giziew.org

መድኃኒዓለም የሴቲቱ ዘር

“በአንተ (በሰይጣን) እና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ”
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

አዳም በኤድን ገነት ሲበድል ሞት በሰው ሁሉ ላይ ነገሠ። ይህ ሞት ዕድሜ ጠብቆ ወይም በሌሎች ምክንያቶች የሚከሰተው ሞት ብቻ ሳይሆን የዘላለም ሞት ነው። ኃጢአት ዋጋ ያስከፍላል፤ ደመወዝ አለው። “ሞት ነው” ይለናል መጽሐፍ ቅዱስ (ሮሜ 6፡23)። ይህ ሞት ደግሞ ዘላለማዊ ነው። እዚሁ ጥቅስ ላይ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት” ነው ካለ በኋላ ሲቀጥል፤ “የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል የዘላለም ሕይወት ነው” ይለናል።

ይህንን የዘላለም ሕይወት እውን ለማድረግ አምላክ ራሱ ዋጋ እንደሚከፍል አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። አዳምና ሔዋን ከበደሉ በኋላ ይህ ተስፋ አዘል ትንቢት ተሰጣቸው። “በአንተ (በሰይጣን) እና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ” (ዘፍጥረት 3፡15)። ይህንን ተስፋ ይዘው የእግዚአብሔር ሰዎች መንግሥት የጌታችንና የመሲሑ የሚሆንበትን እየናፈቁ አለፉ። ከግብጽ ባርነት “በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ” ነጻ የወጡት እስራኤላውያንም ለበርካታ ዓመታት የበግ ደም በቤታቸው መቃንና ጉበን ላይ በመቀባት ፋሲካን በተስፋ ሲያከብሩ ኖሩ።

ሆኖም የሴቲቱ ዘር የተባለው መሲሕ አራት ሺህ ዓመታትን ጠብቆ፤ የሰው ሥጋ ለብሶ መጣ፤ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ሆነ – አማኑኤል! ወደ ጠላት ወረዳ ሲመጣ ምንም መከላከያ አልነበረውም። እልፍ አእላፋት መላእክትን ማዘዝ የሚችለውና እነርሱም በፍጹም ደስታ የሚታዘዙለትን ኃያላንን ይዞ ሳይሆን በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ ረዳተቢስና ተከላካይ አልባ ሆኖ ባዶ እጁን ነበር የመጣው።

በአፈ ጮሌነትና በክፉ የማታለል ሥራው የዚህችን ዓለም ግዛት ከአዳም የነጠቀው ዲያቢሎስ፤ የሰማይ ልዑል የሆነውን ተወዳጁን የሱስ በግላጭ፣ በራሱ ሜዳ ላይ ሲያገኘው እንዴት እንደሚያሰቃየውና እንደሚያጠፋው የሚያወጣው ዕቅድ አልበቃ አለው። በሙሉ ኃይሉ ከመላው የአጋንንት ሠራዊት ጋር ሆኖ መድኃኒታችንን ገና ከህጻንነቱ ጀምሮ አንገላታው፣ አሰቃየው፣ አስጨነቀው፤ በመጨረሻም እጅግ አዋርዶ አሰቃቂውን የመስቀል ሞት እንዲሞት በጲላጦስ አስፈረደበት።

በዚህ ሁሉ ውስጥ አንዳችም ቃል ያልተናገረው መድኃኒዓለም አስፈሪ፣ አስከፊና አስጨናቂ የሆነውን የዘላለም ሞት ጎዳና ብቻውን ሄደበት። በጣዕር ተይዞ ባለበት ጊዜ በምድር ላይ ተዘርሮ ወደ አባቱ የሰቆቃ ድምፁን አሰማ። “ፈቃድህ ቢሆን ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ” በማለት ደጋግሞ በብርቱ ቃተተ። ልጁን “አምላክ ሆይ” በማለት የሚጠራው አባቱም ጽዋውን ጠጣው አለው።

“ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች” በማለት ደጋፊ ፈልጎ ለደቀመዛሙርቱ የልቡን ጭንቀት የተናገረው ርኅሩኁ ጌታችን በዚያች ወሳኝ ሰዓት ከጎኑ የሚቆም አጣ። እነርሱም በእንቅልፍ ተይዘው ስቃዩን ለመጋራት አልቻሉም። አይዞህ ባይ አጥቶ በሁሉም ተተወ። የዘላለምን ሞት ብቻውን ሲጋፈጥ ነፍሱ ዛለች፤ “ላቡም እንደ ደም ነጠብጣብ ወደ ምድር” ፈሰሰ። ፍጹም ኃፍረትና እጅግ ውርደት የሞላበትን የመስቀል ሞት ለመሞት የቀራንዮን ኮረብታ ሲወጣ ጉልበት ስላልነበረው በምድር ላይ ተደፋ። ለቀናት ምንም ሳይመገብ ብዙ መንገላታትና ግርፋት ስለደረሰበት ኃይልም አልቀረውም ነበር።

በቀራንዮ ኮረብታ በወንጀለኞች መካከል የወንበዴዎች ቁንጮ ተደርጎ ተሰቀለ። የሚሞትላቸውን ጌታ፤  ንጉሥ ከሆንህ “ራስህን አድን” እያሉ ሲሳለቁበት ለነበሩት፤ “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” በማለት ማለደላቸው። ለሰው ልጅ መዳን የሚስያፈልገውን ዋጋ አንዳች ሳያጓድል ፍጹም መስዋዕትነት ከፈለ። የእግዚአብሔርንም መኃሪነት፣ ቅን ፈራጅነትና ጻድቅነት ለዩኒቨርስ በማሳየት በደሙ ማኅተም ለዘላለም አተመው። ዕርቃኑን ተሰቅሎ የዲያቢሎስን ሽንገላና ማታለያ ለዓለማት ሁሉ ዕርቃኑን አወጣው!

ሁሉን ካከናወነና ካጠናቀቀ በኋላ መራራውን ሆምጣጤ በመቀበል “ተፈጸመ” አለ!

አዘጋጆቹ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *