giziew.org

የአረንጓዴው ሰንበት እንቅስቃሴ

የአረንጓዴው ሰንበት አቀንቃኞች የሚሉት ፕላኔታችን ለማዳን ዋናውና ብቸኛ መፍትሔ ምንም አለማድረግ ነው፤ ምንም ባለማድረግ ልንታደጋት እንችላለን ይላሉ።
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

አረንጓዴ ሰንበት ማለት ከሃይማኖት ጋር ባልተገናኘ መልኩ አንድ የዕረፍት ቀን ማድረግ ነው። ይህም ከኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች (ስልክ፣ ታብሌት፣ ኮምፒውተር፣ …)፣ ከመኪና፣ ወዘተ በመራቅ ወይም በመነቀል ከቤተሰብ፣ ከወዳጅ፣ ከጓደኛ፣ ከራስ ጋር ምግብ በመመገብ፣ በመዘመር/በመዝፈን፣ በመጠጣት፣ በመጫወት፣ በማሰላሰል አንድ ሙሉ ቀን ምንም ሳይሠሩ መዋል ነው። በተለይ ደግሞ ከተፈጥሮ ጋር መገናኘትና ወደ ኤደን መመለስን አበክሮ የሚደግፍ እንቅስቃሴ ነው። በሰበቡም ተፈጥሮን እንታደጋለን ይላል።

አረንጓዴ ሰንበት የሚከበርበት ቀን በአብዛኛው የሳምንቱ መጨረሻ ሲሆን ለብዙዎች አመቺ እየሆነ የመጣው ቀን እሁድ ነው። ለምሳሌ ያህል በሜክሲኮ እኤአ ከ2007 ዓም ከምሮ 55 ኪሜ (30 ማይል) መንገድ በየእሁዱ ይዘጋል። መኪና አይተላለፍም፤ ዜጎች በእግር፣ በብስክሌት፣ በኤሌትሪክ በሚሠሩ ባለሁለት ጎማ ተንቀሳቃሾች፣ ስኩተር፣ ስኬትቦርድ፣ ወዘተ ብቻ ነው የሚጠቀሙት።

በሀገሬው አፍ “ሙዌቤቴ ኤን ቢሲ” ወይም “በብስክሌት መንቀሳቀስ” ተብሎ የሚጠራው ዘመቻ አካል ሆኖ በየእሁዱ ከጠዋት ሁለት ሰዓት እስከ ከሰዓት ስምንት ድረስ የሚዘልቅ ነው። በኮሎምቢያና ሌሎች ሀገራትም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ በስፋት እየተለመደ መጥቷል።

የአረንጓዴው ሰንበት አቀንቃኞች የሚሉት ፕላኔታችን ለማዳን ዋናውና ብቸኛ መፍትሔ ምንም አለማድረግ ነው፤ ምንም ባለማድረግ ልንታደጋት እንችላለን ይላሉ። ስለዚህ ከሥራ፣ ከመንዳት፣ ከመብረር፣ ስልክ ከመጠቀም፣ ከቴክኖሎጂ በመፋታት፣ ገበያ ከመሄድ፣ ከሕንጻ በመገለል ከዕረፍት ቀኑ በፊት ምግብ አዘጋጅቶ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ሲያወጉ፣ ሲበሉ፣ ሲጠጡ፣ መዋል፤ ይህ ነው አረንጓዴው ሰንበት። ለዚህም ነው እንደ ሜክሲኮ ባሉ ሀገራት የሚደረገውን ከመኪና ነጻ ቀን አረንጓዴው ሰንበት የሚደገፈው።

የአረንጓዴው ሰንበት እንቅስቃሴ መሥራች የሆነው ይሁዲው ጆናታን ሾርሽ ሲናገር፤ ጉዳዩ ከሃይማኖት ወይም ከእግዚአብሔር ወይም ከሆነ አምላክ ጋር የተገናኘ አይደለም ይላል። እንደ ማስረጃም የሜክሲኮውን ልምምድ ይጠቅሳል። በቦጎታ ከተማ ኮሎምቢያ የሚደረገውና በእንግሊዝ የሚከናወነው የጨዋታ ፕሮግራም አብሮ የሚጠቀስ ነው።

አይሁዳውያን “የሥርየት ቀን” ወይም “ዮም ኪፖር” የሚሉት በዓላቸውን ሲያከብሩ ሁሉም ነገር ስለሚዘጋ በዚያ ዕለት የሚከሰተው የአየር ብክለት ከ70 እስከ 99 በመቶ ይቀንሳል በማለት የእስራኤል የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ያወጣውን መረጃ የአረንጓዴ ሰንበት አቀንቃኞች እንደ ዋቢ ይጠቅሳሉ።

ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ተፈጥሮም ዕረፍት ያስፈልጋታል የሚለው የእንቅስቃሴው አራማጆች አባባልን በመጥቀስ ሾርሺ ሲናገር፤ አረንጓዴ ሰንበት ምድራችንን ወደ ተፈጠረችበት እውነተኛ ሰንበት አከባበር ይመልሳታል ይላል።

የአረንጓዴ ሰንበት እንቅስቃሴ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብዛት ተቀባይነትን እያገኘ የመጣ ሆኗል። በፖላንድ ማንኛውም ዓይነት የንግድ ሱቆች እሁድ ዕለት መዘጋት ከጀመሩ አምስት ዓመት ሆኗቸዋል፤ በ2020 ዓም ነው የተጀመረው። በየዓመቱ ለበዓል ተብሎ ከሚፈቀዱት ሰባት ወይም ስምንት እሁዶች በስተቀር ሱቅ ከፍቶ የተገኘ ይቀጣል። ሌሎች ሀገራትም ተመሳሳይ እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ።  

ባለፈው መስከረም ወር ሕይወቱን ያጣው ቻርሊ ከርክ የአንድ ዕረፍት ቀን ደጋፊ ነበር። ሰዎች ከሥራ፣ ከስልክ፣ ወዘተ ተገልለው ከራሳቸው ወይም ከቤተሰባቸው ጋር የሚያሳልፉት አንድ ያልተቋረጠ የ24 ሰዓት ዕረፍት እንደሚያስፈልጋቸው በተደጋጋሚ ሲናገር ተደምጧል።

መጽሐፍ ቅዱስ፤ ሰንበት የፍጥረትና የመዳናችን ምልክት የሆነች የዕረፍት ቀን ናት ይላል። እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ከፈጠረ በኋላ በሰባተኛው ቀን አርፏል። “አረፈ” የሚለው ቃል ከሥራ ድካም ማረፍ ሳይሆን “አቆመ” የሚለውን ትርጉም የያዘ ነው (ኢያሱ 5፡12)።

እግዚአብሔር በስድስት ቀን ምድርን ጥንቅቅ አድርጎ፣ አንዳችም ሳይጎድልባት፣ እጅግ ፍጹም አድርጎ ሠራትና ሁሉን ሲያጠናቅቅ ሥራውን አቆመ (ዘፍጥረት 2:1-3)። የፈጠረውን ሰውንም እኔ ሁሉን ሠርቼ ፈጽሜልሃለሁ፤ አንተ ምንም መሥራት አያስፈልግህም (ጸጋ)፤ ዕረፍ ብሎ ኑሮውን በዕረፍት (በአምላኩ ላይ ፍጹም በመታመን) እንዲኖር ሕይወቱን በሥራ ሳይሆን በሰንበት አስጀመረው። 

በኤድን ገነት ገና ኃጢአት ሳይገባ፤ ገና አይሁድ የሚባል ሕዝብ ከመነሳቱ በፊት ሰንበት የተሰጠው በተለይ የፍጥረት ማስታወሻ ምልክት ሆኖ ነበር። ከዚያም ከግብፅ ባርነት ነጻ ለወጡት አይሁዳውያን፤ በዘጸአት 20 እንደምናነበው፤ በሲና ተራራ ላይ ሕጉ ከመሰጠቱ በፊት በሰንበት ሁሉም ሕግና ትዕዛዝ ተሰናስሎና ተቆራኝቶ ነበር። ሰንበት የቀን ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ከዚያ ያለፈ ረቂቅ ትርጉም፣ ጥልቅ ተጽዕኖ ያለው ነው።

በዘጸአት 16 ላይ ስለ መናው መውረድ በሚናገረው ክፍል ለእስራኤላውያን የተሰጠው ትዕዛዝ መናው ለስድስት ቀን (ከእሁድ እስከ አርብ) እንደሚወርድና አርብ ዕለት ግን እጥፍ እንደሚወርድ ነበር (ዘጸአት 16፡15-26)።

በሰንበት መና አይወርድም ተብሎ ተነግሯቸው ለመልቀም የወጡ ሰዎች ግን ነበሩ። በእነዚህ ሰዎች ያዘነው እግዚአብሔር ለሙሴ “ትእዛዞቼንና ሕጎቼን ለመጠበቅ እስከ መቼ እንቢ ትላላችሁ?” አለው (ዘጸአት 16፡28)። አስርቱ ትዕዛዛት ገና በዘጸአት 20 ከመሰጠቱ በፊት፥ አስር መሆናቸውም ገና ሳይታወቅ፥ እንዴት ነው እግዚአብሔር አንድ የሰንበት ትዕዛዝ ስለተሻረ “ትእዛዞቼንና ሐጎቼን” የማትጠብቁት ለምንድነው ያለው? ጊዜ ወስደን በጥልቀት ልናስብበትና ልናሰላስለው የሚገባ ጥያቄ ነው።

የኃጢአት ተምሳሌት ከሆነችው ግብፅ ባርነት እስራኤላውያን ነጻ ሲወጡ ሰንበት ከኃጢአት ባርነት በክርስቶስ ወደሚገኝ ጽድቅ ማመላከቻ ሆኖ ተጠቅሶ እናነባለን። በዘዳግም አሥርቱ ትዕዛዛት ሲደገሙ ስለ አራተኛው ትዕዛዝ በዘጸአት 20 ከተነገረው ተጨማሪ ሃሳብ ተጠቅሶ እናነባለን፤ “አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ አስብ፤ እግዚአብሔር አምላክህ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ ከዚያ አወጣህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ የሰንበትን ቀን ትጠብቅ ዘንድ አዘዘህ” (ዘዳግም 5፡15)። ሰንበት በእግዚአብሔር የመፈጠራችን ምልክት ብቻ ሳይሆን በእርሱ እንደገና የመፈጠራችን፤ የመዋጀታችን ማኅተማችንም ነው።

እግዚአብሔር አምላክህ እንዳዘዘህ (ከኤድን ጀምሮ) የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ ጠብቅ። ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፥ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር አምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ እንደምታርፍ ሎሌህና ገረድህ ያርፉ ዘንድ፥ አንተ ወንድ ልጅህም ሴት ልጅህም ሎሌህም ገረድህም በሬህም አህያህም ከብትህም ሁሉ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ (ሥራ ባጠቃላይ ይዘጋል፤ እንስሳትም፥ ተፈጥሮም፥ ሁሉም ያርፋል)። አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ አስብ፤ እግዚአብሔር አምላክህ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ ከዚያ አወጣህ (ፈጣሪህ ብቻ ሳይሆን ዳግም የፈጠረህ አዳኝህም ነው)፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ የሰንበትን ቀን ትጠብቅ ዘንድ አዘዘህ (ዘዳግም 5:12-15)።

የሰው ልጅ ገዳዳ ነው፤ ያንጋደደውም ኃጢአት ነው፤ አምላክ የሰጠውን እውነተኛ ሰንበት ማክበርና ከእንስሳ ጀምሮ ተፈጥሮ ጭምር ማረፍ ሲገባው አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ … እያለ ከአምላኩ የራቀ የቀለም ሰንበት በማክበር መከራውን ያያል። ሰንበት ቀለም ይኖራት ካልን አንድ ነው፤ እርሱም ሰማያዊ ነው።

ጥበበሥላሴ መንግሥቱ


የቅርብ ጽሁፎች

በ Facebook ይከተሉን

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *