እነዚህ የሽያጭ ሰዎች ወደየቤቱ በመሄድ የዱቄት ወተቱን ጥቅም አሳማኝ በሆነ መንገድ በማቅረብ፣ ለእናቶችም በነጻ በመስጠት እንዲሞክሩት ያደርጋሉ። በአብዛኛው ጡት በማጥባት ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት እናቶች የተነገራቸውን በማመን ልጆቻቸውን የጠቀሙ መስሏቸው የዱቄት ወተቱን በመስጠታቸው ችግር ውስጥ ይገባሉ።

አንዱ ችግር እናቶቹ ንጹህ ውሃ በማይገኝበት አካባቢ የሚኖሩ በመሆናቸው ዱቄቱን የሚበጠብጡበት ውሃ ልጆቻቸውን ለከፋ ሕመም መዳረጉ ነው። ሁለተኛው ሕጻናቱ የዱቄቱን ወተት ከለመዱ በኋላ የእናታቸውን ጡት በመተው የዱቄት ወተቱ ጥገኛ መሆናቸው ነው። መጀመሪያ የተሰጣቸው ነጻ ጣሳ ዱቄት ካለቀ በኋላ እናቶቹ ሌላ ለመግዛት ውድ ይሆንባቸዋል። ጡት ወደማጥባት እንዳይመለሱ ሕጻናቱ ሳይጠቡ በቆዩበት ጊዜ ጡታቸው እየደረቀ ከመሄዱ ባሻገር ሕጻናቱ የዱቄት ወተት ስለለመዱ ጡት ወደ መጥባት በፍጹም መመለስ የማይፈልጉ ሆኑ። በመሆኑም ለሕጻናት ዕድገትና መፋፋት እንዲጠቅም በሚል ሽፋን ሲከፋፈል የነበረው ወተት ሕጻናቱን ለመቀንጨር አንዳንዶቹም ለሞት ዳርጓቸዋል።
መልካም መስለው በሚቀርቡ ነገሮች መታለል ያልተለመደ ነገር አይደለም፤ መልካም የተባለውም መልኩን ቀይሮ የጭቃ ጅራፉን ሲመዝና እንደ እባብ መናደፍ ሲጀምር ማስደንገጡ አይቀሬ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ መልካም መስሎ ስለጀመረና በኋላ ግን መልኩን በመቀየር ከተገመተው ውጪ ሌላ ገጽታ ስለያዘ “አውሬ” በምሳሌያዊ መልኩ ይናገራል።
“ሌላም አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፥ የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ ሁለት ቀንዶችም ነበሩት እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር” ራዕይ 13፡11።
ነገሩ ግራ የሚያጋባ ብቻ ሳይሆን የሚያስፈራም ነው። የበግ የሚመስሉ ቀንዶች ያሉትና በግ ነው ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ እንስሳ በሚገርም ሁኔታ ማንነቱ ተቀይሮ “እንደ ዘንዶ” መናገር ይጀምራል። ይህ ከአንድ ጽንፍ ወደሌላው የተፈናጠረው “እንስሳ” በግልጽ የተቀመጠ ነው – ለስላሳና የዋህ ከሚባል በግነት እሣት ወደሚተፋ አስፈሪ ዘንዶነት! ይህንን ትንቢታዊ ምሳሌ ለመረዳት “አውሬ”፣ “ከምድር መውጣት”፣ “የበግ ቀንዶች” እና “ዘንዶ” የሚሉትን በዝርዝር መመልከቱ ጠቃሚ ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ተምሳሌታዊ (ምልክት) አፈታት መሠረት፤
“ዘንዶ” የሚለው ቃል በቀዳሚነት የሚያመለክተው ሰይጣንን ነው። ከዚያ ሲያልፍም በሰይጣን መሪነትና ውክልና የእርሱን ሥራ የሚፈጽሙትንም ቃሉ ያካትታል። “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ” ራዕይ 12፡9። የሚከተሉት ጥቅሶች ደግሞ ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣሉ፤ ኢሳይያስ 27፡1 እና 30፡6፤ መዝሙር 74፡13-14፤ ሕዝቅኤል 29፡3 (እዚህ ጥቅስ ላይ ፈርዖን “ዘንዶ” ተብሏል) እና ኤርምያስ 51፡34።
“አውሬ”፤ “አራተኛይቱ አውሬ በምድር ላይ አራተኛ መንግሥት ትሆናለች” ዳንኤል 7፡23። በዚህ ጥቅስ መሠረት “አውሬ” የሚለው ቃል መንግሥትን ወይም የፖለቲካ ኃይልን የሚያመለክት ነው።
በራዕይ 17፡15 ላይ “አለኝም፦ ጋለሞታይቱ የተቀመጠችባቸው ያየሃቸው ውኃዎች፥ ወገኖችና ብዙ ሰዎች አሕዛብም ቋንቋዎችም ናቸው” ይላል። ይህ ጥቅስ “ውኃዎች” የሚለውን ትንቢታዊ ምልክት ሲተነትነው “ወገኖች፣ ብዙ ሰዎች፣ አሕዛብም፣ ቋንቋዎች” በማለት በርካታ ሕዝብ የሰፈረበት ወይም በሕዝብ የተሞላ ቦታ ነው ይላል። በዳንኤል 7፡3 ላይ አራት አራዊት ከባሕር ሲወጡ ዳንኤል እንደተመለከተ ይናገራል። እነዚህም አውሬዎች ወይም መንግሥታት ከባሕር ወይም ሕዝብ በብዛት ከሰፈረበት ቦታ የወጡ ናቸው። መንግሥታቱም ባቢሎን፣ ሜዶ ፋርስ፣ ግሪክና ሮም ነበሩ (ዳንኤል 2 እና 7፡4-7)። ከዚህ ጥቅስ በመነሳት “ውኃ” ትንቢታዊ ትርጉሙ ብዙ ሕዝብ የሰፈረበትን የሚያመለክት ከሆነ በተቃራኒው “ምድር” የሚለው ቃል ብዙ ሕዝብ ያልሰፈረበትን ቦታ የሚያመለክት ነው በሚለው መተርጎም ይቻላል። ስለዚህ በግ የሚመስለው አውሬ ከምድር መውጣቱ ይህ መንግሥት የሚነሳው ሕዝብ በብዛት ካልሰፈረበት አካባቢ ነው ለማለት እንችላለን።
“ቀንድ” የሚለው ቃል እንደ ዐውዱ በተወሰነ መልኩ ተቀራራቢ ትርጉም ያለው ቃል ነው፤ ይኸውም ኃይላትን፣ ንጉሥን፣ ብርታትን፣ ጥንካሬን የሚያመለክት ነው። ለምሳሌ ዳንኤል 7፡24 ላይ ቀንዶች ነገሥታትን (መሪዎችን) እንደሚያመለክቱ ይናገራል፤ “አሥሩም ቀንዶች ከዚያ መንግሥት የሚነሡ አሥር ነገሥታት ናቸው”። “ከምዕራብ ወገን አንድ አውራ ፍየል በምድር ሁሉ ፊት ላይ ወጣ፥ … ለፍየሉም በዓይኖቹ መካከል አንድ ታላቅ ቀንድ ነበረው … አውራውም ፍየል የግሪክ ንጉሥ ነው፤ በዓይኖቹም መካከል ያለው ታላቁ ቀንድ መጀመሪያው ንጉሥ ነው” (ዳንኤል 8፡5፣21)። “ዓይኖቼንም አንሥቼ እነሆ፥ አራት ቀንዶች አየሁ። ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረውን መልአክ፦ እነዚህ ምንድር ናቸው? አልሁት። እርሱም፦ እነዚህ ይሁዳንና እስራኤልን ኢየሩሳሌምንም የበተኑ ቀንዶች (መንግሥታት፣ ኃይላት) ናቸው ብሎ መለሰልኝ” (ዘካርያስ 1፡18፣19፤ ራዕይ 17፡12)።
ስለዚህ “ሌላም አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፥ የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ ሁለት ቀንዶችም ነበሩት እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር” የሚለውን ትንቢት በዚህ መልኩ ልንፈታው እንችላለን፤ “ሌላም አውሬ (መንግሥት) ከምድር (ሰው በብዛት ካልሰፈረበት ቦታ) ሲወጣ አየሁ፥ የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ (የመንግሥቱ መርኾዎች የሆኑ) ሁለት ቀንዶችም ነበሩት፤ እንደ ዘንዶም (እንደ ዲያቢሎስ) ይናገር ነበር” (ራዕይ 13፡11)።
ይህንን በግ የሚመስል አውሬ ማንን እንደሚያመለክት ለመረዳት ከመጽሐፍ ቅዱስና ከታሪክ ጥቂት ነገሮችን መመልከት ያስፈልጋል።
ከዚህ አውሬ በፊት በራዕይ 13 ላይ አንድ ነብር የሚስል ከባሕር የወጣ አውሬ እንዳለ እናነባለን (ራዕይ 13፡1-10)። “አንድም አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፥ በቀንዶቹም ላይ አሥር ዘውዶች በራሶቹም ላይ የስድብ ስም ነበረ። ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፥ እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች፥ አፉም እንደ አንበሳ አፍ ነበሩ። ዘንዶውም ኃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን ሰጠው” (ራዕይ 13፡1-2)።
ይህንን አውሬ ይመስላሉ ተብለው የተጠቀሱት አውሬዎች፡- አንበሳ፣ ድብ እና ነብር በዳንኤል 7፡4-8 ላይ የተጠቀሱት ናቸው። እነዚህ የዚያን ጊዜውን ዓለም የገዙ ነገሥታትም አንበሳው ባቢሎንን (612 – 539 ከልደት በፊት)፣ ድቡ ሜዶና ፋርስን (539 – 331 ከልደት በፊት)፣ ነብሩ ግሪክን (331 – 168 ከልደት በፊት)፣ አስፈሪው አውሬ ደግሞ አረመኔውን ሮም (168 ከልደት በፊት – 476 ዓም) የሚያመለክቱ ናቸው። ይኸው የመንግሥታት መዘርዝር በሌላ መልኩ በዳንኤል 2 ላይ በወርቅ፣ በብር፣ በነሐስና በብረት ተብራርቶ እናነባለን።


ከ476 ዓም ጀምሮ እስከ 538 ዓም ባሉት ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስ እንደተነበየው ሮምን ተክቶ ዓለምን የገዛ ብቸኛ ኃይል አልነበረም (ዳንኤል 2፡41-44)። ነገርግን በዳንኤል 7፡8 ላይ ከአስፈሪው አውሬ በኋላ ነቢዩ ዳንኤል አስር ቀንዶች እንደወጡና ከእነዚህም ቀንዶች መካከል ሦስቱን ቀንዶች አሸንፎ አንድ ትንሽ ቀንድ እንደወጣ ይናገራል። አሥሩ ቀንዶች የሚያመለክቱት ከሮም በኋላ የተከፋፈሉትን የአውሮጳ መንግሥታት ናቸው፤ እነዚህም በዘመኑ አጠራር ቪዚጎት የተባሉት (ስፔን)፣ አንግሎ-ሳክሰን (እንግሊዝ)፣ ፍራንክ (ፈረንሳይ)፣ አሌማኒ (ጀርመን)፣ በርገንዲያን (ስዊትዘርላንድ)፣ ሎምባርድ (ጣሊያን)፣ ሱዬቪ (ፖርቱጋል)፣ ሔሩሊ (የጠፋ መንግሥት)፣ ኦስትሮጎት (የጠፋ መንግሥት) እና ቫንዳል (የጠፋ መንግሥት) ናቸው። ሦስቱ መንግሥታት ለምን ጠፉ?

ሦስቱ ቀንዶች ሔሩሊ፣ ኦስትሮጎት እና ቫንዳል የጠፉበት ምክንያት ሃማኖታዊና ፖለቲካዊ እንደሆነ በታሪክ ይጠቀሳል። እነዚህ ሦስት መንግሥታት የክርስቶስን ባሕርይ በተመለከተ ለረጅም ጊዜ ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብተው ነበር። ይህ በታሪክ “የአርዮስ ውዝግብ” ተብሎ የሚጠራው ሲሆን ዋናው አቀንቃኝ አርዮስ የተባለ የአሌክሳንደሪያ ግብጽ የነገረመለኮት ሊቅ ነበር። በወቅቱ የሮም ቤተክርስቲያን አስተምህሮውን በምንፍቅና መድባውና አውግዛው የነበረ ሲሆን ንጉሥ ቁስጠንጢኖስ በ325ዓም በኒቂያ የቤተክርስቲያን በመጥራት ትምህርቱን እንዲወገዝ አስደረገ። አሁን ላይ ሆነን የዚያን ጊዜውን ውሳኔ ስናጠናው ጉዳዩ የክርስቶስን ባሕርይ የተመለከተ ብቻ ሳይሆን አስተምህሮን (ዶክትሪንን) በተመለከተ የመሻርም ይሁን የማጽደቅ ኃላፊነት የማነው የሚለውን በማያወላዳ ሁኔታ ያረጋገጠ ሆኖ እናገኘዋለን። የሮም ቤተክርስቲያን በዘመኑ በነበራት የፖለቲካ ድጋፍ ነገሥታትን ተጠቅማ እነዚህን መንግሥታት እንዲጠፉ ካስደረገች በኋላ አጼ ጁስቲኒያን የሮሙን ሊቀጳጳስ የክርስትና እምነት ጠባቂና “የመናፍቃን አራቂ” የሚለውን የሹመት ስም አጎናጸፋቸው።
ከአስፈሪው አውሬ በኋላ የወጣው ትንሽ ቀንድ በዚህ መልኩ ከአስሩ ቀንዶች (መንግሥታት) መካከል ሦስቱን እንደነቀላቸው ትንቢቱ ይናገራል (ዳንኤል 7፡8)። በመሆኑም ከአራተኛው አውሬ (ከሮም መንግሥት) በኋላ የተነሳና ሦስት ነገሥታትን በመንቀል በምድረ አውሮጳ ኃያል ሆኖ ለ1,260 የትንቢት ቀናት (ራዕይ 12፡6) ወይም ዓመታት የዚያን ጊዜውን ዓለም ሲገዛ የነበረው፣ በሃይማኖት ካባ ተሸፍኖ እንደ መንግሥት አውሮጳን የተቆጣጠረው የሮም ጳጳሳዊ ሥርዓት ነው (በሌላ ስሙ ጳጳሳዊ ሮም ይባላል)። ይህ ከአውሮጳ ነገሥታት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ለዘመናት ሲሠራ የነበረው ኃይልና በራዕይ 13፡1-10 ላይ ከባሕር የወጣው አውሬ አንድና ተመሳሳይ ናቸው።
ይህ ጳጳሳዊ ኃይል አውሮጳን በገናናነት ሲገዛ መቆየቱ የታሪክ ድርሳናት በዝርዝር ያስረዳሉ። በተለይ “የጨለማው ዘመን” ተብሎ በሚታወቀው ጊዜ (538ዓም – 1798ዓም) ይህ ኃይል ከነበረው ሃይማኖታዊ ሥልጣን በተጨማሪ የአውሮጳን ነገሥታት በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ ያለ ሮም ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ ንግሥናን መቀበል የሚችል ንጉሥ እንዳይኖር እስከማድረግ ደርሶ ነበር። ይህንን ሥልጣኑን የተቀናቀኑትንም ልክ ሲያስገባ እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል።
ለአብነትም ያህል በ11ኛው ክፍለዘመን በርዕሳነ ሊቀጳጳስ (ፖፕ) ግሪጎሪ 7ኛ እና አጼ ሔንሪ 4ኛ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ መመልከቱ በቂ ፍንጭ ይሰጣል። በወቅቱ (እኤአ በ1056 ዓም) የስድስት ዓመት ልጅ የነበረው ሔንሪ የጀርመን ንጉሥ ሆኖ ይሾማል። የንግሥና ዘመኑ ከ1056 ዓም ጀምሮ ቢቆጠርም ዘውድ የደፋውና አጼ ሆኖ ብቻውን ማስተዳደር የጀመረው በ1084 ዓም ነበር፤ ከዚያ በፊት የነበሩትን ዓመታት ከእናቱ ጋር በጥምረት ነበር የገዛው። በተለምዶ የጀርመን ነገሥታት የቅድስት ሮም አጼ ተብለው ይሾሙ ስለነበር ሔንሪም ይህንኑ ሥልጣን ተጠቅሞ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳትን የምሾመውና የምሽረው እኔ ነኝ የሚል መመሪያ ያወጣል።

ይህ የሔንሪ አካሄድ ያልጣማቸው የሮሙ ርዕሳነ ሊቀጳጳስ ግሪጎሪ 7ኛ ትክክል አይደለህም በማለት ደብዳቤ ይጽፉለታል። በወቅቱ እኚሁ ሊቀጳጳስ በታሪክ “የግሪጎሪ ተሃድሶ” የሚባለውንና 27 ነጥቦችን ያካተተ Dictatus papae (“papal dictation”) ወይም “የሊቀጳጳሱ የቃል ጽሕፈት” የሚል መመሪያ አውጥተው ነበር። ከእነዚህ 27 ነጥቦች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ይገኙበታል፤ ጳጳሳት መሾምም ሆነ ማውረድ የሚችለው ርዕሳነ ሊቀጳጳስ (ፖፑ) ነው፤ ልዑላን ሁሉ የፖፑን እግሩን ብቻ ነው መሳም የሚችሉት፤ በየአብያተ ክርስቲያናቱ መጠራት ያለበት ስም የሊቀጳጳሱ ብቻ ነው፤ ነገሥታትንና አጼዎችን ከሥልጣናቸው ማስወገድ የሊቀጳጳሱ ብቻ ሥልጣን ነው፤ ሊቀጳጳሱን ማንም ሊፈርድበት አይችልም፤ ሲኖዶሱን ሳይሰበስብ ሊቀጳጳሱ ጳጳሳትን መሾምም መሻርም ይችላል፤ የሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እስካሁን ስህተት ፈጽማ አታውቅም፣ ወደፊትም ለዘላለም ስህተት አትፈጽምም፤ ወዘተ የሚሉ ነበሩ።

ሔንሪ 4ኛ ግን እነዚህን መመሪያና ደንቦች በመቃወም የራሴን ጳጳሳት የምሾመውና የምሽረው እኔ ነኝ በማለት የርዕሳነ ሊቀጳጳሱን (የፖፑን) ሥልጣን ይጋፋል። ይህንን ያልተቀበሉት ግሪጎሪ 7ኛም የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ይጽፉለታል። እርሱም ያንን አልሰማም በማለት ጠንከር ያለ የተቃውሞ ደብዳቤ በምላሹ ይጽፍላቸዋል። በመጨረሻም ሊቀጳጳሱ ሔንሪን ያወግዙትና ከቤተክርስቲያኗ ያስወግዱታል (excommunicate ያደርጉታል)፤ ከዚህ ሌላ በእርሱ ሥር የነበሩትን ዜጎች (አብዛኛዎቹ ካቶሊኮች ናቸው) ከሔንሪ ነጻ መውጣታቸውንና ለእርሱ መታዘዝም ሆነ ግብር መክፈል እንደሌለባቸው ጨምረው ያውጃሉ። በካቶሊክ አስተምህሮ መሠረት በዚህ መልኩ የተወገዘ ሰው ከቤተክርስቲያን መዝገብ የሚፋቅ ብቻ ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ ባይኖረውም ከሰማይም ነው የሚታቀበው ተብሎ ይታመናል። ሁኔታው ያሳሰበውና ዓመጽ ይነሳብኛል ብሎ የሰጋው ሔንሪም ይቅርታ እንዲጠይቅ በተደረገበት ተጽዕኖ ምክንያት ሊቀጳጳስ ግሪጎሪ 7ኛን ይቅርታ ሊጠይቅ በአስከፊው የአውሮጳ ክረምት የሦስት ቀን ጉዞ ወደ ሮም ያደርጋል። በወቅቱ ሊቀጳጳሱ ካኖሳ በተባለች ሰሜናዊ የጣሊያን ከተማ ይገኙ ስለነበር እዚያ ድረስ ይሄዳል፤ ጉዞውም በታሪክ “የካኖሳው ጉዞ” ተብሎ ይጠራል።
ሔንሪ እዚያ እንደደረሰ ፖፕ ግሪጎሪ 7ኛ ወዲያው ሊቀበሉት ስላልፈለጉና እርሱን አዋርደው በመላው አውሮጳ ለሚገኙት ነገሥታት ትምህርት የሚሆን መልዕክት መላክ ስለፈለጉ፤ አጼ ሔንሪ ይቅርታ እየለመነ በአስከፊው ብርድና በረዶ ውጪ እንዲቆይ አደረጉት። በመጨረሻም ጫማውን አውልቆ በባዶ እግሩ በበረዶ ላይ ሆኖ ወደ ሊቀጳጳሱ እንዲገባና እግራቸውን በመሳም ይቅርታ እንዲማጸን አስደረጉት።
ይህ ጳጳሳዊ ሥልጣን በዚህ መልኩ በገናናነት ቢቀጥልም እስከመጨረሻው ግን አልዘለቀም። በአውሮጳ ኃያል ሆኖ የተነሳው ናፖሊዮን ቦናፓርት ይህንን ለ1,260 ዓመታት ተንሰራፍቶ የቆየውን የሮም ሊቀጳጳስ ሥልጣን የሚገታ ተግባር ፈጸመ። ለዘመናት የቆየውን የሮም ሊቀጳጳስ ንጉሥን የመሾም ሥልጣን ናፖሊዮን በመቃወምና ማንም ከእርሱ በላይ እንዳልሆነ ለማሳየት ራሱን አጼ በማድረግ ዘውድ በራሱ ላይ ደፋ። ይህ ብቻ ሳይሆን የጦር አዛዡን ጄኔራል በርቲየርን በመላክ እኤአ በ1798 ዓም በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበሩት ሊቀጳጳስ (ፖፕ) ፓየስ 6ኛ የተባሉትን ከሥልጣናቸው በማንሳት ወደ ፈረንሳይ በግዞት ላካቸው። ከ18 ወራት በኋላ እርሳቸውም በግዞት እያሉ አረፉ።
ይህ ለ1,260 ዓመታት ሰፍኖ የቆየው ጳጳሳዊ ሥርዓት በዚህ መልኩ ሲዳከም ወይም በራዕይ 13፡3 መሠረት “ለሞት የሚያደርስ ቊስል” ከተቀበለ በኋላ በዚያው ዘመን አካባቢ ስለተከሰተ ነገር ራዕይ 13፡11 እንዲህ ይላል “ከዚያም ሌላ አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፤ እርሱም እንደ በግ ሁለት ቀንዶች ነበሩት፤ ነገር ግን እንደ ዘንዶ ይናገር ነበር”። ይህ “አውሬ” ወይም መንግሥታዊ ኃይል ከበርካታ ማንነቱ በተጨማሪ በተለይ የሮም ጳጳሳዊ ኃይል በተዳከመበት ወቅት፣ ሕዝብ በብዛት ካልሰፈረበት ወይም “ከምድር” የወጣ መሆኑና አጀማመሩ እንደ በግ ጉዳት የማያደርግ ለስላሳና መልካም መሆኑና ሁለት ቀንዶች የነበሩት መሆኑ ልዩ መለያዎቹ ናቸው ። እነዚህን መለያዎች ይዘን በ18ኛው ክፍለዘመን መጠናቀቂያ አካባቢ በዓለም ላይ የተነሳ ኃይል ማነው ብለን ብንጠይቅ ከአሜሪካ ሌላ የምናገኘው የለም። (ለአብነት ያህል አሜሪካ በተመሠረተችበት ጊዜ የሕዝቧ ቁጥር 2.5 ሚሊዮን ብቻ ነበር። በአሁኑ ጊዜ (በ2024) የአሜሪካ ሕዝብ ቁጥር ከ332 ሚሊዮን በላይ ነው።)

አሜሪካ ከአነሳሷ በጣም ሰላማዊ አገር ነበረች። በእርግጥ ወደ አዲሷ ምድር የመጡት አውሮጳውያን በአሜሪካ ይኖሩ በነበሩት ተወላጅ ሕንዶች (ሬድ ኢንዲያንስ) ላይ እጅግ የከፋ መከራ ቢያደርሱም አሜሪካ አነሳሷ ግጭት የወለደው አይደለም፤ በአብዛኛው ሰላማዊ የሚባል ነበር። በተለይ በአውሮጳ ይካሄድ የነበረው የሃይማኖት መብት ረገጣ ያስመረራቸው ወደ አዲሱ አገር ተሰድደው በመምጣት የመሠረቷት ከመሆኗ አንጻር አሜሪካ የክርስቲያን (የፕሮቴስታንቶች) አገር እንድትሆን አድርጓል። ይህም ክርስቲያናዊ እሴት በሕገ መንግሥቱም ሆነ በአጠቃላይ የአገረ መንግሥት ምሥረታ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል።
የታሪክ ምሑራን እንደሚሉት ወደ አሜሪካ መጥተው አገር የመሠረቱት ሰዎች የአውሮጳው ጳጳሳዊ አገዛዝ ከመንግሥት ጋር በመተባበር ያደረሱባቸውን ግፍ በመቃወም ስለነበር እንደ መፈክር ያነገቡትና የሚከተሉት መርኽ “ሃይማኖት ያለ ጳጳስ፤ አገር ያለ ንጉሥ” የሚል ነበር። በምትኩ ፕሮቴስታንታዊነት እና ሪፓብሊካዊነት ዋንኞቹ መርኾዋቸው ሆኑ። ይህም ከምድር በወጣው በግ ሁለት ቀንዶች ተመስሎ እናነባለን፤ “ሌላም አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፥ የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ ሁለት ቀንዶችም ነበሩት” (ራዕይ 13፡11)።
ይህ አውሬ በግ መሆኑ አጀማመሩ ሰላማዊና ንጽሕናን የተላበሰ መሆኑን የሚያመላክት ነው። የአሜሪካ የነጻነት ድንጋጌ (ዴክላሬሽን ኦቭ ኢንዲፔንደንስ) እንዲህ ይላል “ሰዎች ሁሉ ነጻ እና እኩል ሆነው መፈጠራቸውን፤ አንዳንድ የማይገሰሱ መብቶች እንደተሰጧቸው፤ ከእነዚህም መካከል ሕይወት፣ ነጻነት እና ደስታን መሻት መሆናቸውን፤ እነዚህም እውነቶች ለራሳቸው ምስክር እንደሆኑ እናምናለን” የሚል ነው። ከዚህ አንጻር ሃይማኖት በፕሮቴስታንታዊ መርኽ መንግሥት ደግሞ በሪፓብሊክ ወይም በሕዝብ ውክልና የሚተዳደር መሆን አለበት በሚል ገና ከጅምሩ የአገረ መንግሥት ምሥረታው መነሻ ሃሳብ የሆነው። ይህ ንጽሕና ግን እንደተባለው አይቀጥልም፤ ይህንኑ በግ መሰል አውሬ “እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር” ይላል (ራዕይ 13፡11)።
በመጽሐፍ ቅዱስ “በግ” የክርስቶስ ተምሳሌት ሆኖ ነው የምናነበው (ዮሐንስ 1፡29)። በራዕይ 13፡11 የተጠቀሰው ግን በግ ብቻ ሳይሆን “አውሬም” ነው። ከዚያ ሲያልፍ የሚናገረው “እንደ ዘንዶ” ነበር (ራዕይ 13፡11)። ይህ በጣም አሳሳችና አምታች የሆነ ባሕርይ ያለው በግ መሆኑ ያሳየናል። እንደ ቤት እንስሳ በግ ነው ተብሎ ሲጠበቅ አውሬ ነው፤ ከዚያ ሲያልፍ ደግሞ እንደ ዘንዶው ማለትም እንደ ዲያቢሎስ፣ ሰይጣን ወይም በኤደን ገነት ሔዋንን እንዳሳሳታት እባብ አሳሳች ነው።

በብሉይ ኪዳን ነቢያት የእግዚአብሔር አፍ ሆነው ያገለግሉ እንደነበር ይህም በግ የዘንዶው አፈቀላጤ ሆኖ እናየዋለን። በዚህም ምክንያት ይህንን ከምድር የወጣውን አውሬ በሌሎቹ የራዕይ መጽሐፍ ክፍሎች “ሐሰተኛ ነቢይ” በማለት ይጠራዋል (ራዕይ 16፡13፤ 19፡20፤ 20፡10)። ሔዋን የተሳሳተችው ከእባቡ ይወጣ በነበረው ንግግር ነበር (ዘፍ. 3፡1-5)። ይህ በበግ የተመሰለው አውሬም የዘንዶው አፍ በመሆን ቀልብን የሚስቡና የሚማልሉ ነገሮችን በመናገር እውነትን ይበርዛል፤ ሐሰትን ይነዛል፤ በክርስትና ስም ክርስትናን ያበላሻል፤ ሰዎችንም ያስታል። ከዚህ ሲያልፍም “ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰለት ለፊተኛው አውሬ (ጳጳሳዊ ሥርዓት) ምድርና በእርሱ የሚኖሩት እንዲሰግዱለት ያደርጋል” (ራዕይ 13፡12)።
የነጻነትና የዴሞክራሲ ፋናወጊ የሆነችው አሜሪካ በዚህ ልክ በመውረድ የሃይማኖትን ነጻነት ከሰዎች በመንፈግ አስገዳጅ ሕጎችን ታወጣለች ብሎ ማመን ሊከብድ ይችላል። ሆኖም ግን የአሜሪካንንን ፖለቲካ በቅርብ ለሚከታተል ይህ ሁኔታ በተግባር እየተፈጸመና ሥር እየሰደደ የመጣ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም። ዙሩ እየከረረ ሲሄድም የሃይማኖት ነጻነት አጥተው የነበሩትን ያስጠለለችው አሜሪካ መልኳን በመቀየር ለመጀመሪያው አውሬ (ጳጳሳዊ ሥርዓት) ምስል በማቆም ወይም አስገዳጅ ሃይማኖታዊ ሕግጋትን ታወጣለች ይለናል ራዕይ 13፡14። ይህ በአሜሪካ (ሐሰተኛው ነቢይ) የተመሰለው በግ መሰል አውሬ ለመጀመሪያው አውሬ ሲል የሚያወጣውን ትዕዛዝ ሰዎች በእጃቸው (ለመኖር ሲሉ) ወይም በግምባራቸው (አምነውና ፈቅደው) ምልክት እንዲቀበሉ ያስገድዳቸዋል (ራዕይ 13፡16)። አንቀበልም የሚሉትን ያሳድዳል፤ የሞት አዋጅም ያውጃል (ራዕይ 13፡15)።
ሃሳቡን ጠቅለል ለማድረግ ከምድር የወጣው በአሜሪካ የተመሰለው በግ መሰሉ አውሬ እንደ ዘንዶ መናገር በሚጀምርበት ጊዜ አራት ነገሮች ይከሰታሉ፤
- “በፊተኛውም አውሬ ሥልጣን በእርሱ ፊት ሁሉን ያደርጋል” (ራዕይ 13፡12)። ከባህር የወጣው አውሬ የሮም ጳጳሳዊ ሥርዓት እንደነበር ተመልክተናል። ይህ ኃይል የጨለማው ዘመን በሚባለው የመካከለኛው ዘመን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን አሳድዷል ፤ገድሏል። ልክ እንደዚህ አሳዳጅ ኃይል አሜሪካም እንደ ዘንዶው መናገር ስትጀምር ሰዎችን ወደ አስገዳጅ ሃማኖታዊ ሥርዓት ታስገባለች፤ እምቢ የሚሉትንም ታሳድዳለች።
- “ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰለት ለፊተኛው አውሬ ምድርና በእርሱ የሚኖሩት እንዲሰግዱለት ያደርጋል” (ራዕይ 13፡12)። አሜሪካ የዓለም መንግሥታትን በመምራት ሓሳዊ ክርስቶስ ለሆነው የጳጳሳዊ ኃይል እንዲሰግዱ ወደማስገደድ ሥራ ውስጥ ትገባለች። (ሓሳዊ ክርስቶስ ማለት ሐሰተኛ ወይም ጸረ ክርስቶስ ማለት ብቻ ሳይሆን የክርስቶስ ቦታ ለኔ ይገባኛል ማለትም ነው)።
- “የሰይፍም ቍስል ለነበረውና በሕይወት ለኖረው ለአውሬው ምስልን እንዲያደርጉ በምድር የሚኖሩትን ይናገራል” (ራዕይ 13፡14)። አሜሪካ ከባህር ለወጣውና ቁስሉ ለተፈወሰለት አውሬ (ጳጳሳዊ ሥርዓት) ሃይማኖታዊ ሕግጋትን ትደነግጋለች። የጨለማው ዘመን በሚባለው ወቅት ዓለምን ሲቆጣጠር በነበረው ጳጳሳዊ ሥርዓተ ዘመን እንደነበረው አሁንም እንዲሁ ሃይማኖትን ከመንግሥት ጋር በማጋባት አሜሪካ ምስለ ጳጳሳዊ ሥርዓትን ትዘረጋለች።
- “ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ሁሉ (ያስገድላቸዋል)” (ራዕይ 13፡15)። ዓለምን በኃያልነት የምትመራው አሜሪካ ለዚህ ለጳጳሳዊ ሥርዓት የሚቆመውን ምስል “አንቀበልም”፣ “አንሰግድም” የሚሉ ሁሉ እንዲገደሉ የዓለምን መንግሥታት ታስተባብራለች። የዓለም መንግሥታትም አንታዘዝም ባዮችን ለመግደል የሚያስችል የሞት አዋጅ ያውጃሉ። (ዝርዝር መረጃ በጥያቄና መልስ ዓምዳችን አሜሪካ በእርግጥ በትንቢት የተጠቀሰች አገር ናት? በሚል ርዕስ ሥር ይገኛል)
በመጨረሻው ዘመን ሰዎች ከሁለት በአንዱ ጎራ እንዲሰለፉ የሚያደርጋቸው ዋና ጉዳይ አምልኮ ይሆናል። ይህ ደግሞ በሰማይ የጀመረ እንደሆነ ኢሳይያስ 14 እና ሕዝቅኤል 28 ይነግሩናል። ሉሲፈር የእግዚአብሔርን ዙፋን አጥብቆ ተመኘ፣ አምልኮና ስግደት የሚገባኝ ለእኔ ነው አለ። ኃይሉን ሲያስተባብር ከመላዕክት ሲሶውን አታላይ በሆነው ችሎታው ተጠቅሞ ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ አሳመናቸው። ይህንኑ የማሳሳቻ ስልት ተጠቅሞ ሔዋንን ካታለለ በኋላ የዚህች ምድር ገዢ እንደሆነ አደርጎ ራሱን ቆጠረ። በመጨረሻው ዘመንም ስግደትና አምልኮ የሚገባው ለኔ ነው በሚል አንታዘዝም በሚሉት ላይ እርምጃ ይወስዳል።
ስግደት ማን እንደሚገባው ቃሉ ሲነግረን፤ “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት” ይላል (ራዕይ 14፡7)።
ጥበበሥላሴ መንግሥቱ










