- መሉው መጽሐፍ ቅዱስ ከ532 ቋንቋዎች በላይ ሲታተም፤ በከፊል (አዲስ ኪዳን) በ2883 ቋንቋዎች ታትሟል።
- መጽሐፍ ቅዱስ የአንድ ሰው ውጤት ሳይሆን የበርካታ ጸሐፍት ስብስብ ነው፤ እነዚህም እረኞችን፣ ነገሥታትን፣ ገበሬዎችን፣ ካህናትን፣ ገጣሚዎችን፣ አሣ አጥማጆችን፣ ወዘተ ያካተተ ነው።
- ብሉይ ኪዳንን ለመጻፍ 1000 ዓመታትን ሲወስድ አዲስ ኪዳን ግን ከ50 – 75 ባሉት ዓመታት ውስጥ ተጠናቅቋል።
- በግምት በየዓመቱ 100 ሚሊዮን ቅጂዎች ይሸጣል።
- ረጅሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፍ መዝሙር 119 ነው፤ 176 ቁጥሮች አሉት። አጭሩ ደግሞ መዝሙር 117 ነው፤ ቁጥሮቹም ሁለት ብቻ ናቸው።
- መጽሐፍ ቅዱስን ከላቲን ወደ እንግሊዝኛ ለመጀመሪያ ጊዜ የተረጎመው ጆን ዊክሊፍ (1320 – 1384) ነው። በወቅቱ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይነበብ ገዝታ የነበረችው የሮም ካቶሊክ ቤ/ክ ይህንን የትርጉም ሥራ በመሥራቱ መቀጣጫ ይሆን ዘንድ ጆን ዊክሊፍ ከሞተ በኋላ (በ1428 አካባቢ) አስከሬኑን አስቆፍራ አውጥታ አቃጥላዋለች።
- የመጀመሪያውን አዲስ ኪዳን ያተመው ዊሊያም ቲንደል (1494 – 1536) ሲሆን እርሱም ሥራው እንደ ጥፋት ተቆጥሮበት በመጀመሪያ በማነቅ ከተገደለ በኋላ በእሳት ተቃጥሏል።
- በ2016 በተደረገ የዳሰሳ ጥናት፤ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች፣ ከወጣቶች ይልቅ አረጋውያን፣ ከነጮችና ሌሎች ዘሮች ይልቅ ጥቁሮች መጽሐፍ ቅዱስን ያነባሉ።
- በኢትዮጵያ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ኦሮሚኛ የተረጎሙት ኦናሲሞስ ነሲብ ናቸው (እኤአ 1856 – 1931)። ይህንን በማድረጋቸው ለስደት የተዳረጉት ኦናሲሞስ፤ ሲወለዱ ስማቸው ሒካ ይባል የነበረ ሲሆን ክርስትናን ከተቀበሉ በኋላ ኦናሲሞስ የሚለውን ስም ወስደዋል። ከእርሳቸው በፊት ሩፎ የተባሉ አስፈላጊ የሚባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ወደ ኦሮሚኛ ተርጉመዋል።