አንባቢ ሆይ!
ተረግመህና መተውን ተለማምደህ ታውቃለህን? ያመንካቸው፣ በጣም የምትወዳቸው ሰዎች ትተውህ፣ “ለምን ተዉኝ?” ብለህ ጠይቀህ ታውቃለህን?
ምናልባት ይህን የመተውና የመረገም ልምምድ በሰዉኛ እይታ ተለማምደነው እናውቅ ይሆናል። በዚህች አጭር ጽሁፍ በሚወዳቸውና በሚወደው የተተወውን፣ ስለ ተውትና አንቅረው ስለተፉት ሲል እርግማን የሆነውን የኢየሱስን የመስቀል ላይ ልምምድ በጨረፍታ ለማየት እንሞክራለን።
ኢየሱስ በመስቀል ላይ እያቃሰተ ሳለ በታላቅ ድምፅ “አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ?” የሚል አስገራሚ ጩኸት ጮኸ።
“በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ፦ኤሎሄ፥ ኤሎሄ፥ ላማሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? ማለት ነው” (የማርቆስ ወንጌል 15፥34)።
አስገራሚ ጩኸት! አስገራሚ ጥያቄ!
እግዚአብሔር በዘላለማዊነቱ ሦስትነቱ [አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ] አንዱ ለአንዱ ከራስወዳድነት የፀዳ ፍቅርን፣ አንድነትን እንጂ መለያየትን፣ አንዱ ከአንዱ መራቅን ሲያሳይ ተጽፎ አናነብም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ፍቅር ነውና። በፍጥረቶቹም ላይ የተገለጠዉ የእርሱ ፍቅር “አልተዋችሁም” የሚል ነው።

“በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ አልተውህም” (መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 1፥5)።
እንዲያውም “አማኑኤል” የሚለው የኢየሱስ ስም እግዚአብሔር በኃጢአት ምክንያት የተለየውን ሰብዓዊ ዘር በመካከሉ እንደሚሆን የሚያረጋግጥልን ተስፋ ነው። ይሁን እንጂ ይህን የኮበለለውን የሰው ዘር ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ለማድረግና እግዚአብሔር እንዳልተወን ለማረጋገጥ በመካከላችን ያደረው ክርስቶስ በቀራንዮ መስቀል ግን ጌታ (አምላኬ) ሆይ ለምን ተዉኸኝ? በማለት የመተውን (“ተ” ጠበቅ ብሎ) ጎምዛዛ ፅዋ ሲጎነጭ እናያለን።
እግዚአብሔርም ኢየሱስን ለዓለም ሲያስተዋውቀው እንዲህ ነበር ያለው፤ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ” (የማቴዎስ ወንጌል 17፥5)።
በእርግጥ እግዚአብሔር እንዲህ የሚወደውን ልጁን በቀራንዮ መስቀል ላይ ትቶት ነበርን? ተረግሞስ ነበርን?
እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ “መተው” እና “መረገም” የሚሉትን ፅንሰ ሃሳቦች በያኔው ዓለም መነጽር መመልከትና ታሪካዊ ዳራቸዉን ማወቅ ያስፈልጋል።
“መረገም/የተረገመ” የሚለው ቃል ጥቅም ላይ በዋለበት በኦሪት ዘዳግም 21፡23 ላይ “በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና” ይላል (ዘኍልቍ22 እና ኢያሱ 8፡29 ይመልከቱ)። እዚህ ላይ እንደምናየው፤ በአይሁዶች ዘንድ አንድ ሰው “የተረገመ ነው፤ የሞት ፍርድ ይገባዋል” ተብሎ ሲረጋገጥ በእንጨት ላይ ይሰቀላል ማለት ነው። ለሮማዉያን ደግሞ ከሲሮፊኒቃዉያን በተዋሱት መሠረት ወንጀለኛን በመስቀል ላይ እንዲሰቀል የማድረግ ተግባር ወንጀለኛው እንደ አገር መክዳት ዓይነት ወንጀል ሲፈጽም ይከናወናል። በመሆኑም አይሁዶች ጲላጦስ ኢየሱስን በመስቀል ላይ እንዲሰቅለው ሲለምኑት በልባቸው የነበረው ኢየሱስ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ እንደሆነ ነው።

በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነው ሲባልም የተወገደ፣ የተቆረጠ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ዕጣ ፈንታ የሌለው፣ ከመንግሥቱ የተለየ፣ በእግዚአብሔር ለዘላለም የተተወና ጭራሽ የትንሳኤ ተስፋ የሌለው ማለት ነው። እንግዲህ ይህ ዓይነት ፍርድ የኃጢአት ዋጋን መቀበል/የዘላለም ሞትን መሞት ማለት ሲሆን የሁሉም ሰው ዕጣ ፈንታ ደግሞ ይኸው ነበረ። ክርስቶስ ግን ያ አጋፔ (ከራስ ወዳድነት የፀዳ) ፍቅር ግድ ብሎት ለእኛ የሚገባዉን እርግማንና መተው ተተወ፤ እርግማን ሆነ።
“በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን” (ገላትያ 3፡13)።
“የሰማነውን ነገር ማን አመነ? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ? በፊቱ እንደ ቡቃያ፣ ከደረቅም መሬት እንደ ወጣ ሥር በቀለ፤ የሚስብ ውበት ወይም ግርማ የለውም፤ እንድንወደውም የሚያደርግ መልክ አልነበረውም። በሰዎች የተናቀና የተጠላ፣ የሕማም ሰውና ሥቃይ ያልተለየው ነበር። ሰዎች ፊታቸውን እንደሚያዞሩበት ዐይነት፣ የተናቀ ነበር፤ እኛም አላከበርነውም። በርግጥ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ፤ እኛ ግን በእግዚአብሔር እንደ ተመታ፣ እንደ ተቀሠፈ፣ እንደ ተሠቃየም ቈጠርነው። ነገር ግን እርሱ ስለ መተላለፋችን ተወጋ፤ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ በእርሱ ላይ የወደቀው ቅጣት ለእኛ ሰላም አመጣልን፤ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ እያንዳንዳችንም በየመንገዳችን ነጐድን፤ እግዚአብሔርም፣ የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ ጫነው። ተጨነቀ፤ ተሠቃየም፤ ነገር ግን አፉን አልከፈተም፤ እንደ ጠቦትም ለዕርድ ተነዳ፤ በሸላቾች ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ አፉን አልከፈተም። በማስጨነቅ (በእስር) እና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኀጢአት ተመቶ፣ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ፣ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? በአፉ ተንኰል ሳይገኝበት፣ ምንም ወንጀል ሳይሠራ፣ አሟሟቱ ከክፉዎች፣ መቃብሩም ከባለጠጎች ጋር ሆነ። መድቀቁና መሠቃየቱ ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር፤ እግዚአብሔር ነፍሱን የኀጢአት መሥዋዕት ቢያደርገውም እንኳ፣ ዘሩን ያያል፤ ዕድሜውም ይረዝማል፤ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ሥቃይ በኋላ፣ የሕይወት ብርሃን ያያል፤ ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬ በዕውቀቱ ብዙዎቹን ያጸድቃል፤ መተላለፋቸውንም ይሸከማል። ስለዚህ ድርሻውን ከታላላቆች ወይም ከብዙዎች ጋር እሰጠዋለሁ፤ ምርኮውን ከኀያላን ወይም፣ እጅግ ብዙ ከሆኑ ጋር ይካፈላል፤ እስከ ሞት ድረስ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠቱ፣ ከክፉ አድራጊዎችም ጋር በመቈጠሩ፣ የብዙዎችን ኀጢአት ተሸከመ፤ ስለ ዐመፀኞችም ማለደ” (ትንቢተ ኢሳይያስ 53፡1-12)።
አዎን፣ በእርግጥም ኢየሱስ እኛን ከዘላለም ሞት ለማዳን ሲል እርሱ መራራውን በእግዚአብሔር የመተውን ፅዋ ተጎንጭቷል። ስለ እኛ ተረግሟል፣ ኃጢአት ተደርጓል።
“እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው” (2ኛ ቆሮንቶስ 5፤21)።
ጌታችን በመስቀል ላይ እያለ “አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ?” ያለውም በእግዚአብሔር የተተወ፣ የትንሳኤ ተስፋም የሌለው ሆኖ ስለተገነዘበ ነበር። አዳኛችን በዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ስሜት እያለፈም እንኳ ከራሱ አብልጦ እኛን ወደደ። እኛ እንኖር ዘንድ እርሱ ሞተ። “አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ?” ብሎ ለጮኸው ጩኸት የማፅናኛ ቃል ባይሰጠውም እምነቱን በአባቱ ላይ አድርጎ አሸለበ።

“ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፦ አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ። ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ” (ሉቃስ 23፡46)።
መታመኑን በእግዚአብሔር ላይ አድርጎ ህይወቱን አሳልፎ የሰጠው ክርስቶስ በእግዚአብሔር ኃይል ሞትን ድል አድርጎ ተነስቷል። እግዚአብሔርም ያለ ልክ ከፍ ከፍ አድርጎታል። “በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው” (ፊልጵስዩስ 2፣9-11)።
ለዚህ አፍቃሪ ወዳጃችን፤ መተውን ለተተወልን፤ እርግማናችንን ለወሰደልን፤ ፍጥረት ሁሉ በፍቅርና ሙሉ አመኔታ እንዲህ እያሉ ያከብሩታል፤ “በታላቅም ድምፅ፦ የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ። በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ፦ በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ” (ራእይ 5፣12-13)።
አሜን!
ፋንታሁን መላኩ