በመካከለኛው ምስራቅ ታሪክ ትልቁ የተባለውን የግብረሰዶማውያን (LGBTQ+) ፌስቲቫል እ.ኤ.አ. በሰኔ 2026 በሙት ባህር (Dead Sea) አካባቢ እስራኤል ለማስተናገድ መዘጋጀቷ ተሰማ።
ኢየሩሳሌም ፖስት እንደዘገበው፤ “ፕራይድ ላንድ/Pride Land” (“የኩራት ከተማ”) የተሰኘው ይህ አዲስ ፌስቲቫል ከሰኔ 1 እስከ ሰኔ 4 ቀን 2026 ዓም (June 1-4) ድረስ የሚቆይ ሲሆን፣ በይሁዳ በረሃ መካከል በቀለማት ያሸበረቀች “የኩራት ከተማ” በመፍጠር ፌስቲቫሉን ለማካሄድ መታቀዱን ገልጿል።
ዝግጅቱ ከተራ ድግሶችና ትርኢቶች ባለፈ ለ24 ሰዓታት ሙሉ የሚቆይና ምንም የማይቋረጥ ማኅበረሰባዊ ድባብ ለመፍጠር ያለመ ሲሆን፣ ለዚሁ ዝግጅት በታሰበው ቀጠና ውስጥ የሚገኙ 15 ሆቴሎች፣ የባሕር ዳርቻዎች እና የማዕከላዊ ትርኢት መድረኮች የዝግጅቱ አካል በመሆን በማንኛውም ሰዓት ያልተቋረጠ አገልግሎት እንዲሰጡ ተመድበዋል።
ከምሽት መዝናኛዎች ጎን ለጎን ፌስቲቫሉ የባሕልና የኪነጥበብ ማዕከላትን፣ የመዝናኛ ቦታዎችን፣ እንዲሁም የሕፃናት መጫወቻዎችንና ለቤተሰብ ተስማሚ የሆኑ ልዩ ልዩ መርኃግብሮችን ያካተተ እንደሚሆን ተነግሯል። አንዳንድ አገልግሎቶች በልዩ ትዕዛዝ እንዲሰጧቸው ለሚፈልጉም እንደሚያገኙ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።
የፌስቲቫሉ ዋና አዘጋጅና የሃሳቡ አመንጪ የሆኑት አሮን ኮኸን እንደተናገሩት “ይህ በረሓ ላይ የሚገነባው ከተማ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ኢንቨስትመንት የወጣበት ሲሆን፣ በዓይነቱ እስካሁን ካደረግናቸው ዝግጅቶች ሁሉ ትልቁ ነው” ብለዋል።
“ከዚህም በላይ ለማደግ እንፈልጋለን” ያሉት አሮን ኮኸን “ከምንም ተነስተን፣ በሚሊዮን የሚቆጠር መዋዕለ ንዋይ አፍስሰን፣ ባካባቢው ያሉትን ሆቴሎች በሙሉ ለአራት ቀን ገዝተን፣ ጭው ባለ በረሓ ላይ የምንገነባው ከተማ በዘላቂነት ሲታወስ የሚቆይና የሚቀጥል ልምምድ እንዲሆን እንፈልጋለን” ብለዋል።
ይህ የአንድ ጊዜ የሰዶማውያን መሰባሰቢያ ፌስቲቫል ሳይሆን የሙት ባሕርን አካባቢ ለግብረሰዶማውያን ቋሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የታሰበ እንደሆነ ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም በእስራኤል የሚገኙ ሰዶማውያን ዋና መሰባሰቢያቸው ከሆነው ቴል አቪቭ ከተማ ውጪ ወደ ሌሎችም እንዲስፋፋ ለማድረግ የታለመም ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ዝግጅቱ እስራኤል በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የቱሪስት ፍሰቷ ቀንሶ በሚገኝበት አስቸጋሪ ወቅት ላይ የሚካሄድ ቢሆንም፣ የዝግጅቱ አስተባባሪዎች በዓሉ ማኅበረሰባዊ ግልፅነትንና አብሮነትን ለዓለም የሚያሳይ መልዕክት አለው ሲሉ አስታውቀዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት ምዕራፍ 18 ላይ የአብርሃም ወንድም ልጅ የሆነው ሎጥ ይኖርበት የነበረው ሰዶምና ገሞራ ከተማ ክፋታቸው ወደ ሰማይ በመድረሱ እግዚአብሔር በእሣት ሊያጠፋቸው እንደሆነ ተናግሮ ነበር።
መልዕክቱን ሰምቶ ከከተማዋ መውጣት ያቃተውን ሎጥና ቤተሰቡን ለመታደግ የመጡትን መላእክት የከተማዋ ሰዎች የሎጥን ቤት በመክበብ “በዚህ ሌሊት ወደ ቤትህ የገቡት ሰዎች ወዴት ናቸው?” እንግዶችህን አውጣ፤ ወሲብ እንፈጽምባቸው፣ እናስነውራቸው እያሉ አደጋ ለማድረስ ሲቃረቡ መላእክቱ ዓይናቸውን እንዳሳወሯቸው ላይ ይናገራል (ዘፍጥረት 19:4-11)።
በዚህ እጅግ አስነዋሪና አስጸያፊ ተግባር ላይ የተሳተፉት እነማን እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር፤ “ከብላቴናው ጀምሮ እስከ ሽማግሌው ድረስ በየስፍራው ያለው ሕዝብ ሁሉ” ነበሩ ይላል (ዘፍጥረት 19:4)።
አሁን የሙት ባሕር የሚባለው “በእሳትና ዲን” የተቃጠሉት የሰዶምና ገሞራ ከተሞች አካባቢ የሚገኝ ሕይወት አልባ ስፍራ ነው። ይህ ምንም አይነት አሣ የሌለበት የውሃ ስብስብ፥ ከአካባቢው ወንዞች ውሃ የሚቀበል ግን መልሶ ምንም የማይሰጥ፥ እንደ ስሙ ሙት የኾነ ሥፍራ ላይ ነው ሰዶማውያን ይህንን ፌስቲቫል ለማድረግ ያቀዱት።
የሰዶምና ገሞራ ክፋት እጅግ በመብዛቱና ኃጢአታቸው እጅግ በመክበዱ የተነሳ ሰማይ በእሳትና ዲን በጎበኘው ስፍራ ላይ ነው የዘመናችን ሰዶማውያን “በመካከለኛው ምስራቅ ታሪክ ትልቁ የተባለውን የግብረሰዶማውያን ፌስቲቫል” ያዘጋጁት። መልዕክታቸው ግልጽ ነው!
“አንባቢው ያስተውል”










