giziew.org

“ለፍላፊው” ማነው?

በምኩራብም፣ “በየቀኑ በገበያ” የሚያገኛቸውን ሲያነጋግር በመጨረሻ ዋንኞቹን ፈላስፋዎች አገኛቸውና እነሆ ወንጌል፤ የምስራች አላቸው። እነርሱ ግን “ምስር ብላ” አላሉትም፤ ይልቁንም “ለፍላፊ” ብለው አዋረዱት...
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

በሄደበት ሁሉና ባገኘው አጋጣሚ ስለ ክርስቶስ የሚመሰክረው ሐዋርያው ጳውሎስ በሁለተኛው ሐዋርያዊ ጉዞ አቴና (አቴንስ) ላይ ይገኛል። ወደ ቆሮንቶስ ከተማ ከመሄዱ በፊት በአቴና ጢሞቴዎስን እና ሲላስን እየጠበቀ ነው።

በአቴና ሐዋሪያው እንደ ቱሪስት ወጣ ብሎ ከተማዋን መቃኘት ጀመረ። የሚያየው ነገር አልጥም አለው፤ ከቦታ ወደ ቦታ እየተሻሻለ ይሄዳል ሲል እንዲያውም ባሰበት፤ አቴና የጣዖት ማሳ ነች። “በከተማው ጣዖት መሙላቱን እየተመለከተ መንፈሱ ተበሳጨበት” (የሐዋ. ሥራ 17፡16)።

ለነዚህማ ወንጌልን ደህና አድርጌ ነው የምነግራቸው በማለት በምኩራብም፣ “በየቀኑ በገበያ” የሚያገኛቸውን ሲያነጋግር በመጨረሻ ዋንኞቹን ፈላስፋዎች አገኛቸው። ከኤፊቆሮሳውያን እና ከኢስጦይኮች አንዳንዶቹን አግኝቶ እነሆ ወንጌል፤ የምስራች አላቸው። እነርሱ ግን “ምስር ብላ” አላሉትም፤ ይልቁንም “ለፍላፊ” ብለው አዋረዱት።

“ለፍላፊ” የሚለው ቃል በተጻፈበት የግሪክ ቋንቋ “ጥሬ ለቃሚ” ማለት ነው። የግሪክ ፈላስፋዎች አንድ ሰው በእነርሱ ልክ የማይፈላሰፍ ግን የባጥ የቆጡን የሚዘባርቅ መሆኑን ሲያዩና ሲሰሙ የሚጠቀሙበት ቃል ነው። ጥሬ ለቃሚ ወፍ በየገበያው የወዳደቀ ጥራጥሬ የምትለቅም እና በዚያ የምትኖር ነች።

አቴናውያኑ ፈላስፎች ጳውሎስንም ያሉት ከየቦታው የለቃቀመውን ልክ ትልቅ ዕውቀት፣ ምጡቅ ፍልስፍና እንዳለው አድርጎ ያወራል ነበር። በዘመናችን አነጋገር፤ አንድን የዘርፉ ባለሙያ፣ በትምህርቱ የዶክትሬት ዲግሪ ያለውን ከፌስቡክ፣ ከቴሌግራምና ከቲክቶክ ባጭሩ ከማኅበራዊ ሚዲያ የለቃቀመውን እንደ ራሱ ዕውቀት አድርጎ የሚያወራ ብሎ እንደ መስደብ ነው።

ፈላስፎቹ ይህንን ያሉበት ዋናው ምክንያት ሐዋርያው ስለ “ኢየሱስና የትንሣኤው ወንጌል” ስለ ሰበከላቸው ነው (ቁጥር 18)። ከፈላስፎቹ ንጽረተዓለም አኳያ ጳውሎስ የተናገረው ስለ ሁለት አማልክት ነበር፡- ኢዬሱስ (Ἰησοῦν, g2424) እና አናስታሲስ (ትንሣኤ፣ ἀνάστασιν, g386)። በግሪኩ ትርጓሜ መሠረት፤ ኢየሱስ የወንድ ጾታ ስም ነው፤ አናስታሲስ ደግሞ የሴት ጾታ ስም ነው።

ለአቴናውያኑ ፈላስፎች ጳውሎስ የሚናገረው የመሰላቸው ስለ አማልክት ነበር፤ አንዱ የወንድ ጾታ ያለው (ኢዬሱስ)፣ ሌላዋ ደግሞ የሴት ጾታ ያላት (አናስታሲስ)። ለዚህም ነው በቁጥር 18 ላይ “ስለ አዳዲስ ባዕዳን አማልክት የሚናገር ይመስላል” ያሉት።

በመጨረሻም እስቲ ጉዱን እንየው ብለው ይኼ ወሬ ለቃቃሚ፣ ለፍላፊ፣ የሚናገረውንም የማያውቅ ዕድል እንስጠውና እንዲህ እያምታታ ስለጠቀሳቸው አማልክት እንስማው በማለት አርዮስፋጎ ላይ ዲስኩር እንዲሰጥ ጋበዙት። ግን ማነው “ለፍላፊ” የነበረው? መጽሐፍ የሚለውን እንይ፤

ጳውሎስ ስለ ራሱ ሲናገር፤ “በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ (በታላቁ መምሕር ገማልኤል የተማርሁ) ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ” ይላል (ፊልጵስዩስ 3፡5-6)።

ጳውሎስን “ለፍላፊ” ስላሉት አቴናውያኑ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፤ “የአቴና ሰዎች ሁሉና በዚያ የኖሩ እንግዶች አዲስ ነገርን ከመናገርና ከመስማት በቀር በሌላ ጉዳይ አይውሉም ነበርና” (የሐዋ. ሥራ 17፡21) – ማኅበረ ለፍላፊ!

በሐዋርያት ሥራ 17፡18 ላይ የተጠቀሰውን “ለፍላፊ” የሚለውን ተመሳሳይ የግሪክ ቃል ባይጠቀምም ለጢሞቴዎስ ሲመክረው ሐዋርያው እንዲህ ብሎታል፤ “ጢሞቴዎስ ሆይ፥ በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ፥ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ”። መልዕክቱ ለኛም ነው!      

ጥበበሥላሴ መንግሥቱ

የቅርብ ጽሁፎች

በ Facebook ይከተሉን

Share Your Thoughts

Your email address will not be published. Required fields are marked *