giziew.org

ጲላጦስ

ጲላጦስም አይሁድን፦ እነሆ ንጉሣችሁ አላቸው። እነርሱ ግን፦ አስወግደው፥ አስወግደው፥ ስቀለው እያሉ ጮኹ።
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ሊነጋ ሲል … አርብ። የአይሁድ ሸንጎ አባላትና ካህናት እስረኛቸው የሱስን ይዘው ወደ ጲላጦስ መኖሪያ ሄዱ። ሮማዊው ገዥ ፍርድ ለመስጠት ከተኛበት ሲቀሰቀስ የተለየ ቀን ይገጥመኛል ብሎ አልጠበቀም። ግትርና ጨካኝ ዳኛ እንደነበረ ይነገርለታል።1

የዚያ አርብ ባለጉዳዮች በፋሲካ በዓል ምክንያት ላለመርከስ ብለው ወደ ፍርዱ አዳራሽ መግባት ስላልፈለጉ ጲላጦስ ብርዱን ተቋቁሞ ወደ በረንዳው ወጥቶ አናገራቸው። የሸንጎው አባላትና ካህናት ክሶቻቸውን በጩኸት ያሰማሉ። ካሉት ውስጥ ግን የጲላጦስን ጆሮ የሳበው “ደግሞም እኔ ‘ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ’ ሲል አገኘነው” የሚለው ነው (ሉቃስ 23:1)። የመንግሥት ሹም እንደመሆኑ መጠን ከሥልጣን ጋር የተገናኘ ነገር ያሳስበዋል።

ፊቱ የቆመውን እስረኛ ደጋግሞ አይቶታል። ጲላጦስ ከጦር ሜዳና ከአስተዳደር ልምዱ የተነሳ ብዙ ወንጀለኞችን አይቷል። ፊቱ የቀረበው ተከሳሽ የበደለኛ መልክ የለውም፤ እንዲያውም “‘ንጉስ ነኝ’ ብሏል” የሚለውን ክስ ከመስማቱ በፊት የሱስ ታላቅ ሥልጣን ያለው ግለሰብ ሊሆን ይችላል የሚለው ግምት ሳይፈልገው ተሰምቶታል። እስረኞች ለፍርድ ወደ እርሱ ሲመጡ በጭንቀት ይንቀጠቀጣሉ፤ በተጎሳቆለው የየሱስ ፊት ላይ ግን ፍርሃት የሌለበት ሰላም ጎልቶ ይታያል። ነገሩን በግሉ ማጣራት የፈለገው ጲላጦስ የሱስ ከከሳሾቹ ተለይቶ ወደ ፍርዱ አዳራሽ እንዲገባ ነገረው። በሩ ሲዘጋ የከሳሾቹ ጩኸት ጋብ አለ።

ጲላጦስ የየሱስን ፊት በአክብሮት ተመለከቶ ልቡ ያጓጓውን ጥያቄ አቀረበ — “ንጉሥ ነህ እንዴ? የአይሁድ ንጉሥ ነህ?”

የየሱስ ዓይኖች ጠልቆ የሚገባ ኃይል አላቸው። ሲያይ ላይ ላዩን ብቻ አይደለም። ሰዎችን ሲመለከት ውጪያቸው ያለውን የግብዝነት ሽፋን አልፎ የልባቸውን እውነተኛ ታሪክና ዝንባሌዎች ማንበብ ይችላል። ከዚህ ጥልቅ ዕውቀት ጋር የማይለየው መለኮታዊ ርኅራኄውም ዓይኖቹ ላይ ሁልጊዜ ይታያል። ከየሱስ ጋር በግል የተነጋገሩ ሁሉ ስለ የሱስ ዓይኖች ኃይል መመስከር ይችላሉ።

ጲላጦስ በአትኩሮት የሚመለከተውን የሱስ አየው። ትንሽነቱ ተሰማው። ፍርሃት ወረረው። መዳን ይፈልጋል። ዕረፍት ይፈልጋል ግን ዕርዳታ መጠየቁን አልቻለበትም። የሱሰ የልቡን ትግል አይቶ አዘነለት። ደግነት ባለሰለሰው ድምጽ እንዲህ አለው፤ “ይህ ሐሳብ የራስህ ነው? ወይስ ሌሎች ስለ እኔ የነገሩህ?” (ዮሐ 18፦34)።

ጲላጦስ ግራ ገባው። ለካስ ፍርድ ቤቱ ድረስ የመጣው እስረኛ ሕይወቱን ካጨለመው መንፈሳዊ ደዌ ሊያድነው ይችላል። ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ ሆነበት። ይሁዳ በሮም ግዛት ሥር ናት፤ ጲላጦስ በሠንሠለት በታሰረው የሱስ ላይ ሊፈርድ ተቀምጧል። አሁን ነገሩ ሲበራለት ግን የሮሙ ገዢ በሕይወት እስራት ተቆልፎ ከአይሁዱ እስረኛ መፍትሄ መጠየቅ ሊያስፈልገው ሆነ።

ነፍሱ ለነፃነት ታገለች። ተራ የነበረው አርብ ቀን ድንገት የሕይወቱ ጥያቄዎችና ችግሮች የሚፈቱበት ቀን ወደ መሆን አዘንበለ። ነገሩን በፍጥነት አሰላው፤ የሱስ የያዘው መፍትሔ በሌላ መንገድ ቢመጣ ለውሳኔ ይቀል ነበር። ይህ የመዳን አጋጣሚ ከኑሮው ጋር ባልተነካካ መንገድ ለምን አልመጣም? ይህንን እስረኛ የሕይወቱ መሪ ቢያደርገው እብደት ነው፤ ሰው ምን ይለዋል? ሥልጣኑን አሰበ። ይህን ሥልጣን ለማግኘት ያለፈበት ውጣ ውረድ ታወሰው። በአይሁድ ግዛት ያለውን ፖለቲካዊ አለመረጋጋት አሰበ፤ በየሱስ ጉዳይ ላይ አይሁዶች የሚፈልጉትን ብያኔ ባያገኙ በቄሣር ፊት እንደሚከሱት ያውቃል።

“ጲላጦስም መልሶ፣ ‘እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወደ እኔ የላኩህ የራስህ ወገኖችና የካህናት አለቆች ናቸው፤ ለመሆኑ ምን አድርገህ ነው?’ አለው” (ዮሐ 18:35)። ጲላጦስ ትዕቢቱን ማሸነፍ አቃተው። የነፍሱን ዘላለማዊ ፍላጎቶች አፍኖ ወደ ፍርድ ወንበሩ ተመልሰ። ከፈጣሪው በላይ ለመሆን ፈለገ። የንግግሩ ትርጉም እንዲህ ነው፤ “እኔኮ አይሁዳዊ አይደለሁም፤ ሮማዊ ነኝ። አንተ ደግሞ ወደኔ የመጣኽው ለፍርድ ነው። ቦታችንን አንርሳ።”

ታላቁ የዕድል በር እየተዘጋ ነው። ጲላጦስ ልቡን ለዓለም ቢሸጥም አምላክ ግን አልተወውም። ትግሉ ቀጠለ። የሱስ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም” አለው (ዮሐ 18:35)። የሰማዩን መንግሥት ውበት አሳይቶ በምድር ሥልጣን እንዳይታለል በጥበብ መከረው። የጲላጦስ ሚስት የሱስን በህልም አይታ የተሳሳተ ፍርድ እንዳይሰጥ አስጠነቀቀችው። በቀኝና በግራ የየሱስን መለኮታዊ ማንነት የሚጠቁሙ ምልክቶች በፍጥነት ከበቡት። እውነት ፊት ለፊቱ ቆሞ አየው፤ ከእውነት ከሆነ ድምፁን መስማት እንደሚችል የሱስ ሲነግረው “እውነት ምንድነው?” ብሎ ጠየቀው። መልሱን ለመስማት ግን አልታገሰም። የየሱስን ከሳሾች ለማስተናገድ ወደነበሩበት ተመለሰ።

እንደ አወጣጡ ግን አልገፋም፤ ጲላጦስ አመነታ፤ በየሱስ ጉዳይ ላይ ትክክለኛ ፍርድ መስጠት አቃተው። እውነትን ካየና ካወቀ በኋላ ለእውነት የመቆሙ ዋጋ ከጠበቀው በላይ ሆነበት። ከየሱስ ለመገላገል ብሎ ወደ ሄሮድስ ላከው። የሱስ ግን ለፍርድ ተመለሶ ወደ ጲላጦስ መጣ። ከባድ ቀን–ከባድ አርብ ሆነበት። ንፁህ ሰው መሞት የለበትም። ምን ያድርግ ጲላጦስ? የሱስን ምን ያድርገው? ቢያስገርፈውስ? ከሳሾቹ ይረኩ ይሆን?

ጲላጦስ ለአይሁዶች በዓመት አንድ እስረኛ ይፈታ ነበር። ያንን አጋጣሚ ተጠቅሞ የሱስን ቢያስፈታውስ? ጲላጦስ ሥልጣንና ዝናውን ይዞ የሱስን ለማስተናገድ ሞከረ፤ ለብዙ ሰዓታት ለውሳኔ ሲንገዳገድ ቆየ። ሃቀኛ ፍርድ ሳይሰጥ ሃቀኛ ለመሆን ተመኘ። በመጨረሻም “ከዚህ ሰው ደም ንፁህ ነኝ። እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት” የሚል አደናጋሪ ነገር ተናግሮ እጆቹን ታጠበ።

ከዚያች ቀን–ከዚያች አርብ በኋላ ጲላጦስ ሰላም አጣ። ከሮምና ከአይሁዶች ጋር በሰላም ለመኖር ብሎ የሰላምን ጌታ አሳልፎ ለሞት የሰጠው ጲላጦስ የተረጋጋ ዕንቅልፍ መተኛት አቃተው። የሱስን ሊረሳው አልቻለም። እንዴት ይርሳው? የሱስ እንዴት ይረሳል? በህልሙ ወደ ፍርድ አዳራሹ ተመልሶ የሱስን ይፈልገዋል። ቀን ሃሳቡ ይበታተናል፤ ይጨነቃል። የምግብ ፍላጎቱ ጠፋ፤ በማያፈናፍን የቁጭት ማነቆ ውስጥ ገባ። ኑሮው ጣዕም አጣ። የሱስን እንዴት ይርሳው?

መጨረሻው አላማረም፤ የሱስ ከተሰቀለ ጥቂት ዓመታት በኋላ ጲላጦስ ራሱን ገደለ።2

___________________________

1 Philo of Alexandria, the Embassy to Caligula, pp. 299-305

2 Eusebius of Caesarea, Pontius Pilate. Encyclopedia Britannica

ድርባ ፈቃዱ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *