“የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፣ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና” (1ቆሮ. 1፡18)
በዚህች በምንኖርባት ምድር በነጻ የምናገኘው ነገር የለም። ለምናገኛቸው ነገሮች ሁሉ በሆነ መንገድ ዋጋ እንከፍላለን። ባንከፍል እንኳን ሁልጊዜ ውለታ መላሾች መሆናችን ይሰማናል። ስለዚህም ይሆናል አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የሆነ መልካም ነገር ሲያደርጉልን ባለዕዳ የሆንን መስሎ የሚሰማን እና “ውለታ መላሽ ያድርገኝ” ወይም “አንተ እኮ ባለውለታዬ ነህ!” ብለን የምንናገረው።
መልካም አድራጊው ሰውም ምንም እንኳን በቀጥታ ባይናገርም፣ ለሌሎች ሰዎች የሠራቸውን ውለታዎች በማሰብ አብዛኛውን ጊዜ ውስጣዊ ኩራት ይሰማዋል። በሠራው ጥሩ ሥራ መጠን ምስጋና እና ምላሽ ሳያገኝ ሲቀር ደግሞ “እኔ ሁልጊዜ ሰውን እረዳለሁ፣ ምላሽ ግን አላገኝም” ወይም ደግሞ “እኔ ይሄንን ሁሉ ነገር ሳደርግለት፣ እርሱ ግን አንድም ነገር አድርጎልኝ አያውቅም” ብሎ ያስባል። ያለክፍያ መልካምን ማድረግ ጅልነት መስሎ ይታየዋል።
ከእነዚህ ምሳሌዎች ሁለት ነገሮችን እንረዳለን፡- 1ኛ) መልካም ነገር የሚደረግላቸው ሰዎች ድርጊቱን እንደስጦታ ሳይሆን፣ መመለስ እንዳለበት ውለታ ይመለከቱታል። 2ኛ) በአንጻሩም ደግሞ፣ መልካም አድራጊዎች ለበጎ ድርጊታቸው ምስጋና ወይም መልስ ሳያገኙ ከቀሩ እንደተጎዱ ይሰማቸዋል።

ሁለተኛውን ነጥብ በአንድ ገጠመኝ ጎላ ላድርገው፡- እሠራበት በነበረ አንድ ቦታ አብራኝ ትሠራ የነበረች የሥራ ባልደረባዬ፣ መሥሪያ ቤቱ አንድ ልምምድ እንደነበረው አጫወተችኝ። ይኸውም፣ የሠራተኞች ልደት በደረሰ ጊዜ ለባለልደቱ ገንዘብ አዋጥቶ የልደት ስጦታ የመግዛት ልምድ ነበር። ይሄ ልምምድ ግን አሁን እንዳቆመ ስትነግረኝ፣ “ያቆመበት ምክንያት ምንድን ነው?” ብዬ ጠየኳት። እርሷም፣ ሁልጊዜ የአንድ የሥራ ባልደረባ የልደት ቀን ሲደርስ ገንዘቡን አሰባስባ ስጦታውን የምትገዛ እርሷ እንደነበረች፣ የእርሷ ልደት ሲደርስ ግን የሥራ ባልደረቦችዋ ለእርሷ ገንዘብ በማዋጣት ስጦታ ገዝተው እንዳላበረከቱላት ነገረችኝ። በዚህም ምክንያት “እኔን የማያስቡኝ ከሆነ፣ እኔ ለምን ለእነርሱ አስባለሁ?” በማለት መዋጮ በማሰባሰብ ለባለልደት የሥራ ጓደኞቿ ስጦታን መስጠት አቆመች።
ስለዚህ ሰዎች ስንባል በነጻ ሲሰጠን ውለታ መመለስ እንዳለብን፣ በነጻ ስንሰጥ ደግሞ ምላሽ ማግኘት እንዳለብን ይሰማናል። ከሕጻንነታችን ጀምሮ በእንደዚህ አይነት መልክ ነው ያደግነው። “ጥሩ ልጅ ከሆንህ፣ እወድሃለሁ፣ … ስጦታ እሰጥሃለሁ፣ … አስቸጋሪ ልጅ ከሆንህ ግን ጅቡ ይበላሃል፣ … አላናግርህም፣ … ልጄ አይደለህም …” እንላለን፤ ወይም ስንባል አድገናል። ከዚህም የተነሳ የምንሰጠው ወይም የምንቀበለው ፍቅር ሁልጊዜ በድርጊት ላይ የተመሠረተ ነው። ያለተጨባጭ ምክንያት መውደድን ወይም መወደድን አናውቅም። ስለዚህም ይመስለኛል “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ነው” የተባለው።
ለመሆኑ የመስቀሉ ቃል ምንድን ነው? የመስቀሉ ቃል ወንጌል ነው! ወንጌልስ ምንድን ነው? ወንጌል መልካም ዜና ነው! መልካሙስ ዜና ምን ይላል? “የምድር ሰዎች ሁሉ ስሙኝ! እኔ ፈጣሪያችሁ ነኝ፣ በጣም እወዳችኋለሁ! በግድየለሽ አኗኗራችሁ እኔ ለእናንተ ስላለኝ ስሜት ግድ እንደማይሰጣችሁ ብታሳዩኝም፣ እኔ ግን እወዳችኋለሁ! ስለዚህም ከዘላለም ጀምሮ ከእኔ ጋር ሲኖር የነበረውንና የሚኖረውን፣ በጣም የምወደውን እና የማከብረውን ልጄን፣ በእውነት ለእናንተ ያለኝን የፍቅር ስሜት እንዲነግራችሁና በተግባር እንዲያሳያችሁ ወደ እናንተ ላክሁት። እርሱም እያለቀሰ፣ ደስተኛ የምትሆኑበትን መንገድ እየተናገረ፣ እንዲሁም መልካም የሆነውን ነገር እያደረገላችሁ በእኔ ልብ ውስጥ ስለእናንተ ያለውን መልካም ሃሳብ አሳያችሁ። በመጨረሻም እንደማትፈልጉት ብትነግሩትም፣ እርሱ ግን ከእኔ ተለይታችሁ እንድትሞቱ ሳይሆን ለሁልጊዜ ከእኔ ጋር እንድትኖሩ ስለፈለገ በፈቃደኝነት በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ሞተ። ከመሞቱ በፊት ግን፣ ይቅርታ እንዳደርግላችሁ ለመነኝ። እኔም ይህንን ለማድረግ ከልብ ፈቃደኛ ነኝ። ይቅር እንድላችሁ አንዳች ነገር መክፈል የለባችሁም። ያለባችሁን ዕዳ ሁሉ ልጄ ከፍሎላችኋል። ይህንን ካመናችሁ ወደ እኔ፣ ወደምወዳችሁ አባታችሁ ከመጣችሁ በደስታ ልቀበላችሁ ፈቃደኛ ነኝ። አስታውሱ፣ ወደ እኔ ኑ! የምላችሁ “መልካም አድርጉና እወዳችኋለሁ” ለማለት ሳይሆን፣ እንዲሁ ከነማንነታችሁ ስለምወዳችሁ ነው። ከሞት ያስነሳሁት ልጄም ይወዳችኋል። ለዚህ የፍቅር ጥሪዬ የምትሰጡትን መልስ ለመስማት በጉጉት እጠባበቃለሁ”።
“ይህን ሁሉ መከራ እንዲቀበል የእኔ ፈቃድ ነበር፣ የእርሱም ሞት የኃጢአትን ይቅርታ የሚያስገኝ መስዋዕት ነበር … ሕይወትን ከሚያሰቃይ ከብዙ መከራ በኋላ፣ የሕይወትን ብርሃን በማየት እንደገና ደስ ይለዋል፣ ያን ሁሉ መከራ የተቀበለውም በከንቱ አለመሆኑንም ይገነዘባል፣ በእርሱ ደስ የሚለኝ የእኔ ፍጹም አገልጋይ ብዙዎች ሊቀበሉት የሚገባውን ቅጣት ተሸክሞ እነርሱን ከኃጢአት ነጻ ያደርጋል” (ኢሳይያስ 53፡10-11)።
በነጻ መስጠትም ሆነ መቀበል ላልለመድን ለእኛ ጥቅም ፈላጊ ሰዎች ይህ መልእክት ሞኝነት ይመስላል። ከራሳቸው ባሻገር በመመልከት በዚህ ባለመልካም ዜና አምላክ እጅ ላይ ሕይወታቸውን የሚያኖሩ ሰዎች ግን ለዘላለም እንዲያው እንደነበሩ አይቀሩም፣ ይለወጣሉ! አዲስ ሕይወትን መኖርን ይጀምራሉ! በነጻ ተወድደዋልና በነጻ ይወዳሉ! በነጻ ተቀብለዋልና በነጻ ይሰጣሉ!
እንደዚህ ያለ፣ ትርጉምና እርካታን የሚሰጥ ሕይወት ሌላ የትም አይገኝም! ይህ ሕይወትን የሚቀይር ኃይል የሚገኘው መልካም በማድረግ፣ ሃይማኖተኛ በመሆን፣ ምጽዋት በመጸወት ወዘተ ሳይሆን፤ ይህንን እስከሞት ድረስ የወደደንን አምላክ የሕይወታችን መሪ በማድረግ ነው። በራስ ወዳድነትና በጥቅም ፈላጊነት ያልተበከሉ መልካም ድርጊቶች የዚህ የፍቅር ግንኙነት ፍሬዎች ናቸው። ለብዙዎች ሞኝነት የሚመስለው ይህ መልዕክት፡- የይቅርታ፣ የደኅንነት እና የበጎ ነገሮች ሁሉ ምንጭ የሆነው የእግዚአብሔር ጥበብ ነው (ኤፌሶን 1፡7-8)። ለእርስዎስ?
(ምንጭ፡- ፓ/ር ስምረት መሐሪ፣ የትንቢት ቃል መጽሔት፣ መጋቢት 1993)