giziew.org

“ለመሆኑ፣ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?”

ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና፦ በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን? አለው።
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት አካባቢ “የኢትዮጵያ ንግሥት የህንደኬ ባለሟልና የሀብት ንብረቷ ሁሉ አዛዥ (በዥሮንድ ወይም በዘመኑ አጠራር የገንዘብ ሚኒስትር)” የነበረው ሹም ወደ ኢየሩሳሌም ለስግደት መጥቶ ነበር (ሐዋ. 8፡26-40)። ስግደቱን ጨርሶ ሲመለስም በጉዞው ላይ የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ እያነበበ ሳለ ፊሊጶስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ቀረብ በማለት አነጋገረው። ንግግሩንም በጥያቄ ነበር የጀመረው፤ እንዲህ በማለት፤ “ለመሆኑ፣ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?”

ሹሙ ግን አላስመሰለም፤ እውነትን ፈላጊና ቅቡል ልብ ያለው ሰው በመሆኑ “የሚያስረዳኝ ሰው ሳይኖር እንዴት አድርጌ አስተውላለሁ?” በማለት ነበር ጥያቄውን በጥያቄ የመለሰው። ፊሊጶስንም ወደ ሠረገላው እንዲወጣ በመለመን እንዲያስረዳው ጠየቀው። ፊሊጶስም ሹሙ ያነብብ የነበረው በትንቢተ ኢሳይያስ 53 ላይ ስለ ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ መድኃኒዓለምነት የሚያወሳ ክፍል እንደሆነ በመንገር አስተማረው።

ልበ ብርሃኑ ሹም የተማረውን አስደናቂ ትምህርት በመቀበል ወዲያው በተግባር ተረጎመው፤ “እነሆ፤ ውሃ እዚህ አለ፤ ታዲያ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” አለው። ፊልጶስም፣ “በፍጹም ልብህ ካመንህ መጠመቅ ትችላለህ” አለው። ጃንደረባውም፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ” ሲል መለሰለት፤ “(ሹሙም) ሠረገላውም እንዲቆም አዘዘ። ከዚያም ሁለቱ አብረው ወደ ውሃው ወረዱ፤ ፊልጶስም ጃንደረባውን አጠመቀው።” ኢትዮጵያዊው ብርሃነ ወንጌልን ለአገሩ ይዞ ሲሄድ ፊሊጶስ ደግሞ ለሌላ የወንጌል ሥራ ሌላ ቦታ ተገኘ።

የምናነበውን ማወቅ ለዕውቀት ብቻ ሳይሆን ለውሳኔም ይረዳናል። በተለይም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ለሚፈጠሩብን ጥያቄዎች አስረጅ ፍለጋ ከመቸገር በዚህ የጊዜው ልዩ ዕትም በዘጠኝ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ መልሶች አዘጋጅተናል። ርዕሶቹም የሚከተሉት ናቸው፤

1. ታላቁ ውዝግብ፤

2. ክርስቶስ ፅድቃችን፤

3. ጥምቀት፤ መታጠብና መንጻት፤

4. ቤተመቅደስ፡ የምስክሩ ታቦት ማደሪያ፤

5. ታሪክ የረሳው ቀን፤

6. ሙታን በርግጥ ሞተዋል? የት ነው ያሉት?

7. ራስን መቆጣጠር፡ የክርስቲያን ኑሮ፤

8. የጌታ ዳግም ምፅዓት፣ ሺሁ ዓመትና አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር፤

ይህ ዓይነቱን አስረጅ ጽሁፍ ወደፊት ከተሳካልን ሌሎች ርዕሶችን ጨምረን በመጽሐፍ መልክ የምናወጣው ይሆናል። ላሁኑ ግን በነዚህ ርዕሶች ላይ የሰፈረውን ሃሳብ በቅንነትና በፀሎት መንፈስ እንዲያነቡ እንጋብዝዎታለን። ይህ ንባብ ለዕውቀት ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያዊው ባለታሪክ ለውሳኔም የሚያደርስዎት ይሆን ዘንድ ፀሎታችን ነው።

አዘጋጆቹ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *