አስጨናቂው የዚህ ምድር ኑሮ ሰዎችን ከሰብዓዊ ባህርይ በማስወጣት ሊታሰብ በማይችል የሕይወት መስመር ውስጥ ሲከታቸው ይስተዋላል። “የቸገረው እርጉዝ ያገባል፤ ጫን ያለበትም እመጫት” እንደሚባለው፤ ሰው ሲቸግረው፣ ሲጨንቀው፣ መግቢያ መውጫው ሲጠፋበት፤ የኑሮ ማዕበል ሲያላጋው፤ ወጀቡ ሊደፍነው ሲደርስ አድርግ የተባለውን ብቻ ሳይሆን ያልተጠየቀውንም ለመፈጸም ብዙ ርቀት ይሄዳል። ጠንቋይ፣ አዋቂ፣ ወዘተ ቤት በመሄድ፤ ገብር የተባለውን በመገበር ከችግሩ ለመላቀቅ፤ ሸክሙን ለማራገፍ ሄዶ ሌላ ችግር፣ ሌላ ሸክም ተሸክሞ ይመጣል። የፈለገው ቢሳካለት እንኳን እንዴት እንዳገኘው ስለሚያውቅ በአንድ በኩል ያዝኩት ያለውን መልሶ እንዳያጣው በሌላ ደግሞ እንዴት እንዳገኘው ሰዎች እንዳያውቁበት ለመሸፈን በሚያደርገው የሚከሰተው የኅሊና ጭንቀት ሌላ ዕረፍት የሚያሳጣ ጉዳይ ይሆናል። ይህም “መፍትሔ” የሚባለውንም አግኝቶ እንኳን በማያቋርጥ የችግር አዙሪት ውስጥ እንደሚገባ የሚሳይ ነው።
ወጣቱ ልጅ አንድ አዋቂ ነው የሚባል ሰው ዘንድ ሄዶ “የወደፊት ሕይወቴ ምን እንደሆነ ለማወቅ ፈልጌ ነው” ይላል። ጠንቋዩም “ሠላሳ ዓመት እስኪሞላህ በድህነት፣ በስቃይና በመከራ ትኖራለህ” ይለዋል። ልጁ 29ኛው ዓመት ላይ ነበረና አንድ ዓመት ነች የቀረችን በሚል ተደስቶ “ከዚያስ፤ ከ30ኛው ዓመት በኋላ፤ ሕይወቴ ምን ይመስላል?” በማለት በተስፋ ሲጠይቅ “አዋቂው” መልሶ “ከዚያማ ችግርህን ትለምደዋለህ” በማለት መለሰለት።
በዚህ ምድር ሳለን ችግር ቢያጥቡት እንደማይጠራ ሽንፍላ ነው። አበቃ፣ ከችግር ነጻ ሆንሁ የምንልበት ዘመን ሳይኖር ነው የዚህች ምድር ሕይወታችንን የምናጠናቅቀው። በተለያዩ መንገዶች ለችግሮቻችን ማቃለያ ያገኘን ቢመስለን እንኳን የችግር አዙሪት ግን አይፋታንም። መፍትሔ ችግርን የሚወልድ እየሆነ በመቀጠል ዕረፍት ዓልባ ሕይወት በሁሉም የኑሮ ዕርከን ላይ የሚገኝ ሰው ነባራዊ እውነታ ነው። ድሃው መፍትሔ ዓልባ ሕይወት የሚኖር ይመስለዋል። ብዙ ሃብት ያካበተውን ደግሞ ችግር ዓልባ ኑሮ የሚኖር ቢመስለንም ሌሎች በርካታ ሃብት ወለድ ችግሮች ሰንገው እንደያዙት እንዘነጋለን። በጣም ጥቂቶች ግን በማግኘትም ቢሆን በማጣት ሲቅበዘበዙ አይታዩም። ምሥጢሩ ምንድነው ብለን ብንጠይቅ፤ ምላሹ መስከን፣ መረጋጋትና ማረፍ ሆኖ እናገኘዋለን።
በአሁኑ ጊዜ በባዕድ አምልኮነት የምናውቀው ማጭበርበርና ጥንቆላ በክርስትና ስም መልኩን ቀይሮ የወቅቱ እውነታ እየሆነ መምጣቱ እጅግ የሚረብሽ ነው። በአሠራሩ ከጥንቆላ በምንም ያልተለየው የዘመኑ የብልጽግና ወንጌልና የሃሰተኛ ነቢያት፣ ሐዋርያትና መሰል ግለሰቦች ተግባር ብዙዎችን እያታለለ ያለው በእግዚአብሔር ስም የሚካሄድ በመሆኑ ነው። አንዳንዴም በረቀቀና በተጠና ሥልት ለሰዎች ችግር ቅጽበታዊ ምላሾች መሰጠታቸው ሌላው ማሳሳቻ ነው። ወደ እነዚህ ቦታዎች የሚሄደው ሕዝብ አገኘሁ በሚለው ነገር እንኳን ተማምኖ ለመቀመጥና በሕይወቱ ለመርካት እያቃተው ደጋግሞ ወደተለያዩ ቦታዎች ለተመሳሳይ ተግባር ሲጎርፍ ይስተዋላል። ዕረፍት እና ሰላም “በአዋቂ” አይመጣም። የብልጽግና ወንጌል አስተምህሮ፣ የዘመናችን “ነቢያት” እና “ሐዋርያት” ሳይሆኑ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ብቻ ነው ዕረፍትን የሚሰጠን።
ጌታችን ለደቀመዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፤ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም” (ዮሐንስ 14፡27)። በእግዚአብሔር ላይ የማይነቃነቅ፣ የተተከለ፣ የጸና ሕይወት የምትመራ ነፍስ እንደ ኢዮብ “ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤ ነገር ግን መንገዴን በፊቱ አጸናለሁ” ትላለች (ኢዮብ 13፡15)።
ሸክም የሚቀለው እንደኛው ሰው ወደ ሆኑ ደካማ ፍጡራን በመሄድ ሳይሆን እግዚአብሔርን በማወቅና በእርሱ ላይ ፍጹም በመተማመን ነው። እርሱም እንዲህ ይላል፤ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” (ማቴዎስ 11፡28-30)።
ጥበበሥላሴ መንግሥቱ