giziew.org

ቀራንዮ – ሞት የሞተበት!

መስቀሉን ሸፍኖት የነበረው ጨለማ በድንገት እንደለቀቀ እንደ መለከት ከሩቅ በሚሰማ ድምፅ የሱስ “ተፈፀመ!” ሲል ጮኸ። ... ከዚያ በኋላ ራሱን በደረቱ ላይ ጣል አድርጎ አረፈ
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

“ቀራንዮ ወይም የራስ ቅል ወደ ተባለ ስፍራም በደረሱ ጊዜ በዚያ ኢየሱስን ሰቀሉት”። “እንዲሁም ኢየሱስ ህዝቡን በገዛ ራሱ ደም ለመቀደስ ከከተማው በር ውጭ መከራን ተቀበለ” (ዕብ. 13፡12)። የእግዚአብሔርን ህግ በመተላለፋቸው አዳምና ሄዋን ከኤደን ተባረሩ። የእኛ ቤዛ የሆነው የሱስ ከኢየሩሳሌም ክልል ውጭ መሰቃየት ነበረበት። ከባድ ወንጀለኞችና ነፍሰ ገዳዮች በሚገደሉበት ከከተማው በር ውጭ ሞተ። “ክርስቶስ ስለእኛ እንደ እርግማን ሆኖ ከህግ እርግማን ዋጀን፣” የሚለው አነጋገር ትልቅ ትርጉም ያለው ነው (ገላ.3፡13)።

የሱስ ከፍርድ አዳራሹ ወጥቶ ወደ ቀራንዮ በተወሰደ ጊዜ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተከተለው። የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት ወሬው በመላው ኢየሩሳሌም ስለተሰማ ከኅብረተሰቡ በተለያየ ደረጃ የሚኖረው ሕዝብ ወደ መሰቀያው ቦታ ጎረፈ። ካህናቱና ሹማምንቱ ክርስቶስ በእጃቸው እንዲገባ ከተደረገ በክርስቶስ ተከታዮች ላይ ጉዳት ላለማድረስ ቃል ስለገቡ በኢየሩሳሌምና በአካባቢው የሚኖሩ ተከታዮቹ ከህዝቡ ጋር ተቀላቅለው ሄዱ።

የሱስ ከጲላጦስ አደባባይ ወጥቶ በሩን እንዳለፈ ለበርባን መሰቀያ ተብሎ የተዘጋጀውን መስቀል በቆሰለውና በሚደማው ትከሻው ላይ አሸከሙት። የበርባን ጓደኞች የነበሩ ሁለት ሰዎች የሞት ፍርድ ተበይኖባቸው ስለነበር እነርሱም መስቀሎቻቸውን እንዲሸከሙ ተደረገ። አዳናችን በደረሰበት ስቃይ ምክንያት አቅም ስላነሰው የተጫነበትን ሸክም መቻል አቃተው። ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የፋሲካን እራት ከበላ ወዲህ እህል ውሀ አልቀመሰም ነበር። በጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ ከሰይጣን ሰራዊት ጋር በነበረው ግብግብ ብዙ ተሰቃየ። አሳልፎ በተሰጠ ጊዜ እጅግ ተሰቃየ፤ ደቀ መዛሙርቱም ትተውት ሲሸሹ አየ። መጀመሪያ ወደ ሀና ቀጥሎ ወደ ቀያፋ ከዚያ በኋላ ወደ ጲላጦስ ተወሰደ። ከጲላጦስ ወደ ሄሮድስ ከተላከ በኋላ እንደገና ተመልሶ ወደ ጲላጦስ እንዲመጣ ተደረገ። በዚያ ሌሊት የደረሰበት እንግልት፣ ስድብ፣ ፌዝና ግርፋት የሰውን ነፍስ እስከ መጨረሻው የሚፈታተን ነበር። የሱስ አባቱን የሚያስከብር ነገር ብቻ ከመናገር ውጭ ሌላ ነገር ሳይናገር ሁሉን ነገር በዝምታ ቻለ። የደረሰበትን አሳፋሪና የሀሰት ምርመራ ሁሉ በክብርና በቁርጠኛነት ተቋቋመ። ነገር ግን ከሁለተኛው ግርፋት በኋላ መስቀሉን ባሸከሙት ጊዜ ሰብዓዊነት መቋቋም ተሳነው። ሰውነቱ ዝሎ መስቀሉን እንደተሸከመ ወደቀ።

ከኋላው ይከተሉት የነበሩት ሰዎች ደክሞት እየተንገዳገደ እንደሚሄድ እያዩ አላዘኑለትም። እንዲያውም መስቀሉን መሸከም ስላቃተው ይተናኮሉትና ይሰድቡት ነበር። ከወደቀበት አንስተው መስቀሉን ሲያሸክሙት እንደገና ተመልሶ ወደቀ። በዚህ ጊዜ ጠላቶቹ መስቀሉን ተሸክሞ መሄድ እንደማይችል ገባቸው። ይህን የሀፍረት ሸከም በማን ላይ እንደሚጭኑትም ግራ ገባቸው። ለፋሲካው በዓል የሚያረክሳቸው ስለሚሆን አይሁዳውያን መስቀሉንም መሸከም አልፈለጉም። ለአድማ ከመጡት ሰዎች መካከል እንኳ መስቀሉን በመሸከም ራሱን ለማዋረድ ፈቃደኛ የሆነ አንድም ሰው አልተገኘም።

ስምዖን የቀሬናው

በዚህ ጊዜ ስምዖን የተባለ አንድ የቀሬና ሰው ከገጠር ወደ ከተማ ሲሄድ የሱስን ይዘው ከሚሄዱት ሰዎች ጋር ተገናኘ። ህዝቡ ይናገሩ የነበረው የብልግና ንግግርና ለአይሁድ ንጉስ መንገድ ልቀቁለት! እያሉ በተደጋጋሚ በንቅት ስሜት ሲጮኹ ሰማ። ቆሞ በሀዘንና በመገረም ሲመለከት የየሱስ ጠላቶች ይዘው መስቀሉን አሸከሙት።

ስምዖን ደቀ መዝሙር አይሁን እንጂ ስለ የሱስ የሚያውቅ ሰው ነበር። ልጆቹ የየሱስ አማኞች ነበሩ። መስቀሉን ተሸክሞ ቀራንዮ ማድረስ ለስምዖን ትልቅ በረከት ስለሆነ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ላጋጠመው እድል ባለውለታ ሆነ። በዚህ ጥሩ አጋጣሚ ምክንያት ስምዖን የክርስቶስን መስቀል በራሱ ፍላጎት ደስ እያለው እንደተሸከመ ኖረ።

በርካታ ርኅሩኅ ሴቶች

ኃጢአት የሌለበቱ ጌታ በአሰቃቂ ሁኔታ ወደሚሞትበት ቦታ ሲሄድ ይከተሉት ከነበሩት ሰዎች መካከል ብዙ ሴቶች ነበሩ። እነዚህ ሴቶች ስለ የሱስ ያስቡ ነበር። ከእነርሱ መካከል አንዳንዶቹ ከዚያ በፊት አይተውታል፣ አንዳንዶቹ ቀደም ሲል ህሙማንን ወደ እርሱ ያመጡ ነበሩ። አንዳንዶቹም የሱስ ከደዌ የፈወሳቸው ነበሩ። በየሱስ ላይ ስለደረሰው ግፍና በደል በሰሙ ጊዜ ልባቸው የሚጨነቅለትንና የሚወዱትን ጌታ ይከተለው የነበረው ሕዝብ ለምን እንደጠላው ይገርማቸው ነበር። የተናደደው ሕዝብ የሚፈፅመውን ድርጊትና የካህናቱንና የሹማምንቱን የቁጣ ንግግር ችላ በማለት ሴቶቹ ለየሱስ የነበራቸውን ርህራሄ ከመግለፅ ወደኋላ አላሉም። የሱስ ሰውነቱ ዝሎ መስቀሉን እንደተሸከመ ሲወድቅ ባዩ ጊዜ ሃዘናቸውን በለቅሶ ዓይነት ጩኸት ገለፁ።

የየሱስን ስሜት የሳበው ይህ ብቻ ነበር። ምንም እንኳን የዓለምን ኃጢአት በመሸከሙ ምክንያት ስቃይ ቢበዛበትም ይህን ዓይነት ሀዘን ችላ ማለት አልቻለም። እነዚህን ሴቶች በርህራሄ ዓይን ተመለከታቸው። እነዚህ ሴቶች አማኝ ስላልነበሩ ያዘኑለት የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ በመሰቃየቱ ሳይሆን በሰብዓዊ የርህራሄ መንፈስ ተገፋፍተው ነው። የሱስ የእነርሱን ሀዘኔታ ችላ አላለም እንዲያውም የእነርሱ ሀዘኔታ እርሱ ለእነርሱ የበለጠ እንዲያዝንላቸው ስለ አደረገው “እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች! ስለ ራሳችሁና ስለ ልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ስለ እኔ አታልቅሱ” አላቸው። የሚታየው የኢየሩሳሌም መደምሰስ ነበር። አሰቃቂ የሆነው የኢየሩሳሌም መደምሰስ በደረሰ ጊዜ ኢየሱስ ያለቅሱ የነበሩት ሴቶች ከነልጆቻቸው ሲጠፉ ታዩት።

የሱስ ከኢየሩሳሌም ጥፋት ባሻገር ትልቁ የፍርድ ቀን ታየው። ንስሀ ያልገባችው የኢየሩሳሌም ከተማ ጥፋት በዓለም ላይ የሚደርሰው የመጨረሻው ጥፋት ምሳሌ ሆኖ ታየው። “በዚያ ጊዜ ሰዎች ተራራዎችን በላያችን ውደቁ! ኮረብቶችንም ሸሽጉን! ማለት ይጀምራሉ። እንግዲህ ይህ ሁሉ ነገር በእርጥብ እንጨት ላይ የሚደረግ ከሆነ በደረቅ እንጨት ላይማ ምን ይደረግ ይሆን?” አለ። እርጥብ እንጨት ሲል ምንም እንከን የማይገኝበትን የዓለም አዳኝ የሆነውን ራሱን ማለቱ ነው። እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ ያለውን ቁጣ በተወዳጁ ልጅ ላይ አወረደው። የሱስ ስለ ሰዎች ኃጢአት መሰቀል ነበረበት። ኃጢአትን በመስራት የሚቀጥል ሰው ምን ዓይነት ስቃይ ይደርስበት ይሆን? ንስሀ የማይገቡና የማያምኑ ሁሉ በቋንቋ ሊገለፅ የማይቻል ሀዘንና ስቃይ እንደሚደርስባቸው ያውቃሉ።

ከሆሳዕና እስከ “ስቀለው”

አዳኛችን ለመሰቀል ወደ ቀራንዮ ሲሄድ ከተከተሉት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በአህያ ላይ ተቀምጦ በድል አድራጊነት ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ የዘምባባ ዝንጣፊ እያውለበለቡና የደስታ መዝሙር እየዘመሩ ያጀቡት ናቸው። ያን ጊዜ ሰዎች ያደረጉትን ተከትለው የውዳሴ መዝሙር የዘመሩለት አንዳንድ ሰዎች በዚያው አንደበታቸው “ስቀለው! ስቀለው!” የሚል ጩኸት አብረው አስተጋቡ። የሱስ በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም በገባበት ወቅት የደቀ መዛሙርቱ ተስፋ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነበር። በዚያን ጊዜ ወደ እርሱ መቅረብ ክብር ስለመሰላቸው ወደ እርሱ በጣም ተጠጉ። አሁን ግን ውርደት በደረሰበት ጊዜ ከሩቅ ተከተሉት። እያዘኑ ተስፋ በመቁረጥ አንገታቸውን ደፉ። የሱስ “እረኛውን መትቼ እገድላለሁ፣ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ ተብሎ ተፅፎአልና በዚህች ሌሊት ሁላችሁም ትክዱኛላችሁ፣” ሲል የተናገረው ተረጋገጠ (ማቴ. 26፡31)።

ማርያም፤ ከግርግም እስከ ቀራንዮ

ከመሰቀያው ቦታ በደረሱ ጊዜ እስረኞቹ ለማሰቃያ በተዘጋጀው መሳሪያ ላይ ታሰሩ። ሁለቱ እስረኞች በመስቀል ላይ ላለመታሰር ታገሉ የሱስ ግን ምንም የመከላከል ሙከራ አላደረገም። የየሱስ እናት በተወዳጁ ደቀ መዝሙር በዮሐንስ እየተረዳች ልጅዋን እስከ ቀራንዮ ተከተለችው። የሱስ ሰውነቱ ዝሎ መስቀሉን እንደተሸከመ ሲወድቅ ስላየችው የቆሰለውን ራሱን በእጆችዋ ደገፍ ልታደርግለትና በህፃንነቱ ደረትዋን ይንተራስ የነበረውን ግንባር ልታጥብለት ብትችል ደስ ባላት ነበር። ነገር ግን ይህን የማድረግ ዕድል አላገኘችም። እርስዋ እንደ ደቀ መዛሙርቱ የሱስ ኃይሉን በመጠቀም ራሱን ከጠላቶቹ እጅ ያድናል የሚል ተስፋ ነበራት። ቢሆንም አሁን ስለደረሰበት ሁኔታ አስቀድሞ የተናገረውን ባስታወሰች ቁጥር ልብዋ ይሸበርባት ነበር። ሁለቱ ሌቦች በመስቀል ላይ ሲታሰሩ ባየች ጊዜ ለሙታን ህይወትን የሰጠ ጌታ ራሱን ለስቅላት አሳልፎ ይሰጥ ይሆን? እያለች በጭንቀት ትጠባበቅ ነበር። የእግዚአብሔር ልጅ በጭካኔ ለመገደል ራሱን አሳልፎ ይሰጥ ይሆን? አለች። ስለ የሱስ መሲህነት የነበራትን እምነት መተው ይኖርባት ይሆን? በደረሰበት ችግር እርዳታ የመስጠት እድል ባይኖራት የደረሰበትን ሀፍረትና ሀዘን ዝም ብላ ትመልከት? የየሱስ እጆች በመስቀሉ ላይ ተዘርግተው በምስማር ሲቸነከሩና ምስማሮቹ ለስላሳ ስጋውን በስተው ሲገቡ በማየታቸው እጅግ ያዘኑት ደቀ መዛሙርቱ ራስዋን የሳተችውን የየሱስን እናት ከዚያ ዘግናኝ ትእይንት ለማራቅ ተሸክመው ወሰዷት።

የሚያደርጉትን አያውቁምና …

አዳኛችን የማጉረምረም ወይም የቅሬታ ድምፅ አላሰማም። በፊቱ ላይ እርጋታና ፍፁም ሰላም ሲታይበት በግንባሩ ላይ ትልልቅ የላብ ጠብታዎች ይታዩ ነበር። በዚያ ወቅት በግንባሩ ላይ የነበረውን ላብ የሚጠርግለት ወይም ሰብዓዊ ልቡን ለማረጋጋት በታማኝነት ከጎኑ ቆሞ የሚያፅናናው ሰው አልተገኘም። ወታደሮቹ ያን ሁሉ አሰቃቂ ድርጊት እየፈፀሙበት ሳለ የሱስ “አባት ሆይ! የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው!” በማለት ለጠላቶቹ ፀለየላቸው። የሱስ የራሱን ስቃይ ችላ ብሎ ስለ አሳዳጆቹ ኃጢአትና ስለሚደርስባቸውም ቅጣት ተጨነቀ። የጭካኔ ድርጊት የፈፀሙትን ወታደሮች አልረገማቸውም። እቅዳቸው ስለተሳካላቸው በየሱስ መሰቃየት በተደሰቱት ካህናትና ሹማምንት ላይ የበቀል እርምጃ እንዲወሰድባቸው አልጠየቀም። በዚህ ፈንታ ስለ ድንቁርናቸውና ኃጢአታቸው አዘነላቸው። “የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው!” ብሎ ፀለየላቸው።

እነዚያ ሰዎች እንዲያ የሚያሰቃዩት የጠፋውን ሰብዓዊ ዘር ከዘላለም ጥፋት ለማዳን የመጣውን ጌታ መሆኑን ቢያውቁ ኖሮ ጸጸትና ድንጋጤ ይይዛቸው ነበር። ነገር ግን የሱስ አዳኛቸው መሆኑን አውቀው የመቀበል እድል ስለነበራቸው አለማወቃቸው ከኃጢአተኛነት ነፃ ሊደርጋቸው አልቻለም። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ኃጢአታቸውን አውቀው ንስሃ የሚገቡና የሚመለሱ ነበሩ። አንዳንዶቹ ንስሃ ባለመግባታቸው ምክንያት የሱስ ስለ እነርሱ ያቀረበው ፀሎት መልስ እንዳያገኝ አደረጉ። ያም ሆነ ይህ በዚያ ወቅት የእግዚአብሔር እቅድ በመፈፀም ላይ ነበር። የሱስም በአባቱ ፊት የሰው ዘር ጠበቃ የመሆን መብቱን እያስከበረ ነበር።

በዚያን ጊዜ የሱስ ለጠላቶቹ የፀለየው ፀሎት ዓለምአቀፋዊ ነው። ያ ፀሎት ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ጊዜ ፍፃሜ ድረስ የኖረውን ወይም የሚኖረውን ማንኛውንም ኃጢአተኛ ይመለከታል። እያንዳንዱ ሰው የሱስን የመስቀል ወንጀል ይመለከተዋል። እንደዚሁም እያንዳንዱ  ሰው ይቅርታ ተደርጎለታል። የሚፈልግ ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅና የዘላለም ህይወት ወራሽ መሆን ይችላል።

“የናዝሬቱ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ”

የሱስ በመስቀሉ ላይ በምስማር እንደተቸነከረ መስቀሉ በጠንካራ ሰዎች ተነስቶ በተዘጋጀለት ቦታ ላይ በኃይል ተተከለ። ይህ በሚደረግበት ጊዜ በየሱስ ላይ ትልቅ ስቃይ አደረሰበት። ጲላጦስ በዕብራይስጥ፣ በላቲንና በግሪክ የተፃፈ ማስታወቂያ በክርስቶስ ራስጌ በመስቀሉ ላይ አኖረ። ማስታወቂያው “የናዝሬቱ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ሲሆን ስያሜው አይሁዶችን አስቆጣቸው። አይሁዶች ቀደም ሲል በጲላጦስ አደባባይ “ስቀለው!” “ከቄሳር በቀር ሌላ ንጉስ የለንም” ሲሉ ጮኸው ነበር (ዮሐ.. 19፡15)። ሌላ ንጉስ ለመኖሩ እውቅና የሚሰጥ ሁሉ ከዳተኛ ነው ሲሉ አበክረው ተናገሩ። ጲላጦስ የፃፈው በስሜታቸው የገለፁትን ነበር። እነርሱ የአይሁድ ንጉሥ ከሚለው በስተቀር ሌላ ተቃውሞ አልነበራቸውም። ይህ ማስታወቂያ አይሁዶች ለሮም መንግስት ታማኝ የመሆናቸው ማረጋገጫ ነበር። ይህ ማስታወቂያ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ ብሎ የሚነሳውን ማንኛውንም ሰው አይሁዶች የሞት ፍርድ እንደሚፈርዱበት ያረጋግጣል። ካህናቱ ሳያውቁት ወሰናቸውን አለፉ። የሱስን ለመግደል በሚያሴሩበት ጊዜ ቀያፋ ህዝቡን ለማዳን አንድ ሰው ቢሞት የተሻለ ነው ሲል ተናግሮ ነበር። ታዲያ አሁን ግብዝነታቸው ተጋለጠ። ክርስቶስን ለማጥፋት ሲሉ የማንነታቸውን ህልውና ከአደጋ ላይ ለመጣል ዝግጁ ሆኑ።

ካህናቱ የሰሩት ነገር ወደ ምን እንደሚያመራ በገባቸው ጊዜ ማስታወቂያውን እንዲቀይር ጲላጦስን ጠየቁት። “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ብለህ አትፃፍ፣ ነገር ግን ይህ ሰው እኔ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ ብሎአል ብለህ ፃፍ፣” አሉት። ጲላጦስ ግን ቀደም ሲል ባሳየው ድክመት ተናድዶ ስለነበርና ካህናቱንና ሹማምቱን በቀናተኝነታቸውና በተንኮላቸው ምክንያት ንቆአቸው ስለነበር በግድ የለሽነት “የፃፍሁትን ፅፌአለሁ፣” ሲል መለሰላቸው።

ያ ማስታወቂያ እንደዚያ ተፅፎ እንዲሰቀል ያደረገ ከአይሁዶችና ከጲላጦስ በላይ የሆነ አንድ ኃይል ነበር። በእግዚአብሔር ፀጋ ይህ ማስታወቂያ ሰዎች ቅዱሳት መፃህፍትን እንዲመረምሩ ለማድረግ አሳባቸውን የሚቀሰቅስ ነበር። የሱስ የተሰቀለበት ቦታ ለኢየሩሳሌም ቅርብ ስለነበር ከልዩ ልዩ ቦታ ወደ ከተማው መጥተው የነበሩትን ሰዎች ማስታወቂያው ስለ የሱስ መሲህነት እንዲያስታውሱ አደረጋቸው። ስለዚህ ይህ ማስታወቂያ እግዚአብሔር በመራው እጅ የተፃፈ ህያው እውነት ነበር።

ትንቢቱና ፍጻሜው

የሱስ በመስቀል ላይ የተሰቃየው አስቀድሞ በተነገረ ትንቢት መሠረት ነው። ከመሰቀሉ ብዙ ምዕተ ዓመታት አስቀድሞ አዳኛችን ስለሚደርስበት ችግር ትንቢት ተናግሮ ነበር። “ክፉ ሰዎች እንደ ውሻ መንጋ ከበቡኝ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩ። አጥንቶቼ ተቆጠሩ፣ ጠላቶቼም በጥላቻ አይን ተመለከቱኝ። ልብሶቼን ተከፋፈሉ፣ በእጀ ጠባቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፣” ሲል ተናግሮ ነበር (መዝ. 22፡16-18)። ስለ ልብሱ የተነገረው ትንቢት ከየሱስ ጠላቶች ወይም ወዳጆች የተሰጠ አንድም መመሪያ ወይም ጣልቃገብነት ሳይኖር ተፈፀመ። የየሱስ ልብስ በመስቀል ላይ ለሰቀሉት ወታደሮች ተሰጠ። ወታደሮቹ ልብሱን በሚከፋፈሉበት ጊዜ በመካከላቸው የነበረውን ጭቅጭቅ የሱስ ይሰማ ነበር። “እጀ ጠባቡ ሳይሰፋ ከላይ እስከታች ወጥ ሆኖ የተሰራ፣” ስለነበር “ለማን እንደሚደርስ ለማወቅ ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ አንቅደደው ተባባሉ።”

በሌላ ትንቢት አዳኛችን “ስድብ ልቤን ስለሰበረው ተስፋ ቆረጥሁ፣ የሚያስተዛዝነኝ ሰው ፈለግሁ ነገር ግን ማንም አልነበረም። የሚያፅናናኝ ሰው ፈለግሁ ነገር ግን ማንም አልተገኘም። በምግቤ ውስጥ መራራ ነገር ቀላቀሉ፣ በጠማኝም ጊዜ በውሀ ፈንታ ሆምጣጤ ሰጡኝ” ሲል ተናግሮ ነበር (መዝ. 69፡20-21)። በመስቀል ላይ የስቃይ ሞት ለሚሞቱ ሰዎች የህመሙን ስሜት ለመቀነስ ሲባል የሚያደነዝዝ መድኃኒት መስጠት ይፈቀድ ነበር። ይህ ለየሱስ ቀርቦለት ነበር ነገር ግን አእምሮውን የሚያደነዝዝ ነገር መውሰድ ስላልፈለገ ቀምሶ ተወው። በእምነት እግዚአብሔርን መጠማጠም ነበረበት። የኃይሉ ምንጭ ይህ ብቻ ነበር። ህሊናውን ቢያደነዝዝ ኖሮ ለሰይጣን ጥቃት ይመቻች ነበር።

“የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ …”

የሱስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እያለ ጠላቶቹ ቁጣቸውን ገለፁ። ለመሞት በማጣጣር ላይ በነበረው ጌታችን ላይ ካህናት፣ ሹማምንትና ፀሀፍት ከአድመኛው ሕዝብ ጋር ተባብረው አፌዙበት።

የሱስ በተጠመቀና በተራራ ላይ በተለወጠ ጊዜ ክርስቶስ ልጁ መሆኑን በመግለፅ እግዚአብሔር ተናግሮ ነበር። እንደዚሁም የሱስ አሳልፎ ከመሰጠቱ በፊት እግዚአብሔር አብ የየሱስ መለኮታዊነት ማስረጃ የሆነውን ድምፁን አሰምቶ ነበር። አሁን ግን ከሰማይ ምንም ድምፅ አልተሰማም። ስለ የሱስ የተሰማ ምስክርነትም አልነበረም። ክፉ ሰዎች ያደረሱበትን መከራና ፌዝ ብቻውን ተጋፈጠ።

“የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ እስቲ ከመስቀል ውረድ” “እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠው መሲህ ከሆነ እስቲ ራሱን ያድን፣” እያሉ አላገጡበት። የሱስ በምድረ በዳ በተፈተነ ጊዜ ሰይጣን “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ እስቲ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ”፤ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ እስቲ ከዚህ (ከቤተ መቅደስ ጣራ) ወደታች ዘለህ ውረድ፣” ብሎ ነበር። ማቴ. 4፡3፣6። የሱስ በተሰቀለ ጊዜ ሰይጣንና መላእክቱ ሰው መስለው ከዚያ ነበሩ። ቀንደኛው ጠላትና ሰራዊቱ የካህናቱና የሹማምንቱ ተባባሪ ነበሩ። የህዝቡ መምህራን ምንም የማያውቁትን ተራ ሰዎች እንዲያውም ብዙዎቹ በሀሰት ለመመስከር እስከተጠሩበት ጊዜ ድረስ አይተውት በማያውቁት በየሱስ ላይ እንዲፈርዱ አነሳሱዋቸው። ካህናቱ፣ ሹማምንቱ፣ ፈሪሳውያንና ተራው ሕዝብ በሰይጣናዊ እብደት አንድ ግንባር ፈጠሩ። የሀይማኖት መሪዎች ከሰይጣንና ከመላእክቱ ጋር ተዋሀዱ፣ የእርሱ ትእዛዝ ፈጻሚም ሆኑ።

የሱስ እየተሰቃየ በሞት አፋፍ ላይ ሆኖ ካህናቱ “ሌሎችን አዳነ ራሱን ግን ማዳን አይችልም። እርሱ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ እስቲ አሁን ከመስቀል ይውረድ እኛም እንመንበት፣” ብለው የተናገሩትን እያንዳንዱን ቃል ሰማ። ክርስቶስ ከመስቀል መውረድ ይችል ነበር። ነገር ግን ኃጥአን በእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታንና ተተቀባይነትን ያገኙት እርሱ ራሱን ማዳን ስላልፈለገ ነው።

የትንቢት ተርጓሚዎች የተባሉት ሰዎች በአዳኛች ላይ ባፌዙበት ጊዜ ይህን ነገር እንደሚያደርጉ መንፈስ አስቀድሞ የተናረውን ቃል መደጋገማቸው ነበር። ይሁን እንጂ ህሊናቸው ስለታወረ በትንቢት የተነገረውን እየፈፀሙ መሆኑ አልታያቸውም። በማፌዝ “እሱ በእግዚአብሔር ታምኖአል የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎአል። ስለዚህ እግዚአብሔር የሚወደው ከሆነ  እስቲ አሁን ያድነው፣” ብለው የተናገሩት የምስክርነት ቃል ለዘመናት ሁሉ ሲነገር እንደሚኖር አላወቁም። እነዚህ ቃላት የተነገሩት ለፌዝ ቢሆንም ሰዎችን ከቀድሞው የበለጠ ቅዱሳት መፃህፍትን እንዲመረምሩ አድርገዋቸዋል። አስተዋይ ሰዎች አዳመጡ፣ መረመሩ፣ በጥልቀት አሰቡ፣ ፀለዩም። የክርስቶስን ተልዕኮ ምንነት እስኪረዱ ድረስ ጥቅስን ከጥቅስ እያወዳደሩ በማጥናት እረፍት የሌላቸው ሰዎች ተነሱ። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሰቀሉ ምክንያት ሰዎች ከዚያ በፊት ስለ እርሱ ካወቁት የበለጠ አጠቃላይ እውቀት አገኙ። ስቅለቱን ላዩና እርሱ የተናገረውን ለሰሙ ብዙ ሰዎች የእውነት ብርሀን በራላቸው።

“አቤቱ አስበኝ”

የሱስ በመስቀል ላይ ሆኖ በሚሰቃይበት ወቅት አንድ የሚያፅናናው ነገር ተገኘ። ይህም ንስሀ የገባው ሌባ የፀለየው ፀሎት ነው። ከየሱስ ጋር የተሰቀሉት ሁለት ሰዎች መጀመሪያ የሱስን ይሰድቡትና ያፌዙበት ነበር፤ በተለይ አንደኛው ከስቃዩ የተነሳ ተስፋ የቆረጠና እልኸኛ ነበር። ሁለተኛው ግን ከዚያ የተለየ ነበር። ይህ ሰው ልቡ የደነደነ ወንጀለኛ ሳይሆን በመጥፎ ጓደኞች ተመርቶ ወንጀል የሰራና በመስቀሉ ዙሪያ ቆመው የሱስን ይሰድቡ ከነበሩት ሰዎች ከአብዛኛዎቹ የተሻለ ወንጀለኛ ነበር። ሰውዬው ቀደም ሲል የሱስን የሚያውቅና ትምህርቱን አምኖ የተቀበለ ነበር፣ ነገር ግን በካህናቱና ሹማምንቱ ተፅዕኖ ከየሱስ እንዲርቅ ተደረገ። የህሊና ወቀሳውን ለማጥፋት ሲል ቀስ በቀስ ወደ ኃጢአት ማጥ ስለገባ በወንጀለኛነት ተያዘ፣ ወንጀለኛነቱ በምርመራ ስለተረጋገጠበት በስቅላት እንዲሞት ተፈረደበት። ይህ ሰው በፍርድ ቤቱ አዳራሽና ወደ ቀራንዮ በተደረገው ጉዞ ከየሱስ ጋር ነበር። ጲላጦስ “እነሆ ምንም በደል እንዳላገኙበት እንድታውቁ፣” ብሎ የተናገረውን ሰምቷል (ዮሐ. 19፡4)። ይህ ወንጀለኛ የየሱስን አምላካዊ ባህርይ ልብ ብሎ ተመልክቷል፣ የሚያሰቃዩትን ሰዎች በርህራሄ መንፈስ ይቅርታ ሲያደርግላቸውም አይቷል።

በመስቀል ላይ ሆኖ ትልልቅ የሀይማኖት ሊቃውንት ጌታ የሱስን ለማዋረድ አፋቸውን ለስድብ ሲከፍቱ አይቷቸዋል። ራሳቸውን ሲነቀንቁበትም ተመልክቷል። የወንጀል ተባባሪ ጓደኛው “አንተ መሲህ አይደለህምን? እስቲ በል ራስህንና እኛን አድን!” እያለ ሲዘልፈው ሰማ። አልፎ ሂያጆች የሱስን በመደገፍ ሲናገሩ አዳመጠ። የሱስ የተናገረውን እየጠቀሱ ሲያወሩና ስለ ፈፀማቸው ድርጊቶች ሲናገሩ ሰማ። በዚህ ጊዜ ቀደም ሲል በየሱስ መሲህነት ያመነው ትውስ አለውና ወደ ወንጀለኛ ባልደረባው ዘወር ብሎ “አንተ ደግሞ በሞት ፍርድ ላይ እያለህ እንኳ እግዚአብሔርን አትፍራምን?” አለው። እነዚህ በሞት አፋፍ ላይ ያሉ ሌቦች በዚያ ጊዜ ሰውን የሚፈሩት ምንም ምክንያት አልነበረም። ቢሆንም ከሁለቱ ወንጀለኞች አንዱ ሊፈሩት የሚገባ አምላክ እንዳለና የሚያስደነግጥ ጊዜ እንደሚመጣ አመነ። በኃጢአት እንደተበከለ የዚህ ሰው የህይወት ታሪክ ወደ ፍፃሜ ለመድረስ ተቃርቦ ነበር። “እኛ ባደረግነው በደል ምክንያት ቅጣት መቀበላችን የተገባ ፍርድ ነው። ይህ ሰው ግን ምንም ጥፋት አላደረገም፣” ሲል እያቃሰተ ተናገረ።

አሁን ጥያቄ፣ ጥርጣሬና ሀፍረት ሁሉ ጠፋ። ይህ ሌባ በወንጀሉ ምክንያት የሞት ፍርድ በተበየነበት ጊዜ ተስፋ ቆርጦ ነበር፣ አሁን ግን አዲስና ጥሩ አስተሳሰብ በውስጡ ማንሰራራት ጀመረ። የሱስ ህሙማንን እንደፈወሰና ኃጢአትን ይቅር እንዳለ የተናገረው ሁሉ አንድ በአንድ ትዝ ይለው ጀመር። በየሱስ የሚያምኑ ሰዎች እያለቀሱ በሚከተሉት ጊዜ ይናገሩ የነበረውን ሰምቶ ነበር። በየሱስ ራስጌ የተሰቀለውን ማስታወቂያ አንብቦ ነበር። ከአልፎ ሂያጆች መካከል አንዳንዶቹ ማስታወቂያውን በሀዘንና በፍርሀት አንዳንዶቹ ደግሞ በንቀትና በፌዝ ሲያነብቡ አይቷል። መንፈስ ቅዱስ ኅሊናውን ብሩህ ስላደረገለት ስለ የሱስ ማንነት መረጃዎች ቀስ በቀስ ተያያዙለት። በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሰውነቱ የቆሳሰለውና መሳቂያና መሳለቂያ የሆነው የሱስ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው የእግዚአብሔር በግ መሆኑን አወቀ። ይህ አቅመቢስ የሆነና  በሞት አፋፍ ላይ የነበረ ሰው በሞት አፋፍ ላይ ለነበረ አዳኝ ራሱን በሰጠ ጊዜ የተስፋና የስቃይ ስሜት በተቀላቀለበት አንደበት “አስበኝ አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ፣” ሲል ጮኸ። መልሱን ወዲያው አገኘ። ፍቅር፣ ርህራሄና ኃይል በተሞላበት፣ በለሰለሰና ጣዕመ ዜማ ባለው አነጋገር አዳኛችን “እውነት እልሀለሁ ዛሬ፤ ከእኔ ጋር በገነት እንድትሆን፣” ሲል አረጋገጠለት።

የሱስ ለረጅም ጊዜ እየተሰቃየ ይሰማ የነበረው ስድብና ፌዝ ብቻ ነበር። በመስቀል ላይ ተንጠልጥሎ ከፌዝና ከእርግማን ሌላ የሚሰማው ነገር አልነበረም። ከደቀመዛሙርቱ የእምነት መግለጫ ድምፅ ለመስማት ጓጉቶ ነበር ነገር ግን በዚህ ፈንታ የሰማው “እኛ ግን እስራኤልን የሚያድን እርሱ ነው ብለን ተስፋ አድርገን ነበር” የሚል የሀዘን እንጉርጉሮ ብቻ ነው። ጌታችን በሞት አፋፍ ላይ ከነበረ አንድ ሌባ የእምነትና የፍቅር መግለጫ ንግግር መስማቱ ምን ያህል አስደስቶት ይሆን! የአይሁድ መሪዎች በናቁትና ደቀ መዛሙርቱ እንኳ መለኮታዊነቱን በተጠራጠሩት ሰዓት ለዘላለማዊ ህይወት የተዘጋጀ አንድ ምስኪን ሌባ የሱስን ጌታ ብሎ ጠራው። የሱስ ተአምራት በሠራ ጊዜና ከሞት ከተነሳ በኋላ ብዙዎች ጌታ ሊሉት ዝግጁ ነበሩ ነገር ግን በመስቀል ላይ ተቸንክሮ ሊሞት በተቃረበበት ሰዓት ከህይወቱ በመጨረሻዋ ደቂቃ አካባቢ ንስሀ ገብቶ ከዳነው ሌባ በስተቀር ጌታ ብሎ የጠራው ማንም የለም።

በመስቀሉ አጠገብ የቆሙ ሰዎች ሌባው የሱስን ጌታ ሲለው ሰሙት። ንስሀ የገባው ሰውዬ አነጋገር ትኩረታቸውን ሳበው። በመስቀሉ ግርጌ ሆነው ስለ ክርስቶስ ልብስ ይጨቃጨቁና እጣ ይጣጣሉ የነበሩም ጩኸታቸውን አቁመው አዳመጡ። የቁጣ ንግግራቸውን ጋብ አድርገው ከየሱስ አንደበት የሚወጣውን መልስ ለመስማት አፋቸውን ከፍተው ተጠባበቁ።

የሱስ ለሰውዬው የዘላለም ህይወት ተስፋ በሰጠው ጊዜ መስቀሉን እንደመሸፈን አድርጎት የነበረውን ዳመና ዘልቆ የመጣ ብሩህ ብርሀን ታየ። ንስሃ የገባው ሌባ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ስላገኘ ፍፁም ሰላም አገኘ። ክርስቶስም በውርደቱ መካከል ክብር አገኘ። በሰው ዘንድ የተሸነፈ የመሰለው ጌታ አሸናፊ ሆነ፣ ኃጢአት ተሸካሚ መሆኑም ታወቀ። ሰዎች በስጋዊ አካሉ ላይ ኃይላቸውን ማሳየት፣ በሾህ አክሊል ጆሮ ግንዱን መውጋት፣ ልብሱን ገፍፈው ስለ ልብሱ መጨቃጨቅ ይችላሉ ነገር ግን ለኃጢአት ይቅርታ የመስጠት ኃይሉን ሊነጥቁት አልቻሉም። በሞቱ ስለ መለኮታዊነቱና ስለ እግዚአብሔር ክብር መሰከረ። ጆሮው ቶሎ የማይሰማ፣ እጁም ለመፈወስ ያጠረ አይደለም። በእርሱ አማካይነት ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ሁሉ ፈፅሞ ለማዳን መለኮታዊ ስልጣን አለው።

“እውነት እልሀለሁ ዛሬ፤ ከኔ ጋር በገነት እንድትሆን።” ክርስቶስ ንስሀ ለገባው ሌባ በዚያው ቀን ይዞት ገነት እንደሚገባ ተስፋ አልሰጠውም ምክንያቱም የሱስ ራሱ በዚያ ቀን ወደ ገነት አልሄደምና። በመቃብር ውስጥ ከቆየ በኋላ በትንሳኤ ዕለት ጥዋት “ገና ወደ አባቴ አልወጣሁምና፣” ሲል ተናግሯል (ዮሐ. 20፡17)። ነገር ግን ሽንፈትና ጨለማ የሰፈነበት በመሰለው የስቅለት ቀን ለሰውዬው ወደ ገነት የመግባት ተስፋ ተሰጠው። የሱስ እንደ ወንጀለኛ በተሰቀለበት ቀን ንስሀ ለገባው ወንጀለኛ “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ!” ሲል አረጋገጠለት።

ቀንደኛው ወንጀለኛ

“ከኢየሱስ ጋር ሁለት ወንበዴዎችን አምጥተው አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው” እርሱን በመካከል አድርገው ሰቀሉ። ይህ እንዲሆን መመሪያ የሰጡ ካህናቱና ሹማምንቱ ናቸው። ክርስቶስ በመካከል ሆኖ እንዲሰቀል የተደረገበት ምክንያት ከሶስቱ ከፍተኛው ወንጀለኛ እርሱ መሆኑን ለማሳወቅ ነው። ይህ በመሆኑ “ከክፉ አድራጊዎችም ጋር ተቆጥሮአል፣” የሚለው ትንቢት ተፈፀመ (ኢሳ. 53፡12)። ካህናቱ የድርጊታቸው ትክክለኛ ትርጉም አልገባቸውም። የሱስ ከሌቦች መካከል መሰቀሉ የሚያመለክተው መስቀሉ በኃጢአት በጠፋ ዓለም መካከል የተተከለ መሆኑን ነው። በዚህ መስቀል ላይ ንስሀ ለገባው ሌባ የተነገረው የኃጢአት ይቅርታ በዓለም ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ የሚያበራ የተስፋ ብርሀን ፈነጠቀ።

የሱስ ከፍተኛ የህሊናና የአካል ጭንቀት በሚያሰቃየው ወቅት ራሱን ችላ ብሎ ለሌሎች ብቻ በማሰብ ያን ሌባ እንዲያምን ሲያደፋፍረው ባዩ ጊዜ መላእክት የፍቅሩ ወሰን የለሽነት አስገረማቸው። ያ ሁሉ ውርደት በደረሰበት ወቅት የሱስ ነቢይ እንደመሆኑ መጠን ለኢየሩሳሌም ሴቶች ትንቢት ተናገረ፤ ካህንና ጠበቃ እንደመሆኑም የእርሱን ገዳዮች አባቱ ይቅርታ እንዲያደርግላቸው ተማፀነ፤ አፍቃሪ አዳኝ በመሆኑም ንስሀ የገባውን ወንጀለኛ ኃጢአቱን ይቅር አለለት።

“እናቴ ሆይ! እነሆ ልጅሽ!”

የሱስ በዙሪያው የነበረውን ሕዝብ በዓይኑ ሲቃኝ ሀሳቡ በአንድ ሰው ላይ አረፈ። በመስቀሉ አጠገብ እናቱ በዮሐንስ ተደግፋ ቆማ አየ። ማርያም ከልጅዋ ተለይታ መቆየት ስላልቻለች ዮሐንስም የሱስ በህይወት ብዙ እንደማይቆይ ስላወቀ ወደ መስቀሉ መልሶ አመጣት። የሱስ በሞት አፋፍ ላይ እያለ እናቱን አስታወሰ። በሀዘን የተጎሳቆለውን የእናቱን ፊትና ዮሀንስን እየተመለከተ እናቱን “እናቴ ሆይ! እነሆ ልጅሽ!” አላት፤ ዮሐንስንም “ይህችውልህ እናትህ!” አለው። ዮሐንስ የሱስ የተናገረው በትክክል ስለገባው አደራውን ተቀበለ። ወዲያውኑ ማርያምን ወደ ቤቱ ወስዶ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ልዩ እንክብካቤ አደረገላት። አዛኙና አፍቃሪው አዳኛችን በዚያ የአካልና የህሊና ስቃይ መካከል ለእናቱ ተጨነቀ። የሱስ ለእናቱ እንክብካቤ የሚሆን ገንዘብ አላዘጋጀላትም ነገር ግን እርሱ በዮሐንስ ልብ ላይ የተቀረፀ ስለሆነ ለዮሐንስ እናቱን እንደተከበረ የመታሰቢያ ቅርስ አድርጎ አስረከበው። እናቱ እርሱን ስለወደደችው የሚወዳትና የሚራራላት ሰው አዘጋጀላት። ዮሐንስም እርስዋን እንደተቀደሰ አደራ አድርጎ በመቀበሉ ትልቅ በረከት አገኘ። ማርያም ለዮሐንስ የተወደደ ጌታው የዘወትር ማስታወሻ ሆነችለት።

የሱስ ለእናቱ ያሳየው ፍፁም የሆነ ፍቅር በምሳሌነቱ የዘመናት ጭጋግ ሳይከልለው እንደ ንፁህ ሉል ሲያንፀባርቅ ኖረ። የሱስ ለሰላሳ ዓመታት ያህል የጉልበት ስራ እየሰራ የቤተሰብን ኃላፊነት ለመወጣት አስተዋፅኦ አድርጓል። አሁን ደግሞ በመሰቃየት ላይ እያለ ላዘነችውና ባልዋ ለሞተባት እናቱ መንከባከቢያ ማዘጋጀት እንዳለበት አልረሳም። እያንዳንዱ የጌታ ደቀ መዝሙር ይህ ዓይነት መንፈስ ሊኖረው ይገባል። የክርስቶስ ተከታይ የሆኑ ሁሉ ወላጆቻቸውን ማክበርና ለወላጆቻቸው መጠንቀቅ እንዳለባቸው ከሀይማኖታቸው የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ማወቅ አለባቸው። አባትና እናት የክርስቶስ ፍቅር ከነገሠበት ልብ ጥንቃቄና ርህራሄ አይነፈጋቸውም።

መድኃኒዓለም፤ ቤዛና መድኅን

የክብር አምላክ የሆነው የሱስ ለሰብዓዊ ዘር ቤዛ ሆኖ የሚሞትበት ሰዓት ተቃረበ። ውድ ህይወቱን አሳልፎ በመስጠቱ የሱስ በድል አድራጊነት ደስታ አልተኩራራም። ሁሉም ነገር ተስፋ አስቆራጭ ሆነበት። ከባድ ሸክም የሆነበት የመሞት ፍርሀት አይደለም። በአንደበት ሊገለፅ የማይቻል ስቃይ ያመጣበት ህመም የመስቀል ውርደት አልነበረም። በዓለም ላይ እንደ የሱስ የተሰቃየ ማንም የለም። ለስቃዩ ዋና ምክንያት የሆነው ግን ለኃጢአት የነበረው የጥላቻ ስሜትና ሰዎች ኃጢአትን በመለማመድ የኃጢአትን ግዙፍነት ለማየት ዓይናቸው መታወሩን ማወቁ ነው። ኃጢአት የሰውን ልብ ምን ያህል አጥብቆ እንደያዘና ከኃጢአት ኃይል ነፃ ለመውጣት ፈቃደኛ የሚሆኑ ሰዎች ምን ያህል ጥቂት እንደሆኑ ግልፅ ሆኖ ታየው። ያለ እግዚአብሔር እርዳታ ሰብዓዊ ዘር ሁሉ እንደሚጠፋ አወቀ፤ በቂ እርዳታ ማግኘት ሲችሉ ብዙ ሰዎች እንደሚጠፉም ታየው።

የሱስ የእኛ ቤዛና መድኅን ስለሆነ ኃጢአታችንን ተሸከመ። እኛን ከህግ ቅጣት ለማዳን ሲል እንደ ህግ ተላላፊ ተቆጠረ። የአዳም ዘር ሁሉ ኃጢአት ልቡን አስጨነቀው። እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ ያለው ቁጣና በአመጽ ምክንያት የሚሰማው ቅሬታ የልጁን ነፍስ አስጨነቃት። ክርስቶስ መላ ህይወቱን ስለ አባቱ የመሀሪነትና የይቅር ባይነት መልካም ታሪክ ለወደቀው ዓለም ሲያበስር ኖረ። የብስራቱ ርዕስ መዳን ከኃጢአተኛ ሁሉ ለባሰ ኃጢአተኛ የሚል ነው። አሁን ግን በላዩ ላይ ባረፈው የኃጢአት ሸክም ምክንያት የአባቱን ይቅር ባይ ፊት ማየት አልቻለም። የመረረ ስቃይ በደረሰበት ወቅት የአባቱ መለኮታዊ ገፅታ ከእርሱ በመራቁ የአዳኛችን ልብ በሀዘን ምን ያህል እንደተጎዳ ሰው ሙሉ በሙሉ ሊረዳው አይችልም። በዚህ ምክንያት የደረሰበት ስቃይ እጅግ የከፋ ከመሆኑ የተነሳ በሥጋዊ አካሉ ላይ የደረሰው ጉዳት እንዳልተሰማው ይቆጠራል።

ሰይጣን በከባድ ፈተና የሱስን ልብ አስጨነቀው። አዳኛችን ከመቃብሩ በር አሻግሮ ማየት ተሳነው። ከመቃብር በአሸናፊነት እንደሚነሳና የሚከፍለው መስዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንደሚያገኝ ተስፋ ማድረግ ተሳነው። ኃጢአት እጅግ አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ እርሱና አባቱ ለዘላለም ተለያይተው የሚቀሩ መሰለው። በዚህ ጊዜ የሱስ ይሰማው የነበረው ስቃይ ለኃጢአተኛው ሰብዓዊ ዘር የሚደረገው የምህረት ምልጃ ካበቃ በኋላ ኃጢአተኞች ከሚሰማቸው ስቃይ ጋር ይመሳሰላል። የእግዚአብሔርን ልጅ የጎዳውና የጠጣውንም ፅዋ እጅግ የመረረ ያደረገው በሰው ምትክ ሆኖ የእግዚአብሔርን ቁጣ እንዲቀበል ያደረገው የኃጢአት ምንነት ስለተሰማው ነው።

ከስድስት እስከ ዘጠኝ ሰዓት

የአዳኛችንን ተስፋ የመቁረጥ ስቃይ መላእክት በመገረም ተመለከቱ። የሰማይ ሠራዊት ያን አስከፊ ትዕይንት ላለማየት ፊታቸውን ሸፈኑ። ግዑዙ ፍጥረትም ለተዋረደውና በሞት አፋፍ ላይ ላለው ፈጣሪዋ ማዘንዋን ገለፀች። በእኩለ ቀን ላይ ለመሬት ሙሉና ብሩህ ብርሃንዋን ትሰጥ የነበረችው ፀሀይ በድንገት ድርግም አለች። አስከሬን የያዘ ሳጥን በጥቁር ግምጃ እንደሚሸፈን ዓይነት ጥቅጥቅ ያለ ጨለማ መስቀሉን ሸፈነው። “ከቀኑም ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ።” ይህ ጨረቃ ወይም ከዋክብት እንደሌሉበት እኩለ ሌሊት ጥቅጥቅ ያለ ጨለማ የተከሰተው በፀሀይ ግርዶሽ ወይም በሌላ ተፈጥሮአዊ ክስተት ምክንያት አይደለም። ይህ ጨለማ ከዚያ ጊዜ በኋላ የሚመጣው ትውልድ እምነቱ የፀና እንዲሆን እግዚአብሔር ያዘዘው ተዓምራዊ ምስክርነት ነው።

ያ ጥቅጥቅ ጨለማ እግዚአብሔርን ከመታየት ከለለው። አብ ጨለማን ሽፋን አድርጎ ክብሩን ከሰብዓዊ ዓይን ሰወረ። በዚህ ወቅት እግዚአብሔርና መላእክቱ በመስቀሉ አጠገብ ነበሩ። እግዚአብሔር አብ ከልጁ ጋር ሆነ። ይሁን እንጂ ከዚያ መኖሩ አልተገለፀም። ክብሩ ዳመናውን አልፎ ቢገለጥ ኖሮ ከዚያ የነበሩት ሰዎች በሙሉ ያልቁ ነበር። ያ ቢሆን ደግሞ በእግዚአብሔር ከዚያ መገኘት ክርስቶስ አይፅናናም ነበር። የሱስ የወይን ጠጅ መጭመቂያውን ብቻውን ረገጠ ከህዝቡም አንድ ሰው ከእርሱ ጋር አልተገኘም።

እግዚአብሔር በልጁ ላይ የደረሰውን የመጨረሻ ሰብዓዊ ስቃይ በጥቅጥቅ ጨለማ ከለለው። ክርስቶስ ሲሰቃይ ያዩ ሁሉ መለኮታዊነቱን አውቀዋል። ያ ሰብዓዊ ፍጡራን ያዩት ፊት ፈፅሞ የሚረሳ አልነበረም። የቃየል ፊት ነፍሰ ገዳይነቱን እንዳሳወቀበት ሁሉ እንዲሁም በክርስቶስ ፊት ላይ የእግዚአብሔር ገፀ ባህርይ የሆነው ንፅህና፣ ፍፁም ሰላማዊነትና ርህሩህነት ይታይበት ነበር። የየሱስ ከሳሾች ግን ለሰማይ ማህተም ደንታ አልነበራቸውም። የሱስ የሚያፌዙበት ሰዎች ቀና ብለው እየተመለከቱት ለረጅም ሰዓታት ሲሰቃይ ቆየ፣ በኋላ ግን እግዚአብሔር በምህረቱ በካባው ከለለው።

በቀራንዮ ላይ የመቃብር ፀጥታ የሰፈነበት መሰለ። በመስቀሉ ዙርያ ተሰብስቦ የነበረው ሕዝብ ምክንያቱ ያልታወቀ ፍርሀት አስጨነቀው። ስድቡና እርግማኑ ሁሉ በድንገት ተቋረጠ። ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች በመሬት ላይ ተዘረሩ። አንዳንድ ጊዜ ዳመናውን ዘልቆ በሚታየው ብልጭታ አማካይነት መስቀሉና የተሰቀለው አዳኝ ይታዩ ነበር። ካህናቱ፣ ሹማምንቱ ፀሀፍት፣ ወንጀለኛ ሰቃዮችና ለአድማ የተጠራው ሕዝብ ቅጣታቸውን የሚያገኙበት ጊዜ የመጣ መሰላቸው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንዳንድ ሰዎች የሱስ ከመስቀል ወርዶ ሊመጣ ነው እያሉ ማሾክሾክ ጀመሩ። አንዳንዶቹ ከፍርሀት የተነሳ እየጮኹና ደረታቸውን እየመቱ በዳበሳ ወደ ከተማው ለመመለስ ሞከሩ።

“ኤሎሄ! ኤሎሄ!”

በዘጠነኛው ሰዓት ህዝቡን የሸፈነው ጨለማ ቢወገድም የሱስን እንደ ከለለው ቆየ። ይህ ጨለማ የየሱስን ልብ ያስጨነቀው ስቃይ ምሳሌ ነበር። ማንም ሰብዓዊ ዓይን በመስቀሉ ዙሪያ የነበረውን ጨለማ አልፎ ለማየት እንዳልቻለ ሁሉ እንደዚሁም የክርስቶስን ነፍስ ከብቦ ያስጨንቃት የነበረውን ጥቅጥቅ ጨለማ አልፎ ለማየት የቻለ ማንም የለም። የሱስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እያለ የመብረቅ ብልጭታው ወደ እርሱ የሚምዘገዘግ ይመስል ነበር። በዚህ ጊዜ የሱስ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ። የሱስን ከብቦት የነበረው የውጨኛው የጨለማ ሽፋን በተነሳ ጊዜ ይህን ሰው ሰማይ ተበቀለው፣ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላለ የእግዚአብሔር ቁጣ ወረደበት የሚል የብዙ ሰዎች ጩኸት ተሰማ። በእርሱ ከሚያምኑ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ያሰማውን ጩኸት በሰሙ ጊዜ ተስፋ ቆረጡ። እግዚአብሔር የሱስን ከተወው ተከታዮቹ በምን መተማመን ይችላሉ?

ጨለማው ከተጨነቀው የክርስቶስ መንፈስ ላይ በተነሳ ጊዜ የሱስ የስጋዊ ስቃይ ተሰማውና “ጠማኝ” አለ። ከሮማውያን ወታደሮች አንዱ የደረቁት የየሱስን ከንፈሮች ስላየ አዝኖ “ስፖንጅ አምጥቶ ሆምጣጤ ሞላበት። በመቃ ላይ አድርጎም ኢየሱስ እንዲጠጣ አቀረበለት።” ካህናቱ ግን በየሱስ ስቃይ አፌዙ። መሬትዋ በጨለማ በተሸፈነች ጊዜ እነዚህ ካህናት በፍርሀት ተውጠው ነበር ነገር ግን ድንጋጤአቸው ከለቀቃቸው በኋላ የሱስ ያመልጥ ይሆናል የሚል ስጋታቸው እንደገና አስጨነቃቸው። “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” ሲል የተናገረውንም አጣምመው ተረጎሙት። በከፍተኛ ንቀትና በማንቋሸሽ “ይህስ ኤልያስን ይጠራል!” ተባባሉ። “ቆይ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደሆነ እንይ!” እያሉ ከስቃዩ ለማዳን የነበራቸውን የመጨረሻ ዕድል ነፈጉት።

እንከን የማይወጣለት የእግዚአብሔር ልጅ ሰውነቱ ቆሳስሎ፣ ለእርዳታ የሚዘረጉ እጆቹ በምስማር ከእንጨት ላይ ተቸንክረው፣ የፍቅር አገልግሎት ለመስጠት መጓዝ የማይሰለቻቸው እግሮቹ በግንድ ላይ በካስማ ተመትተው፣ ያ ንጉሣዊ ራሱ በሾህ አክሊል ተበሳሰስቶና የሚንቀጠቀጡት ከንፈሮቹ የወዮታ ጩኸት እያሰሙ በመስቀል ላይ ተንጠለጠለ። ከራሱ፣ ከእጆቹና፣ ከእግሮቹ የፈሰሰው ደም፣ መላ አካሉን ያጎሳቆለው ጣዕረ ሞት አባቱ ፊቱን ከእርሱ ስለመለሰ የተሰማው በአንደበት ሊገለፅ የማይቻል ስቃይ ሁሉ ተዳምሮ የእግዚአብሔር ልጅ ይህን ሁሉ የኃጢአት ፍዳ የተቀበለው የሞትን ኃይል አሸንፎ ለአንተ የገነትን በር ለመክፈት ሲል ነው እያለ ለእያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር የሚናገር መልእክት ነው። ኃይለኛውን የባህር ማዕበል ፀጥ ረጭ እንዲል አድርጎ በአረፋ የተሸፈነውን የውሀ ፈረሰኛ ያስወገደው፣ የጠፉ ዓይኖችን እንዲያዩ ያደረገውና ሙታንን ያስነሳው ጌታ አንተን ስለወደደህ ራሱን በመስቀል ላይ ሰዋ። የኃጢአት ተሸካሚ የሆነው ጌታ ፍትሀዊ የሆነውን መለኮታዊ ቁጣ ችሎ ለአንተ ሲል እንደ ኃጢአተኛ ሆነ።

“ተፈፀመ!”

ከዚያ ቆመው ይመለከቱ የነበሩት ሰዎች ፀጥ ብለው የአስፈሪውን ትዕይንት ፍፃሜ ይጠባበቁ ነበር። የፀሀይ ብርሃን ቢታይም መስቀሉ በጨለማ እንደተሸፈነ ቆየ። ካህናቱና ሹማምንቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለከቱ ከተማዋና የይሁዳ መስኮች በከባድ ዳመና ተሸፍነው አዩ። የፅድቅ ፀሀይና የዓለም ብርሀን የሆነው ጌታ በአንድ ወቅት ተወዳጅ ከነበረችው ከተማ ብርሃኑን አነሳ። አስፈሪ የሆነው የእግዚአብሔር የቁጣው ብልጭታ ለመጥፋት በተዘጋጀችው ከተማ ላይ ተነጣጠረ።

መስቀሉን ሸፍኖት የነበረው ጨለማ በድንገት እንደለቀቀ እንደ መለከት ከሩቅ በሚሰማ ድምፅ የሱስ “ተፈፀመ!” “አባት ሆይ! እነሆ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ!” ሲል ጮኸ። በዚያች ወቅት በመስቀሉ ላይ ብርሀን ስለወጣ የአዳኛችን ፊት እንደ ፀሀይ በደመቀ ክብር አበራ። ከዚያ በኋላ ራሱን በደረቱ ላይ ጣል አድርጎ አረፈ።

በእግዚአብሔር ፈፅሞ ችላ የተባለ በመሰለበት በዚያ አስከፊ የጨለማ ወቅት ክርስቶስ የመጨረሻውን ሰብዓዊ የወዮታ ፅዋ ጠጣ። በዚያ እጅግ አስጨናቂ ጊዜ የሱስ የተማመነው ከዚያ በፊት በአባቱ ዘንድ ተቀባይነት እንደነበረው ባየው ማረጋገጫ ነው። የአባቱን ባህርይ፣ ፍርዱ ፍትሀዊ መሆኑን፣ መሀሪነቱንና ታላቅ ፍቅሩን ያውቅ ነበር። የሱስ የአባቱን ትእዛዝ ለመፈፀም ምንጊዜም ደስታኛ ስለነበር እምነቱን በዚህ አባቱ ላይ አደረገ። ራሱን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ስላስገዛ አባቱ እንደተለየው ይሰማው የነበረው ስጋት ለቀቀው፤ ስለዚህ ክርስቶስ በሀይማኖት አሸናፊ ሆነ።

እንደዚህ ያለ ትእይንት በዓለም ከቶ ታይቶ አይታወቅም። በዚያ የነበሩት ሰዎች አፍዝ አደንግዝ እንደያዛቸው ሁሉ አፋቸውን ከፍተው አዳኛችንን አንጋጠው ይመለከቱት ነበር። መሬት እንደገና በጨለማ ተሸፈነች፣ የነጎድጓድ ድምፅም ተሰማ። ወዲያውኑ ከባድ የመሬት መናወጥ ደረሰ። በነውጡ ምክንያት ሰዎች እየተናጡ ተደራርበው ወደቁ። በአካባቢው ከነበሩ ጋራዎች  የተሰነጠቀው አለት እንደ ናዳ እየተንከባለለ ወደ ደልዳላው ቦታ ወረደ። መቃብሮች ተከፍተው ሬሳዎች እየተስፈነጠሩ ወጡ። መላው ፍጥረት የሚንቀጠቀጥ መሰለ። ካህናት፣ ሹማምንት፣ ወታደሮች፣ ወንጀለኛ ሰቃዮች ከዚያ የነበሩ ሰዎች ሁሉ እንደ ድዳ አንደበታቸው ታስሮ በመሬት ላይ ተዘረሩ።

“ተፈፀመ!” የሚለው ጩኸት ከየሱስ አንደበት በወጣበት ወቅት ካህናት በቤተ መቅደሱ ውስጥ ስርዓተ አገልግሎት ያካሂዱ ነበር። ጊዜው የምሽት መስዋዕት የሚቀርብበት ሰዓት ስለነበር የየሱስ ምሳሌ የሆነው የመስዋዕት በግ ለመታረድ ቀረበ። ካህኑ የተዋበውን ልብሰ ተክህኖ ተጎናፅፎ አብርሀም ልጁን ለመሰዋት በተዘጋጀ ጊዜ እንዳደረገው ቢላዋውን በእጁ ይዞ ቆመ። ህዝቡም በከፍተኛ ጉጉት ይመለከቱ ነበር። ነገር ግን ጌታ ራሱ ስለቀረበ መሬት ተናወጠች። የቤተ መቅደሱን የውስጠኛውን መጋረጃ የማይታይ እጅ ከላይ እስከ ታች ተርትሮ ከሁለት ስለከፈለው በአንድ ወቅት የእግዚአብሔር ክብር መግለጫ የነበረው ቦታ ለህዝቡ ክፍት ሆኖ ታየ። የእግዚአብሔር ክብር ይገለጥ የነበረው የፅላቱ ክዳን በሆነው የስርየት መክደኛ ከሚባለው በላይ ነበር። ይህን ክፍል ከሌሎቹ የቤተ መቅደሱ ክፍሎች የሚለየውን መጋረጃ መክፈት የሚፈቀድለት ሊቀ ካህኑ ብቻ ነበር። ሊቀ ካህኑ በዓመት አንድ ጊዜ የህዝቡን ኃጢአት ለማስተሰረይ ወደዚህ ክፍል ይገባ ነበር።

አሁን ግን ይህን ክፍል (ቅድስተ ቅዱሳን) ከሌላው የሚለየው መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀደደ። ስለዚህ የምድራዊ ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ቅድስናው አከተመ።

የቤተ መቅደሱ መጋረጃ መቀደድ ትልቅ ፍርሀትና ትርምስ አስከተለ። ካህኑ ለመስዋዕት የቀረበውን በግ ለማረድ ተዘጋጅቶ ነበር። ነገር ግን ቢላዋው ከእጁ ወደቀ በጉም አመለጠ። በእግዚአብሔር ልጅ ሞት ምሳሌያዊው መስዋዕት በእውነተኛው መስዋዕት ተተካ። ትልቁ መስዋዕት ተሰዋ። ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግቢያው በር ተከፈተ። ለሁሉም አዲስና ህያው መንገድ ተዘጋጀ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ኃጢአተኛና ያዘኑ ሰብዓዊ ፍጡራን የሊቀ ካህን መምጣት መጠበቅ አላስፈለጋቸውም። ከዚያ ጊዜ በኋላ አዳኛችን ካህንና ጠበቃ ሆኖ በሰማየ ሰማያት ያገለግላል። የቤተ መቅደሱ መጋረጃ በተቀደደ ጊዜ አንድ ድምፅ ለስግደት ለመጡት ሰዎች ለኃጢአት ስርየት የሚቀርበው መስዋዕትና ቁርባን አከተመ ያላቸው ይመስል ነበር። የሱስ በቃሉ መሰረት “አምላኬ ሆይ! በመፅሀፍ ስለ እኔ እንደተፃፈ ፈቃድህን ለመፈፀም መጥቻለሁ፣” አለ፤ “በዚህ ሁኔታ ሁለተኛውን ዓይነት መስዋዕት በቦታው ለመተካት የመጀመሪያውን ዓይነት መስዋዕት ሽሮአል”፤ “ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ በማያዳግም ሁኔታ መስዋዕት ሆኖ በመቅረቡ ምክንያት ተቀድሰናል”፤ “ክርስቶስ ግን ለዘላለም የሆነውን አንዱን መስዋዕት ካቀረበ በኋላ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ተቀምጦአል” ዕብ. 10፡7፣ 9፣ 10፣ 12።

(ይህ ጽሁፍ “ቀራንዮ” በሚል ርዕስ “የዘመናት ምኞት” በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 78 ላይ ይገኛል፤ ጽሁፉ የተመሠረተው ማቴ. 27፡31-53፣ ማር. 15፡20-38፣ ሉቃ. 23፡26-46፣ ዮሐ. 19፡16-30 ላይ ነው፤ ተርጓሚ አበበ ብዙነህ)


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *