giziew.org

ቀራንዮና ኮሮና

የሞት መድኃኒቱ ሞት ነው። በሞት ፍርሃት ምክንያት የሚንቀጠቀጠው ሥጋ ካልሞተ መዳን አንችልም
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

በሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወቅት፤ ፈረንሳይን ከጀርመኖች እጅ ለማስለቀቅ በተደረገው ፍልሚያ ትልቅ ሚና የነበረው የኖርማንዲው ወረራ ነው። በጦርነቱ ላይ የተሰማሩትን የአሜሪካ ወታደሮች፤ ከአውሮፕላን ዘለው መሬት ላይ ከማረፋቸው በፊት ተኩሰው ሊገድሏቸው የተዘጋጁ ጀርመናዊ የምድር ተዋጊዎች ነበሩ።

በዚያ ውጊያ ከተሳተፉት የአሜሪካ ወታደሮች ውስጥ አንዱ፤ ከመዝለሉ በፊት በአውሮፕላን ውስጥ ያጋጠመውን አንድ ልዩ ክስተት ተርኳል። አብሮት ሲበር የነበረው ወታደር እጆች በደም የረጠቡ መሆናቸውን ተመልክቶ፤ “ምን ሆነህ ነው እጆችህ የሚደሙት?” ብሎ ይጠይቀዋል። ያ ወታደር የራሱን እጆች ትኩሩ ብሎ አይቶ ወደ ጠያቂው እጆች በመመልከት፤ “ያንተም እጆች እኮ በደም ተሸፍነዋል” ብሎ መለሰለት። ሰዎች አሰቃቂ ጣዕር ውስጥ ሲገቡ የደም ሥሮቻቸው ተቀደው ደማቸው ከላብ ጋር በመቀላቀል ከሰውነታቸው ሊፈልቅ እንደሚችል አዋቂዎች ይናገራሉ። ወታደሮቹ ሞትን ፊትለፊት ሊጋፈጡ እንደሚችሉ በማወቅ ላባቸው ደም ሆነ። የሞት ፍርሃት አደማቸው።

ከብዙ የሰው ልጅ ፍርሃቶች ጀርባ የሚያንዣብበው የሞት ፍርሃት ነው። ሞት በበሽታ ወይም በአደጋ መልክ ሲያጠላ “መጨረሻው ምን ይሆን?” ያስብላል። በአሁኑ ጊዜ ዓለምን እያሸበረ ያለው የኮሮና ወረርሽኝ የዚህ ማሳያ ነው። በበሽታው ፍርሃት ምክንያት የዓለም ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሕይወት እየተናጉ ናቸው። ሰዎች መረጋጋት ተስኗቸው አእምሮ በሚያቃውስ ጭንቀት ውስጥ ሲገቡ እናያለን። ታላቁ ፍርሃታቸው የሞት መንጋጋ ውስጥ እንገባ ይሆን የሚለው ነው። ጨለማው መቃብር የታሪካቸው መጨረሻ ስለሚመስላቸው፤ ዋና ጭንቀታቸው ከሰው ቁጥጥር ድንገት አፈትልኮ የሚያመልጠውን ምድራዊው ሕይወት ማራዘም ሆኗል። ኮሮናን ለመከላከል ብዙ ጥረትና ገንዘብ የሚከፈልበት ምክንያቱ ይህ ነው።

ለመሆኑ ኮሮና የሚፈራው ለምንድነው? ሞትን የምንፈራው ለምንድነው? ከዓቅማችን በላይ ሆኖ በእኛ ላይ ኃይል ያለው ነገር መሆኑ በእርግጥ አስፈሪ ነው። ከዚህ ሌላ ግን የሞት አለቃ ሆኖ ሰዎችን በሽብር ለማንበርከክ የሚፈልግ ረቂቅ ኃይል እንዳለ ደግሞ ቃሉ ያስተምራል።

ሰይጣንና ሞት መሠረታዊ ትሥሥር አላቸው። ሞት የሕይወት ተቃራኒ ስለሆነ ሕይወት ከሆነው አምላክ የተለየ ሁሉ ለሞት ተጋላጭ ነው። ይህ ተጋላጭነት እንዲስፋፋ ኃጢአትና እርኩሰትን ተወዳጅ አድርጎ ሰዎችን ለዘመናት ከፈጣሪ ሲለይ የቆየው ሰይጣን ነው። በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን አምላክ ባህርይ ሳናስተውል ሰይጣን በዘላለማዊ ድንጋጤና መንቀጥቀጥ ውስጥ ታስረን እንድንኖር ይፈልጋል። ታሪክና ዕለታዊ የዜና ዘገባዎች የሚያሳዩት ይህ እኩይ ዓላማው እንደተሳካለት ነው።

ኃጢአት ባለበት ሞት አለ። ሞት ባለበት ሁሉ ደግሞ ገዢ ፍርሃት አለ። ሲዖል በነገሠበት ቦታ መኖር ሞትን በመጠበቅ መንገዳገድ ማለት ነው። የመድኅን ድርጅቶች ለአደጋዎችና ለሰው ፍርሃት ከለላ እንሆናለን ብለው ትርፋማ ንግድ ቢመሠርቱም፤ ከሞትና ከሞት ፍርሃት ግን ማንንም ማላቀቅ አይችሉም። ወደ መቃብር ቁልቁል የሚያንደረድረው መንገድ “የኑሮ ትግል” ሳይቀናቸው በተሰዉ ሰዎች የተነጠፈ ነው። ታዲያ መፍትሄው ምንድነው? የሞት እውነታ የእኔነትን ክብር ስለሚጎዳ ከውርደት ለመሸሽ ሰዎች ከመፍትሔው ይልቅ ክህደትን ይመርጣሉ። “‘ከሞት ጋር ቃል ኪዳን ገብተናል፤ ከሲኦልም ጋር ስምምነት አድርገናል፤ ውሸትን መጠጊያችን፣ ሐሰትን መደበቂያችን አድርገናል፤ ታላቅ መቅሠፍት እየጠራረገ ሲያልፍ፣ ሊነካን አይችልም’ በማለት ታብያችኋል” (ኢሳ. 28:15)። ምድራዊ መፍትሔዎች ዘላለማዊ አይደሉም። የሕክምና ሳይንስ፣ የፖለቲካ ለውጥ ወይም አንዳንድ ሐሰተኛ መምህራን እንደሚሉት የሰዎችን “ዕምቅ መለኮታዊ ባህርይ” ማዳበር ሞትን አያሸንፉም።

የሞት መድኃኒቱ ሞት ነው። በሞት ፍርሃት ምክንያት የሚንቀጠቀጠው ሥጋ ካልሞተ መዳን አንችልም። ጌታችን እንደተናገረው፤ “የስንዴ ቅንጣት መሬት ላይ ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች” (ዮሐ. 12:24)። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ወደነገሠባት ምድራችን የመጣው ሊሞት ነው። በመሞቱ ከሰይጣን ጋር ፊትለፊት ተጋጥሟል። ክርስቶስ ከሞት ለማምለጥ ሳይሞክር፤ የማናውቀውን ፍርሃትና ውርደት ተጋፍጦ በታላቅ ሐዘን አንገቱን አዘቅዝቆ ሞቷል። እርሱ ግን ተራ ሞት አልሞተም። ከመቃብር ማዶ ያለውን የብርሃን ትንሳኤና ሕይወት በጉልህ የሚያሳይ ሞት ነው የቀመሰው።

“ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ እርሱ ራሱ ደግሞ ያንኑ ተካፈለ፤ ይኸውም በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያቢሎስን በሞቱ ኀይል እንዲደመስስ ነው። እንዲሁም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሀት ባርነት የታሰሩትን ነጻ እንዲያወጣ ነው” (ዕብ. 2:14-15)።

ክርስቶስ በምድር የለበሰው እኛን በሞት ፍርሃት አስሮ የሚያንገላታንን ሥጋ ነው። ፍርሃትና አለማመን ያስቸገረውን ሥጋ ያሸነፈው እንደኛ ሰው ሆኖ ነው። በዚህ ሥጋ ውስጥ ኖሮ ተስፋ በሚያስቆርጡ ሥነልቦናዊ ስቃዮች ያልተፈተነ ሰው የለም። በብቸኝነት ጨለማ ውስጥ ሁሉም የሚያውቀው አስፈሪና ጥንታዊው የሞት ፉጨት አለ። ወደዚህ ጥልቅ የስሜት ጓዳ ገብቶ ነው ጌታችን ከጠላት ጋር ፊትለፊት የተዋጋው።

ስለ ውጊያው ጌታችን ምን ብሏል? “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝናለች” (ማቴ. 26:38)። በክርስቶስ ላይ የተከመረው ሐዘን ፊቱን በደም ላብ አጥቦ ወደ ሞት አፋፍ አደረሰው። ያንን ሐዘንና የደም ላብ እንዴት አሸነፈው? “ኢየሱስ በዚህ ምድር በኖረበት ዘመን ከሞት ሊያድነው ወደሚችለው ጸሎትንና ልመናን ከታላቅ ጩኸትና ከእንባ ጋር አቀረበ፤ ፍጹም ትሑት ሆኖ በመታዘዙም ጸሎቱ ተሰማለት። የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም እንኳ፣ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ በዚህም ፍጹም ሆኖ ከተገኘ በኋላ፣ እርሱን ለሚታዘዙ ሁሉ የዘላለም ድነት ምክንያት ሆነላቸው” (ዕብ. 5:7-9)። የጌታችን ጩኸትና እንባ በፍርሃትና ጣዕረ ሞት ለዘመናት የተሰቃየውን የሰውን ዘር ሁሉ የሚጠቀልል ነው። በርሱ የሕመም ጩኸት ምክንያት እኛ የደስታ መዝሙር ተቀበልን። እንባው እንባችንን አጥቦ በደኅንነት ሳቅ እንድንፈነድቅ አድርጓል። ሊውጠን ያሰፈሰፈው የሲዖል ስግብግብ አፍ ተዘግቶ የሰማይ ደጆች ወለል ብለው ተከፈቱ።

ቀራንዮ ስለ ሞት አሰቃቂነትና ስለ እግዚአብሔር ጥልቅ ፍቅር ይመሰክራል። ሞትን እንዳንፈራ ከመቃብር ባሻገር ያለውን ዘላለማዊ ሕይወት አሳይቶናል። ከሁሉ በላይ ግን ፍቅሩን አቅምሶ ፍርሃት ከልባችን እንዲወገድና በነፃነት እንድንኖር ጠርቶናል። “በፍቅር ፍርሀት የለም፤ ፍጹም ፍቅር ግን ፍርሀትን አውጥቶ ይጥላል፤ ፍርሀት ከቅጣት ጋር የተያያዘ ነውና። የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም” (1ዮሐ. 4:18)።

ሰሞኑን በፍጥነት እየተዛመተ ያለው የኮሮና በሽታ በሰዎች ልብ መደናገጥን ፈጥሯል። ሞትን በመፍራት ሰዎች ሥራቸውንና ማኅበራዊ ሕይወታቸውን ሸሽተው፣ በር ዘግተው እንዲቀመጡ አድርጓል። ይህ ሁኔታ የተሻለ ሰማያዊ ሕይወት እንዳለን ረስተን በምድሩ ጎደሎ ሕይወት ላይ በፍርሃት እንድንጠመድ የሚያስገድድ ይመስላል። ሞትን ያሸነፈው አምላክ ግን በኮሮና ፍርሃት እንድንቀጠቀጥ አይፈልግም። ፍቅሩ በልባችን ካለ ምንም ሊያሸብረን አይገባም። “እጁን በላዬ ጭኖ እንዲህ አለኝ፤ ‘አትፍራ፤ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም እኔ ነኝ፤ እኔ ሕያው ነኝ፤ ሞቼ ነበር፤ እነሆ አሁን ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፤ የሞትና የሲኦል መክፈቻም በእጄ ነው” (ራዕ 1:17-18)።

በመጨረሻው ዘመን፤ ዓለም ታይቶ በማይታወቅ መከራ ውስጥ ስትገባ ድል ነሺ የሚሆኑት በሞት ፍርሃት ላይ ድል የተቀዳጁ ናቸው። በፈተና ከመብረክረክ ይልቅ የክርስቶስን መስዋዕታዊ ሕይወት በማስታወስ በፍቅሩ ኃይል የሞትን ፍርሃት ፊትለፊት ይጋፈጣሉ።

“እነርሱም በበጉ ደም፣ በምስክርነታቸውም ቃል፣ ድል ነሱት፤ እስከ ሞት ድረስ እንኳ፤ ለነፍሳቸው አልሳሱም” (ራዕ 12:11)። ይህን ድል ለመቀዳጀት ያለን የልምምድ ጊዜ አሁን ነው። በየቀኑ አይኖቻችንን ወደ ቀራንዮ ከፍታ ማዞር ያስፈልገናል። የአምላክን ፍቅር ያስተዋለ ሰው ለምድራዊ ነፍሱ በመሣሣት አላስፈላጊ ጭንቀት ውስጥ አይገባም፤ መሣሣት የፍርሃትና የሞት ነውና። ነፃነትና የተትረፈረፈ ሕይወት ግን ቀራንዮ ላይ በፈሰሰው በግ ደም ተገኝቷል። ይህንን ታሪካዊ ድል ለሚዘክረው ፋሲካ እንኳን አደረሰን!

ድርባ ፈቃዱ


የቅርብ ጽሁፎች

በ Facebook ይከተሉን

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *