giziew.org

ፋሲካ

"እርሱ ግን ስለመተላለፋችን ቆሰለ፤ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደህንነታችንም ተግሳፅ በእርሱ ላይ ነበረ። በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን”
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

የፋሲካ በዓል በሀገራችን ከታላላቅ በዓላት አንዱ ሲሆን በበለጠ የሚታወቀው ዘመድ አዝማድ፤ ጎረቤት ጓደኛ ተሰባስበው አብረው በመሆን በሚበሉትና በሚጠጡበት ገፅታው ነው። በሌሎች ሀገሮችም ቢሆን ሰዎች ትኩረታቸውን በእርስበርስ ላይ በማድረግ ስጦታን በመለዋወጥ እና በመገባበዝ ሲያከብሩት ማየት የተለመደ ነው።

የፋሲካን ታሪክ አጀማመር ከሥር መሠረቱ ማወቅ ጠቀሜታው ዛሬ በአካባቢያችን ከምናየው እና ከምንታዘበው ጊዜያዊ እና ኃላፊ ደስታ በላይ ሲሆን ለእያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር የዘለዓለማዊ ህይወት መዳረሻ ምክንያት ነው።

እግዚአብሔር ሰውን በአምሳሉ ፈጥሮ ለዘለዓለም በገነት ምንም ሳይጎድልበት እንዲኖር ያወጣውን ዕቅድ ኃጢያት ባበላሻበት ጊዜ ሰው በገዛ ምርጫው ከወደቀበት የዘለዓለም ሞት ሊያድነው አንድ ልጁን ወደ አለም ላከ። ልጁም የኃጢያትን ዋጋ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በመሞት ከፈለ፤ ነቢዩ ኢሳያስ ይህንን ታላቅ ክስተት ሲዘግብ በኢሳ 53፡-4-5 ላይ “በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ህመማችንንም ተሸክሟል፤ እኛ ግን እንደተመታ በእግዚአብሔርም እንደተቀሰፈ እንደተቸገረም ቆጠርነው። እርሱ ግን ስለመተላለፋችን ቆሰለ፤ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደህንነታችንም ተግሳፅ በእርሱ ላይ ነበረ። በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን” በማለት በመስቀል ላይ ያየውን ስቃይና የቆሰለው ቁስል የሞተውን ሞት የእኛን ቦታ ወስዶ እና ኃጢያት ተሸክሞ እንደተቀበለው በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርቶ ተናገረ።

ዛሬ የፋሲካን በዓል እያንዳንዳችን የምህረት፣ የደህንነትና የዘለዓለማዊ ህይወት ታሪክ መጀመሪያ አድርገን ብንወስደው በሌላ ነገር ላይ ያለን ትምክህታችንና ምድራዊ ኩራታችን ሁሉ ከእኛ በተወገደ ነበር። “እኛ ግን እንደተመታ በእግዚአብሔር እንደተቀሰፈ እንደተቸገረም ቆጠርነው” የሚለው ዓረፍተነገር ሰይጣን የመስቀሉን እውነት በማጣመም ክርስቶስ የተሰቃየውና የቆሰለው ለእኛ እንዳልሆነ አድርገን እንድናይ ለማድረግ ጥረት ያደርጋል።

የመስቀሉ እውነት የተረዳው ጳውሎስ በገላትያ 6፡14 ላይ “ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበትን እኔም ለዓለም የተሰቀልኩበትን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ” በማለት ክርስቶስ የተሰቃየው ስቃይና የሞተው ሞት የእርሱ ስቃይና ሞት መሆኑን ገለፀ። ይህንኑ ሀሳብ ሲያጠናክር በገላትያ 2፡20 ላይ “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ እኔም አሁን ህያው ሁኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ህያው ሆኖ ይኖራል” አለ። ክርስቶስ ስለ ኃጢያታችን የከፈለው ዋጋ በዓለማችን ክብርና ታላቅ አድርገን ከምናያቸው ነገሮች ሁሉ የበለጠ ነው። ትክክለኛው የሰብዓዊ ፍጡር ኃጢያት ዋጋ የተከፈለው በቀራንዮ መስቀል ላይ ነው። በዚያ ላይ ተሰቅሎ የከፈለውም ክርስቶስ ነው።

በሮሜ 6፡23 “የኃጢያት ዋጋ ሞት ነውና የእግዚአብሔር የፀጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘለዓለም ህይወት ነው” ይላል። እዚህ ላይ ኃጢያትን ከዘለዓለም ህይወት ጋር ሲያነፃፅረው እናያለን። በሌላ አነጋገር የኃጢያት ዋጋ የዘለዓለም ሞት ሲሆን የእግዚአብሔር የፀጋ ስጦታ ግን የዘለዓለም ህይወት ነው ማለት ነው።

ክርስቶስን በእምነት መቀበል ማለት የመስቀል ሞቱን ስለእኛ የሞተበትና የኃጢያታችን ዋጋ የተከፈለበት አድርገን መውሰድ ማለት ነው፤ ጳውሎስ “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ” ያለው ለዚህ ነው። ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ ጳውሎስ በዚያ አልነበረም። በእምነት ግን ክርስቶስ ኃጢያቱን ተሸክሞ እንደተሰቀለ አመነ። ክርስቶስ ምንም ኃጢያት አልነበረበትም። በ2ቆሮ 5፡21 “እኛ በእርሱ ሁነን የእግዚአብሔር ፅድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢያት ያላወቀውን እርሱን ስለእኛ ኃጢያት አደረገው” በማለት እግዚአብሔር ኃጢያት የሌለበትን ልጁን የእኛን ኃጢያት እንዲሸከም እንዳደረገው ይመሰክራል።

እንግዲህ እነዚህን የእግዚአብሔር ቃል እውነቶች በፅሞና ከተቀበልን የፋሲካን ትክክለኛ ትርጉም ልንገነዘብና በምስጋና በተሞላ ልብ ልናስበው ልናከብረው፤ በዓመት አንድ ጊዜ ብች ሳይሆን ሁልጊዜ በልባችን የምንከባከበው እውነት ይሆናል።

በቀራንዮ መስቀል ላይ የፈሰሰው የክርስቶስ ደም የማያነፃው ኃጢያት ከቶ የለም። በ1ቆሮ 5፡7 “ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶዋልና” ይላል። የከበደብንንና ለመዘርዘር እንኳን የሚያስፈራንን ኃጢያታችንን ይዘን ወደ እርሱ እንቅረብ፤ እርሱም ይቅር ሊለን ተዘጋጅቷል። “ወደ እኔ የሚመጣውን ከቶ ወደ ወጪ አላወጣውም ” ብሎዋልና (ዮሐ. 6፡37)። እንዲሁም በኢሳ 1፡18 “ኑ እና እንወቃቀስ ይላል እግዚአብሔር ኃጢያታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደአመዳይ ትነፃለች እንደ ደምም ብትቀላ እንደባዘቶ ትጠራለች”።

ፋሲካችን ክርስቶስ የተሰቃየው፣ የተሰቀለው፣ የሞተውና የተነሳው ስለ እኔና ስለ እናንተ ነው። የምህረትና የዘለዓለም ህይወት ጥሪ በፊታችን ተዘርግቷል፣ በእምቢተኝነታችን ካልሆነ በስተቀር የምንጠፋበት ምንም ምክንያት የለም። “እንግዲህ ንቃ ንሰሀም ግባ” (ራዕ 3፡19) በሚለው መሠረት ይህንን ከጥሪዎች ሁሉ በላይ የሆነውን ጥሪ ሰምተንና ተቀብለን ከኃጢያት ሸክማችን ነፃ ወጥተን ለተዘጋጀልን ለዘለዓለም ህይወት እንድንዘጋጅ አሁን በእምነት ወደ እርሱ እንቅረብ።

ፓ/ር አገኘሁ ወንድም


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *