giziew.org

“Easter” ፋሲካ አይደለም

የትንሣኤ ክብረበዓልን ወደ “ኢስተር” እንዲቀየር መደረጉ እሁድ (ሰንደይ - የፀሐይ ቀን) ቅዱስ ቀን ተደርጎ እንዲወሰድና በክርስትና ውስጥ የድንግል አምልኮ እንዲጀመር በር ከፍቷል
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

በእንግሊዝኛ “Easter” (ኢስተር) እየተባለ ለፋሲካ የሚውለው ስም ፋሲካን የሚያመላክት አይደለም።

ከቃሉ ትርጉም ብንነሳ፤ “ኢስተር” የሚለው ቃል የጌታችንን እና የመድኃኒታችንን ትንሣኤ የሚያመላክት አንዳችም መልዕከት የለውም። “ኢስተር” የሚለው ቃል የመጣው በጥንት ዘመን የመዋለድ፣ የልምላሜ፣ የመራባት አምላክ ነች ተብላ ከምትጠራው ኢሽታር ከምትባለው እናት ሴትአምላክ ነው። ይህ የጣዖት አምልኮ ሥርዓት ይካሄድ የነበረው ክርስትና ከመጀመሩ ከበርካታ ዓመታት በፊት እንደነበር የታሪክ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ። በተለያዩ አገራት “ኢሽታር” የሚለው ስም “አስታርቴ” ወይም “አሽቶሬት” እየተባለ ይጠራል።

ይህ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የተጀመረ የጣዖት አምልኮ የሚከበረው በጸደይ ወቅት፣ ፀሐይ ስትወጣ መሆኑ የትንሣኤ ክብረበዓልን ወደ “ኢስተር” እንዲቀየር ከማድረጉ ባሻገር እሁድ (ሰንደይ – የፀሐይ ቀን) ቅዱስ ቀን ተደርጎ እንዲወሰድና በክርስትና ውስጥ የድንግል አምልኮ እንዲጀመር በር ከፍቷል።

ጌታችን ወደምድር መጥቶ ህይወቱ መስዋዕት አድርጎ ከመስጠቱ በፊት ዲያቢሎስ በተለያዩ የጣዖት አምልኮ ሃይማኖቶች ውስጥ ሞትንና ትንሣኤን የሚመስሉ ልምምዶች እንዲኖሩ አድርጓል። በዚህም ምክንያት በርካታዎች የደኅንነትን ሃሳብ አቃልለው እንዲመለከቱ ያደረገ ሲሆን ወደ ክርስትና ለሚመጡት ደግሞ ቀድሞ የሚያመልኳቸውን አማልክት የክርስትና ስም እየሰጡ ወደ ቤ/ክ በቀላሉ እንዲገቡ ተደርጓል።

ኢሽታር

ቀደምት በነበሩ የጣዖት አምልኮዎች ውስጥ በተለይ ባቢሎናውያን በሚከተሉት እምነት፤ ታሙዝ የተባለው አምላክ ከሞት መነሳትን በተመለከተ ከኢሽታር ጋር ልዩ ግንኙነት ነበረው። የታሙዝ ታሪክ ትርጉምና ዓላማ የሌለው የማያቋርጥ የህይወት ዑደት ነው። በባቢሎናውያኑ እምነት መሠረት ታሙዝ በየዓመቱ ይሞታል ከዚያም በፀደይ ወር ከሞት በትንሣኤ ይነሳል። ከሞት የምታስነሳው ደግሞ “ኢሽታር” የተባለቸው ሴት አምላክ ነች። በአረማውያን ዘንድ ይህ ታሙዝ የሚነሳበት ቀን የሰማይ ንግሥት፤ እናት አምላክ ተብላ ለምትጠራው ኢሽታር ተቀድሶ ተሰጥቷል። ይኸው ስም በክርስትና ውስጥ ተግባራዊ ሆኖ መሰማት ከጀመረ በርካታ መቶ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ይህች እንደ እናት የምትታየው ጣዖት በተለያዩ አምላኪዎች ዘንድ በእነዚህ ስሞች ትጠራለች፤ አስታርቴ፣ ኢሽታር፣ አሽቶሬት፣ ሳይቢሊ፣ ርሂያ፣ ዲሜተር፣ አፍሮዳይት፣ ቬኑስ፣ ዳያና እና ፍሪ ናቸው። ኢስተር የተጀመረው ክርስቶሰን ለማክበር በማሰብ ሳይሆን ይህቺን እናት አምላክ ለማክበርና ለማምለክ ሆን ተብሎ የክርስትና ካባ እንዲደርብ በማድረግ ነው። የኢሽታር አምላኪዎች ይህቺን የመዋለድ ሴትአምላክ የሚመስሉት በእንቁላልና በጥንቸል ሲሆን ይኸው ምሳሌ ከክርስትናም ሆነ ከትንሣኤ ጋር ምንም ግንኙነት ሳኖረው በኢስተር አከባበር ውስጥ ትልቁን ሥፍራ ይዞ ይገኛል። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ በርካታ ክርስቲያኖች ኢስተርን እንደ ጌታችን ትንሣኤ አድርገው ያከብሩታል። 

በአሁኑ ጊዜ በክርስትና ውስጥ ትልልቅ ሥፍራ ተሰጥቷቸው የሚከበሩት በዓላት በቀጥታ የተወሰዱት ከጣዖት አምልኮ ነው። እነዚህን በዓላት በተደጋጋሚ ከማክበርና ብዙ ከመለማመድ የተነሳ በርካታዎች ከጣዖት አምልኮ የተቀዱትን እንደ ክርስትና ልምምዶች በመውሰድ ለአንዳንዶቹም የክርስትና ስም በመስጠት አከባበሩ ሥር እንዲሰድድ ብዙ ረድቷል።

ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ ብሎ ለሚጠይቅ መጽሐፍ ቅዱስ ምላሽ ይሰጣል። ሐዋሪያው ጳውሎስ የሃሰት ትምህርት ወደ ቤተክርስቲያን እንደሚገባ የኤፌሶን ሽማግሌዎችን ሲሰናበት በዚህ መልኩ አስጠንቅቋቸው ነበር፤

“ለራሳችሁና መንፈስ ቅዱስ ኤጲስቆጶሳት ወይም ተመልካች፣ ጠባቂዎች አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ተጠንቀቁ፤ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ጠብቁ። እኔ ከሄድሁ በኋላ፣ ነጣቂ ተኵላዎች መጥተው በመካከላችሁ ሰርገው እንደሚገቡና ለመንጋውም እንደማይራሩ ዐውቃለሁ። ከእናንተው መካከል እንኳ የራሳቸውን ደቀ መዛሙርት ለማፍራት እውነትን የሚያጣምሙ ይነሣሉ” (ሐዋ. 20፡28-30)።

ሐዋሪያው ጴጥሮስ ደግሞ ይህንኑ የሃሰት ትምህርት ጉዳይ በዚህ መልኩ ገልጾታል፤

“ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት በሕዝቡ መካከል እንደ ነበሩ እንዲሁም በእናንተ መካከል ሐሰተኞች መምህራን ይነሣሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው ጥፋት የሚያስከትል የስሕተት ትምህርት በስውር ያስገባሉ፤ በዚህም በራሳቸው ላይ ድንገተኛ ጥፋት ያመጣሉ። ብዙዎች አስነዋሪ ድር ጊቶቻቸውን ይከተላሉ፤ በእነርሱም ምክንያት የእውነት መንገድ ይሰደባል። እነዚህ ሐሰተኞች መምህራን እየተስገበገቡ በፈጠራ ታሪካቸው ይበዘብዙዋችኋል” (2ጴጥ. 2፡1)።

ይህንን በመሰለ የተጠና ስልት ዲያቢሎስ የስቅለትንና የትንሳኤን ሃሳብ ከክርስቲያኖች አእምሮ በመውሰድ አልባሌና ምንም ጥቅም በሌላቸው ከንቱ የአጋንንት ሥራዎች የሰዎች አእምሮ እንዲጠመድ አድርጓል። ምክንያቱም በቀራንዮ ራሱ ተቀጥቅጦ ድል ተመትቷል፤ በትንሣኤ ደግሞ ሞትና ሲዖል ተሸንፈዋል። ጳውሎስ ይህንን ጉዳይ ድንቅ በሆነ መልኩ እንደዚህ ይገልጸዋል፤

“ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ፣ ከእናንተ አንዳንዶቹ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ? የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሣም ማለት ነዋ! ክርስቶስም ካልተነሣ ስብከታችን ዋጋ ቢስ ነው፤ እምነታችሁም ከንቱ ነው። ከዚህም በላይ፣ እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት አስነሥቶታል ብለን በመመስከራችን፣ ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን የማይነሡ ከሆነ፣ ክርስቶስንም አላስነሣውም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ሙታን ካልተነሡ፣ ክርስቶስም አልተነሣም። ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም እስከ አሁን ድረስ ከነኀጢ አታችሁ አላችሁ ማለት ነው። እንዲህም ከሆነ፣ በክርስቶስ ያንቀላፉት ጠፍተዋል ማለት ነው። ክርስቶስን ተስፋ ያደረግነው ለዚህች ሕይወት ብቻ ከሆነ፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን። ነገር ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኵራት ሆኖ በርግጥ ከሙታን ተነሥቶአል። … ከዚያም ግዛትን፣ ሥልጣንና ኀይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ፣ ያን ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል” (1ቆሮ. 15፡12-20፣24)። አሜን!

ከዝግጅት ክፍሉ


የቅርብ ጽሁፎች

በ Facebook ይከተሉን

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *