የትዳር ብክነት ወይም ውድቀት የሚወሰነው ገና ከጅምሩ ነው። ትዳር መመሥረት የሚያስቡ ሰዎች ከሁሉ ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ነገር ጉዳዩን ከተራ ውሳኔዎች በላይ መሆኑን በመገንዘብ በጥንቃቄና በጸሎት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ነው።
ሊያስቡበት ከሚገባቸው ነገሮች ዋናው ሊመሠርቱት የሚያቅዱት ትዳር እግዚአብሔር የሚከብርበት ነው ወይ? ብሎ ራስን መጠየቅ ሲሆን እንደ መመሪያ አድርጎ ሊከተሉት የሚገባ ጉዳይ ደግሞ መሠረቱ በተቀደሰ ዓላማ ላይ ብቻ የተመሠረተ እንዲሆን ነው።
ከትዳር ምሥረታው ቀጥሎ ባለትዳሮቹ ግንኙነታቸው ሁሉ እግዚአብሔር የሚከብርበት ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ በጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። ይህንን በተሳካ መንገድ ለማከናወን በየዓመቱ ግንኙነታቸውን በጋራ መገምገምና ማስተካከል ያለባቸውን ማወቅና መተግበር አስፈላጊ ነው።
በትዳር ውስጥ የልጆች በረከት እንዳለ ማወቅና ስለ ልጆቻቸው ማቀድ ያለባቸውን በቅድሚያ ማሰብና ማቀድ ተገቢ ነው። ልጆችን ያለዕቅድ ወደዚህ ዓለም አምጥቶ ለእነርሱም ሆነ ለሌሎች ሸክም እንዲሆኑ የማድረግ ኃላፊነት አልተሰጣቸውም። (Messages to Young people p. 462)
በዚሁ መጽሐፍ ላይ ስለልጆቻቸው የወደፊት ሕይወት ስለትምህርታቸውና ቀጥሎ ስለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ሳያቅዱ መቅረት ማለት ልጆች ተገቢውን ጥንቃቄ ምግብና ልብስ እንዳያገኙ ማድረግ ስለሆነ ወንጀል ነው ይላል።

ሌላው በጣም አሳሳቢና መቀጨት ያለበት የትዳር ሕይወት ጋሬጣ በስሜታዊነት ሠንሰለት መተብተብ ነው። ባለንበት ክፉ ዓለም ስሜታዊነትን እንደመልካም ነገር የሚታይና ተገቢውን ትኩረት እያገኘ አይደለም።
ስሜታዊነት የሥጋን ፍትወታዊ ፍላጎት ለማርካት ሲባል ሊገታ በማይቻል ግፊት መሄድ ሲሆን ምክኒያታዊነትን ቁጥጥርን የማይቀበል አደገኛ አካሄድ ነው። ውጤቱም ስቃይና ሞት ነው።
በዚህ አደገኛ ባህሪ ብዙውን ጊዜ የጥቃት ሰለባዎች የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ጥቃት አድራሾችም በስሜታዊ ወጥመድ ውስጥ ያሉ የገዛ ባሎቻቸው ናቸው። እነዚህ በስም ባሎች ቢባሉም በባህሪያቸውና በአደራረጋቸው በትዳር ጓደኞቻቸው ላይ ጭካኔንና በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ሊደረጉ የማይገባቸውን ድርጊቶችን የሚፈፅሙ ናቸው።
ስሜታቸውን ከማርካት አልፈው ስለ ሚስቶቻቸው የወደፊት ሕይወት ሊገጥሟቸው ስለሚችሉ የኑሮም ሆነ የጤና ችግሮች ደንታ የላቸውም። ከዚህ የተነሳ እናቶች የመከራ ሕይወት እንዲኖሩ ምክኒያት ይሆናሉ። በየዓመቱ ልጆችን በልጆች ላይ መውለድ ለልጆቻቸው የሚሰጡትን ምግብና የሚያለብሷቸውን ልብስ እንዲሁም ለጤናቸው የሚያስፈልጓቸውን ጥንቃቄዎች በማጣት መሰቃየት ወዘተ።
ዓለማችን ይህንንና ይህንን በሚመስሉ ስቃዮች ተሞልታለች፤ ስቃዩን የበለጠ መራራ የሚያደርገው ደግሞ የክርስቲያን ባለትዳሮች በዚህ የስሜታዊነት ሠንሠለት ተተብትበው ማየት ነው።
ከዚህ አደጋ ለመራቅ መሻትን መግዛት ወይም ራስን መቆጣጠር ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባል። በሮሜ 8፡13 ላይ እንዲህ የሚል ቃል አለ “እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና በመንፈስ ግን የሰውነትን (የሥጋን) ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ”።
መሻትን መግዛት የእግዚአብሔር ስጦታ እንጅ በራሳችን ኃይል የምንፈፅመው አይደለም። ታዲያ ምን ያስፈራናል? በዮሐ 3፡34 ላይ ደግሞ “… እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና…” ይላል። ይህ ማለት የሥጋን ፍላጎትና ስሜታዊነትን የምናሸንፍበትን መንፈስ እግዚአብሔር ይሰጠናል። ሲሰጥም አትረፍርፎ ነው። በመንፈሱም የማናሸንፈው ኃጢያት የለም። ምንም ጊዜ ሳናባክን አሁን ይህን እንዲሰጠን እንለምን። ከልብ የነገሩትን የሚሰማ የለመኑትን የሚሰጥ አምላክ መንፈሱን አትረፍርፎ ይሰጠናል። ስሜታዊነታችንንም አሸንፈን ለትዳር ጓደኛችንና ለልጆቻችን በረከት እንሆናለን።
ፓስተር አገኘሁ ወንድም










