giziew.org

ጥቂት ስለ መጀመሪያው ያማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም

አባ አብርሃም ሲተረጉሙ ይጽፉ የነበረው በእጃቸው ሲኾን፣ በርሳቸው የእጅ ጽሕፈት ከዘፍጥረት እስከ ራዕይ ያለው ያማርኛ ትርጉም 9,539 ቅጠል (ገጽ) ኾኗል። የትርጉም ሥራቸውን በ1818 ከፈጸሙ በኋላ...
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

የታሪክ መዛግብት እንደሚያሳዩት የመጀመሪያውን ሙሉ ያማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ የተረጎሙት አባ አብርሃም (ፈረንጆቹ አቡ ሩሚ/አባ ሮሜ ይሏቸዋል) ናቸው። በሕይወታቸውና ሥራዎቻቸው ላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ሊቃውንት አባ አብርሃምን ጎጃም እንደተወለዱ ሲጽፉ አንዳንዶች ደግሞ የጎንደር ሰው ያደርጓቸዋል። የትውልድ ዘመናቸው 1750 እ.ኤ.አ. ገደማ እንደኾነም ይገመታል (በተለይ እስካልተጠቀሰ ድረስ እዚህ ጽሑፍ ውስጥ የሚገኙት ቀናት/ዓመታት በሙሉ እ.ኤ.አ. ናቸው)።

አባ አብርሃም በታሪክ ከሚታወቁበት ነገር አንዱ በጥንታውያን ቋንቋዎች ላይ የነበራቸው ጥልቅ እውቀት ነበር። በ1772 ጎንደር ላይ መጽሐፈ ሄኖክን ከኢትዮጵያ ወስዶ ለምዕራቡ ዓለም በማስተዋወቁ የሚታወቀው ጀምስ ብሩስ አስተርጓሚና መምህር ኾነው እንደሠሩ ይነገራል። በ1778 አካባቢ ከአገራቸው ወጥተው ካይሮንና ቅድስት ኢየሩሳሌምን ጎብኝተው፣ በሶሪያ–አርመን–ፋርስ አድርገው ህንድ እንደደረሱ፣ በዚያም እውቁን ኦሬንታሊስት ሰር ዊልያም ጆንስን ግእዝ፣ ዐማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር እንዳስተማሩት ተጽፏል።  

ወደ አገራቸው ተመልሰው ጥቂት ከኖሩ በኋላ ከዕለታት በአንዱ ቀን ወደ ቅድስት ኢየሩሳሌም በመጓዝ ላይ ሳሉ ካይሮ ሲደርሱ በጠና ታመሙ። ካይሮ የነበረው የፈረንሳይ ቆንጽላ ጽሕፈት ቤትም የሕክምና እርዳታ ሰጥቷቸው በእግዚአብሔር ቸርነት ሊድኑ ችለዋል። ከዳኑ በኋላ የቆንጽላ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ የነበረው አሰሊን (Asselin de Cherville) የጥንታዊ ቋንቋዎች እውቀታቸውን አይቶ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ዐማርኛ እንዲተርጉሙ/ለት ጠየቃቸው፣ ተስማሙ።

ከ1808–1818 ድረስ ለ10 ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ዐማርኛ ተረጎሙ። ትርጉማቸውንም የሠሩት ዐረብኛ መጽሐፍ ቅዱስን ዋና ምንጭ (Vorlage) አድርገው ጎን ለጎን ደግሞ አስፈላጊ ኾኖ ሲገኝ የዕብራይስጡን ማሶራ፣ የሰባ ሊቃናቱን ትርጉም፣ የሲሪያኩን ፔሺታ፣ የግእዙን ትርጉም እና ሌሎችን ጥንታውያን ቅጅዎችን እያመሳከሩ እንደነበረ ተጽፏል። ዋናውን የትርጉም ሥራ ራሳቸው ቢሠሩትም የአሰሊንን እገዛም አግኝተዋል። አሰሊን በነዚያ 10 ዓመታት ዘወትር ማክሰኞ እና ቅዳሜ የቤታቸውን በር ዘግተው ሲተረጉሙ እንደሚውሉ መስክሯል።

አባ አብርሃም ሲተረጉሙ ይጽፉ የነበረው በእጃቸው ሲኾን፣ በርሳቸው የእጅ ጽሕፈት ከዘፍጥረት እስከ ራዕይ ያለው ያማርኛ ትርጉም 9,539 ቅጠል (ገጽ) ኾኗል። የትርጉም ሥራቸውን በ1818 ከፈጸሙ በኋላ ቅድስት ኢየሩሳሌም ደርሰው ወደ ካይሮ እንደተመለሱ በ1819 ከዚኽ ዓለም ድካም ዐርፈዋል።

የአባ አብርሃምን ባለ 9,539 ቅጠል ብራና የብሪታንያና የውጭ አገራት መጽሐፍ ቅዱስ ማሕበርን (British and Foreign Bible Society) ወክሎ ዊሊያም ጆዌት ከአሰሊን እጅ ሚያዚያ 10፣ 1820 በ£1,250 (ፓውንድ ስተርሊንግ) ገዝቶታል። በመጨረሻም ብራናውን ፕሮፌሰር ሳሙኤል ሊ መርምሮት እና ቶማስ ፔል ፕላት አሰናድቶት፤   

  1. አራቱ ወንጌሎች በ1824፣
  2. ሙሉ ሐዲስ ኪዳን በ1829፣
  3. መዝሙረ ዳዊት በ1833፣
  4. አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት 1837፣ እንዲኹም
  5. ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ በ1840 ታትመው ለንባብ በቅተዋል።

የ1840ው እትም የመጀመሪያው ሙሉ እትም ሲኾን የተለያዩ የመጽሐፉ ክፍሎች (መዝሙር፣ ወንጌሎች) እንደገና እየታተሙ ተሰራጭተዋል። በተጨማሪም ጀርመናዊው ክራፕፍ ከዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ጋራ እያመሳከረ የተወሰነ እርማት ካደረገለት በኋላ ከ1871–1873 በሦስት ቅጽ አሳትሞታል። በመጨረሻም በ1886 (1879 በኢትዮጵያ አቆጣጠር) የመጨረሻውና አኹንም ድረስ አገልግሎት የሚሰጠው እትም ታትሟል።  

የመጀመሪያዎቹ ቅጅዎች ለምን መታረምና መሻሻል አስፈለጋቸው? የመጀመሪያዎቹ ቅጅዎች ተሻሽለውና ታርመው ከታተሙት የኋለኞቹ እትሞች ጋራ ሲመሳከሩ መጠነኛ ልዩነት ያሳያሉ። ከልዩነቶቹ መካከል ሦስቱ የሚከተሉት ናቸው።     

  1. አባ አብርሃም በተረጎሙትና በኋላ ታርመው/ተሻሽለው በወጡት እትሞች መካከል ያለው መሠረታዊ ልዩነት የአገባብ/Syntax (በዓረፍተ ነገር ውስጥ ያሉት ቃላት አደራደር ቅደም ተከተል) ነው። ብዙ ጊዜ በግእዝ፣ በዐረብኛና በዕብራይስጥ፣ ግስ (ማሠሪያ አንቀጽ) ከባለቤትና ከተሳቢ ቀድሞ ይመጣል። ባማርኛ ዓረፍተ ነገር ግን ግስ ባለቤትንና ተሳቢን ይከተላል። ለምሳሌ ባማርኛ “አበበ በሶ በላ” እንላለን። በሦስቱ ጉምቱ ሴማውያን ቋንቋዎች ግን መደበኛው የዓረፍተ ነገር ቅርጽ “በላ አበበ በሶ” ነው። የአባ አብርሃም ትርጉም የዓረፍተ ነገሮቹ ቅርጽ ሲታይ ለትርጉማቸው እንደ ምንጭ የተጠቀሙበቱ ዐረብኛው መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉማቸውን እንደተጫነው ያስታውቃል። የመጀመሪያዎቹን ቅጅዎች ያረሟቸው ሰዎች የመጽሐፉ ዓረፍተ ነገሮች ዐማርኛ እንዲመስሉ ብዙ አሻሽለዋቸዋል፣ አኹንም ግን ዓረፍተ ነገሮቹ ሙሉ በሙሉ ዐማርኛ አይመስሉም። ለምሳሌ ዘፍጥረት 1፡1 አባ አብርሃም “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ፈጠረ ሰማይንና ምድርን” ብለው ነው የተረጎሙት። ያረሙት ሰዎች “ፈጠረ”ን ተሳቢዎቹን ተከትሎ እንዲመጣ በማድረግ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” ብለውታል።
  2. ከዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ጋራ እየተመሳከረ ልዩነት ባሳየባቸው ቦታዎች እንዲሻሻል ተደርጓል። 
  3. አንዳንድ ቃላት የተሻለ ሐሳብን ይገልጣሉ በተባሉ ዐዳዲስ ቃላት ተተክተዋል። ለምሳሌ መዝሙር 1፡5 1833 ላይ ታትሞ በወጣው መዝሙረ ዳዊት፤

“ስለዚኸም፡ አይነሡም፡ ዝንጎች፡ በደይን፡ ኃጢአተኞችም፡ በጻድቃን፡ ምክር፡ አይገኙም።” ሲል የ1886/1879ቱ እትም ደግሞ “ስለዚኽ: ክፎች፡ በፍርድ፡ አይቆሙም፡ ኃጢአተኞችም፡ በጻድቃን፡ ማኅበር።” ይላል። የግእዙ “ደይን” እና የዕብራይስጡ “ዲን” (דין) ኹለቱም ፍርድ ተብለው ይተረጎማሉ። ምንም እንኳን ትርጉሙ አንድ አይነት ቢኾንም “ደይን” በ“ፍርድ” ተተክቷል።  

ከ200 ዓመታት በፊት የተተረጎመውና በ1886/1879 የታተመው ያማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ያስተረጎሙት መጽሐፍ ቅዱስ ከ1962/1954 በኋላ እስኪተካው ድረስ ብቸኛውና ለብዙዎች ብርሃን የነበረ ያማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር።

በተጨማሪም፣ የሼኽ ዘከርያ ተማሪዎች ይኽንን መጽሐፍ እያጠኑ ነበር ወንጌልን የተማሩ፣ ያስተማሩም። ለሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን መመሥረት ይኽ መጽሐፍ ቅዱስ በማንም እና በምንም የማይተካ ሚናን ተጫውቷል።

ፋንታኹን መላኩ ሲሳይ

ዋቢ መጻሕፍትና ጥናታዊ ጽሑፎች

Fellman, Jack, “The First Amharic Bible Translation,” in The Bible Translator Vol. 28, No. 1, 1977, pp. 154–155.  

Jones, William. “Conversations with Abram, an Abyssinian, concerning the City of Gwender and the Sources of the Nile,” Asiatick Researches, 1788, pp. 383–388.

Jowett, William. Christian Researches in the Mediterranean, London, 1822.

Kleiner, Michael. “Abu Rumi,” in Encyclopaedia Aethiopica. V. 1. Edited by Siegbert Uhlig. Harrassowitz: Wiesbaden, 2003, pp. 53–54.

Meley Mulugetta. “Reflections on Abu Rumi’s Amharic Translation of the Book of Ruth,” Aethiopica 12 (2009), pp. 136–142.    

Pankhrust, Richard. “Two Forgotten Ethiopian Scholars of the Late Eighteenth and Early Nineteenth Centuries: Abu Rumi and Liq Atsqu,” Ethiopian Observer, Vol. 12, No. 2, 1969, pp. 140.

Platt Thomas Pell (ed.). Biblia sacra amharica. Sub auspiciis D. Asselini, rerum gallicarum apud Aegyptios procuratoris, in linguam amharicam vertit Abu Rumi Habessinus. London 1840.

Psalterium Davidis Amharice. London. 1833.    

Stoffregen-Pedersen, Kirsten, “Bible Translation into Amharic” in Encyclopaedia Aethiopica. V. 1. Edited by Siegbert Uhlig. Harrassowitz: Wiesbaden, 2003, pp. 574–575.     

Ullendorff, Edward, Ethiopia and the Bible, London, 1968.

መጽሐፍ ቅዱስ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት የ1886/1879 እትም።

ፎቶዎቹን የወሰድነው ከዚህ እና ከዚህ ነው

የቅርብ ጽሁፎች

በ Facebook ይከተሉን

Share Your Thoughts

Your email address will not be published. Required fields are marked *