giziew.org

“ተፈፀመ!”

ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ፦ ተፈጸመ አለ፥ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ።
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ክርስቶስ የመጣበትን ተልዕኮ ሳያከናውን ህይወቱ አላለፈችም፤ ስለሆነም የመጨረሻ እስትንፋሱን በተነፈሰ ጊዜ “ተፈፀመ!” ሲል ጮኸ (ዮሐ. 19፡30)። ጦርነቱ በድል ተፈጸመ። የሱስ ድልን የተጎናፀፈው በራሱ ኃይል ነው። ድል በማድረጉም ሰንደቅ ዓላማውን ከሁሉ በላይ ከፍ አድርጎ አውለበለበ መላእክትስ በዚህ ድል አልተደሰቱምን? በየሱስ አሸናፊነት ሰማየ ሰማያት የድሉ ተሳታፊ ሆኑ። ሰይጣን ድል ተመታ፣ መንግሥቱንም እንዳጣ አወቀ።

ለመላእክትና በኃጢአት ላልተበከሉት ዓለማት “ተፈጸመ!” የሚለው አነጋገር ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። ታላቁ የማዳን ሥራ መጠናቀቁ እንደ እኛ ለእነርሱም ጠቀሜታ አለው። ምክንያቱም የክርስቶስ ድል አድራጊነት የሚያስገኘውን ውጤት ከእኛ ጋር ይሳተፋሉና።

የሰይጣን ትክክለኛ ባህርይ እስከ ክርስቶስ ሞት ድረስ ለመላእክትና በኃጢአት ላልወደቁት ዓለማት ግልፅ አልነበረም። ይህ ቀንደኛ ከሀዲ ማንነቱን በማታለል ዘዴው ስለሸፋፈነው መርሆውን ቅዱስ ፍጡራን እንኳ ሊያስተውሉት አልቻሉም ነበር። ስለዚህ ያመፀበትን ትክክለኛ ምክንያት ለማወቅ አልቻሉም።

በእግዚአብሔር ላይ ያመፀው ይህ ፍጡር አስገራሚ ኃይልና ክብር ነበረው። ስለዚህ እግዚአብሔር ሉሲፈር ሆይ! “በጥበብ የተሞላህና እጅግ መልከ ቀና በመሆንህ የፍፁምነት ምሳሌ ነበርህ” አለው (ሕዝ. 28፡12)። ሉሲፈር ጠባቂ ኪሩብ ስለነበር በእግዚአብሔር ፊት ይቆም ነበር። ከፍጡራን መካከል እጅግ ከፍተኛ ደረጃ የተሰጠው ሲሆን የእግዚአብሔርን ዕቅድ ለመላው ዩኒቨርስ (ፍጥረተ-ዓለም) ለማሳወቅ ግንባር ቀደም ነበር። ኃጢአት ከሰራ በኋላ በማታለል ኃይሉ የበለጠ ስለተካነበትና እግዚአብሔር ከፍተኛ ማዕረግ ሰጥቶት ስለነበር ትክክለኛ ባህርዩን ለማወቅ አዳጋች ሆነ።

አንድ ሰው ትንሽ ጠጠር መወርወር እንደማያዳግተው ሁሉ እንዲሁም እግዚአብሔር ሰይጣንን እና አይዞህ ባዮቹን ሁሉ መደምሰስ አላቃተውም ነበር። ነገር ግን አመፅን በኃይል ማሸነፍ ስላላስፈለገ ይህን ከማድረግ ተቆጠበ። ኃይል መጠቀም የሰይጣን መንግሥት ባሕርይ ነው። የእግዚአብሔር መርህ ከዚህ የተለየ ነው። የእግዚአብሔር ኃይል የተመሰረተው በርኅራኄ፣ በምህረትና በፍቅር ላይ ስለሆነ የእንቅስቃሴ ስልቱ ሁሉ ይህን መርህ የተከተለ ነው። የእግዚአብሔር መንግሥት በስነምግባር ሕግ የሚመራ ስለሆነ በእርሱ ዘንድ ልቀው የሚታዩት ኃይላት እውነትና ፍቅር ናቸው።

እግዚአብሔር ሁሉ ነገር ዘላለማዊ ዋስትና ያለው እንዲሆን ስለሚፈልግ ሰይጣን የመንግሥቱን መርሆች ለማዳበር ጊዜ እንዲሰጠው በሰማይ ጉባኤ ተወሰነ። ሰይጣን የእርሱ መርሆች ከእግዚአብሔር መርሆች የተሻሉ ናቸው የሚል አቋም ስለያዘ ዓለማት በሙሉ የሰይጣንን መመሪያዎች እንዲያውቁ በሥራ ላይ አውሎ እንዲያሳይ ጊዜ ተሰጠው።

ሰይጣን ሰውን ስላሳሳተ እግዚአብሔር ሰውን የማዳን ዕቅድ አዘጋጀ። ክርስቶስ ሰውን ከወደቀበት ለማንሳት ለአራት ሺ ዓመታት ሲታገል ሰይጣን በበኩሉ በነዚህ ዓመታት ሰውን የበለጠ ለማዝቀጥና ለማጥፋት ተጣጣረ። ዓለማት ይህን ትርዒት ልብ ብለው ተመለከቱ።

ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ ሰይጣን ያለ የሌለ ኃይሉን አሰባስቦ በእርሱ ላይ አነጣጣረበት። የሱስ ገና በቤተልሔም ህፃን ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ይህ ያለአግባብ ሥልጣን የያዘ ጠላት የሱስን ለማጥፋት ተጣጠረ። ሰይጣን የሱስ ፍፁም የሆነ የህፃንነት አስተዳደግ እንዳይኖረው፣ እንከን የሌለበት የመካከለኛ ዕድሜ ባለቤት እንዳይሆን፣ የተቀደሰ አገልግሎትና ነውር የሌለበት መስዋዕት ለማቅረብ እንዳይችል ለማድረግ የተቻለውን ያህል ሞከረ። ነገር ግን የሱስን ኃጢአት እንዲሠራ ለማድረግ ስላልቻ ተሸነፈ።

የሱስን ተስፋ ለማስቆረጥና ወደ ዓለም የመጣበትን ሥራ እንዲተው ለማድረግ አልቻለም። ከምድረ በዳው ፈተና ጀምሮ እስከ ቀራንዮው ስቃይ ድረስ የሰይጣን የቁጣ ማዕበል የሱስን አዋከበው፤ ነገር ግን ቁጣው በጨመረ መጠን የሱስ የአባቱን እጅ የበለጠ አጥብቆ በመያዝ በደም ጎዳናው ላይ ጉዞውን ቀጠለ። ሰይጣን የሱስን ለማጥቃትና ለማሸነፍ ያደረገው ጥረት ሁሉ እንከን የሌለበትን የክርስቶስ ባሕርይ የበለጠ ጎልቶ እንዲታይ አደረገው።

ሰማይና በኃጢአት ያልወደቁ ዓለማት በሙሉ ይህን ተጋድሎ አይተዋል። የዚህን ትግል የመጨረሻ ትዕይንት በከፍተኛ ጉጉት ተከታትለውታል። አዳኛችን ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ ሄዶ ከፊቱ በተደቀነው ታላቅ ጨለማ ምክንያት ነፍሱ ምን ያህል እንደተጨነቀች ተመልክተዋል። “አባት ሆይ! የሚቻል ከሆነ ይህ የመከራ ፅዋ ከእኔ ወዲያ ይለፍ” ሲል ያሰማውን የመረረ ጩኸት ሰምተዋል (ማቴ. 26፡39)። አባቱ ስለተለየው ከሞት ጋር ከሚደረግ የመጨረሻ ትልቅ ትግል በበለጠ ምሬት እንዳዘነ አይተውታል። በዚያን ጊዜ የደም ላብ ከቆዳው እየፈለቀ በመሬት ላይ ተንጠባጠበ። የመከራው ፅዋ እንዲቀርለት ሦስት ጊዜ የጭንቀት ፀሎት አቀረበ። ይህንን ሁሉ ስቃይ ማየት ስለዘገነነው እግዚአብሔር ልጁን የሚያፅናና መልእክተኛ ላከ።

የሱስ ለነፍስ ገዳዮች አሳልፎ ሲሰጥና እየተፌዘበትና እየተሰቃየ ከአንዱ ፍርድ ቤት ወደ ሌላው እያጣደፉ ሲወስዱት የሰማይ ነዋሪዎች ተመለከቱ። ከዝቅተኛ ቤተሰብ በመወለዱ ጠላቶቹ መዘባበቻ ሲያደርጉትም አዩ። በጣም እንወድሃለን ከሚሉት ደቀመዛሙርቱ አንዱ እየማለና እየተገዘተ ሲክደው ሰሙ። ሰይጣን በሰዎች ልብ ላይ የሚያካሂደውን የእብደት ሥራ ሁሉ ተመለከቱ። አዳኛችን በእኩለ ሌሊት በጌቴሴማኒ እንደ ክፉ አድራጊ ተከብቦ ሲያዝ፣ ከቤተመንግሥት ወደ ፍርድቤት እየተጎተተ ሲወሰድ፣ በተከሳሽነት ሁለት ጊዜ በካህናት ፊት፣ ሁለት ጊዜ በአይሁድ ሸንጎ ፊት፣ ሁለት ጊዜ በጲላጦስ ፊት፣ አንድ ጊዜ በሄሮድስ ፊት ከቀረበ በኋላ የሞት ፍርድ ተበይኖበትና ተገርፎ ሕዝቡ እያፌዘበትና የኢየሩሳሌም ሴቶች እያለቀሱለት ያን ከባድ መስቀል ተሸክሞ ሲሄድ ማየት እንዴት ያለ ዘግናኝ ትእይንት ነው!

ክርስቶስ ከራሱ ደም እየወረደና በግንባሩ ላይ ደም የተቀላቀለበት ላብ ተቋጥሮ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ማየት ለሰማይ ፍጡራን አሳዛኝና አስገራሚ ነበር። ከእጆቹና ከእግሮቹ የሚፈሰው ደም መስቀሉን ለመትከል በተቦረቦረው ዓለት ላይ ይንጠባጠብ ነበር። የሰውነቱ ክብደት እጆቹን ወደታች ስለሳባቸው በእጆቹ መዳፍ ላይ በተተከለው ምስማር ምክንያት የተፈጠረው ቁስል እየሰፋ ሄደ። አዳኛችን የዓለምን ኃጢአት በመሸከሙ ከክብደቱ የተነሳ ነፍሱ ስለተጨነቀች ትንፋሹ ቁርጥ ቁርጥ አለ። መድኃኒዓለም ያን ሁሉ ግፍና መከራ እየተቀበለ ሳለ “አባት ሆይ! የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው!” ብሎ መፀለዩ የሰማይን ነዋሪዎች አስገረማቸው (ሉቃ. 23፡34)። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ ሰዎች ግን የተወደደውንና ብቸኛውን የእግዚአብሔርን ልጅ ሕይወት ለማጥፋት ቆመው ነበር። ይህ ለሰማይ ነዋሪዎች ምን ዓይነት ትዕይንት ይሆን!

የጨለማው ዓለም ገዦችና ባለሥልጣናት በመስቀሉ ዙሪያ ተሰብስበው በዲያብሎሳዊ ዘዴያቸው የሰዎችን ኅሊና እያደነዘዙ እንዳያምኑ ያደርጓቸው ነበር። እግዚአብሔር እነዚህን ፍጡራን (ቀድሞ መላእክት የነበሩ አሁን አጋንንት የሆኑ) በዙፋኑ ፊት እንዲቆሙ በፈጠራቸው ጊዜ የተዋቡና ክብር የተጎናፀፉ ነበሩ። ተወዳጅነታቸውና ቅድስናቸው ለተሰጣቸው ከፍተኛ ደረጃ ተስማሚ ነበር። በእግዚአብሔር ጥበብ የበለፀጉና ሰማያዊ ትጥቅ የለበሱ ነበሩ። እነዚህ ፍጡራን የኃያሉ አምላክ እግዚአብሔር አገልጋዮች ነበሩ። ነገር ግን ከአሁኑ ሁኔታቸው እነዚህ የወደቁ መላእክት በሰማያዊ አደባባዮች ያገለገሉና ግርማ ሞገስ የተጎናጸፉ ሱራፌሎች እንደነበሩ ማወቅ የሚችል ማን ነው?

የሰይጣን ወኪሎች ከክፉ ሰዎች ጋር በመተባበር ሰዎች ክርስቶስ የኃጢአተኞች መሪ ነው ብለው በማመን እንዲጠሉት አደረጓቸው፤ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ ያፌዙበት የነበሩት ሰዎች አስቀድሞ ባመፀው በሰይጣን መንፈስ የተሞሉ ነበሩ። ሰይጣን እነዚህ ሰዎች አሳፋሪና እጅግ አፀያፊ የሆነ ንግግር እንዲናገሩ አደረጋቸው። የጠብ አጫሪነት መንፈስ አሳደረባቸው፤ ነገር ግን ይህ ሁሉ ምንም አልጠቀመውም።

ክርስቶስ አንዲት ኃጢአት እንኳ ብትገኝበትና ሰይጣን ካደረሰበት አሰቃቂ ስቃይ ለማምለጥ ትንሽ ቢያፈገፍግ ኖሮ የሰውና የእግዚአብሔር ጠላት የሆነው ሰይጣን ድል አድራጊ በሆነ ነበር። ነገርግን ክርስቶስ ራሱን ዝቅ አድርጎ ሞተ፤ እምነቱና ለእግዚአብሔር የነበረው ተገዥነት እጅግ ፅኑ ነበር፤ “ከዚህ በኋላ አንድ ታላቅ ድምፅ በሰማይ እንዲህ ሲል ሰማሁ እነሆ ማዳንና ኃይል መንግሥትም የአምላካችን ሆኖአል! ሥልጣንም የመሲሑ ሆኖአል1 ምክንያቱም ወንድሞቻችንን በአምላካችን ፊት ቀንና ሌሊት ሲያሳጣቸው የነበረ የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአል” (ራዕይ 12፡10)።

ሰይጣን የማታለያ ሽፋኑ እደተቀደደ ገባው። አስተዳዳሩም ላልወደቁት መላእክትና ለመላው ዩኒቨርስ ግልፅ ሆነ። ነፍሰ ገዳይ መሆኑንም በይፋ አሳወቀ። የእግዚአብሔርን ልጅ ደም በማፍሰሱ የሰማይ ነዋሪዎችን ድጋፍ እንዲያጣ አደረገው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተግባር እንቅስቃሴው ውሱን ሆነ። ሰይጣን የተለያዩ ባህርያትን በመላበስ ከሰማይ አደባባዮች ለሚመጡ መላእክት የክርስቶስን ወንድሞች (የክርስቲያኖችን) ልብስ በኃጢአት የቆሸሸ፣ ህይወታቸውም የረከሰ አድርጎ የሚያቀርበው ክስ ተቋጨ። ሌሎች ዓለማት ስለ ሰይጣን የነበራቸው በጎ አስተያየት አከተመ።

ይህም ሆኖ ሰይጣን እንዲጠፋ አልተደረገም። መላእክት የታላቁን ተጋድሎ መሠረታዊ ምክንያት ገና በትክክል አላስተዋሉም ነበር። የተጋድሎ ምሥጢር ይፋ መውጣት ነበረበት። ለሰው ደህንነት ሲባል የሰይጣን ኅልውና መቀጠል አስፈላጊ ሆነ። ሰዎችም ሆኑ መላእክት በክርስቶስና በሰይጣን መካከል ያለውን ልዩነት ማየት አለባቸው። ሰው ከሁለቱ የየትኛው አገልጋይ መሆን እንደሚፈልግ ራሱ መወሰን አለበት።

ታላቁ ተጋድሎ በተጀመረ ጊዜ ሰይጣን የእግዚአብሔርን ህግ መጠበቅ እንደማይቻል፣ ፍትህና ምህረት እርስ በእርሳቸው የሚቃረኑ እንደሆኑና የእግዚአብሔርን ህግ የሚተላለፍ ሰው ለጥፋቱ ይቅርታ የሚያገኝበት ሁኔታ እንደሌለ ይፋ አድርጎ ነበር። ለኃጢአት ቅጣት መኖር አለበት፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በኃጢአት ምክንያት ሰውን የማይቀጣ ከሆነ የፍትህና የእውነት አምላክ ሊሆን አይችልም ሲል ሰይጣን ተከራከረ። ሰዎች (አዳምና ሔዋን) የእግዚአብሔርን ህግ ሲጥሱና ትእዛዙን ሲተላለፉ ባየ ጊዜ ሰይጣን በጣም ደስ አለው። የእግዚአብሔርን ህግ መጠበቅ እንደማይቻልና ሰው ይቅርታ ሊያገኝ እንደማይችል ተረጋገጠ ሲል አወጀ። እርሱ በአመፅ ምክንያት ከሰማይ እንደተባረረ ሁሉ እንዲሁም መላው ሰብዓዊ ዘር ከእግዚአብሔር ፊት መወገድ አለበት ሲል ተሟገተ፤ ለኃጢአተኛ ምህረት ካደረገ እግዚአብሔር ቅን ፈራጅ ነው ሊባል አይችልም የሚል ክርክርም አቀረበ።

ይሁን እንጂ ሰው በኃጢአተኛነቱ ከሰይጣን የተለየ ነው። ምክንያቱም ሉሲፈር ኃጢአት የሠራው የእግዚአብሔር ግርማ በሚያበራበት በሰማይ ነው። ለማንም ፍጡር ከተደረገው በበለጠ አኳኋን ለእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር ተገልፆለት ነበር። ሰይጣን የእግዚአብሔርን ባህርይና ደግነት እያወቀ በራስ ወዳድነት መንፈስ የራሱን ፍላጎት ለመከተል መረጠ። ይህ ምርጫ የመጨረሻው ስለሆነ ከዚህ በኋላ ሰይጣንን ለማዳን እግዚአብሔር ምንም ማድረግ አልቻለም። ሰው ግን አሳሳች በሆነው በሰይጣን የክርክርና ረቂቅ ብልጣብልጥነት ስልት ተታለለ። ሰው የእግዚአብሔር ፍቅር ስፋቱና ርዝመቱ፣ ቁመቱና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደሆነ አያውቅም ነበር። ስለዚህ ሰው የእግዚአብሔርን ፍቅር በማወቅ የመዳን ተስፋ ነበረው። የእግዚአብሔርን ባህርይ በመመልከት ወደ እርሱ የመቅረብ ተስፋ አገኘ።

ስለዚህ የእግዚአብሔር ምህረት በክርስቶስ አማይነት ለሰው ተገለጠ። ምህረት ከፍትህ ተለይቶ አይታይም። ህግ የእግዚአብሔር ባህርይ መግለጫ ስለሆነ ሰውን ከወደቀበት ቦታ ለመገናኘት ከህግ አንዲት ጭረት ወይም አንዲት ነጥብ መለወጥ አላስፈለገም። እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን በክርስቶስ አማካይነት ራሱን ሰዋ እንጂ ህግን አልለወጠም። “እግዚአብሔር በክርስቶስ አማካይነት ሰዎችን ሁሉ ከራሱ ጋር አስታረቀ” (2 ቆሮ. 5፡19)።

ህግ የተቀደሰ ህይወትና ፍፁም የሆነ ባሕርይ ይጠይቃል፤ ነገር ግን ይህ ከሰው አይገኝም። ሰው የእግዚአብሔር ቅዱስ ህግ የሚጠይቀውን ማሟላት አይችልም። ክርስቶስ ግን እንደ ሰው ሆኖ ወደ ዓለም በመምጣት ቅዱስ ህይወት ኖረ፣ ፍፁም የሆነ ባሕርይም አዳበረ። ስለዚህ እርሱን ለሚቀበሉት ሁሉ ይህንን ዓይነት ህይወት በነፃ ይሰጣል። የሱስ በሰው ምትክ ስለኖረ ሰዎች በእግዚአብሔር መሐሪነት የቀድሞው ኃጢአታቸው ሁሉ ይቅር ይባልላቸዋል። ከዚህም በላይ ክርስቶስ ሰዎችን በእግዚአብሔር ባሕርይ ያንጻቸዋል። ክርስቶስ ሰዎች ጠንካራና የተዋበ መንፈሳዊ ህይወት እንዲኖራቸው ባህርያቸውን በመለኮታዊ ባሕርይ አምሳያ ይቀርፃል። በዚህ አኳኋን የህግ ፅድቅ በምእመናን ህይወት ይንፀባረቃል። “እግዚአብሔር ራሱ ፃድቅ መሆኑን የሚያሳየው በኢየሱስ የሚያምኑትን ሁሉ በማፅደቅ ነው” (ሮሜ. 3፡26)።

የእግዚአብሔር ፍቅር በመሐሪነቱ ብቻ ሳይሆን በፍትሐዊነቱም ይገለፃል። ፍትህ የእግዚአብሔር ዙፋን መሠረትና የፍቅሩ ፍሬ ነው። ሰይጣን ምህረትን ከእውነትና ከፍትህ ነጥሎ ለማየት ነበር ያቀደው። በእግዚአብሔር ህግ የተገለፀው ፅድቅ የሰላም ተፃራሪ ነው በማለት ለማሳመን ተመኘ። ክርስቶስ ግን ምህረት፣ እውነትና ፍትህ በእግዚአብሔር ዕቅድ በምንም አኳኋን የማይለያዩና አንዱ ያለሌላው መኖር እንደማይችል አሳየ። “ፍቅርና እውነት ይተቃቀፋሉ፣ ፅድቅና ሰላም ይሳሳማሉ” (መዝ. 85፡10)።

ክርስቶስ በህይወቱና በሞቱ የእግዚአብሔር ፍትሐዊነት መሐሪነቱን እንዳልሰረዘው፣ ኃጢአት ይቅር ሊባል የሚቻል መሆኑን፣ ህግ ፅድቅ መሆኑን ሙሉ በሙሉ በተግባር ሊተረጎም እንደሚቻል አስመስክሯል። ስለዚህ የሰይጣን ክስ ሐሰት መሆኑ ታወቀ። እግዚአብሔርም ለሰው ስለ ፍቅሩ የማያጠራጥር ማስረጃ ሰጠ።

ሰይጣን የፈፀመው ሌላ የማታለል ሥራ መጋለጥ ነበረበት። ሰይጣን ምህረት ፍትህን እንደሚፃረርና የክርስቶስ ሞት የአባቱን ህግ እንደሚሽር አሳውቆ ነበር። ነገር ግን ህግን መለወጥ ወይም መሻር የሚቻል ቢሆን ኖሮ ክርስቶስ መሞት ባላስፈለገውም ነበር። ህግን መሻር ማለት ኃጢአትን ዘላለማዊ ማድረግና ዓለምን በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ማዋል ማለት ነው። የሱስ መስቀል ላይ የተሰቀለበት ዋና ምክንያት ህግ የማይለወጥ ስለሆነና ሰው ሊድን የሚችለው የህግን መመሪያ በማክበር ብቻ በመሆኑ ነው። ክርስቶስ የህግ መሠረት ያደረጋቸውን ሁኔታዎች ሰይጣን የህግ አፍራሽ አስመስሎ ተረጎማቸው። ይህ ሁኔታ በየሱስና በሰይጣን መካከል ባለው ትልቅ ተጋድሎ የመጨረሻውን ግጭት ያስከትላል።

ባለንት ዘመንም፣ ሰይጣን በእግዚአብሔር የተነገረው ህግ ስህተት አለበት፤ አንዳንድ ዝርዝር ሁኔታዎችን አያካትትም በማለት ይከራከራል። ለዓለም የሚያቀርበው የመጨረሻው ትልቁ ማታለያውም ይኸው ነው። ሰዎች ከእግዚአብሔር ህግጋት አንዱን ችላ ካሉ ዕቅዱ ስለሚሳካለት ሰይጣን መላውን ህግ ማውገዝ አያሻውም። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ሰው ከትእዛዞች አንዱን አፍርሶ የቀሩትን ሁሉ ቢፈፅም እንኳ ሁሉን እንዳፈረሰ ይቆጠራል” (ያዕ. 2፡10)። ሰዎች ከህግ አንዱን ትዕዛዝ ለመሻር ከተስማሙ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ዋሉ ማለት ነው። ሰይጣን የእግዚአብሔርን ህግ በሰብዓዊ ህግ በመተካት ዓለምን ለመቆጣጠር ይፈልጋል። ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ በትንቢት ተነግሯል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በሰይጣን ውክልና የክህደትን ሥራ ስለሚሠራው ኃይል መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ትንቢት ሰጥቷል፤ “በትዕቢትም በልዑል ላይ ይናገራል፣ የልዑልንም ቅዱሳን ይሰብራል (ያስጨንቃል)። ዘመንና ህግንም ይለውጥ ዘንድ ያስባል” (ዳን. 7፡25)።

በተለይ በመጨረሻው ዘመን ሰዎች የእግዚአብሔርን ህግጋት በመፃረር የራሳቸውን ህጎች እንደሚያወጡ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ራዕይ 13፡11-18)። እነዚህን ህግጋት ለማስከበር ባላቸው ቀናኢነት ሰዎችን ለመጨቆንና ህሊናቸውን ለማስገደድ ይሻሉ፤ (ይህንን በማይቀበሉ ላይ ደግሞ የሞት ፍርድ እንዲወጣባቸው የመንግሥትን ሥራአስፈጻሚነት ይጠቀሙበታል (ዳን. 3፡ 13-18 እና ራዕይ 13፡16 ያነጻጸሩ)።

በሰማይ የእግዚአብሔርን ህግ ለማፋጥት የተጀመረው ዘመቻ እስከ ጊዜ ፍፃሜ ድረስ ይቀጥላል። ይህን በተመለከተ እያንዳንዱ ሰው ይፈተናል። መታዘዝ ወይም አለመታዘዝ ለሚለው ጥያቄ ከመላው ዓለም ውሳኔ ይጠበቃል። ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ህግና በሰው ህግጋት መካከል እንዲመርጡ ይጠየቃሉ። በዚህ ምክንያት ሰዎች በሁለት ክፍል ይመደባሉ። በእያንዳንዱ ሰው ላይ የሚታየው ባህርይ ሰዎች በታማኝነት በእግዚአብሔር ጎን የቆሙ ወይም የአመጽ መሪ በሆነው በሰይጣን ጎን የተሰለፉ መሆናቸው ይታወቃል።

ይህ ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ ፍፃሜ ይሆናል። እግዚአብሔር የህጉን ትክክለኛነት ያስመሰክራል፣ ህዝቡንም ነፃ ያወጣል። ሰይጣንና በእርሱ አመፅ የተባበሩ ሁሉ ይለያሉ፤ ኃጢአትና ኃጢአተኞች ከሥር እስከ ቅርንጫፍ (ማለትም ሥሩ ሰይጣን፣ ቅርንጫፎቹ ተከታዮቹ) ይደመሰሳሉ (ሚል. 4፡1)። ያን ጊዜ ስለ ኃጢአት መሪው “ልብህን ከፍ ከፍ አድርገሀልና የእግዚአብሔር ልብ እንደሆነ… የምትጋርድ ኪሩብ ሆይ ከእሳት ደንጊያ መካከል አጠፋሁኽ”። “ለኃጢአተኛ ጥቂት ጊዜ ቀረው አይገኝም። ቦታውን ትሻለህ አታገኘውም”። “አህዛብ ሁሉ ከዚህ የከፋ የመከራ ፅዋ ይጠጣሉ፣ የጠጡትም ሁሉ እንዳልነበሩ ይሆናሉ” ሲል የተፃፈው ቃል ይፈፀማል (ሕዝ. 28፡6-19፣ መዝ. 37፡10፣ አብድዩ 16)።

ይህ ድርጊት እግዚአብሔር በኃይሉ ተመክቶ የሚፈፅመው አይደለም። ምህረቱን ችላ የሚሉ ሰዎች የሥራቸውን ዋጋ ያገኛሉ። አንድ ሰው የኃጢአት አገልጋይ ለመሆን ሲወስን የህይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር ራሱን ያገላል። “ከእግዚአብሔርም ሕይወት (ይለያል)” (ኤፌ 4፡18)። ክርስቶስ “የሚያጣኝ ሁሉ ግን ራሱን ይጐዳል፤ የሚጠሉኝም ሁሉ ሞትን ይወዳሉ” ይላል (ምሳ. 8፡36)። የእግዚአብሔር ሰዎች ባህሪያቸውን በፈለጉ አቅጣጫ እንዲያዳብሩና የህይወታቸውን መመሪያ ለመወሰን እንዲችሉ የህልውና ጊዜ  ሊሰጣቸው ይገባል። ይህን ዕድል ካገኙ በኋላ የምርጫቸውን ውጤት ያገኛሉ። ሰይጣንና ተባባሪዎቹ የአመፅ ኑሮ በመኖር ከእግዚአብሔር ጋር መስማማት ስለማይችሉ የእግዚአብሔር ፊት የሚያቃጥል እሳት ይሆንባቸዋል። ባህርዩ ፍቅር የሆነው አምላክ በግርማ ሞገሱ ያጠፋቸዋል።

በታላቁ ተጋድሎ መጀመሪያ ላይ ይህ ሁሉ ለመላእክት ግልፅ አልነበረም። ሰይጣንና ሠራዊቱ የኃጢአታቸውን ውጤት እንዲያገኙ ቢደረግ ኖሮ ይጠፉ ነበር፣ ነገር ግን የኃጢአት የመጨረሻው ውጤት ሞት መሆኑ ለሰማይ ነዋሪዎች ግልፅ አይሆንም ነበር። በዚህ ምክንያት ስለ እግዚአብሔር ደግነት የሚኖራቸው ጥርጣሬ በአእምሯቸው ውስጥ የጥፋት ፍሬ የሚያፈራ የኃጢአት ዘር ይሆን ነበር።

ታላቁ ተጋድሎ በሚያበቃበት ጊዜ ግን ይህ ስጋት አይኖርም። በዚያን ጊዜ ኃጥአንን የማዳን ዕቅድ ይጠናቀቃል፤ የእግዚአብሔር ትክክለኛ ባሕርይም ለፍጥረት ሁሉ ግልፅ ይሆናል። እንደዚሁም የእግዚአብሔር ህግ ፍፁም የማይለወጥ መሆኑ ይታወቃል። የኃጢአት ምንነትና የሰይጣን ባህርይ ይፋ ይወጣሉ። በዚያን ጊዜ የኃጢአት ፍፃሜ ማግኘት የእግዚአብሔርን ፍቅር ያረጋግጣል፣ ፈቃዱን መፈፀም ደስታቸው በሆነውና ህጉ በልባቸው በተፃፈው በዩኒቨርስ ነዋሪዎች ፊትም ክብሩ መሠረት ያለው እንዲሆን ያደርገዋል።

በዚያን ጊዜ መላእክት ሁሉን ነገር ስለሚያስተውሉ የክርስቶስን መስቀል መለስ ብለው ሲመለከቱ ይደሰታሉ፣ ኃጢአትና ሰይጣን ለዘላለም መጥፋታቸውን፣ ሰው ከኃጢአት መዳኑ እንደተረጋገጠና መላው ዩኒቨርስ ዘላለማዊ የሆነ የደህንነት ዋስትና እንዳገኘ ያውቃሉ። ክርስቶስ በቀራንዮ መስቀል ላይ የከፈለው መስዋዕት ውጤቱ ምን እንደሚሆን በትክክል አውቆ ነበር። ይህንን ሁሉ አስቀድሞ በማየት ነው በመስቀል ላይ ሆኖ “ተፈጸመ!” ሲል የጮኸው። (የዘመናት ምኞት፤ ገጽ 758-764)

ትርጉም፤ አበበ ብዙነህ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *