“ሰንበት ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና ሰሎሜ ሄደው የኢየሱስን ሥጋ ለመቀባት ሽቱ ገዙ። በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ጠዋት በማለዳ፣ ገና ፀሓይ እንደ ወጣች፣ ወደ መቃብሩ በመሄድ ላይ ሳሉ፣ ‘ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጃፍ ላይ ማን ያንከባልልልናል?’ በማለት እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። ቀና ብለው ሲመለከቱ፣ በጣም ትልቅ የነበረው ድንጋይ ከደጃፉ ላይ ተንከባሎ አዩ። ወደ መቃብሩ እንደ ገቡም፣ ነጭ ልብስ የለበሰ ጐልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ ‘አትደንግጡ፤ የምትፈልጉት የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ነው፤ እርሱ ተነሥቶአል፤ እዚህ የለም፤ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ ይኸውላችሁ። ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስ፣ “ቀድሞአችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል፤ እንደ ነገራችሁ እዚያ ታገኙታላችሁ” ብላችሁ ንገሯቸው” (ማርቆስ 16፡1-7)።
በሉቃስ ወንጌል ላይ ከዚህ ክስተት ውስጥ አንዳንዶቹ ለየት ባለ መልኩ ተገልጿል። “ሕያው የሆነውን እርሱን ለምን ከሙታን መካከል ትፈልጋላችሁ? እርሱ ተነሥቶአል! እዚህ የለም፤ ደግሞም በገሊላ በነበረ ጊዜ ምን እንዳላችሁ አስታውሱ፤ ‘የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥ፣ ሊሰቀልና በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ይገባል’ ብሎ ነበርና። ሴቶቹም በዚህ ጊዜ ቃሉን አስታወሱ። ሴቶቹ ከመቃብሩ ስፍራ ተመልሰው ይህን ሁሉ ነገር ለዐሥራ አንዱና ለተቀሩት ሁሉ ነገሯቸው። ይህን ለሐዋርያት የነገሯቸውም፣ መግደላዊት ማርያም፣ ዮሐና፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና ከእነርሱ ጋር የነበሩት ሌሎች ሴቶች ነበሩ። እነርሱ ግን ሴቶቹ የተናገሩት ቃል መቀባዠር ስለ መሰላቸው አላመኗቸውም።” (ሉቃስ 24፡6-11)።
ዕለተ አርብ ጌታ የሱስ ከተሰቀለና ሰንበትን በመቃብር ካሳለፈ በኋላ የሌሊቱ ጨለማ አልፎ ጎህ ሳይቀድ መግደላዊት ማርያም በጠዋት ወደ ድንጋዩ መቃብር መጣች። ከሌሎቹ ሴቶች ጋር በመቃብሩ ቦታ ለመገናኘት ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ማርያም ግን እዚያ ስትደርስ ማንም አልቀደማትም ነበር። የጌታቸውን ሥጋ ለመቀባት ሽቱና ቅባት አዘጋጅተው የመጡት ሴቶች ክብራቸውን ለመቋቋም የሚያቅት መላዕክት ባዩ ጊዜ እጅግ በመደንገጥ ፊታቸውን ወደ ምድር አቀረቀሩ። መላዕክቱ ከሴቶቹ ጋር ከመነጋገራቸው በፊት ክብራቸውን ለመሸፈን ቢገደዱም ሴቶቹ ግን ክብር በተሞላበት ፍርሃት ይንቀጠቀጡ ስለነበር እንዲህ አሏቸው፤ “አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትፈልጉ (እናውቃለን)፤ እርሱ በዚህ የለም፤ እንደ ተናገረው ተነሥቶአል፤ ኑና ተኝቶበት የነበረውን ቦታ እዩ” (ማቴዎስ 28፡5-6፤ ሉቃስ 24፡4-6)።
ከሴቶቹ ቀድማ የመጣችው መግደላዊት ማርያም “ገና ጨለማ ሳለ ማለዳ ወደ መቃብር መጣች ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች። እየሮጠችም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር መጥታ፦ ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም አለቻቸው። ስለዚህ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ” (ዮሐንስ 20፡2-3)። እዚያም እንደደረሱ ወደ መቃብሩ ገብተው ተመለከቱ፤ ጌታ ከተከፈነበት የተልባ እግር በስተቀር ምንም እንደሌለ አረጋግጠው ወደቤታቸው ሲመለሱ “ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር” (20፡11)።
“ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች። እነርሱም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? አሉአት። እርስዋም፦ ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም አለቻቸው። ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም። ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው። ኢየሱስም፦ ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ፦ ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም፦ መምህር ሆይ ማለት ነው” (ዮሐንስ 20፡11-16)።
የሱስ መጀመሪያ የተገለጠው “ሰባት አጋንንት ላወጣላት ለመግደላዊት ማርያም” ነበር (ማርቆስ 16፡9)። በመሆኑም ልቧ በደስታ በመሞላቱ ከእንግዲህ ወዲህ ማልቀስ አያስፈልጋትም። ነገር ግን ሄዳ ከክርስቶስ ጋር ለነበሩት ሁሉ የሆነውን ስትነግራቸውና “እነርሱም ሕያው እንደ ሆነ ለእርስዋም እንደ ታያት ሲሰሙ አላመኑም።”
ማርያም ባልነበረችበት ጊዜ ወደ መቃብሩ ከሌላ አቅጣጫ መጥተው ለነበሩት ሴቶች የሱስ ተገልጦ ነበር። መልአኩ ለሴቶቹ ይህንን መልዕክት ሰጣቸው፤ “ፈጥናችሁ ሂዱና ለደቀ መዛሙርቱ፣ ‘ከሙታን ተነሥቶአል፤ ቀድሞአችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል፤ በዚያ ታዩታላችሁ’ ብላችሁ ንገሯቸው” (ማቴዎስ 28፡7)። አስራአንዱ ደቀመዛሙርት ስለ ክርስቶስ መነሳት ምንም መገለጥ ባልነበራቸው ጊዜ ሴቶቹ አስደናቂውን ዜና ለደቀመዛሙርቱ ለመናገር ሄዱ። “ወዲያው ኢየሱስ አገኛቸውና፣ ‘ሰላም ለእናንተ ይሁን!’ አላቸው። እነርሱም ወደ ኢየሱስ ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት። ኢየሱስም፣ ‘አትፍሩ፤ ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው፤ በዚያ ያዩኛል’ አላቸው” (ማቴዎስ 28፡9-10)። ይህንን በማለት ክርስቶስ በገሃድ ከወንድሞቹ ጋር ለመገናኘት በገሊላ ቀጠሮ ያዘ። የክርስቶስን አስከሬን በመቃብሩ ውስጥ ለማግኘት ሴቶቹ በሄዱ ጊዜ መድኃኒዓለም አስቀድሞ ነግሯው የነበረውን ያስታወሳቸው ማነው? ከመቃብር እነሳለሁ ያለው ክርስቶስ ነበር።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የማርቆስ ወንጌል መዘንጋት የሌለበትን አስደናቂ ነገር እንዲህ በማለት አስፍሯል፤ “ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስ፣ ‘ቀድሞአችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል፤ እንደ ነገራችሁ እዚያ ታገኙታላችሁ’” በማለት ነበር መልአኩ ለሴቶቹ የነገራቸው (ማርቆስ 16፡7)። እነዚህ ሴቶች ለጴጥሮስ እጅግ የሚያጽናና መልዕክት እንዲያደርሱ ነበር የተነገራቸው። የሱስ ጴጥሮስን ለመጨረሻ ጊዜ ያየው ሦስት ጊዜ በመደጋገም እየተራገመ በካደው ጊዜ ስለነበር በዚህ ወቅት በስም መጠራቱ ይቅርታ ማግኘቱን ያመላክታል።
“ሕያው የሆነውን እርሱን ለምን ከሙታን መካከል ትፈልጋላችሁ? እርሱ ተነሥቶአል! እዚህ የለም፤ ደግሞም በገሊላ በነበረ ጊዜ ምን እንዳላችሁ አስታውሱ፤ ‘የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥ፣ ሊሰቀልና በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ይገባል’ ብሎ ነበርና”። ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ የሰጣቸው አስደናቂ መመሪያ በፍጹም ሊዘነጋና ኃይሉንም ሊያጣ የሚገባው አልነበረም። ሆኖም ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር በነበረበት ጊዜ በተደጋጋሚ ያስተማራቸውን ትምህርቶች ማስታወስ የግድ ስለሆነ መልአኩ እንዲህ አላቸው፤ “በገሊላ በነበረ ጊዜ ምን እንዳላችሁ አስታውሱ፤ ‘የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥ፣ ሊሰቀልና በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ይገባል’ ብሎ ነበርና”። ይህ ሃሳብ ወደልባቸው ሳይመጣ በመቅረቱ ደቀመዛሙርቱን አስገርሟቸዋል። በእርግጥም የእርሱ ቃል ለምን ይረሳል?
ለዚህ ዘመንና ለእያንዳንዳችን የተሰጠን መልዕክትም ይኸው ነው፤ “ሕያው የሆነውን እርሱን ለምን ከሙታን መካከል ትፈልጋላችሁ? እርሱ ተነሥቶአል! እዚህ የለም!”
(ምንጭ፤ Ms 115, 1897 The Risen Savior. October 14, 1897)
ትርጉም፡ ጥበበሥላሴ መንግሥቱ