giziew.org

በቀራንዮ ኮረብታ ሞት ሞተ

የሴቲቱ ዘር የሆነው መሢሕ ጌታ ወደዚህች ምድር መጥቶ፣ ነቁጥ አልባ ፍጹምና ንጹህ ሕይወት ኖሮ፣ በጠላት ወረዳ ውስጥ ብቻውን ሞትን ተጋፈጠ፤ ሞትን ለዘላለም ለመግደል ሕይወቱን ለዘላለም አሳልፎ ሰጠ
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

አዳም ሲበድል ሞት ወደ ምድር ገባ። የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ዕጽዋት፣ እንስሳት፣ የባህር ፍጡራን፣ የሰማይ ወፎች፣ ወዘተ በሙሉ ሟች ሆኑ። ምድር እሾህ እንድታበቅል ተረገመች፤ አየሩ በሞት ታወደ፤ የሞት ማዳበሪያ አፈሩን አረከሰው፤ የሞት መውጊያ እያንዳንዱን ፍጡር ነደፈ፤ ፍጡርም ከሞት ማምለጥ የማይችል ዓቅመቢስ ሆነ፤ የፍጥረት የመጨረሻ ማስፈራሪያ ሞት ሆነ፤ ሞት በሕይወት ላይ አጓራ፤ ፍጥረትም በፍርሃት አንገቱን ደፋ፤ ሞት በማናለብኝነት በሕይወት ላይ ነገሠ።

አዳም የግዛት ሥልጣኑን አስረክቦ ሞት በነገሠበት ጊዜ እግዚአብሔር ሞትን ድል እንደሚያደረግ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። ይህም ተግባራዊ የሚሆነው የሴቲቱ ዘር በሆነው በጌታችንና መድኃኒታችን ክርስቶስ እንደሆነ ሲናገር እንዲህ አለ፤ “እርሱ (ጌታችን) ራስህን (የሰይጣንን) ይቀጠቅጣል፥ አንተም (እባቡ ወይም ሰይጣን) ሰኰናውን (ተረከዙን) ትቀጠቅጣለህ” (ዘፍጥረት 3፡15)። ሞት በሕይወት ላይ ደረቱን ነፍቶ የበላይነቱን ለዘላለም ሳይጎናጸፍ ገና ከጅምሩ ኪሣራ ገጠመው፤ ሕልሙ ቅዠት ሆነ። የሴቲቱ ዘር የሆነው መድኅን ክርስቶስ በሞቱ ሞትን ይቀጠቅጠዋል፣ ይገድለዋል በማለት ኃያሉ አምላክ እግዚአብሔር በሥልጣን ተናገረ።

ይህንን ተስፋ የአዳም ቀጣይ ዘሮች ለመቀበል አዳገታቸው፤ ኃጢአትን መረጡ፤ ሞትን አነገሡ። የእግዚአብሔር ተቃዋሚ ሆኑ፤ ክፋታቸው በዛ፤ የልባቸው አሳብና ምኞት ያለማቋረጥ ሁልጊዜ ክፉ ሆነ (ዘፍጥረት 6፡5)።

ዲያቢሎስና የሥጋቸው ሃሳብ ሽምጥ ሲጋልባቸው የነበሩ እነዚህ ሰዎች፤ በክፉ ተግባራቸው የመሲሑን መምጫ መንገድ አጥብበው በሰፊው ጎዳና ወደ ሞት ነጎዱ። እግዚአብሔር ግን ያቺን የጠበበች መንገድ ጠብቆ የመሢህ መምጫ አደረጋት። “የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” (ገላትያ 4፡4)።

የሴቲቱ ዘር የሆነው መሢሕ ጌታ ወደዚህች ምድር መጥቶ፣ ነቁጥ አልባ ፍጹምና ንጹህ ሕይወት ኖሮ፣ በጠላት ወረዳ ውስጥ ብቻውን ሞትን ተጋፈጠ፤ የምድርን የእሾህ ዕርግማን አክሊሉ አድርጎ ከፍ ብሎ ታየ፤ ፍጥረተ ዓለም ሁሉ በገሃድ እያየው ዲያቢሎስንና ሞትን በቀራንዮ ከፍታ ላይ ግብግብ ገጠመ፤ ሞትን ለዘላለም ለመግደል ሕይወቱን ለዘላለም አሳልፎ ሰጠ፤ “ተፈጸመ” በማለት ሞትን በሞቱ ድል ነሳ። ለኃጢአት የሚገባውን መስዋዕትነት በመክፈል የእባቡን ጭንቅላት ቀጠቀጠ። በቀራንዮ ኮረብታ ሞት ሞተ።

ጌታችንን ከመስቀል አውርደው በመቃብር ባኖሩት ጊዜ ተስፋ ያልቆረጠው ሞት ከሲዖል (መቃብር) ጋር ሆነው ጌታችንን በመቃብሩ አሽገው ለማኖር አሤሩ። እርሱ ግን ሰንበትን እንደ ትዕዛዙ በመቃብር ካሳለፈ በኋላ እሁድ ጠዋት “ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?” በማለት ሞትን በትንሣኤ ጦር ወጋው፤ መቃብርንም ወደራሱ መቃብር በመክተት የአዳምን ዘር ከሞት ኩነኔ ነጻ አወጣው።

ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ወደዚህች ምድር ህጻን ሆኖ በመወለድ ሞትን ብቻውን በመጋፈጥ ድል ያደረገው መድኅናችን፤ በሞት ላይ የመጨረሻውን ምት ለመሠንዘር የክብር አክሊል ተጎናጽፎ፣ የነገሥታት ንጉሥ ሆኖ ይመጣል። ከዚያም የመጨረሻው መጨረሻ ሲሆን፣ በጻድቃንና ኃጥዓን ላይ የመጨረሻው ውሳኔ ሲሰጥ የፍጻሜው ፍጻሜ ይሆናል። ሞትና መቃብርም በእሣት ባሕር ይጣላሉ (ራዕይ 20፡14)፤ የሕይወት መዓዛ አየሩን ይሞላዋል፤ ሰብዓዊ ፍጡርና ተፈጥሮ በአንድ ላይ ሞትን ድል ላደረገው አምላካቸው ይቀኛሉ፤ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት ለዘላለም ያዜማሉ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

አዘጋጆቹ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *