giziew.org

“ጌታ ተነስቷል!”

"ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው፦ ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም።"
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ያለው ሌሊት ቀስ በቀስ ሊነጋ ተቃረበ። ጎህ ከመቅደዱ በፊት ያለው ከባድ የጨለማ ሰዓት ደረሰ። እስከዚያ ሰዓት ድረስ ክርስቶስ በጠባብዋ መቃብር ውስጥ እንደ እስረኛ ሆኖ ቆየ። በዚያ ሰዓት የመቃብሩ በር የተዘጋበት ትልቅ ድንጋይና ማሸጊያው ማኅተም እንዳለ ሲሆን የሮማውያን ወታደሮችም በዘብ ጥበቃ ሥራቸው ላይ ነበሩ። እንደዚሁም በዓይን የማይታዩ የርኩስ መንፈስ ሠራዊት የመቃብሩን ቦታ ከብበው ይጠብቁ ነበር። የሚቻለው ቢሆን ኖሮ ሰይጣን የክህደት ሠራዊቱን በማስተባበር የእግዚአብሔርን ልጅ በመቃብር ውስጥ ለማስቀረት መቃብሩን ለዘላለም ታሽጎ እንዲኖር ለማድረግ ይፈልግ ነበር። ነገር ግን ከሰይጣን ሠራዊት የበለጠ ኃይል ያላቸው የሰማይ መላእክት የህይወት ጌታን ለመቀበል በመቃብሩ ዙሪያ ተሰበሰቡ።

“እነሆ ታላቅ  መናወጥም ሆነ። የእግዚአብሔር መልክተኛ ከሰማይ ወርዷልና።” ይህ መልአክ የእግዚአብሔርን ግርማ ሞገስ ተጎናፅፎ ከሰማይ በወጣ ጊዜ የእግዚአብሔር የክብሩ ብርሃን ከፊት ለፊቱ እያበራ ይመራው ነበር። “የመልአኩ ፊት እንደ መብረቅ ያበራ ነበር፣ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። ጠባቂዎቹ መልአኩን ከመፍራት የተነሳ በመንቀጥቀጥ እንደ በድን ሆኑ።”

ካህናትና ሹማምንት ሆይ! የዘበኞቻችሁ ኃይል የት ደረሰ? የሰውን ኃይል ፈርተው የማያውቁት ጀግና ወታደሮች ጦርና ጎራዴ በሌለበት ጦርነት እንደተማረኩ ሆኑ። እነዚያ መቃብሩን ለመጠበቅ የተመደቡ ወታደሮች ያዩት ሟች የሆነ የሰብአዊ ጦረኛ ፊት ሳይሆን ከእግዚአብሔር ሠራዊት መካከል እጅግ በጣም ኃያል የሆነውን መልአክ ፊት ነው። ይህ የእግዚአብሔር መልእክተኛ የሰይጣንን (ሰይጣን ከሰማይ ከመውደቁ በፊት የነበረውን) ማዕረግ የወረሰ ነው። በቤተልሔም ኮረብታዎች ላይ የክርስቶን ልደት ያበሰረውም እርሱ ነው። ይህ መልእክተኛ በቀረባት ጊዜ መሬት ተናወጠች፣ የሰይጣን ሰራዊትም ሸሹ። በመቃብሩ በር ላይ የነበረውን ድንጋይ ባንከባለለው ጊዜ መላው ሰማይ ወደ ምድር የወረደ ይመስል  ነበር። ወታደሮቹ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ያን ትልቅ ድንጋይ እንደ ጠጠር ሲወረውረው ተመለከቱ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ! አባትህ ይጠራሀል ውጣ እያለ ሲጮኽ አዳመጡ። ወዲያውኑ የሱስ ከመቃብር ሲወጣ ከማየታቸውም ሌላ በተከፈተው መቃብር ላይ ሆኖ “እኔ ነኝ ትንሳኤ ህይወትም፣” ብሎ ሲናገር ሰሙት። የሱስ ግርማ ሞገስ ተጎናፅፎ ከመቃብር በወጣ ጊዜ የመልአክ ሠራዊት በአክብሮት እየሰገዱና የውዳሴ መዝሙር እየዘመሩ ተቀበሉት።

የሱስ ህይወቱን አሳልፎ በሰጠበት ሰዓት መሬት ተንቀጥቅጣ ነበር፣ እንደዚሁም ህይወቱን በድል አድራጊነት ባስመለሰበት ሰዓት መሬት ተንቀጠቀጠች። ሞትንና መቃብርን ያሸነፈው ጌታ በድል አድራጊነት ከመቃብር በወጣ ጊዜ መሬት ተንቀጠቀጠች፣ የመብረቅ ብልጭታ ታየ፣ የነጎድጓድ ድምፅም ተሰማ። ጌታ የሱስ ወደዚች ዓለም ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ  ምድር ብቻ ሳትሆን ሰማይ ጭምርም ይናወጣል፤ “ምድር ራስዋ እንደ ሰከረ ሰው ትንገዳገዳለች፣ በአውሎ ነፋስ እንደተገፋ ጎጆም ትናወጣለች”፤ “ሰማይም እንደ ብራና ተጠቅልሎ ይወገዳል”፤ “ፍጥረት ሁሉ በእሳት ተቃጥሎ ይጠፋል። ምድርና በእርስዋ ላይ ያለው ነገር ሁሉ ይቃጠላል”፤ ”እግዚአብሔር ግን የሕዝቡ መጠጊያ (ተስፋ) ነው። ለእስራኤልም ልጆች ኃይል ነው” (ዕብ. 12፡26፤ ኢሳ. 24፡20፤ 34፡4፤ 2ጴጥ. 3፡10፤ ኢዮኤል 3፡16)።

የሱስ በሞተ ጊዜ ወታደሮቹ መሬቷ በእኩለ ቀን በጨለማ ስትሸፈንና እንደዚሁም በትንሳኤው ጊዜ መላእክት ሌሊቱ እንደ ቀን እንዲያበራ ሲያደርጉ አይተዋል፤ በተጨማሪም የሰማይ ነዋሪዎች አንተ የሰይጣንንና የጨለማን ኃይል ያሸነፍህ፣ ሞትንም ድል ያደረግህ ነህ እያሉ ለክርስቶስ በታላቅ ደስታ በድል አድራጊነት ስሜት ሲዘምሩለት ሰምተዋል። ሮማውያን ወታደሮች ክርስቶስ በክብር ከመቃብር ሲወጣ አይተዋል። ከጥቂት ጊዜ በፊት ባፌዙበትና በተሳለቁበት ጌታ ፊት ላይ ዓይኖቻቸውን ተክለው ተመለከቱ። ይህን ባለግርማ ሞገስ ፊት ባዩ ጊዜ በፍርድ ቤቱ አዳራሽ ያዩትና የሾህ አክሊል የደፉበት እስረኛ ትዝ አላቸው። በደረሰበት የጭካኔ ግርፋት ምክንያት ሰውነቱ ተላልጦ ያለ አንዳች ማጉረምረም በሄሮድስና በጲላጦስ ፊት ቆሞ የነበረው እርሱ መሆኑን አስታወሱ። በመስቀል ላይ በምስማር ተቸንክሮ ሳለ ካህናቱና ሹማምንቱ ከመጠን በላይ በመደሰት “ሌሎችን አዳነ ራሱን ግን ማዳን አይችልም፣” (ማቴ. 27፡42) እያሉ ራሳቸውን የነቀነቁበት እርሱ መሆኑን አወቁ። በአዲሱ የዮሴፍ መቃብር ውስጥ የነበረውም እርሱ ራሱ ነው። በመለኮት አዋጅ  ከመቃብር ግዞት ነፃ ስለወጣ በመቃብሩ ላይ የነበረው ግዙፍ ተራራ ሊያስቀረው አልቻለም።

ሮማውያኑ ወታደሮች መላእክቱንና ባለ ግርማ ሞገሱን አዳኝ ባዩ ጊዜ ህሊናቸውን ስተው በመውደቅ እንደ በድን ሆኑ። ይህ ሰማያዊ ሠራዊት ከዓይናቸው እንደተሰወረ ከወደቁበት ቦታ ተነስተው እየተርበተበቱ በሩጫ ወደ አትክልቱ በር ሄዱ። እንደ ሰከረ ሰው እየተንገዳገዱ ወደ ከተማው ሄደው ላገኙት ሁሉ የደረሰባቸውን አስገራሚ ነገር ተናገሩ። እነርሱ ቀጥታ ወደ ጲላጦስ ለመሄድ አስበው ነበር፣ ነገር ግን የአይሁድ መሪዎች ወሬውን ሰምተው ስለነበር ወታደሮቹ መጀመሪያ ወደ እነርሱ እንዲመጡ ላኩባቸው። ወታደሮቹ ፊታቸው ገርጥቶ በፍርሀት ይንቀጠቀጡ ስለነበር ክርስቶስ ከሞት የመነሳቱ ታሪክ በፊታቸው ላይ ይነበብ ነበር። ወታደሮቹ ሌላ ነገር ለማሰብ ወይም ለማውራት ጊዜ ስላልነበራቸው ያዩትን ሁሉ አንድም ሳያስቀሩ ተናገሩ። ጭንቀት በተሞላበት አነጋገር የተሰቀለው የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ መልአኩ የሰማይ ባለግርማ፣ የክብር ንጉሥ እያለ ሲጠራው ሰምተናል አሉ።

የካህናቱ ፊት እንደ ሬሳ ፊት ሆነ። ቀያፋ ለመናገር ቢሞክርም ከንፈሩ ተንቀሳቀሰ እንጂ የተሰማ ድምፅ አልነበረም። ወታደሮቹ ታሪኩን ተናግረው እንዳበቁ ከሸንጎው አዳራሽ ሊወጡ ሲሉ አንድ ድምፅ እንዲቆዩ ነገራቸው። ቀያፋ እንደ ምንም ብሎ ለመናገር ስለቻለ ቆዩ፣ ያያችሁትን ለማንም አትናገሩ አላቸው።

ወታደሮቹ “እኛ ተኝተን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት፣” የሚል የሀሰት ሪፖርት እንዲያቀርቡ ነገራቸው። ይህን በማድረጋቸው ካህናቱና ሹማምንቱ ራሳቸውን ትዝብት ላይ ጣሉ። ወታደሮቹ እንዴት ደቀ መዛሙርቱ ተኝተን ሳል አስከሬኑን ሰረቁብን ማለት ይችላሉ? ተኝተው ከነበረስ መሰረቁን እንዴት አወቁ? ደቀ መዛሙርቱ የየሱስን አስከሬን መስረቃቸው ከተረጋገጠ መጀመሪያ የሚወነጅሉዋቸው ካህናቱ አልነበሩምን? መቃብሩን ይጠብቁ የነበሩት ዘበኞች ተኝተው ከሆነስ እነርሱን በጲላጦስ ፊት ለመክሰስ የመጀመሪያ የሚሆኑት ካህናቱ አይደሉምን?

ወታደሮቹ በሥራ ላይ እያሉ እንደተኙ ለማስመሰል የቀረበው አሳብ እጅግ አስደነገጣቸው። በዚያን ጊዜ በሥራ ላይ እያሉ ተኝተው መገኘት በሞት የሚያስቀጣ ጥፋት ነበር። ታዲያ ሀሰት በመናገር ህዝቡን አታልለው የራሳቸውን ህልውና ለአደጋ ያጋልጡን? የጥበቃ  ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንቅልፍ በዓይናቸው ሳይዞር በትጋት ሲጠብቁ አላደሩምን? ለገንዘብ ሲሉ ራሳቸውን ቢያታልሉ እንኳ ምርመራውን እንዴት ሊቋቋሙ ይችላሉ?

ካህናቱ ሥጋት ያሳደረባቸው ምስክርነት እንዳይስፋፋ ለማድረግ ሲሉ ጲላጦስም እንደ እነርሱ ወሬው እንዲስፋፋ የማይፈልግ መሆኑን ለወታደሮቹ  አስረድተው ለህይወታቸው ደህንነት ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ቃል ገቡላቸው። በዚህ መሠረት ወታደሮቹ ታማኝነታቸውን በገንዘብ ሸጡ። እነዚህ ወታደሮች አስደናቂ የሆነ የእውነት መልእክት ይዘው ወደ ካህናቱ  መጡ፤ ነገር ግን ገንዘብና በሉ የተባሉትን የሀሰት ሪፖርት ይዘው ተመለሱ።

ይህ በዚህ እንዳለ ጲላጦስ የየሱስን ከሞት መነሳት አስቀድሞ ሰማ። ምንም እንኳን የሱስን እንዲሞት አሳልፎ መስጠቱ በኃላፊነት የሚያስጠይቀው ቢሆንም ጲላጦስ ብዙ ጭንቀት አልተሰማውም። በየሱስ ላይ የፈረደበት ያለፍላጎቱና የርህራሄ መንፈስ እየተሰማው ቢሆንም የየሱስን መነሳት እከሰማበት ጊዜ ድረስ ልባዊ ፀፀት አልተሰማውም ነበር። አሁን ግን ከፍተኛ ፍርሀት ስለተሰማው ከማንም ጋር ላለመገናኘት ሲል ቤቱን ዘግቶ ተቀመጠ። ነገር ግን ካህናቱ ወደ እርሱ ሄደው ራሳቸው የፈጠሩትን የውሸት ታሪክ ከነገሩት በኋላ ወታደሮቹ በጥበቃ ሥራ ላይ ሳሉ ላደረሱት ጥፋት ይቅርታ እንዲያደርግላቸው ለመኑት። ይህን ለማድረግ ከመስማማቱ በፊት ጲላጦስ ዘበኞቹን ጠርቶ በግል አነጋገራቸው። እነርሱም ለደህንነታቸው በመሥጋት አንድም ነገር ሳይደብቁ ስለነገሩት ጲላጦስ ስለደረሰው ነገር ትክክለኛ ግንዛቤ አገኘ። ስለ ጉዳዩ ብዙ ክትትል ባያደርግም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሰላም አልነበረውም።

የሱስ በመቃብር ውስጥ በነበረ ጊዜ ድሉ የሰይጣን ሆነ። ሰይጣን የሱስ እንደገና ህያው አይሆንም የሚል አጉል ተስፋ ነበረው። የክርስቶስ አስከሬን ለእኔ ይገባኛል በማለትና ክርስቶስን እስረኛ አድርጎ ለማስቀረት በመመኘት መቃብሩን በራሱ ዘበኞች አስጠበቀ። ሰማያዊዩ መልእክተኛ በመጣ ጊዜ የእርሱ መላዕክት ሲሸሹ ባየ ጊዜ እጅግ ተናደደ። ክርስቶስ በድል አድራጊነት ከመቃብር ሲወጣ ባየው ጊዜ የእርሱ መንግሥት አንድ ቀን እንደሚፈፀምና እርሱም የኋላ ኋላ እንደሚሞት አወቀ።

ክርስቶስ እንዲሞት በማድረጋቸው የእስራኤል ካህናት የሰይጣን መሣሪያ ስለሆኑ ሙሉ በሙሉ በእርሱ ቁጥጥር ሥር ዋሉ። ሊወጡ ከማይችሉት ወጥመድ ውስጥ ስለገቡ በየሱስ ላይ በከፈቱት ጦርነት ከመግፋት በስተቀር ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም። የየሱስን ከሞት መነሳት በሰሙ ጊዜ ህይወታቸው በአደጋ ላይ እንደሚወድቅ በማወቅ ህዝቡን ፈሩት። ስለዚህ የነበራቸው ብቸኛ ተስፋ የክርስቶስን ትንሳኤ በመካድ የእርሱን አታላይነት ማሳመን ነው። በዚህ መሠረት ወታደሮቹን በገንዘብ ሸነገሉ፣ ጲላጦስንም ዝም አሰኙ። የሀሰት ወሬአቸውን በሰፊው አሰራጩ፣ ይሁን እንጂ ዝም ሊያሰኙዋቸው የማይችሉ ምስክሮች አጋጠሙዋቸው። ብዙ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ከሞት መነሳት ወታደሮቹ የሰጡትን ምስክርነት ሰምተው ነበር። ከክርስቶስ ጋር ከሞት የተነሱ ሰዎችም ምስክርነታቸውንም የሰሙ ግለሰቦች ያዩትንና ሰሙትን ለካህናቱ ነገሯቸው። ካህናቱና ሹማምንቱ የሱስ በመንገድ ላይ ወይም በየመኖሪያ ቤታችን ፊት ለፊት ይመጣብን ይሆን የሚል ሥጋት አስጨነቃቸው። የበር ቁልፍ ወይም መቀርቀሪያ ከእግዚአብሔር ልጅ ሊጠብቃቸው አልቻለም። በፍርድ ቤቱ አዳራሽ ውስጥ “ደሙ በኛ በልጆቻችንም ላይ ይሁን” (ማቴ. 27፡25) ብለው በጮኹ ጊዜ የነበረው አስፈሪ ትዕይንት ቀንም ሌሊትም በፊታቸው ላይ ተደቅኖ ይታያቸው ነበር። ያ ትዕይንት ከኅሊናቸው ሊጠፋ አልቻለም። የሰላም እንቅልፍ ማግኘትም አልቻሉም።

ኃያሉ መልአክ በክርስቶስ መቃብር አጠገብ ሆኖ አባትህ ይጠራሀል የሚል ጥሪ ባሰማ ጊዜ አዳኛችን በህያውነት ባህርዩ ከመቃብር ወጣ። በዚያን ጊዜ “እንደገና መልሼ የምወስዳት ህይወቴን አሳልፌ ለመስጠት ፈቃደኛ ስለሆንሁ አብ እኔን ይወድደኛል። ህይወቴን በፈቃዴ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ የሚወስዳት ማንም የለም። ህይወቴን አሳልፌ ለመስጠትና መልሼም ለመውሰድ መብት (ኃይል) አለኝ”፤ “ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱትና እኔ በሶስት ቀን እሠራዋለሁ” ብሎ የተናገረው ቃል እውነተኛነት ተረጋገጠ” (ዮሐ. 10፡17፤ 18፤ 2፡19)።

በተከፈተው በዮሴፍ መቃብር ላይ ሆኖ የሱስ በድል አድራጊነት “እኔ ነኝ ትንሳኤ ህይወትም” ሲል አውጇል። እነዚህን ቃላት መናገር የሚችል መለኮታዊ ባህርይ ያለው ብቻ ነው። ማንኛውም ፍጡር የሚኖረው በእግዚአብሔር ፈቃድና ኃይል ነው። ማንኛውም ፍጡር አካል የእግዚአብሔር ህይወት ጥገኛ ነው። ከከፍተኛው ሱራፌል እስከ ኢምንቷ ህዋስ ድረስ ያሉት ፍጡር አካላት ሁሉ የህይወት ምንጭ ከሆነው አምላክ ለህይወት የሚያስፈልጋቸውን ነገር ያገኛሉ። ህይወቴን አሳልፎ ለመስጠትና መልሼ ለመውሰድ ኃይል አለኝ ማለት የሚችል ከእግዚአብሔር ጋር የባህርይ አንድነት ያለው ብቻ ነው። ክርስቶስ በመለኮታዊነቱ የሞትን ማሠሪያ የሚበጥስ ኃይል አለው።

ክርስቶስ በሞት ላንቀላፉት ሁሉ የመጀመሪያ ምሳሌ ሆኖ ተነሳ። በካህኑ እጅ ወደላይና ወደታች የሚወዘወዘው እህል ነዶ የክርስቶስ ምሳሌ ነበር፤ በመሆኑም ነዶው በእግዚአብሔር ፊት በሚቀርብበት ቀን ክርስቶስ ከሞት ተነሳ። ይህ ምሳሌያዊ አገልግሎት ለአንድ ሺ ዓመታት ያህል ሲካሄድ ቆየ። ከየእርሻ ማሳው የሚሰበሰበውን የመጀመሪያ የእህል ነዶ ሕዝቡ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይዘው ይሄዱና በእግዚአብሔር ፊት የምስጋና መግለጫ መባ ሆኖ ሲቀርብ ካህኑ ወደላይና ወደታች ያወዛውዘዋል። በማሳው ላይ ያለው የእህል አዝመራ የሚታጨደውና የሚከመረው የመጀመሪያው ነዶ ለእግዚአብሔር ከቀረበ በኋላ ነው። ለእግዚአብሔር የሚቀርበው የመጀመሪያው ነዶ የመላው አዝመራ ምሳሌ ነው። እንደዚሁም ለሚሰበሰበው ትልቅ መንፈሳዊ አዝመራ ምሳሌ ነው። የእርሱ ትንሳኤ የሞቱ ፃድቃን እንደሚነሱ ምሳሌና ማረጋገጫ ነው። “የሱስ ሞቶ እንደተነሳ ካመንን እንዲሁም በየሱስ ያንቀላፉትን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና” (1ተሰ. 4፡14)።

የሱስ ከመቃብር ሲነሳ ብዙ ምርኮኞችን ይዞ ወጣ። ክርስቶስ በሞተ ጊዜ የደረሰው የመሬት መናወጥ የብዙ ሙታንን መቃብር ስለከፈተ በእነዚህ መቃብሮች ውስጥ የነበሩ ሙታን እርሱ በተነሳ ጊዜ አብረው ተነሱ። ከክርስቶስ ጋር የተነሱት ሰዎች የእግዚአብሔር የስራ አጋሮች የነበሩና ስለ እውነት በመመስከር ህይወታቸውን ያሳለፉ ናቸው። አሁን ከሞት ላስነሳቸው ጌታ ምስክር ሆኑ።

ክርስቶስ በአገልግሎቱ ጊዜ ሙታንን አስነስቷል። በናይን ከተማ የምትኖረውን የመበለት ልጅ፣ የምኩራብ አለቃውን ሴት ልጅና አልዓዛርን ከሞት አስነስቷቸዋል። እነዚህ ሁሉ እንደገና ሟቾች ስለነበሩ ለዘላለም የመኖር ባህርይ አልተሰጣቸውም ነበር። ከክርስቶስ ጋር አብረው የተነሱት ግን ዘላለም ህያው ሆኖ ለመኖር ነው የተነሱት። በሞትና በመቃብር ላይ ለተቀዳጀው ድል እንደ ምርኮኛ ሆነው ወደ ሰማይ ተወሰዱ። እኔ አድኛቸዋለሁና ከእንግዲህ የሰይጣን ምርኮኞች አይደሉም፤ የስቃዩ የመጀመሪያው ፍሬዎች እንዲሆኑ ከመቃብር አውጥቼ ሁለተኛ ሞትና ሀዘን ሳያዩ ለዘላለም ከእኔ ጋር እንዲኖሩ አምጥቻቸዋለሁ አለ የሱስ።

እነዚህ ቅዱሳን ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ለብዙ ሰዎች ታዩ፣ ክርስቶስ ከሞት እንደተነሳና እነርሱንም እንዳስነሳቸው መሰከሩ። በእነርሱ ምስክርነት የትንሳኤ እውንነት ተረጋገጠ። እነዚህ ከሞት የተነሱ ቅዱሳን “ከወገኖቻችን መካከል የሞቱት ተነስተው በህይወት ይኖራሉ፣ በድናቸውም እንደገና ህይወት ያገኛል” የሚለው እውነት ለመሆኑ ማስረጃ ናቸው። የእነርሱ ትንሳኤ “ወደ መቃብር የወረዱ ሁሉ ተነስተው በደስታ እልል ይላሉ። የጠል ነጠብጣብ ለምድር ህይወትን እንደሚሰጥ እግዚአብሔርም ከሞቱ ብዙ ጊዜ የሆናቸው ተነስተው በህይወት እንዲኖሩ ያደርጋል” የሚለው ትንቢት እንደሚፈፀም ማስረጃ ነው (ኢሳ. 26፡19)።

ለምዕመናን ክርስቶስ ትንሳኤና ህይወት ነው። ክርስቶስ ህይወት ስለሆነና ህይወትን መስጥት ስለሚችል በኃጢአት የጠፋን ህይወት ይመልሳል። እርሱ ዘላለማዊነትን የመስጠት ሙሉ ሥልጣን አለው። በሰብዓዊነቱ አሳልፎ የሰጣትን ህይወቱን መልሶ በመውሰድ ለሰብዓዊ ፍጡራን ይሰጣታል። “እኔ  ግን የመጣሁት ህይወት እንዲያገኙና የተትረፈረፈ ህይወት እንዲኖራቸው ነው።” “እኔ ከምሰጠው ውሀ የሚጠጣ ለዘላለም ከቶ አይጠማም ምክንያቱም እኔ የምሰጠው ውሀ ለሚጠጣው ሰው ለዘላለም ህይወት የሚፈልቅ ምንጭ ይሆናል።” “ሥጋዬን የሚበላና ደሜንም የሚጠጣ ሁሉ የዘላለም ህይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን ከሞት አስነሳዋለሁ”።(ዮሐ. 10፡10፤ 4፡14፤ 6፡54)።

ለሚያምን ሰው ሞት ከባድ ነገር አይደለም። ክርስቶስ ሞት የአጭር ጊዜ ጉዳይ መሆኑን ይናገራል። “ቃሌን የሚጠብቅ ከቶ አይሞትም”፣ “ሕይወታችሁ የሆነው ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እናንተ ከእርሱ ጋር ትገለጣላችሁ፤ የክብሩም ተካፋዮች ትሆናላችሁ” (ዮሐ. 8፡51፤ ቆላ. 3፡4)።

በመስቀል ላይ “ተፈፀመ!” ተብሎ በጩኸት የተነገረውን ቃል ሙታን ሰምተውታል። ይህ ቃል የመቃብርን ግድግዳ አልፎ በመግባት ያንቀላፉ ሙታንን ቀሰቀሰ። የክርስቶስ ድምፅ ከሰማይ በሚሰማበት ጊዜ ይህ ሁኔታ በድጋሚ ይፈፀማል። የክርስቶስ ድምፅ በመቃብር ውስጥ ስለሚሰማ በክርስቶስ የሞቱ ሁሉ ይነሳሉ። ክርስቶስ ከሞት በተነሳ ጊዜ የተከፈቱ መቃብሮች ጥቂቶች ነበሩ፤ ለሁለተኛ ጊዜ ሲመጣ ግን በእርሱ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ሙታን ሁሉ ክቡርና ዘላለማዊ ህይወት ለመኖር ይነሳሉ። ክርስቶስን ከሞት እንዲነሳ ያደረገው ኃይል የእርሱን ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም ዓለም ከማንኛውም ሥልጣን፤ ኃይልና ስም ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርጋታል።

(ምንጭ፤ “የዘመናት ምኞት”፤ ምዕራፍ 81፤ ጽሁፉ የተመሠረተው ማቴ. 28፡2-4፣ 11-15፣ ተርጓሚ አበበ ብዙነህ)


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *