giziew.org

የሥጋ ደዌ ያልበገረው ፍቅር

ጥሪውን ከመቀበላቸው በፊት ሮላንድና በርጊታ ስለ በሽታው አሰቃቂ ባሕሪዎች ጥናት አደረጉ። በሥጋ ደዌ ምክንያት እጅና እግሮቻቸው መንቀሳቀስ ያቃታቸው ሕሙማን በቀዶ ጥገናና በሌሎች የሕክምና ዘዴዎች መጠነኛ መሻሻል ሊያሳዩ እንደሚችሉ ተገነዘቡ። ሮላንድ የቀዶ ጥገና ሐኪም ስለነበር ጥሪውን ለመቀበል ወስነው፣ ...
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

አንድ እሁድ ከሰዓት፣ አዲስ አበባ ውስጥ ሰበታ መንገድ ላይ በሚገኘው አለርት ሆስፒታል ጊቢ የሚኖረውን ጓደኛዬን ለመጠየቅ ሄድኩ። በጊዜው ሁለታችንም የሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች ነበርን። በጊቢው ውስጥ ብስክሌት እያሽከረከርን ስንዝናና ድንገት ዕድሜያቸው ከአስር የማይበልጥ አራት ልጆች ወደኛ አቅጣጫ እየሮጡ መጡ።

የልጆቹ ድምፅ ሸካራና ጎርናና ነበር። ሲጠጉን ሁሉም የራስ ፀጉርና ቅንድብ የሌላቸው፣ አፍንጫዎቻቸውና እጆቻቸው የተሸራረፉ መሆናቸውን ሳይ በድንጋጤ ፍሬን ያዝኩ። ከፊቴ ገጽታ መደንገጤንና መከፋቴን የተገነዘቡት ሕፃናት ዞረው ወደ መጡበት ተመለሱ።

ልጆቹ የሥጋ ደዌ ሕሙማን ነበሩ። ይህ ከባድና ተላላፊ ደዌ የሚጎዳው ቆዳን፣ አፍንጫን፣ ላንቃና ዓይኖችን ሲሆን፤ በሽታውን የሚያዛምተው ባክቴሪያ የስሜት ሕዋሳትንም ይገድላል። የበሽታው ሰለባዎች የእጅና የእግር ጣቶቻቸውም እየተበሉ ያልቃሉ።

የአለርት ሆስፒታል በሥጋ ደዌ የሚሰቃዩ ሰዎችን ለማከም የተዘጋጀ ቦታ መሆኑን አውቅ ነበር። በዕድሜ የሚቀርቡኝ የበሽታው ጉዳተኞች ማየቱ ግን ቀፎኝ ነበር። ልጆቹ ከእኔ ጋር መጫወት ፈልገው እንደቀረቡኝ የገባኝ እጅግ ቆይቶ ነው። ሳላውቀው ለሰው ልጆች መሰጠት ያለበትን ርኅራኄ ነፍጌያቸው እንደነበር ዛሬ ሳስብ በእጅጉ አዝናለሁ።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሮላንድና በርጊታ ኬዘን (Roland and Birgitta Kazen) ከሚባሉ ስዊድናዊያን ባልና ሚስት ጋር ተዋወቅሁ። ይኖሩ የነበረው የሥጋ ደዌ የሚሰቃዩ ሕፃናትና አዋቂዎች በሚታከሙበትና በሚያድሩበት አለርት ጊቢ ውስጥ ነው። የተገናኘነው ደግሞ ሮላንድ ሙዚቃ በሚጫወትበትና መዘምራን በሚያሰለጥንበት በፍልውሃ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን ነበር።

ሮላንድና በርጊታ ኢትዮጵያ የገቡት የሥጋ ደዌ ታማሚዎችን ለመርዳት መሆኑን ጥቂት ቆይቼ ሰማሁ። ስለ በሽታው ብዙ ከማወቃቸው በፊት ሮላንድ በስዊድን አገር ሐኪም ሆኖ ያገልግል ነበር። ከዚያም በ1975 (እኤአ) ወደ ሴራሊዮን አገር ሄዶ ማሳንጋ ሆስፒታል ተብሎ በሚጠራው የሥጋ ደዌ ሐኪም ቤት በመሪነት እንዲሠራ ተጠራ።

ጥሪውን ከመቀበላቸው በፊት ሮላንድና በርጊታ ስለ በሽታው አሰቃቂ ባሕሪዎች ጥናት አደረጉ። በሥጋ ደዌ ምክንያት እጅና እግሮቻቸው መንቀሳቀስ ያቃታቸው ሕሙማን በቀዶ ጥገናና በሌሎች የሕክምና ዘዴዎች መጠነኛ መሻሻል ሊያሳዩ እንደሚችሉ ተገነዘቡ። ሮላንድ የቀዶ ጥገና ሐኪም ስለነበር ጥሪውን ለመቀበል ወስነው፣ ስዊድን የነበረውን ቤታቸውን ሸጡና ሻንጣዎቻቸውን ሸክፈው ከሦስት ወጣት ልጆቻቸው (ቶማስ፣ አኔታ፣ እና ማግነስ – Thomas, Agneta and Magnus) ጋር ወደ ሴራሊዮን በረሩ።

በማሳንጋ ሆስፒታል ሮላንድ፣ በርጊታና ልጆቻቸው የሥጋ ደዌ ህሙማንን በመርዳት ሙሉ በሙሉ ተጠመዱ። ሮላንድ ቀዶ ጥገና ሲሰራ ሴት ልጁ በጥንቃቄ ፎቶ ታነሳ ነበር። ፎቶግራፎቹን ሮላንድ ሐኪሞችን ለማስተማር ይጠቀምባቸው ነበር። የቀሩት ልጆቻቸው ጧት ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ መጫወቻዎቻቸውንና የሕፃናት መጽሐፍት ወስደው የሥጋ ደዌ ከያዛቸው ልጆች ጋር ይጫወቱ ነበር።

አሁን ላይ ስጠይቃት በሴራሊዮን ያሳለፉት ጊዜ የሕይወታቸው እጅግ አስደሳች ዓመታት እንደነበሩ በርጊታ ነግራኛለች። ሮላንድ ሥራውን አብዝቶ ይወድ ነበር። ታማሚዎቹን ስለሚወድ እነርሱም ይወዱት ነበር። ከዚህ ባሻገር ሮላንድ በቀዶ ጥገና አዳዲስ አሠራሮች ስለፈጠረ ከእርሱ ለመማር ሐኪሞች ከጎረቤት አገራት ወደ ማሳንጋ ሆስፒታል ይሄዱ ነበር።

በሕክምና ያገገሙትን የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች የሚረዱበትን መንገድ ማመቻቸት ደግሞ የበርጊታ ኃላፊነት ነበር። ከሐኪም ቤት ታክመው የወጡ ወጣቶች ለሁለት ዓመታት የአናጢነት፣ የልብስ ስፌት ወይም የግብርና ትምህርት ይሰጣቸው ነበር። ትምህርቱን ሲያጠናቅቁ ልብስ መስፊያ መኪናዎች ወይም የተለያዩ መሣሪያዎች ተሰጥቷቸው ወደየ አገር ቤታቸው ተመልሰው በተማሩት ሙያ አዲስ ሕይወት እንዲጀምሩ ይደረግ ነበር።

በርጊታ በሥጋ ደዌ ምክንያት ከባሎቻቸውና ከዘመዶቻቸው ለተገለሉ ሴቶች የተለየ ዕቅድ ነበራት። እነዚህ ሴቶች ከሐኪም ቤት ሲወጡ አነስተኛ የንግድ ሥራ እንዲጀምሩ ሩዝ፣ ዘይትና ስኳር እንዲሰጣቸው ታርግ ነበር። በዚህም የሥጋ ደዌን እንደ ሞት መቅሰፍት ይቆጥሩ የነበሩ ዘመዶቻቸውም ያገለሏቸው ሴቶች ላይ መንፈሳዊና ኢኮኖሚያዊ መሻሻል ሊያሳዩ ችለዋል። ይህም ሴቶቹ ከኖሩበት ማኅበረሰብ ጋር ተመልሶ የመቀላቀል በር ከፍቶላቸዋል።

በርጊታ ግን በዚህ አላቆመችም። እናት አባት ለሌላቸው የሥጋ ደዌ ተጠቂ ሕፃናት ብዙ ትጨነቅ ነበር። ስላዘነችላቸውም ቤትና ትምህርት ቤት እንዲሠራላቸውአደረገች።

በመጨረሻም ሮላንድ እና በርጊታ በማሳንጋ ለአስራ አራት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ሮላንድ አዲስ አበባ ካለው አለርት ሆስፒታል የሥራ ጥሪ ደረሰው። ይህ ዓለምአቀፋዊ ተቋም፣ ከፍተኛ የሥጋ ደዌ ሕክምናና የቀዶ ጥገና የሚደረግበት ቦታ ነው። በተጨማሪ ከኢትዮጵያና ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ሐኪሞች ምርምር የሚያደርጉበትና የሚሰለጥኑበት ቦታ ነው። ሮላንድ የማከምና የማስተማር ሥራውን በአለርት ሲቀጥል፣ በርጊታ ደግሞ የዓለም አቀፍ ሥልጠና ኃላፊ ሆነች።

በሥጋ ደዌ ሕክምና ሮላንድ ከፍተኛ ዕውቅና ነበረው። ቤተክርስቲያን ውስጥ ግን ራሱን ዝቅ አድርጎ የሚተጋ መንፈሳዊ ሰው ነበር። የእርሱና የበርጊታ ትኩረት አገልግሎት ላይ ስለነበር ስለሥራቸው የማውራትና ራሳቸውን የማግነን ጥማት አልነበራቸውም።

ሁለቱም ለወጣቶች አስገራሚ ፍቅር ነበራቸው። በተለይም የትምህርት ፍቅር ወይም የሙዚቃ ዝንባሌ ላላቸው ሁሉ ልባቸው ክፍት ነበር። መልካም ምክር ከመለገስ ጀምሮ ባላቸው ዓቅም የተቸገሩ የቤተክርስቲያን ወገኖችን እስከ መርዳት ድረስ ራሳቸውን የሰጡ መልካም ክርስቲያኖች ነበሩ።

ሮላንድና በርጊታ ከአውሮጳ መጥተው የባሕላቸውንና የማንነታቸውን የበላይነት ለማስረጽ እንደሚታገሉ ፈረንጆች አልነበሩም። ባገኙት አጋጣሚ ክርስትና በኢትዮጵያ ባህልና ቋንቋዎች እንዲዳብር የበሰለ ጥረት ያደርጉ ነበር። በተለይም መዝሙሮች በአገር በቀል ቅኝቶች እንዲጻፉና እንዲዘመሩ በማበረታታት ብዙ ለስኬት የበቁ ሥራዎችን ሠርተዋል።

ጡረታ ከወጡ በኋላ ሮላንድና በርጊታ ወደ ትውልድ አገራቸው ስዊድን ተመለሱ። እዚያ እያሉ በስካይፕ አውርተን ነበር። ያኔ ሮላንድ ኢትዮጵያ መመላለሱን እንዳላቆመና ወደ ታንዛኒያም በተደጋጋሚ እንደሚሄድ ነግሮኝ ነበር።

“ጡረታ ወጥተህ የለም እንዴ?” ስለው ፈገግ ብሎ “ጡረታ ስለወጣሁ የማስተዳደር ኃላፊነት የለኝም። ይህ ደግሞ የምወደውን ለማድረግ ነጻነት ይሰጠኛል። ወደ ኢትዮጵያና ወደ ታንዛኒያ የምሄደው ሐኪሞችን ለማስተማር ነው። በተጨማሪ ከወዳጆቼ ጋር በሥጋ ደዌ ቀዶ ጥገናን አስመልክቶ አንድ የትምህርት መጽሐፍ እየጻፍን ነው። ይህን የምናደርገው እኛ በሌለንበት ታማሚዎቹ እንዳይጎዱ ነው” በማለት ነበር የመለሰልኝ።

ይህንን ባወራን በሦስት ዓመቱ ሮላንድ በጠና ታመመ። በርጊታ እንደነገረችኝ እሷና ልጆቻቸው ከብበውት ሲዘምሩ ሮላንድ ወደ ላይ ጠቁሞ በለሆሳስ፤ “ክርስቶስን ተከተሉት” ይል ነበር። ብዙም ሳይቆይ ከዚህ ዓለም ድካም በጌታ አረፈ።

የሮላንድና የበርጊታ ሕይወት በፍቅር ቀለም የተጻፈ ወንጌል ነው። በሙያው ገንዘብ ማካበትና ዝነኛ መሆን ቢፈልግ ሮላንድ አውሮጳ መቅረት ወይም ወደ አሜሪካ መጓዝ ይችል ነበር። እርሱና ሚስቱ ግን የተሻለ ዋጋ ያለውን ሰማያዊ አገልግሎት መረጡ።

“ሙሴ ካደገ በኋላ፣ የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን በእምነት እምቢ አለ። ለጥቂት ጊዜ በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ፣ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን መቀበል መረጠ። ከግብፅ ሀብት ይልቅ ስለ ክርስቶስ መከራን መቀበል እጅግ የሚበልጥ ሀብት መሆኑን ተገነዘበ፤ ወደ ፊት የሚቀበለውን ብድራት ከሩቅ ተመልክቶአልና። የንጉሡን ቊጣ ሳይፈራ ግብፅን ለቆ በእምነት ወጣ፤ የማይታየውንም እንዳየው አድርጎ በመቍጠር በሐሳቡ ጸና” (ዕብራውያን 11:24-27)።

እንደ ጥንቱ ሙሴ ብድራቱን ከሩቅ የተመለከቱት ሮላንድና በርጊታ ድሎት የሞላበትንና የሚሞቀውን ቤታቸውን ሸጠው ወደ ማያውቁት አገር ሄዱ። ሆኖም በዕውር ድንብር አልተጓዙም። ሴራሊዮን ሲደርሱ የተቀበላቸው መድኃኒዓለም ስለ ሥጋ ደዌ በጥልቅ ያውቃል። ለምጻሞችን በገሊላ ይዳስስና ይፈውስ የነበረው ጌታ ለሮላንድ አዳዲስ የቀዶ ጥገና ጥበብ ሰጠው። ጌታ ክርስቶስ ጥንት ለምጻሞች ከፈወሰ በኋላ ወደ ቤታቸው በደስታ እንዲመለሱ ያደረግ ነበር። በዚያው ደግነቱ ደግሞ በአፍሪቃ ታመው የኑሮ መመሳቀል ያስጨነቃቸውን በማቋቋም ሥራ ላይ በርጊታን አሰማራት።

ወደ ኢትዮጵያ ሮላንድና በርጊታ ያመጡት የሚታይና የሚጨበጥ ርኅራኄ ነው። ላገኙት ሰው ሁሉ ይሰጡ የነበረው ክብረት የሰማይ አምላክ ቅርብ መሆኑን እንዳይ አድርጎኛል። ከሁሉ በላይ እኔ ለፈራኋቸው የሥጋ ደዌ ሕሙማን ያሳዩት ፍቅር፤ የጽድቅ ፍሬ በዚህች ጨለማ ምድር ላይ መለምለም እንደሚችል መተዛዘን ላቃተን ሁሉ ያስተምራል።

ሮላንድና በርጊታ ከሦስቱ ልጆቻቸው በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ከመልቀቃቸው በፊት ጁሱፉ (adopted son Jusufu) በሚባል ተጨማሪ ልጅ በጉዲፈቻ ተባርከዋል። ከአራቱ ልጆቻቸው 10 የልጅ ልጆችና 2 የልጅ ልጅ ልጆች አፍርተዋል።

አሁን ላይ የበርጊታ ዕድሜ በዘጠናዎቹ ውስጥ ነው። ጤናዋ እንደምትፈልገው ባለመሆኑ የሰው ድጋፍ ቢያስፈልጋትም ከሁሉ በላይ በፍቅር የሚንከባከባት ኃያል አምላክ እንዳላት በጽኑ ታምናለች። በዚህ ዕድሜዋ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለውን በተቻላት መጠን ትከታተላለች። አገራችንን እያንገዳገደ ያለው ክፍፍልና ጥላቻ የቤተክርስቲያን አባላትን ሊለያይ ይችላል የሚል ፍራቻ አላት።

ፍርሃቷን ማገድ የሚችለው በሷና በሮላንድ ውስጥ የነበረው የመድኃኒታችን የክርስቶስ መንፈስ በልባችን ውስጥ ጌታ ሲሆን ብቻ ነው።

ለአገራችን ኢትዮጵያ እና ለቤተክርስቲያናችን ታላቅ ባለውለታ ለነበረው ዶ/ር ሮናልድ ኬዝን
በዘመኑ ወጣቶች የነበርን ለባለቤቱ በርጊታ ኬዝን እና ቤተሰቡ ከፍ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን

ለሰዎች ሁሉ፣ በተለይም ለተጎዱት የሚያዝን ልብ ይስጠን።

ድርባ ፈቃዱ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *