በገነት ውስጥ ብዙ ዓይነት እንስሶች ነበሩ። ከአራዊት ሁሉ ግን አንድ የተለየ ፍጡር ነበር። “እባብ እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠራቸው የዱር አራዊት ሁሉ ተንኰለኛ ነበረ” (ዘፍጥረት 3:1)።
የዘፍጥረት መጽሐፍ በተጻፈበት የዕብራይስጥ ቋንቋ “ተንኮለኛ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል “ዓሩም” የሚል ሲሆን፤ “ብልጥ”፣ እንዲሁም “ጠቢብ”፣ ወይም “አዋቂ” በሚሉት ቃላትም ሊተረጎም ይችላል።
ኃጢአት ባልነበረበት ዓለም ውስጥ ከክፋት የጸዳ ጥበብ እንደነበረ ማወቁ ወሳኝ ነው። በተጨማሪ ያ ጥበብ በርኩሰት ሲጠለሽ፤ ወደ ተንኮል ሊለወጥ እንደሚችል መረዳት ዛሬ ለምንኖርባት ዓለም እንቆቅልሽ የሆኑ መሠረታዊ ችግሮች መንስኤው ምን እንደሆነ ስለሚገልጥ ነው።
በአይሁድ አስተሳሰብ ጥበብና ውበት የተቆራኙ ናቸው። ጠቢቡ ሰሎሞን ይህንን ሲገልጥ እንዲህ ይላል፣ “ጥበብን አግኛት፤ … በራስህ ላይ ሞገሳማ አክሊል ትደፋልሃለች” (ምሳሌ 4:7፣9)።
የጥበብና የውበት ሁሉ ምንጭ የሰማይ አምላክ ነው። ስለሆነም ሁሉን መልካም አድርጎ ሲፈጠር እባብንም ከአራዊት ሁሉ ውብና ብልህ አድርጎ ሠርቶ ነበር ማለት ነው።

ዘፍጥረት ምዕራፍ 3 ላይ ያለውን ውብና ብልህ እባብ ቀረብ ብለን ስንመረምር ተራ እባብ አለመሆኑን እንረዳለን። ሔዋንን የቀረበበት መንገድ ክፋትና ብልጠት የተሞላበት ስለነበር እባብ የተገለጸበት ቃል “ተንኮለኛ” የሚል ትርጉም ቢሰጠው አይገርምም። ሆኖም ይህ ውብ እንስሳ ክፋት ባልነበረበት ገነት ውስጥ ተንኮልን እንዴት ተማረ? ብለን እንድንጠይቅ ይጋብዛል። በመቀጠል ይህ እባብ ከሔዋን ጋር በሰው ልሳን ሲነጋገር ይታያል። እንስሳት የሰው ንግግር ሰምተው ሲታዘዙ ማየት ያስገርማል፤ ምን ያህል ብልሃት እንዳላቸው ያሳያል። አፋቸውን ከፍተው ሲናገሩ መስማት ግን ያስደነግጣል።
“ሴቲቱንም፣ ‘በእርግጥ እግዚአብሔር ፣ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉ” ብሎአልን?’ አላት” (ዘፍጥረት 3:1)።
ንግግር የሃሳብ መግለጫ ነው። ከምንሰማቸው ቃላት በስተጀርባ መሪ ልብ ተሰውሯል። ይህን ካወቅን እባብ ሔዋንን የጠየቃት ጥያቄ እባብን ወይም አራዊትን የማይመለከት ጉዳይ መሆኑ እጅግ ይገርማል። በገነት ስላለው ጤናማ አየር ወይም ስለ ገነት የመልከዓ ምድር ምቾት ቢያወራ መደነቃችን ይቀንስ ነበር። ከማውራቱ ባሻገር ግን ስለ እግዚአብሔር አስተዳደር ጥያቄ ማንሳቱ ከጥያቄው በስተጀርባ የማን ልብ እንዳለ ይጠቁማል።
ከላይ በዘፍጥረት 3፡1 የተጠቀሰው የእባቡ ጥያቄ ጥርጣሬ የሚያጭርና ቶሎ ለመመለስ የሚያጓጓ ነው። ለሔዋን አዛኝ በመምሰል ፈጣሪ ደስታ ከልካይ መሆኑን ማሰብ እንድትጀምር መራት። ሔዋን የእግዚአብሔር ስም እንዳይጎድፍ በምታደርገው የመከላከል ርብርብ የተሸናፊነት ስነልቦና ውስጥ ገባች።
እባቡ እውነትም ተንኮለኛ ነበር፤ ተንኮሉ ግን ተራ የእንስሳ ተንኮል አልነበረም። ሔዋንን በጥርጣሬ ሸብቦ ወደ ክህደት የሚያስገባ ተንኮል መሆኑን ስናይ ከሰው ብልሃትም ያለፈ ረቂቅ ነገር እንዳለበት ያስታውቃል።
“ሴቲቱም እባቡን እንዲህ አለችው፤ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ‘በአትክልቱ ሥፍራ መካከል ከሚገኘው ዛፍ ፍሬ እንዳትበሉ፤ እንዳትነኩትም፤ አለበለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሏል’” (ዘፍጥረት 3:2-3)።
እባብ ጥያቄውን ያነሳው ካለማወቅ ወይም ከየዋህነት የተነሳ ቢሆን የሔዋን መልስ አጥጋቢ ይሆንለት ነበር። እባቡ ግን እጅግ ተንኮለኛ ነበር፤ ድብቅ ዓላማ ነበረው። መክፈቻው ላይ ያነሳው ጥያቄ ለእኩይ ፍላጎቱ መሸጋገሪያ ነበር።

“እባቡም ሴቲቱን እንዲህ አላት፤ ‘መሞት እንኳ አትሞቱም፤ ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው’” (ዘፍጥረት 3:4-5)።
እባብ ሞትን በለስላሳ አንደበቱና ማራኪ ውበቱ ደብቆ ነው ሔዋንን የቀረበው። አምላክ ላይ ስለማመጽና የኃጢአት መጨረሻ ስለሆነው ሞት በእውነት ማውራት ቢጀምር ሔዋንን ሊያስደንግጣት ይችል ነበር። ስለሆነም ጥያቄውን የዋህ መልክ አስይዞ ሔዋን ራሷ ስለ አመጽና ሞት ግኑኝነት እንድታነሳ መንገድ ከፈተላት።
ቀጥሎም እግዚአብሔርን አለመታዘዝና ሞት ግኑኝነት እንደሌላቸው ተናገረ። “መሞት እንኳ አትሞቱም” በማለት ሞትን ካቀለለ በኋላ፤ ክህደት ሰውን ረቂቅ የሆነ እውቀት አላብሶ ወደ አምላክነት ከፍ እንደሚያደርግ ተናገረ። በሔዋን ላይ ስነልቦናዊ የበላይነት እንደያዘ ግልፅ የሚሆነው የንግግሩ ውጤት ሲታይ ነው። ሞትን እንደ ቀልድ ንቆ ሔዋንን ወደ እግዚአብሔር ከፍታ በቀላሉ የማድረስ ዕውቀት የያዘ መስሎ ሲቀርብ የሔዋንን የማወቅ ጉጉት ገዛ።
“ሴቲቱ የዛፉ ፍሬ ለመብል መልካም፣ ለዐይን የሚያስደስትና ጥበብንም ለማግኘት የሚያጓጓ እንደሆነ ባየች ጊዜ፣ ከፍሬው ወስዳ በላች፤ ከእርሷም ጋር ለነበረው ለባሏ ሰጠችው፤ እርሱም በላ” (ዘፍጥረት 3:6)።
እንዲህ ዓይነቱ የማሳመን ችሎታ እውን ከእንስሳ የፈለቀ ነው? ለመሆኑ ይህ ሔዋንን ያሳሳተው ተንኮለኛ እባብ ማን ነው? የእንስሳ መልክ ይዞ ከሔዋን ጋር ያወራው ማን ነው?
ባለ ራዕዩ ዮሐንስ በሰማይ ጦርነት ከተደረገ በኋላ አንድ እባብ ወደ ምድር መጣሉን ይናገራል።
“ታላቁ ዘንዶ፣ የጥንቱ እባብ ተጣለ፤ እርሱም ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው፣ ዓለምን ሁሉ የሚያስተው ነው፤ እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ” (ራዕይ 12:9)።
ሔዋን በየዋህነቷ ለዘላለም እንዳትኖር በተንኮሉ የጠለፋት ሰይጣን ነው። ይህ እባብ ጥንት በኃጢአት ከመውደቁ በፊት ከመላዕክት ሁሉ በላይ ውብና አዋቂ የነበረው የብርሃን ፍጡር ነው። ራሱን እጅግ በመውደዱና ለመመለክ ስለፈለገ፤ አብረውት የነበሩትን መላዕክት ለማሳሳት ሲል ፈጣሪ የሰጠውን ጥበብና ውበት ተጠቅሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ውሸትና ተንኮልን ፈጠረ። ሆኖም ቀድሞ እውቀትና ውበትን የተሞላ ስለነበር ተንኮለኛ ባህሪውን ለማጋለጥ እጅግ ከባድ ነበር።
ሔዋንን ለማሳሳት ዲያብሎስ በገነት ካሉት እንስሳት ሁሉ እባብን መጠቀሙ አይገርምም። የገነቱ እባብ እንደዛሬ በምድር እየተሳበ፣ ሰዎችንና እንስሳትን አስደንግጦ የሚናደፍ አልነበረም። ዲያብሎስ ከመውደቁ በፊት ከመላዕክት ሁሉ በውበትና በጥበብ ይልቅ እንደነበረው፤ እባብም ከእንስሳት ሁሉ ውብና ብልህ ፍጡር ነበር። ሰይጣን ለውስብስብ ተንኮሉ ተራ እንስሳ መጠቀም ዓላማውን ሊያጋልጥ እንደሚችል ስለገመተ፤ በሚያምርና በገነት ውስጥ በብልሃቱ እውቅና በነበረው እባብ ተመስሎ ለመቅረብ ወሰነ።

ዲያብሎስ እባብን አሳምኖ ወይም አስገድዶ አልተጠቀመበትም። አምላክ የፈጠረው ሁሉ መልካም እንደነበር ቃሉ ይናገራል፤ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ” (ዘፍጥረት 1:31)። መልካም የነበረው ተፈጥሮ በገነት የነበሩትን እንስሳት ያጠቃልላል። ስለሆነም እንስሳት ከሰይጣን አምባገነናዊ ቁጥጥር ውጭ ነበሩ። ታዲያ ዲያብሎስ እንዴት በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን አሳሳታት?
ሰይጣን ራሱ ወደ እባብ ለውጦ ወይም ተመስሎ ነው ሔዋንን ያነጋገራት። ሰይጣን ተለዋዋጭ ውጫዊ ባህሪዎችን በመላበስ የማሳሳት ዓላማውን ዛሬም እንደሚያሳካ ቃሉ ሲናገር እንዲህ ይላል፤
“ነገር ግን እባብ ሔዋንን በተንኰል እንዳሳታት ምናልባት የእናንተም ልቡና ተበላሽቶ ለክርስቶስ ካላችሁ ቅንነትና ንጽሕና እንዳትወሰዱ እሠጋለሁ … ይህም የሚያስደንቅ ነገር አይደለም፤ ምክንያቱም ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋውጣል” (2 ቆሮንቶስ 11:3፣14)።
ዲያብሎስ እግዚአብሔርን ይጠላል። ጥላቻውን በግልፅ ቢያሳይ ግን ብዙ ተቀባይነት እንደማያገኝ ጠንቅቆ ያውቃል። ስለሆነም ሰዎችን ለመተናኮል ዘመድ ወይም አዛኝ ወዳጅ መስሎ መቅረቡን ይመርጣል። ላለፉት ስድስት ሺህ ዓመታት በዚህ ስልት የሰውን ዘር እያሳሳተ ወደ ሞት ገደል አስገብቷል።
ሰይጣን እንደ እስስት ይለዋወጣል። ለሔዋን በተናገረበት ጣፋጭ አንደበት ዛሬም የሚሰሙትን ያሳስታል። በገሃድ ሰይጣን ሆኖ ቢገለጥና፣ ሰዎችን ለርኩሰት ቢያነሳሳ በድንጋጤ እንደሚሸሹት ያውቃል። ክህደትና አመጽ ክፉ መሆናቸውን ብዙዎች በልምድና በምርምር ደርሰውበታል። ስለሆነም ዲያብሎስ መልኩን ለተቀባይ አሳምሮ መቅረቡን ተክኖታል።
ሰይጣን በመጠጥ ቤቶች ሁካታና በጦርነት እልቂት ውስጥ መንገሱ አይደንቅም። በፈላስፎች፣ በሳይንስ ምሁራንና በፖለቲካ መድረኮች ላይ ከፍ ማለቱ ብዙ አይገርም ይሆናል። በምንኖርበት ዘመን ግን ሰይጣን የክርስትና ልብስ ለብሶ፣ ቃለ እግዚአብሔርን በርዕቱ አንደበቱ እየጠቀሰ መስበክ እንደሚችል ብዙዎች አያውቁም። ባለማወቃቸውም ምክንያት ቤተክርስቲያን ውስጥ ብዙዎች በየዋህነት የእባቡን ምክሮች አጣጥመው እየዋጡ ነው።
ጥንት ጳውሎስ ይህንን ፈርቶ የቆሮንቶስን ሰዎች አስጠንቅቆ ነበር። “እንደነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን የሚለዋውጡ፣ ሐሰተኞች ሐዋርያትና አታላዮች ሠራተኞች ናቸው” (2 ቆሮንቶስ 11:13-14)።
በመጨረሻው ዘመን ሐሰተኛ ሐዋርያት እንደሚመጡ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ተንብይዋል። በምንኖርበት ዘመን ይህ ትንቢት አገራችን ውስጥ ሲፈጸም እያየን ስለሆነ ለማመን አይከብድም። የብልፅግናን ወንጌል የሚሰብኩ ሐዋርያት የኢትዮጵያን ቀልብ ገዘተዋል። እውነቱ ግን የክርስቶስን ምድራዊ ድህነትና ስቃይ በመካድ፤ ዓለማዊ ምቾት የጽድቅ ማሳያ መሆኑን የሚሰብኩ ሁሉ የጥንቱ እባብ ሐዋርያት መሆናቸው ነው። እግዚአብሔር ከፈተናና ከሕመም ነጻ የሆነ ምድራዊ ሕይወት እንድንኖር ስላዘዘ በስሙ በሽታን ሁሉ እንፈውሳለን የሚሉ መሃይም ሰባኪዎች፤ ታመውና ታርደው በሞቱት ነቢያትና የዕምነት ሰማዕታት ላይ የሚያላግጡ የዲያብሎስ ልጆች መሆናቸውን ሰዎች ቢያውቁ ከብዙ ሐዘን ይተርፉ ነበር።

ሔዋንን ያደናገራት ድንቅ ነገር ተናጋሪ እባብ ማግኘቷ ነው። አእምሮዋ ድንቁን ነገር ሲያሰላስል እባብ እንደ አምላክ መሆን ትችያለሽ የሚለውን ሃሳብ አቀረበላት። እባብ መናገር ከቻለ እሷ እንደ እግዚአብሔር የማትሆንበት ምን ምክንያት አለ ብላ ይሆን?
ካሉበት ተራ ሕይወት እጅግ ወደላቀ የጥቅም ከፍታ የመሻገር መብት እንዳላቸው ሲነገራቸው ለማመን የሚቸኩሉ ብዙ ክርስቲያኖች አሉ። ይህንን ውሸት የሚሰብከው ሰው ደግሞ እንደ እባቡ ድንቅ አድራጊ ሲሆን የበለጠ ፈታኝ ነው።
ሔዋን ስትፈተን ከኃጢአት የፀዳ መልካም ዓለም ውስጥ ትኖር ነበር። አምላክ ውብ አድርጎ በፈጠራት ምድር ላይ ንግሥት ነበረች። ያጣችውና የጎደለባት ነገር አልነበረም። ሆኖም ምናባዊ የሆነ ጥቅም ለማግኘት ስትል የነበራትን ክብር አጣች። ዓለማችንም የአበሳ ገደል ውስጥ ተቀርቅራ እኛ የመከራው ገፈት ቀማሾች ሆነናል።
ኃጢአት ሰውን አወናብዶ ያዋረደና ዕድሜ ያሳጠረ ክፉ ነገር ነው። በአመጽ የተወጠረው የሰው ልብ ይህንን ውርደት መቀበል ይሳነዋል። ለማምለጥ ሲል አሁንም ወደ አምላክ ከፍታ ለመድረስ ባገኘው ዕድል ሁሉ ይንጠራራል። ንስሐንና ለእግዚአብሔር ሕግጋት መገዛትን እንደ ሽንፈት የሚቆጠረው የሰው ልብ፤ በዘመናት ሁሉ ከፈጣሪው ፈቃድ ጋር ሲዋጋ ቆይቷል። ታዲያ የዚህ ውዝግብ መጨረሻ ምንድነው?
ባለ ራዕዩ ዮሐንስ በዘመን መጨረሻ ስለሚሆነው ሲተነብይ እንዲህ ይላል፣ “ዓለም በሙሉ በመደነቅ አውሬውን ተከተለው። ሰዎችም ለዘንዶው ሰገዱለት” (ራዕይ 13:3-4)።
ሰዎች ለዘንዶው የሚሰግዱለት በዘንዶነቱ ሳይሆን የብርሃን መልአክ በመምሰሉ ነው። የሰዎች ልብ ውስጥ እያደገ ያለው የአመጽ መንፈስ ለሰይጣን ወለል ብሎ የተከፈተ በር ነው። በተጨማሪ ዲያብሎስ ለስድስት ሺህ ዓመታት ሰዎችን በማታለል ያካበተው ልምድ አለ። ይህ የመጨረሻው ዘመን ፈተና ሔዋን ከገጠማት ውሸት የረቀቀ መሆኑን ይጠቁማል።
ሔዋን የተፈተነችው እግዚአብሔርን እንዳታምነው ነው። ክህደቷን ለማሳየት ደግሞ ትዕዛዙን ተላለፈች። ይህ የማይቀየር የዲያብሎስ አሠራር መሆኑ ዛሬም ይታያል። ሰዎች ክህደታቸውን ሕግጋቱን በመጣስ እንዲገልጡ ሰይጣን ቤተክርስቲያን ውስጥ ሆኖ በዘመኑ “ወንጌላውያን” እየሰበከ ነው። ብዙ ቤተ አምልኮዎች በድንቅ፣ በተዓምራትና በሚጥሙ መዝሙሮች የታጀቡ የክህደት ገደሎች ሆነዋል። የአምላክን ትእዛዛት መታዘዝ እንደማያስፈልግና፤ ፀጋው በሚሰጠው “ነፃነት” ከርኩሰት ጋር መኖር ነውር እንደሌለው ብዙዎች የሚያምኑት ስለተሰበከላቸው ነው።
ሔዋን ባለመታዘዝ አልተጠቀመችም። ዛሬም አለመታዘዝ ምንም ጥቅም የለውም። ይልቁንም በዘመኑ መጨረሻ ለሚመጣው ታላቅ ፈተና ተጋላጭ ያደርገናል። ቃሉም ይህንኑ ይላል፤ “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በታረደው በግ የሕይወት መጽሐፍ ላይ ስሞቻቸው ያልተጻፈ የምድር ሰዎች ሁሉ ለአውሬው ይሰግዳሉ” (ራዕይ 13:8)።
በታረደው በግ የሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው የተጻፉላቸው እነማን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ መልሱን ሲሰጥ ይህንን ይላል፤ “የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁና ለኢየሱስም ታማኝ ሆነው በትዕግሥት የሚጸኑ ቅዱሳን” ናቸው (ራዕይ 14:12)።

የእግዚአብሔርን ሕግጋት ማንም ሊያሻሽል ወይም ሊሽር አይችልም። ትእዛዛቱ የሕይወት መሠረት ናቸው። ሰይጣን የአምላክ ትዕዛዛት ተሽረዋል ብሎ ሕዝበ ክርስቲያንን ቢያታልልም፤ ሰው ከአመጽ መንፈስ ሳይላቀቅ ከነርኩሰቱ ሰማይ አይገባም። አሳሳቹ እባብ በብልጠት እያታለለ ሊበልጠን ቢሞክርም ቃሉ የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው እንደሚል በፈሪኻ እግዚአብሔር በምናገኘው ጥበብ ብልጠቱን ልናከሽፍ እንችላለን (ምሳሌ 9፡10)።
ስለዚህ ከሔዋን ስህተት ተምረን ቃለ እግዚአብሔርን ሳናወላውል መታዘዝ ግድ ይላል። ምድራዊ ምቾትና ተዓምራትን መሠረት ያደረገ “ክርስትና” የእባቡ ወንጌል ነው። ሰዎች ከምድር ስቃይና ከሞት ማምለጥ የሚችሉት የእግዚአብሔርን ቃል ጠንቅቆ በመመርመርና በመታዘዝ ብቻ ነው (ሮሜ 2፡13)። የምንድንበት ሌላ ምቹ አቋራጭ የለም (የሐዋርያት ሥራ 4፡12)። መስቀላችንን በትህትናና በንስሐ ተሸክመን ከአሳሳች ወንጌሎች ሁሉ መራቅ አለብን።
በዚህ የመጨረሻ ዘመን የእባቡን ስህተቶች ለመቃወም ማስተዋል ከሚያገኙ ጠቢባን መካከል ያድርገን።
“ብዙዎች ይነጻሉ፤ ይጠራሉ፤ እንከን አልባም ይሆናሉ፤ ክፉዎች ግን በክፋታቸው ይጸናሉ፤ ከክፉዎች አንዳቸውም አያስተውሉም፤ ጠቢባን ግን ያስተውላሉ” (ዳንኤል 12:10)።
ድርባ ፈቃዱ










