giziew.org

ታላቁ ውዝግብና የኢያሱ ጥያቄ

“ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ?” መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ነው ወይስ አይደለም? መልሱስ ምን ይነግረናል?
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

“እንዲህም ሆነ፤ ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዓይኑን አንሥቶ ተመለከተ፥ እነሆም፥ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ ነበር፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ። ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህን? አለው” (ኢያሱ ፭፥፲፫)።

የጦሩ ገበሬ ኢያሱ ወልደ ነዌ ኢያሪኮን በእጁ ሊያስገባ የድል አፋፍ ላይ ነው። “አሞራ በሰማይ ሲያይሽ” ዋለ እንዲሉ ኢያሱ ኢያሪኮን ሲያያት ነው የሰነበተው፤ ሲያንዣብባት። ግን አንድ በጣም ወሳኝና መቅረት የሌለበት ትልቅ ጉዳይ አለ፤ ኢያሪኮን በእጅ ውስጥ የማስገባት የጦርነት ስትራቴጂ!

ኢያሱ የጦር ጄነራል እንደመሆኑ ይህ ጉዳይ አላሳሰበውም ማለት አይቻልም። ከዚያ ሌላ ደግሞ በቁጥር ፲፪ ላይ የተጻፈልን አንድ ጉዳይ አለ። ስደተኛው ሕዝብ ከንዓን ስለገባ መናው መውረድ ቆሟል። “ከምድሪቱ ፍሬ ከበሉ በኋላ መናው ቀረ፤ ከዚያም በኋላ ለእስራኤል ልጆች መና አልመጣላቸውም”። ስለዚህ ለ፵ ዓመት ሳያቋርጥ ሲሰጣቸው የነበረው የምግብ አቅርቦት ተቋርጧል። በምድሪቱ ላይ መኖራቸው የማያጠራጥር ብቻ ሳይሆን የግድም ነው።

ግን ጠላትን የማሸነፊያ ስትራቴጂ፤ የጦር ስልት፤ ሎጂስቲክስ፤ … ምንም የለም።

በዚህ መካከል ነው አንድ አስደናቂ ነገር የሆነው፤ ቃሉም ሲነግረን፤ “እንዲህም ሆነ፤ ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዓይኑን አንሥቶ ተመለከተ፥ እነሆም፥ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ ነበር፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ። ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህን? አለው” (ቁጥር ፲፫)።

“ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ?” መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ነው ወይስ አይደለም? መልሱስ ምን ይነግረናል?  

ጥያቄው ትልቅ ችግር እንዳለበት የተሰጠው መልስ ይነግረናል፤ ተጠያቂው ሲመልስም “አይደለሁም” አለ (ቁጥር ፲፬)። ለምን አይደለሁም አለ? ለምን “ከእናንተ ወገን ነኝ” አላለውም? ወይም ቢያንስ ለምን “ከጠላቶቻችሁ ወገን አይደለሁም” አላለም?

በብሉይ ኪዳን የሚካሄዱ ጦርነቶች በአማልክት መካከል የሚካሄዱና የትኛው አምላክ በጦርነት ድል አድርጎ የበላይ ይሆናል የሚባልበት የአማልክት ግጭት ነው። ፍልስጤማውያን ከእስራኤላውያን ጋር ተዋግተው ያሸነፉና ታቦቱን የማረኩ ጊዜ ወስደው በአምላካቸው ዳጎን ቤት ነበር ያስቀመጡት (፩ኛ ሳሙኤል ፭፡፪)።  

ጣዖታት ከብረትና ከእንጨት የተሠሩ ተራ ምስሎች ሳይሆኑ እርኩሳን መናፍስት፣ አጋንንትና የሰይጣን መለያዎች ናቸው። እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ሲላቀቁ እግዚአብሔር የተናገረው “በግብፅም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ” በማለት ነበር (ዘጸአት ፲፪፥፲፪)።

በዘሌዋውያን ፲፯፥፯ እና ዘዳግም ፴፪፥፲፯ ደግሞ መስዋዕታቸውን ለሰይጣናት (ለአጋንንት) ነው የሚሰውት ይላል እግዚአብሔር። ሐዋርያው ጳውሎስም አሕዛብ መስዋዕት የሚያቀርቡት ለአጋንንት ነው ይለናል (፩ኛ ቆሮንቶስ ፲፥፳)። ስለዚህ የእስራኤል ውጊያ “የእኛና የእነርሱ” ጉዳይ ሳይሆን የእግዚአብሔርና የከሳሹ ሰይጣን ነው።

ስለዚህ በማንኛውም ጦርነት ስትራቴጂ ነዳፊው፣ አዋጊው፤ ተዋጊው በሰልፍ ኃያል የሆነው የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። ለእስራኤል የተነገረው ጸጥ ብሎ የእግዚአብሔርን ክንድ መመልከት፤ ሥራውን ማድነቅ ብቻ ነው (ዘጸአት ፲፬፥፲፫-፲፬)፤ በቀይ ባሕርም፣ በዮርዳኖስም፣ በኢያሪኮም የታየው ይኸው ነው። ለዚህም ነው መላሹ ሲናገር “እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ” ነኝ ያለው። ግን ለምን በዚህ መልኩ ራሱን መግለጽ አስፈለገው? ለምን የጦርነት ስሙን ለኢያሱ ነገረው?

ኢያሪኮ የጨረቃ ሴት አምላክ የአስታሮት ዋና መመለኪያ የርኩሰት ማዕከል ነበረች (አበውና ነቢያት 487.2)። በከንዓን አካባቢ ከምትታወቅባቸው መለያዎቿ አንዱ የጦርነት አምላክ በመባል ነው። አሁን ጦርነቱ የማን እንደሆነ ግልጽ እየሆነ የመጣ ይመስላል። እንግዲህ በዚህ መካክል ነበር እንግዲህ ኢያሱ “ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ?” በማለት የጠየቀው!

እግዚአብሔር ደመኛ ስለሆነና ከነዓናውያንን ሊያጠፋቸው ስለፈለገ ሳይሆን ስላልፈለጉትና ሕይወትን እምቢ ስላሉ ምርጫቸውን ነው ያከበረው። ሕይወትን የናቀና አልፈልግም ብሎ አሻፈረኝ ያለ የሕይወትን ምንጭ ነው አልፈልግም የሚለው። የሕይወትን ጌታ አልፈልግም ብሎ በሕይወት መኖር ደግሞ የማይቻል ነው።

ጨለማና ብርሃን አብሮ መኖር አይችልም። ጨለማ ለብርሃን ቦታ መልቀቁ የግድ ነው። መብራት ሲበራ ብርሃኑ ጨለማውን በየሥርቻው እያሳደደ አይደለም የሚያጠፋው፤ ወይም ጨለማውን አይበቀለውም፤ የብርሃን መከሰት ጨለማን እንዳይኖር ያደርጋል። ጨለማን መምረጥ ደግሞ ጥፋት ያመጣል። ለዚህ ነው በመጽሐፍ ቅዱስ የምናነበው ውጊያ ሁሉ የታላቁ ውዝግብ/ተጋድሎ አካል ነው የሚባለው።

ውጊያው “በእኛና በእነርሱ” መካከል አይደለም። ውጊያው ዩኒቨርስ ዓቀፍ በክፉና በደግ፤ በብርሃንና በጨለማ፤ በእግዚአብሔር ባሕርይና በሰይጣን ከሳሽነት መካከል የሚደረግ እዚህ ምድር ያልተጀመረ ታላቅ ውጊያ ነው።

ውጊያው የኢያሱና የእነዚያኛው ጦር ጀነራል፤ ወይም የእስራኤልና የአሕዛብ አይደለም። “የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ” ሆኖ የመጣው ራሱ መድኃኒዓለም በዚያ ቦታ የተገኘው ውጊያው የራሱ ስለሆነ ነው፤ ከምድራዊ ጉዳይ የላቀ አጽናፈ ዓለሙን (ዩኒቨርስን) የሚመለከት ታላቅ ውጊያ!

እግዚአብሔር ለእስራኤልና እነ ለነኢያሱ ስለወገነ አይደለም መጥቶ እየተዋጋላቸው ያለው። ወይም አረማውያኑን ስለሚጠላቸውና ሊያስወግዳቸው ስለፈለገ አይደለም ሊደመስሳቸው የመጣው። የእግዚአብሔር “ወገንተኝነት” በእኛ ጠባብ አእምሮ ሲመዘን ጥያቄያችን “ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ?” ይሆናል።

ከዚህ ይልቅ ግን “እኔ ከእግዚአብሔር ወገን ነኝ ወይስ አይደለሁም?” ብለን ራሳችንን መጠየቅ ሲገባን ራስን የአምላክ ወገን አድርጎ ሌሎችን በፍረጃ “ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ?” እያልን እንጠይቃለን። ይህንንም የምንለው በእርግጠኛነት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው ብለን ከማመን የተነሳ ብቻ ሳይሆን እርሱ ከእነርሱ ጋር አይደለም በሚል ስሑት አስተሳሰብም ጭምር ነው።

ቤተሰባዊ፣ ደማዊ፣ ብሔረሰባዊ፣ አገራዊ፣ ቤተ ክርስቲያናዊ፣ አጥቢያዊ፣ ኮሚቴያዊ፣ ሚኒስትሪያዊ፣ ወዘተ ማንነት እየፈጠርንና ሰዎችን ሳጥን ውስጥ እያስገባን ከእኛ ጋር ነህ ወይስ ከእነሱ በማለት እንቦድናለን። በጣም ዋልታ ረገጥ የሆነ ጽንፈኛ አመለካከት!

ስለዚህ በክርስትና ሕይወታችን እኛና እነሱ ጨዋታችንን እናቁምና ትክክለኛውን ጥያቄ እንጠይቅ። ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህን ሳይሆን መጠየቅ ያለብን “እኔ ከማን ጋር ነኝ ከፈጣሪዬ ወይስ ከከሳሹ?” የሚለው ነው። ይህ ደግሞ ዕይታን የሚያጠራና ወደ ትክክለኛ ውሳኔ የሚወስድ ይሆናል።

ኢያሱ የተሰጠው መልስ ጥያቄውን አስተካከለለት፤ ብዥታውን አጠራለት፤ አምልኮውን መስመር አስያዘለት፤ ውጊያውን አሸነፈለት። “ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደና” እንዲህ ሲል ጠየቀ፤ “ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድር ነው?” (ቁጥር ፲፬)።

ስለዚህ ጥያቄያችንን ማስተካከያ እናድርግበት፤ ከኢያሱ እንማር፤ “ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ?” ብለን ከመጠየቅ ይልቅ በግምባራችን ተደፍተን እየሰገድን “ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድር ነው?” ብለን የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ የሆነውን ስለ ውጊያው እንጠይቀው!

“እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፥ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” (መዝሙር ፴፬፤፲፰)።

ጥበበሥላሴ መንግሥቱ


የቅርብ ጽሁፎች

በ Facebook ይከተሉን

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *