giziew.org

“ለምን ታለቅሻለሽ?”

የየሱስን አስከሬን የት እንደደረሰ የሚነግራት ሰው ለማግኘት ዞር ብላ ስትመለከት “አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊአለሽ?” የሚል ሌላ ድምፅ ሰማች
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

የሱስ በተሰቀለ ጊዜ በመስቀሉ አጠገብ የነበሩት ሴቶች የሰንበትን ማለፍ ሲጠባበቁ ቆዩ። እነዚህ ሴቶች የየሱስን አስከሬን የሚቀቡበትን ውድ ሽቶ ይዘው ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ጠዋት ቀደም ብለው ተነስተው ወደ መቃብር ቦታ ሄዱ። ተስፋ ቆርጠው ስለነበር የሱስ ከሞት ይነሳል ብለው አላሰቡም። በጉዟቸው ላይ ክርስቶስ የፈፀማቸውን የምህረት ድርጊቶችና የተናገራቸውን አፅናኝ ቃላት እያስታወሱ ይነጋገሩ ነበር። ይሁን እንጂ የሱስ “እንደ ገና ስለማያችሁ ደስ ይላችኋል” ሲል የተናገረውን አላስታወሱም (ዮሐ.16፡22)።

በዚያ ዕለት ወደ ንጋት አካባቢ ስለሆነው ነገር ምንም ዓይነት ግንዛቤ ሳይኖራቸው ተጉዘው መቃብሩ ከሚገኝበት አትክልት ቦታ ለመድረስ ሲቃረቡ “ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጃፍ ማን አንከባልሎ ይከፍትልናል?” ተባባሉ። ሆኖም መቃብሩ የተዘጋበትን ድንጋይ ማንሳት እንደማይችሉ እያወቁ ጉዟቸውን ቀጠሉ። ወደ መቃብሩ የደረሱት የንጋት ጀምበር ገና ሳትወጣ ቢሆንም ድንገት ሳያስቡት በሰማይ ላይ የክብር ብርሃን በራ፤ መሬትም ተንቀጠቀጠች። ወዲያውኑ መቃብሩ የተዘጋበት ድንጋይ እንደተነሳና መቃብሩም ባዶ እንደሆነ አዩ።

ሴቶቹ ወደ መቃብሩ የመጡት ከአንድ አቅጣጫ አልነበረም። ከሁሉ ቀድማ ከመቃብሩ የደረሰችው ማርያም መግደላዊት ስለነበረች መቃብሩ ተከፍቶ ስላየች ይህንኑ ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር በፍጥነት ተመልሳ ሄደች። ማርያም ተመልሳ ከሄደች በኋላ ሌሎቹ ሴቶች ከመቃብሩ ደረሱ። እነርሱ በደረሱበት ሰዓት በመቃብሩ ዙሪያ ብርሃን ይታይ ነበር፣ የየሱስ አስከሬን ግን ከመቃብሩ ውስጥ አልነበረም። በመቃብሩ አጠገብ ትንሽ እንደቆዩ ብቻቸውን እንዳልሆኑ አወቁ። ነጭ ልብስ የለበሰ ጎልማሳ በመቃብሩ አጠገብ ተቀምጦ አዩ። የየሱስን ወዳጆች ላለማስደንገጥ በሰብዓዊ ቅርፅ የተከሰተው ይህ ነጭ ልብስ ለብሶ የታያቸው ጎልማሳ መቃብሩን የከፈተው መልአክ ነው።

በመልአኩ ዙሪያ ያበራ የነበረው ሰማያዊ ክብር ሴቶቹን አስደነገጣቸው። ከፍርሀት የተነሳ ተመልሰው ለመሸሽ ሲሞክሩ መልአኩ “አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትፈልጉ አውቃለሁና፤ እርሱ በዚህ የለም፤ እንደ ተናገረው ተነሥቶአል፤ ኑና ተኝቶበት የነበረውን ቦታ እዩ። አሁንም ፈጥናችሁ ሂዱና ለደቀ መዛሙርቱ፣ ‘ከሙታን ተነሥቶአል’ ብላችሁ ንገሯቸው” በማለት አረጋጋቸው። በድጋሚ ወደ መቃብሩ ውስጥ ሲመለከቱ ሌላ መልአክ በሰው ቅርፅ ሆኖ “ሕያው የሆነውን እርሱን ለምን ከሙታን መካከል ትፈልጋላችሁ? እርሱ ተነሥቶአል! እዚህ የለም፤ ደግሞም በገሊላ በነበረ ጊዜ ምን እንዳላችሁ አስታውሱ፤ ‘የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥ፣ ሊሰቀልና በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ይገባል’ ብሎ ነበርና” የሚል አስደናቂ ዜና ነገራቸው።

ሴቶቹም ተነስቷል! ተነስቷል! በማለት ደጋግመው ጮኹ። አዳኛቸው ህያው እንጂ ሙት ስላልሆነ ሽቶው ከዚያ በኋላ አስፈላጊ አልሆነም። ክርስቶስ ስለ ሞቱ በተናገረ ጊዜ ከሙታን እንደሚነሳ ያለው ሁሉ ትዝ አላቸው። ይህ ለዓለም እንዴት ያለ አስገራሚ ቀን ነበር! “ከዚህ በኋላ ሴቶቹ በፍርሀትና በታላቅ ደስታ ከመቃብሩ በፍጥነት ሄዱ፣ ለደቀ መዛሙርቱም ሊነግሩ ሮጡ”።

መግደላዊት ማርያም ይህን ጥሩ ዜና ስላልሰማች “ጌታን ከመቃብሩ አውጥተው ወስደውታል፣ የት እንዳኖሩት አላውቅም” የሚል አሳዛኝ ዜና ይዛ ወደ ጴጥሮስና ዮሐንስ ሄደች። ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ገስግሰው ከመቃብሩ ደርሰው ሲመለከቱ ማርያም የነገረቻቸው ሁሉ እውነት መሆኑን ተረዱ። የራስ መጠምጠሚያውንና የከፈኑን ጨርቅ ለየብቻው ተጣጥፎ አገኙት፣ የየሱስ አስከሬን ግን ከዚያ አልነበረም። የአስከሬኑ ራስ የተጠመጠመበት ጨርቅና የከፈኑ ጨርቅ በዘፈቀደ የትም ሳይጣሉ በስርዓት ተጣጥፈው ለየብቻቸው ተቀምጠው መገኘታቸው የሱስ መነሳቱን ያመለክታሉ። ዮሐንስም ይህን “አየና አመነ”። ይህ ደቀ መዝሙር የሱስ ከሞት እንደተነሳ የሚናገረውን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል ገና በትክክል አላስተዋለም ነበር፣ አሁን ግን አዳኛችን ስለ ትንሳኤው አስቀድሞ የተናገረውን አስታወሰ።

ጨርቆቹን አጣጥፎ በጥንቃቄ ያስቀመጣቸው ራሱ ክርስቶስ ነበር። ከሰማይ ወደ መቃብር የወረደው ኃያል መልአክና ሌላ አንድ መልአክ በኅብረት የጌታን አስከሬን ሲጠብቁ ከቆዩ በኋላ ኃያሉ መልአክ መቃብሩን ሲከፍተው ሌላው መልአክ ወደ መቃብሩ ገብቶ የሱስ የተገነዘበትን ጨርቅ ፈታው። የከፈን ጨርቁን አጣጥፎ ያስቀመጠው ግን የሱስ ነው። የሰማይ ከዋክብትንና ኢምንትዋን አቶም በሚመራው ጌታ ዘንድ አላስፈላጊ የሚባል ነገር የለም፤ እርሱ በሠራው ነገር ሁሉ ላይ ሥርዓትና ፍፁምነት ይታያል።

ማርያም መግደላዊት ከጴጥሮስና ከዮሐንስ ጋር ወደ መቃብሩ ከሄደች በኋላ እነርሱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሱ እርሷ ግን እዚያው ቆየች። መቃብሩን ወደ ውስጥ እያየች ልቧ በሐዘን ተሞላ። ትኩር ብላ ስትመለከት ሁለቱ መላእክት አንዱ በራስጌ፣ ሌላው በግርጌ ተቀምጠው አየች። መላእክቱም “አንቺ ሴት! ለምን ታለቅሻለሽ?” ብለው በጠየቋት ጊዜ “ጌታዬን ወስደውታል፣ የት እንዳደረጉትም አላውቅም” ስትል መለሰችላቸው።

ይህን ካለች በኋላ የየሱስን አስከሬን የት እንደደረሰ የሚነግራት ሰው ለማግኘት ዞር ብላ ስትመለከት “አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊአለሽ?” የሚል ሌላ ድምፅ ሰማች። እንባ ባፈዘዘው ዓይንዋ ሰው የሚመስል ነገር ስላየች (የመቃብር ቦታው) አትክልተኛ መስሏት “ጌታ ሆይ! አንተ ወስደኸው እንደሆነ የት እንዳደረክኸው እባክህ ንገረኝ፤ እኔ እወስደዋለሁ” አለችው። ይህ የባለፀጋ ሰው መቃብር ለየሱስ መቀበሪያ ለመሆን የሚበዛበት ከሆነ ማርያም ለየሱስ የሚስማማ ማረፊያ ቦታ ለማዘጋጀት ፈቃደኛ ነበረች። ማርያም የየሱስን አስከሬን ለማሳረፍ የፈለገችው ክርስቶስ በቃሉ ከሞት ባስነሳው በአልዓዛር መቃብር ውስጥ ነበር። ያ መቃብር ለጌታዋ መቀበሪያ አይበቃ ይሆን? ለተከበረው ለየሱስ አካል እንክብካቤ ለማድረግ ከሐዘኗ መፅናኛ እንደሚሆናት ግን ተሰማት።

በዚህ ጊዜ የሱስ በተለመደው አነጋገሩ “ማርያም” አላት። የተናገራት ሰው እንግዳ አለመሆኑን በመገንዘብ ዞር ስትል ሕያው የሆነውን የሱስን አየች። ከደስታዋ ብዛት የተነሳ የየሱስ መሰቀል ተዘነጋት። እግሩን በእጆችዋ ጠምጥማ ለመያዝ እንዳሰበች ሁሉ ወደ እርሱ ዘልላ በመቅረብ “ረቡኒ!” አለች። የሱስ ግን እንዳትቀርበው በእጁ ምልክት እየሰጠ “ገና ወደ አባቴ አልወጣሁምና አትያዥኝ (አታዘግዪኝ)፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄጂና እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ እወጣለሁ ብሏል ብለሽ ንገሪያቸው” አላት። ማርያምም ይህን የደስታ መልእክት ይዛ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሄደች።

የሱስ የከፈለው መስዋዕት በአባቱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘ ማረጋገጫ ሳያገኝ የሕዝቡን ምስጋና መቀበል አልፈለገም። ስለዚህ ወደ ሰማይ ወጥቶ ስለ ሰዎች ኃጢአት የከፈለው መስዋዕትነት በቂ እንደሆነና በእርሱም ደም የሰው ዘር ሁሉ የዘላለም ህይወት እንደሚያገኝ ከአባቱ ማረጋገጫ አገኘ። እግዚአብሔር አብ ንስሐ የገቡና ታዛዥ የሆኑ ሰዎችን ሁሉ ለመቀበልና እንደ ልጁ ለመውደድ ከክርስቶስ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አፀደቀ። በዚህ ቃል ኪዳን መሠረት ክርስቶስ ሥራውን ሙሉ በሙሉ እንዲያጠናቅቅና ሰውን “ከጥሩ ወርቅ ይልቅ የተወደደ … ከኦፊር ወርቅም ይልቅ እንዲከበር” አደርገዋለሁ ሲል የገባውን ቃል እንዲፈፅም ተወሰነ (ኢሳ. 13፡12)። የህይወት መስፍን ለሆነው ለየሱስ ክርስቶስ በሰማይና በምድር ሁሉ ላይ ሙሉ ሥልጣንና ኃይል ከተሰጠው በኋላ በኃጢአት ዓለም ውስጥ ለሚኖሩት ተከታዮቹ ኃይልና ክብርን ለማካፈል ተመልሶ መጣ።

አዳኛችን ለቤተክርስቲያኗ ስጦታዎችን ለመረከብ በእግዚአብሔር ፊት በቀረበበት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ባዶውን መቃብር እያስታወሱ ያለቅሱ ነበር። በሰማይ ደስታና ሐሴት በሰፈነበት ቀን ደቀ መዛሙርቱ በጥርጣሬ መንፈስ የተሞሉበትና ግራ የተጋቡበት ቀን ነበር። ሴቶቹ የነገሯቸውን አለማመናቸው እምነታቸው ምን ያህል ደካማ እንደነበር ያሳያል። ስለ ክርስቶስ ትንሳኤ የደረሳቸው ዜና እነርሱ ከጠበቁት የተለየ ስለሆነባቸው ማመን አቃታቸው። የሰዱቃውያንን ትምህርትና ሳይንሳዊ ነው ብለው የሚያስተምሩትን ፅንሰ ሀሳብ ብዙ ጊዜ ከመስማታቸው የተነሳ ስለ ትንሳኤ የነበራቸው አስተያየት የደበዘዘ ነበር። ከሞት መነሳት ምን ማለት እንደሆነ በትክክል ስላላወቁ መቀበል አቃታቸው። (ሰዱቃውያን በሙታን ትንሣኤ አያምኑም ነበር)።

መላእክት ለሴቶቹ “አሁንም ሂዱ ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስ ከዚህ በፊት ኢየሱስ እንደነገራችሁ እርሱ ወደ ገሊላ ቀድሞአችሁ ይሄዳል፤ በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ንገሩአቸው” አሏቸው። እነዚህ መላእክት ክርስቶስ በምድር ላይ ባሳለፈው ህይወት ከመነሻው እስከ መድረሻው አብረውት የነበሩ ጠባቂ መላእክት ናቸው። መላእክቱ በክርስቶስ ላይ የተካሄደውን ምርመራና በኋላም የደረሰበትን ስቅላት አይተዋል። የሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸውን እንደሰሙ እነርሱ ለደቀ መዛሙርቱ የላኩት መልእክት ያስረዳል። ደቀ መዛሙርቱ ይህ ዓይነት መልእክት ሊመጣላቸው የሚችለው ከሞት ከተነሳ ጌታቸው መልዕክተኞች ብቻ መሆኑን አውቀው መልእክቱን አምነው መቀበል ይገባቸው ነበር።

“ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስ … ንገሩአቸው” አሉ መላእክቱ። ጴጥሮስ ክርስቶስ ከሞተበት ጊዜ አንስቶ በፀፀት ቅስሙ ተሰብሮ ሰንብቶ ነበር። ስለ ጌታው የተናገረው አሳፋሪ ክህደትና አዳኛችን በፍቅርና በጭንቀት መንፈስ እንዴት እንደተመለከተው ከፊቱ ላይ ተደቅኖ ይታየው ነበር። ከደቀ መዛሙርቱ ሁሉ የበለጠ የተሰቃየው ጴጥሮስ ነው። መላእክቱ የእርሱን ስም ጠቅሰው መናገራቸው ለጴጥሮስ ፀፀቱ ተቀባይነት እንዳገኘና ኃጢአቱ ይቅር እንደተባለለት ማረጋገጫ ሆነለት።

“ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስ ከዚህ በፊት ኢየሱስ እንደነገራችሁ እርሱ ወደ ገሊላ ቀድሞአችሁ ይሄዳል”። የሱስን የካዱት ሁሉም ደቀ መዛሙርት ናቸው። እርሱ ግን ችላ ብሎ ስላልተዋቸው ከእርሱ ጋር እንዲገናኙ ለሁሉም ጥሪ ላከላቸው። ማርያም መግደላዊት ጌታን እንዳየችው በነገረቻቸው ጊዜ በገሊላ እንደሚገናኛቸው የተላከውን መልእክት ጨምራ ነግራቸው ነበር። ይኸው መልእክት ለሶስተኛ ጊዜ ተልኮላቸዋል። የሱስ ከአብ ዘንድ ደርሶ ከተመለሰ በኋላ ለሌሎቹ ሴቶች ሲገለጥ፤ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። እነርሱም ወደ ኢየሱስ ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት። ኢየሱስም፣ “አትፍሩ፤ ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው፤ በዚያ ያዩኛል” አላቸው።

ከትንሳኤው በኋላ በምድር ላይ የነበረው የክርስቶስ ሥራ ለደቀ መዛሙርቱ የነበረው ፍቅርና ርህራኄ እንዳልተቀነሰ እነርሱን ማሳመን ነው። ህያው አዳኛቸው መሆኑን ለማሳመን፣ እርሱ የመቃብርን ሠንሠለትና የእግር ብረት በሞቱ ስለሰበረ ጠላት የሆነው ሞት ከእንግዲህ ሊያገኘው እንደማይችል ለማሳወቅ፣ ተወዳጅ መምህራቸው በነበረ ጊዜ ለእነርሱ የነበረው ፍቅር እንዳልተቀነሰ ለመግለፅ፣ ሲል በተደጋጋሚ ጎበኛቸው። ከእርሱ ጋር በፍቅር ገመድ አጥብቆ ሊያስራቸው ስለፈለገ (ሴቶቹን) “ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው” አለ።

ደቀ መዛሙርቱ ላይ ከችግር ላይ ችግር የተደራረበባቸው ይመስል ነበር። ከሳምንቱ በስድስተኛው ቀን ጌታቸው ሲሞት አዩ፣ በሚቀጥለው ሳምንት በመጀመሪያ ቀን የጌታ አስከሬን ጠፋባቸው፣ እንዲያውም ህዝቡን ለማታለል ሲሉ አስከሬኑን ሰርቀዋል የሚል ውንጀላ ተሰነዘረባቸው። በእነርሱ ላይ እየተጠናከረ የመጣውን የሐሰት ውንጀላ ሁሉ ለማስተባበል እንደማይችሉ ስለተሰማቸው ተስፋ ቆረጡ። የካህናቱ ጠላትነትና የሕዝቡ ቁጣም አስፈራቸው። ስለዚህ ችግር ባጋጠማቸው ጊዜ ሁሉ ይረዳቸው የነበረው የሱስ ከእኛ ጋር በኖረ ብለው ተመኙ።

ብዙውን ጊዜ “እኛ ግን እስራኤልን የሚያድን እርሱ ነው ብለን ተስፋ አድርገን ነበር” እያሉ በመደጋገም ይናገሩ ነበር። ብቸኝነት እየተሰማቸውና ልባቸው እየታወከ ሳለ የሱስ “እንግዲህ ይህ ሁሉ ነገር በእርጥብ እንጨት ላይ የሚደረግ ከሆነ በደረቅ እንጨት ላይማ ምን ይደረግ ይሆን?” ሲል የተናገረውን አስታወሱ (ሉቃ. 24፡21፤ 23፡31)። በተወዳጁ መምህራቸው ላይ የደረሰው ነገር በማንኛውም ሰዓት በእነርሱ ላይ እንደሚደርስ ስላወቁ በሰገነት ውስጥ ተሰብስበው በሩን በጥብቅ ዘግተው ተቀመጡ።

ይህ ሁሉ ነገር በሆነበት ጊዜ የጌታን መነሳት አውቀው መደሰት በቻሉ ነበር። ማርያምም በአትክልቱ ቦታ የሱስ በአጠገቧ እያለ አለቀሰች። ዓይንዋ በእንባ ተሸፍኖ ስለነበረ የሱስን ማወቅ አልቻለችም። እንደዚሁም የደቀ መዛሙርቱ ልብ በሐዘን ተሞልቶ ስለነበር፤ የመላእክትን መልእክት ወይም የራሱን የክርስቶስን ቃል ማመን ተሳናቸው።

በሐዘን ምክንያት አንገታቸውን የደፉ ሁሉ ቀና እንዲሉ፣ የሱስን ለማየት ዓይኖቻቸው እንዲከፈቱና ድምፁንም ለመስማት ጆሮቻቸው እንዲከፈቱ “በፍጥነት ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ከሞት ተነስቷል” ብላችሁ ንገሯቸው። በትልቅ ድንጋይ በተዘጋው፤ በሮማውያን ማኅተም በታሸገው አዲሱ የዮሴፍ መቃብር ላይ እንዳያተኩሩ ንገሯቸው። ባዶውን መቃብር አትመልከቱ። ተስፋና ረዳት እንደሌላቸው ሰዎች አታልቅሱ። የሱስ ህያው ነው፣ እርሱ ህያው ስለሆነ እኛም ህያው እንሆናለን። ክርስቶስ ተነስቷል! የሚለው የደስታ ዝማሬ የጌታን ውለታ ከማይረሳ ልብና በቅዱስ እሣት ከተነካ አንደበት ያስተጋባ። የሱስ እኛን ለማማለድ ህያው ሆኖ ይኖራል። በዚህ ተስፋ ካመናችሁ ለነፍሳችሁ አስተማማኝ መልህቅ ይሆንላችኋል። ካመናችሁ የእግዚአብሔርን ክብር ታያላችሁ።

ዛሬስ ደቀ መዛሙርቱ እንዳደረጉ የሚያደርጉ ስንት ናቸው? ማርያም ተስፋ በመቁረጥ “ጌታን … ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩት አላውቅም” ስትል የተናገረውችውን የሚያስተጋቡ ስንት ይሆኑ? አዳኛችን “ስለምን ታለቅሻለሽ፤ ማንንስ ትፈልጊአለሽ?” ያለውን ቃል ለስንቶችስ አሁንም እየተነገረ ይሆን? እርሱ በአጠገባቸው እያለ ዓይኖቻቸው በእንባ ስለተሸፈኑ ሊያውቁት አይችሉም። የሱስ ያናግራቸዋል፣ እነርሱ ግን አያስተውሉም።

(ይህ ጽሁፍ የሚከተሉትን ጥቅሶች መሠረት ያደረገ ነው፤ ማቴ. 28፡1፣ 5-8፤ማር. 16፡1-8፤ሉቃ. 24፡1-12፤ ዮሐ. 20፡1-18፤ የተወሰደው ከዘመናት ምኞት ምዕራፍ 82 ሲሆን ርዕሱ “ለምን ታለቅሻለሽ?” የሚል ነው)

ትርጉም አበበ ብዙነህ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *