giziew.org

ክርስቶስ ፋሲካችን

“እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና”
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

“ከዚያም ከብዙ ቀን በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የግብፅ ንጉሥ ሞተ የእስራኤልም ልጆች ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፥ ጮኹም፥ ስለ ባርነታቸውም ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ። እግዚአብሔርም የለቅሶአቸውን ድምፅ ሰማ፥ እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃልኪዳን አሰበ። እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች አየ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ያለውን ነገር አወቀ” (ዘፀአት 2፡23-25)።

በባርነት ቀንበር ሥር በመንገፍገፍ፣ በመጨነቅና ዕርዳታን በመፈለግ በመጮኽ ላይ ለነበሩት እስራኤላውያን፣ በመጨረሻ እግዚአብሔር የለቅሶአቸውን ድምፅ ሰማ፤ ቃልኪዳኑን አሰበ፤ የመጎብኘታቸውም ጊዜ ደረሰ።  

ጊዜው የዛሬ 3,500 ዓመት ገደማ ይሆናል፤ በግብፅ ምድር የተፈጸመ ታሪክ ነው። ቀኑ እጅግ ታሪካዊ ስለሆነ ሁልጊዜ ሲታወስ ይኖራል። ባሮች ነጻ የወጡበት ቀን፣ አዲስ ስብዕና፣ አዲስ ማንነት የተቀበሉበት ቀን፣ አዲስ ጅማሬ ያገኙበት ቀን፣ እንደ ሕዝብና የአምላክ ሠራዊት የተቆጠሩበት ቀን፣ በግብፅ ውስጥ የመጨረሻ ቆይታ የሚያደርጉበት ቀን፣ በግብፅ ውስጥ የመጨረሻ ራት የሚበሉበት ቀን—ፋሲካ! ስለዚህ ከዚህ በፊት ይጠቀሙበት የነበረው የዘመን መቁጠሪያ (ካላንደር) ተለወጠ፤ ያ ወር የወራት ሁሉ መጀመሪያ፣ የዓመትም ሁሉ መጀመሪያ ሆነ።

ከወሩ በአሥረኛው ቀን ተመርጦ ወደቤት የመጣው ጠቦት የቤተሰቡ ሁሉ ዓይን አርፎበታል። ልጆች ሣር ያበሉታል፣ የቤቱ አባወራ ደግሞ በየቀኑ ነውር እንዳለውና እንደሌለው እየተመለከተ ያጣራ ጀምሯል። ጠቦቱ ከጓደኞቹ ተለይቶ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ከመጣ አራተኛውን ቀን አልፏል።

እንዴት እንደሆነ ባይገባውም የቤተሰቡ የበኩር ልጅ ይህ በየቀኑ ሣር የሚመግበው በግ እርሱን ከሞት የሚታደግ መሆኑ ስለተነገረው ያለፉትን አራት ቀናት ጠቦቱን በቅርበት ሲከታተለው ቆይቷል።

ምሽት ላይ ጠቦቱ ሊታረድ ሲል የልጁ አባት የታረደው በግ ደም የሚደረግበትን ጎድጓዳ ሳህን ሮጦ እንዲያመጣ ለልጁ ነግሮት ሳህኑን አምጥቷል። ደሙ በሳህኑ ላይ ተደረገ፤ በጉም ለመብል በሚያመች መልኩ ተበልቶ ወደቤት ገባ። አባወራ፣ እማወራ፣ ልጆች ሁሉ ተሰብስበዋል፣ ወደቤት ያልገባ አንዳች አልነበረም። ልጆች እርስበርሳቸው ንግግር ይዘዋል፤ አንዱ እኔ የምፈልገው ጥብስ ነው ሲል ሌላው ደግሞ ቅቅል ይሻላል እየተባባሉ ይከራከራሉ፤ ቁርጥም የሚፈልግ አልጠፋም። ጥሬውን ሥጋ ወይም ቅቅል መብላት እንደማይቻል ግን አስቀድሞ ተነግሯቸዋል። ምሽቱ እየጠነከረ መምጣት ጀምሯል። ሴቶች ማድቤት ውስጥ ጉድጉድ እያሉ ናቸው።

የነጻነት ጎሕ ሊቀድ የቀረው ጥቂት ጊዜ ነው። ንብረታቸው ሁሉ ለጉዞ እንደተሸከፈ ነው። ዝግጅቱ ሁሉ ስላለቀ ለመጨረሻ ጊዜ ራታቸውን በግብፅ ምድር ለመብላት ወደቤት ገብተው የቤቱን በር ሲዘጉት የቤተሰቡ የበኩር ልጅ የሆነው “አባዬ! አባዬ!” በማለት የበጉ ደም የሞላበትን ጎድጓዳ ሳህን ከሂሶጵ ቅጠል ጋር ይዞ መጣ። “ኦ! ዋናውን ነገር ረስተነው፤ ጎሽ ልጄ” በማለት የሂሶጱን ቅጠል በሳህኑ ውስጥ በመንከር ደሙን በበሩ ሁለት መቃንና ጉበናው ላይ ረጨና “በሉ ልጆች ወደቤት እንግባ” አለ። በሩም ተዘጋ። ይህንን የተመለከተው የቤቱ የበኩር ልጅ ምሥጢሩ የገባው ይመስላል፤ ስለዚህ ደሙ በሩ መቃንና ጉበና ላይ ለምን ይቀባል ብሎ አልጠየቀም።

የሕዝቡ መሪ ሙሴ እንደተናገረው ጠቦቱ ታርዶ፣ ተጠብሶ፣ እርሾ የሌለበት ቂጣ ተጋግሮ ለምግብነት ተዘጋጅቷል፤ አብሮ የሚበላው የሂሶጵ ቅጠልም እንዲሁ። ቤተሰብ ሁሉ ራት ለመብላት ቀረበ። ቤተሰቡ በአንድ ላይ እየተመገበ የቤቱ አባወራ እንደዚህ አለ፤

“ልጆች ዛሬ የታረደው ጠቦት በቤተሰባችን ሊመጣ የነበረውን ሐዘን ያስቀረልን ነው”፤

“አባዬ!” አለ የቤቱ የበኩር ልጅ ቀበል አድርጎ፤ “ጠቦቱ በኔ ፋንታ ነው የሞተው አይደል?” እንደመጠየቅም እንደመመለስም እየተናገረ።

አባትየውም “ልጄ ልክ ነህ፣ ዛሬ በግብፅ ምድር ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚላክ አጥፊ መልአክ የበኩር ልጆችንም ሆነ እንስሳትን ሊገድል ወደ ግብፅ ይመጣል። ነገርግን ነቁጥና ነውር የሌለበትን ጠቦት አርዶ ደሙን በበራፉ ላይ የቀባ ሊመጣ ካለው የሞት መቅሰፍት ያመልጣል። ዛሬ በበር ላይ በቀባነው የጠቦት ደም አንተን እያስመለጥን ነው” አለው። “ይሄ ብቻ ሳይሆን እኛ ሁላችን ከዚህ የባርነት አገር አምልጠን ነገ በነፃነት እግዚአብሔር ወደሚሰጠን አገር መጓዝ እንጀምራለን። ከዛሬ ጀምሮም በየዓመቱ ይህንን ቀን እንደ ዓመትበዓል እናከብራለን”።

ከልጆቹ አንዱ “የበዓሉ ስም ምን ይባላል?” ብሎ ጠየቀ … አባትየውም “ፋሲካ ነው ልጄ ፋሲካ!” ሲል መለሰለት። “ፋሲካ ማለት “ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ” ማለት ነው። አጥፊው መልአክ የደሙን ምልክት ሲመለከት ወደእኛ ቤት ሳይገባ ያልፋል ማለት ነው” አለ አባወራው። “ስለዚህ ይህ የታረደው ጠቦት በልጄ ፋንታ የሞተ ምትክ ሲሆን ደሙ ደግሞ መቅሰፍት ወደቤታችን እንዳይገባ የሚከላከል የደህንነታችን ምልክት ነው” በማለት ለልጁና ለመላው ቤተሰብ አስረዳ።

እኩለሌሊት እንዳለፈ ራቅ ካለ ቦታ ጩኸት መሰማት ጀመረ፤ እየቆየም ጩኸቱ እየቀረበና እየተበራከተ መጣ። ሙሴ እንደተናገረው የአጥፊው መልአክ መቅሰፍት በየግብፃዊው ቤት የሚገኙትን የበኩር ልጆች መግደል ጀምሯል። መላ ግብፅ አለቀሰች። መቅሰፍቱ ወደ ቤተመንግሥትም ሳይቀር ገብቷል። ስለዚህ ፈርዖንም በበኩር ልጁ ሞት ምክንያት እያለቀሰ ነበር። የፈርዖን ኩራቱና ትዕቢቱ ተሰበረ። ወዲያውኑ ሙሴና ሐሮንን ጥሩልኝ አለ። እነርሱም ተጠርተው መጡ። ፈርዖንም ከወትሮው በተለየ ድምፅ ለሙሴና ሐሮን ሕዝባቸውን ይዘው ከግብፅ በአስቸኳይ እንዲወጡ መፍቀዱን ገለፀላቸው።

ሙሴና ሐሮንም ወደ ሕዝባቸው መጥተው ነፃ መውጣታቸውን የምስራች አበሰሩ፤ የነፃ መውጣት ዕልልታ ተሰማ። ነፃ ለመውጣትና ለጉዞ የተዘጋጀው ሕዝብ መንጫጫት ጀመረ። በየጎረቤቶቻቸው የሚገኙ ግብፃውያንን ሲሰናበቱ ለጉዞ የሚሆናቸውን ብርና ወርቅ ተሸለሙ። ነፃ መውጣት እንዴት ደስ ይላል! ሆኖም ግን ራሱን የቻለ ኃላፊነትና ግድርድሮሽ አለው።

ይህን በምናቤ የሳልኩትን ታሪክ በሃሳቤ ሳውጠነጥን ኢሳያስ የተናገረው ትዝ አለኝ። “ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም” (ትንቢተ ኢሳይያስ 53:7)። እንደዚያ ነቁጥ እንዳልተገኘበት ጠቦት ክርስቶስ ኢየሱስ በዚህ ምድር ለ33 ዓመት ሲኖር ምንም ኃጢያትም ሆነ ነውር አልተገኘበትም። ጲላጦስም እንኳ ይህንን ሰው መርምሬው “እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትም” ብሏል (የዮሐንስ ወንጌል 19:6)።

አዎን ክርስቶስ ነውርም ሆነ ነቁጥ ያልተገኘበትን ሕይወቱን በእኔና በእናንተ ፋንታ እንደዚህ ጠቦት መስዋዕት በማድረግ ሰጥቶናል። እርሱ ስለሞተልን እኛ ከዘላለም ሞት አመለጥን፤ እርሱ ምትካችን ነውና። “በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” አለ (ዮሐንስ 1፡29)።

ጳውሎሰም “አሁን ደግሞ ወንድሞች ሆይ! ያስተማርኳችሁን የወንጌል ቃል ላስታውሳችሁ እፈልጋለሁ፤ ይህም የወንጌል ቃል እናንተ የተቀበላችሁትና ጸንታችሁ የቆማችሁበት ነው። እኔ ያስተማርኳችሁን የወንጌል ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ በእርሱ ትድናላችሁ፤ አለበለዚያ ግን ያመናችሁት በከንቱ ነው። እኔ የተቀበልኩትን በመጀመሪያ ደረጃ ያለውን ነገር ለእናንተ አስተላለፍኩላችሁ፤ ያስተላለፍኩላችሁም ነገር በቅዱሳት መጽሐፍት እንደተጻፈው ክርስቶስ ስለኃጢያታችን ሞተ፤ ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ከሞት ተነሣ የሚል ነው” (1ኛ ቆሮንቶስ 15:1-4)። እንግዲህ እኛን ለማዳን የክርስቶስ በእኛ ፈንታ ስለኃጢአታችን መሞቱ ብቻ ሳይሆን መቀበሩም ሆነ በሦስተኛ ቀን መነሣቱ የወንጌል ክፍል ነው ማለት ነው።

በተጨማሪም ጳውሎስ “እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና” በማለት ክርስቶስ ፋሲካችን የመሆኑን ዜና አብስሮልናል (1ኛ ቆሮንቶስ 5:7)። ስለዚህ የክርስቶስ ደም ከጥፋት ያመለጥንበትና እርሱ ምትካችን ሆኖ መሰዋዕት መሆኑን ያሳየናል። ቁምነገሩ ታዲያ ስለዚህ ታላቅ መስዋዕትነት ምን የግል ውሳኔ አድርገናል ለሚለው ጥያቄ የምንሰጠው ምላሽ ነው።

ፓ/ር መስፍን ማንደፍሮ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *