giziew.org

ሙታን በርግጥ ሞተዋል? የት ነው ያሉት?

ሰው ሲሞት ምን ይሆናል? ነፍሱ ወጥታ ወደ ሌላ ቦታ ትሄዳለች? ከሞት በኋላ ሌላ ሕይወት አለ? ገሃነም ምንድነው? ለዘላለም መቃጠልስ በርግጥ እውነት ነው? ወይስ ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ትምህርት ነው? መልሱን ከጽሑፉ ያገኛሉ።
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ስለ ሰው ተፈጥሮ ጥናት የሚያደርጉ ሰዎች ከሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ “የሰው ተፈጥሮ ምን ምን ያካተተ ነው?” የሚለው ነው። ታዲያ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሦስት የተለያዩ አመለካከቶችን ያቀርባሉ። አንደኛው ምልከታ በ1ኛ ተሰሎንቄ 5፡23 ላይ የሚመረኮዝ ሲሆን ይህም፤ ሰው መንፈስ፣ ነፍስና ሥጋ (አካል) የተባሉ ሦስት ክፍሎችን የያዘ ነው የሚለው ነው። ይህ አመለካከትም ትራይኮቶሚ (ሦስትነት) በመባል ይታወቃል።

ሁለተኛው አመለካከት ደግሞ በዘፍ. 2፡7 ላይ የተመሠረተው ሲሆን ይህም ሰው ከአፈርና ከእግዚአብሔር እስትንፋስ በመሠራቱ ሁለት ነገሮችን ያካተተ ነው ይለናል። እነዚህም ማቴሪያላዊ (ቁሳዊ) የሆኑና ያልሆኑ በመባል ይከፈላሉ። ቁሳዊ በመባል የሚታወቀው ክፍል እንደ ደም ሥር፣ ኩላሊት፣ ጭንቅላት፣ እጅ፣ እግርና የመሳሰሉትን የሚያካትት ሲሆን ቁሳዊ ያልሆነው ክፍል ደግሞ ነፍስ፣ መንፈስ፣ አእምሮ፣ ኅሊና፣ ፈቃድ የመሳሰሉት ናቸው ይላል። ይህ ዓይነት የሰው ተፈጥሮ አገላለጽ ደግሞ ዳይኮቶሚ (ሁለትነት) በመባል ይታወቃል።

ሦስተኛው የሰውን ተፈጥሮ የሚገልጸው ሃሳብ በተመሳሳይ መልኩ መነሻ ጥቅሱ ዘፍ. 2፡7 ሲሆን ነገር ግን የሰውን ተፈጥሮ እንደ ሁለት ማየት ትቶ እንደ አንድ ውኁድ አድርጎ የሚያይ ነው። ይህም አመለካከት ሰው መንፈስም፣ ነፍስም፣ ሥጋም ልብም ሆነ ኅሊናም ቢኖረውም፤ እነዚህ አንዱ ከሌላው ተነጣጥለው ኅልውና የሌላቸው ናቸው፤ ስለዚህ ሰው ተነጣጥለው ኅልውና የሌላቸው ክፍሎች ውኁድ ውጤት ነው ይላል። በዚህ ምክንያት ይህ አመለካከት ሞኒዝም (አንድ-ነት) በመባል ይታወቃል።

እነዚህ ሦስት አመለካከቶች ልዩነታቸው ጎልቶ የሚወጣው “ሰው ሲሞት ምን ይሆናል?” የሚለውን ጥያቄ በምንጠይቅበት ጊዜ ነው። የትራይኮቶሚና የዳይኮቶሚ ሃሳብ አራማጆች ሰው ሲሞት ነፍሱ ከሰውነቱ ተለይታ ኅልውና እንዳላት ሲያስተምሩ፤ የሞኖይስት ሃሳብ አራማጆች ደግሞ ነፍስ ከሰውነት ተነጥላ ኅልውና ሊኖራት አይችልም፤ ነፍስ ማለት ሰው ነው፤ ስለዚህ ሰው ሲሞት ነፍስም ትሞታለች በማለት ያስተምራሉ።

ሁላችንም እንደምናውቀው ሞት እጅግ ከማይስተዋሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው። ለብዙዎች ሞት በምሥጢር የተሸፈነ፣ ፍርሃትንና ተስፋ መቁረጥን የሚጭርና በሕይወት እርግጠኛ ባለመሆን መዋለልን የሚፈጥር ጉዳይ ነው። የሚገርመው አንዳንዶች የሚወዷቸው ሰዎች ቢሞቱም እንዳልሞቱ፤ እንዲያውም በሆነ መንገድ አብረዋቸው እንደሚኖሩ ያስባሉ። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ በሥጋ፣ በነፍስና በመንፈስ መካከል ያለው ግንኙነትና ልዩነት ተምታቶባቸዋል።

በዘመናችን ሰይጣናዊ የሆኑ የተለያዩና በርካታ ማታለያዎች ተስፋፍተው ስላሉ ሞትን በተለመከተ እያንዳንዳችን የምንወስደው አቋም ወሳኝነትና አስፈላጊነት ስላለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረዳት ማግኘት እጅግ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ለግምታዊ አስተሳሰብ ምንም ክፍተት ሳንሰጥ ሰው ሲሞት ምን ይሆናል? የሚለውንና ሌሎች ተያያዥ ርዕሰጉዳዮችን እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ የገለጠውን ለመረዳት በጸሎት መንፈስ እናጥና። ከሰው አፈጣጠር እንጀምር፤

  1. ሰው በምድር ላይ እንዴት ተፈጠረ?

“እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ” (ዘፍ. 2፡7)። በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰውን ከምድር አፈር ወስዶ ካበጀውና የራሱን የአምላክን “እስትንፋስ እፍ” ካለበት በኋላ ሰው ሕያው ነፍስ ሆነ። ይህ የሆነው የአምላክ የሕይወት እስትንፋስ ከአፈር ከተሠራው በድን የሰው አካል ጋር ሲደመር ነው፤ ማለትም ሁለቱ (የአምላክ እስትንፋስና ከአፈር የተሠራው የሰው አካል) ሲደመሩ፣ ሲጣመሩ ሰው ሕያው ነፍስ ሆነ።

         (ሰው)ነፍስ = የአምላክ እስትንፋስ + አፈር
  1. ሰው ሲሞት ምን ይሆናል?

“ዐፈር ወደ መጣበት መሬት ሳይመለስ፣ መንፈስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ፣ ፈጣሪህን አስብ” (መክብብ 12፡7)። እዚህ ላይ የምንረዳው ሰው ሲሞት አካሉ ወደ አፈር (መሬት)፣ እስትንፋሱ ደግሞ ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር እንደሚመለስ ነው፤ ይህ ክስተት የሚፈጸመው በዚህ ምድር ላይ በሚገኙ ኃጥአንም ሆነ ጻድቃን ላይ ልዩነት ሳያደርግ ነው። “ሳይመለስ” ከሚለው ቃል በምናገኘው መረዳት መሠረት ሞት ማለት ሁሉ ነገር ቀድሞ ወደ ነበረበት ሁኔታ መመለስ ማለት ነው፤ ሞት ዐፈሩን (የሰውን አካል) ወደ መሬት፤ እስትንፋሱን ደግሞ ወደ ሰጠው እግዚአብሔር ይመልሳል። ለምሳሌ በኬምስትሪ ትምህርት መሠረት ውሃ የሁለት እጅ ሃይድሮጅንና የአንድ እጅ ኦክስጅን ውህደት ውጤት ነው። እነዚህ ሁለት ንጥረነገሮች ሲዋሃዱ ውሃ ይፈጠራል፤ ሲለያዩ ደግሞ ውሃ አይኖርም። የሰውም በሕይወት መኖር የአምላክ እስትንፋስና የምድር ዐፈር ውህደት የፈጠረው ሲሆን ሰው ሞተ ስንል ደግሞ የእነዚህ ሁለት ነገሮች ተነጣጥለው ወደመጡበት መመለስ ነው።

  1. ሰው ሲሞት ከእርሱ ወጥቶ ወደ እግዚአብሔር የሚሄደው እስትንፋስ ምንድነው?
ፎቶው የተወሰደው ከዚህ ነው

“ከመንፈስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ ከሥራም የተለየ እምነት የሞተ ነው” (ያዕቆብ 2፡27)። “በውስጤ የሕይወት እስትንፋስ፣ በአፍንጫዬም ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ እስካለ ድረስ” (ኢዮብ 27፡3)። በመጽሐፍ ቅዱስ አነጋገር ከሰው ወደ እግዚአብሔር የሚመለሰው መንፈስ የሕይወት እስትንፋስ ነው። ይህ እስትንፋስ ወይም መንፈስ ከአካል ተለይቶ የሟቹን ግለሰብ የሚወክል ጥበብ ወይም እውቀት ሆነ ስሜት ወይም ማንነት እንዳለው የሚያስረዳ አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የለም።

  1. ታዲያ ነፍስ ማለት ምን ማለት ነው?

ከላይ በተጠቀሰው ዘፍጥረት 2፡7 መሠረት “ነፍስ” ማለት የሕይወት እስትንፋስ ከአፈር ከተሠራው አካል ጋር ሲገናኝ የሚፈጠረው ሕይወት ያለው ፍጡር ነው። ይህ ነፍስ ወደ ኅልውና የመጣው እስትንፋስና አካል ተገናኝቶ ወይም ተደምሮ በመሆኑ ሁለቱ በተለያዩ ቀን የነፍስ ኅልውና ያከትማል። ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ “ነፍስ” ተብሎ እንደሚጠራ እናነባለን። በቀላሉ “አምስት ሰዎች” ያሉበት ቦታ “አምስት ነፍሳት” ያሉበት ሊባል ይቻላል።

  1. ግን እኮ ዘፍጥረት 2፡7 ላይ “ሕያው ነፍስ ሆነ” ተብሎ የተጠቀሰው “ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ” ተብሎም ይጠቀሳል፤ የትኛው ነው ትክክል?

ይህ የትርጉም መዛባት ነው፤ ዝርዝሩን ባጭሩ እንመልከት፤

“እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ።” ዘፍጥረት 2፡7 (የ1954 ትርጉም)።

“እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ፈጠረ መሬት ከምድር። ባፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት። ሰውም ሕይወት ያለበት ነፍስ ሆነ።” (የ1879 ትርጉም)።

በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 እግዚአብሔር ብርሃንን ከጨለማ እንዳወጣ፤ በምዕራፍ 2 ደግሞ ሰውን ከምድር አፈር እንዴት እንዳበጀው ዘርዝሮ ይናገራል። “ሰውን አበጀ” የሚለውና “የሕይወት እስትንፋስ” የሚሉት አባባሎች እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ሲፈጥር የወሰደው እርምጃ ከፍጥረት ሁሉ ይልቅ ለሰው ልዩ ትኩረት መስጠቱን የሚያሳዩ ናቸው።

“እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ” ዘፍጥረት 2፡7 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)።

“ሰውን አበጀ” የሚለው ቃል ከዕብራይስጡ “ዋይሴር” ከሚለው ግስ የተገኘ ትርጉም ሲሆን፤ ይህም ቃል ስለ እግዚአብሔር ሰውን የመፍጠር ሁኔታ የሚነግረን ስዕላዊ የሆነ አገላለጽን የያዘ ነው። ይኸውም፤

1ኛ፤ “አበጀው” የሚለው ቃል እግዚአብሔር ሰውን እንደ ሸክላ ሠሪ እንደቀረጸው (ኤርምያስ 18፡2) የሚገልጥ ሲሆን፤ ይህም ከፍጥረታት ሁሉ ይልቅ ለሰው ልዩ የፍቅር ትኩረት መስጠቱን የሚያሳይ ነው።

2ኛ፤ እግዚአብሔር ሰውን በገዛ እጆቹ ሲፈጥር ሌሎች ፍጥረታትን ግን በቃሉ ብቻ ነው የፈጠረው፤ ይህ የሚጠቁመን አምላክ በሰው አፈጣጠር ላይ ልዩ የሆነ መጠበብን እንዳደረገ ነው (ኢሳይያስ 44፡9-10)።

3ኛ፤ ይህ በእግዚአብሔር የተበጀው ሰው ያለ አምላክ ድጋፍና ዕርዳታ ለመኖር እንደማይችል የሚጠቁም ነው (ኢሳይያስ 2፡16)።

“የሕይወት እስትንፋስ” የሚለው አገላለጽ ሌሎች ፍጥረታት በአየር ላይ የሚበሩ፣ በውሃ ውስጥ የሚንቀሳቀሱና በምድር ላይ የሚርመሰመሱ ሕይወትን ያገኙት እግዚአብሔር ከተናገረው መለኮታዊ የሥልጣን ቃል መሆኑን፤ ሰው ግን ሕይወትን ያገኘው በአምላኩ እጅ ተበጅቶ ብቻ ሳይሆን የሕይወት እስትንፋስ በአፍንጫው እፍ ተብሎበት፤ ለልዩ ዓላማና በልዩ ትኩረት መፈጠሩን የሚያስረዳ ነው። ይህንን መልካም ዜና ዘፍጥረት 2፡7 ሲያበስር፤ “ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ” ይላል።

ሆኖም ለብዙ ሰዎች አነጋጋሪ የሆነው “ሕያው ነፍስ ሆነ” የሚለው አጻጻፍ ነው። በዚህ ጥቅስ ምክንያት ሰው የተለየ ነፍስ የምትባልና ከአካል ተለይታ የምትገኝ ነገር በውስጡ እንዳለችው ተደርጎ ይታሰባል። ነገርግን ይህንን ጥቅስ መጀመሪያ በተጻፈበት በዕብራይስጡ እና በተለያዩ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በማነጻጸር ስናየው ልዩነቶችን እንመለከታለን።

1879 ትርጉም1954 ትርጉምአዲሱ መደበኛ ትርጉም
ሕይወት ያለበት ነፍስ ሆነሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ

ከእነዚህ ሦስት የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የዕብራይስጡን ቃል ቀጥታ ተጠቅሞ “ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ” በማለት ዘፍጥረት 2፡7ትን በትክክል የተረጎመው አዲሱ መደበኛ ትርጉም ነው።

“ነፌሽ ኻይ” የሚለው የዕብራይስጡ ቃል በአማርኛ “ሕያው ነፍስ” ተብሎ ስምንት ጊዜ በብሉይ ኪዳን የተደገመ ሲሆን፣ የ1879ኙና የ1954ቱ ትርጉሞች  ከአዲሱ መደበኛው ትርጉም ይልቅ “ሕያው ነፍስ” በማለት ትርጉም ሳይቀያይሩ በዘላቂነት በተደጋጋሚ ተርጉመውታል። (ዘፍጥረት 1፡21፣24፣30፤ 2፡7፣19፤ 9፡12፣15፣16 እና ሕዝቅኤል 47፡9ን ይመልከቱ።) ነገርግን ዘፍጥረት 2፡7ን በተመለከተ እነዚህ ሁለት ትርጉሞች (1879ና 1954ቱ ትርጉሞች) በዕብራይስጡ ያልተጻፈ “ያለበት” እና “ያለው” የሚሉ ቃላት የአማርኛው ትርጉም ላይ ጨምረዋል። በመሆኑም በፈጠረው ሰው ውስጥ እግዚአብሔር “ነፍስ” የምትባል ነገር ጨምሯል ብለን በስህተት እንድንረዳ አድርጎናል። ይህም የማኅበረሰባችን ተለምዷዊ አስተሳሰብ በመሆን ተስፋፍቶ ይገኛል።

በዘፍጥረት 2፡7 ላይ የሚገኘው የዕብራይስጡ አገላለጽ ግን ሰው “ነፍስ” የምትባል ልዩ ነገር በውስጡ ይዟል የሚል ሳይሆን፤ ሰው ከግዑዝ (በድን) ፍጥረት ተለይቶ “ሕያው ፍጡር” ሆነ የሚል ነው። በሌላ አገላለጽ በዘፍጥረት 2፡7 መሠረት “ነፍስ” ማለት “ሕያው ፍጡር” ማለት ነው። ስለዚህ ሰው “ሕያው ፍጡር” ሆነ ማለት ከአፈር የተበጀው አካል ሕይወትን አገኘ፣ መንቀሳቀስ፣ ማሽተት፣ ማየት፣ ማሰብ፣ ሃሳቡን መግለጽ፣ ወዘተ ጀመረ ማለት ነው።

በ1954ቱ ትርጉም በዕብራይስጥ “ነፌሽ ኻይ” (ሕያው ፍጥረት) የሚለው አገላለጽ ከዘፍጥረት 2፡7 ሌላ በተወሰኑ ቦታዎች ተጠቅሷል። በዕብራይስጥ “ነፌሽ” ማለት “ፍጥረት”፣ “ኻይ” ደግሞ “ሕያው” ማለት ሲሆን ከዚህ በታች ያሉት ጥቅሶች ይህንኑ ቃል በዚህ መልኩ ተርጉመውታል።

በዘፍጥረት 1፡21 “ሕያዋን ፍጥረታት”፣ 1፡24 “ሕያዋን ፍጥረታትን”፣ 1፡30 “ሕያው ነፍስ”፣ 2፡19 “ሕያው ነፍስ”፣ 9፡12 “በሕያው ነፍስ”፣ 9፡15 “ሕያው ነፍስ”፣ 9፡16 “በሕያው ነፍስ”፣ በመጨረሻ ሕዝቅኤል 47፡9 ላይ “ሕያው ነፍስ” በመባል በ1954ቱ መጽሐፍ ቅዱስ ተተርጉሟል። በእነዚህ ጥቅሶች መሠረት “ነፌሽ ኻይ” ማለት ሕይወት ያለው ተንቀሳቃሽ ፍጥረት ማለት እንጂ ነፍስ ወይም ሌላ ከአካል ተለይታ መኖር የምትችል ረቂቅና ድብቅ ነገር በውስጡ ያለችው ማለት አይደለም።

በአዲሱ መደበኛ ትርጉም “ነፌሽ ኻይ” ከዘፍጥረት 2፡7 ውጪ እንዴት እንደተተረጎመ ስንመለከት ደግሞ፤ በዘፍጥረት 1፡21 “ሕይወት ያላቸው ነገሮች”፣ 1፡24 “ሕያዋን ፍጡራንን”፣ 1፡30 “ሕያዋን ፍጡራን”፣ 2፡19 “ሕያዋን ላላቸው ፍጡራን”፣ 9፡12 “ሕያዋን ፍጡራን”፣ 9፡15ና 16 “ሕያዋን ፍጡራን” ሕዝቅኤል 47፡9 “ሕያዋን ፍጡራን” ተብሏል። በነዚህ ጥቅሶች መሠረት የ“ነፌሽ ኻይ” ጠቅለል ያለ ትርጉም ሕይወት ያላቸው ነገሮች፣ ሕያዋን ፍጡራንና ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ማለት እንደሆነ ለመረዳት አያስቸግርም። ስለዚህ ይህ አባባል ሕይወት ያለው ነገር ወይም ሕይወት ያለው ፍጡር የሚል ትርጉምን የያዘ እንጂ ነፍስ ከአካል ተለይታ በሰው ውስጥ ተሰንቅራ የምትገኝ ነገር መሆኗን የሚያስረዳ አይደለም።

በተጨማሪ በ1879ኙ ትርጉምና በ1954ቱ ትርጉም ላይ የሚገኙት በዘፍጥረት 2፡7 ላይ የአማርኛውን አነባብ ለማሳለጥ በሚል የገቡት “ያለበት” ና “ያለው” የሚሉት ቃላት በእርግጠኝነት በዕብራይስጡ ላይ እንደማይገኙ ከዚህ በታች ከቀኝ ወደ ግራ የተጻፈውን የዕብራይስጥ ጥቅስና ከሥሩ የሚገኘውን የአማርኛ ጥሬ ትርጉም ይመልከቱ።

ይህንን የዕብራይስጥ ዓረፍተ ነገር በግርድፉ ወይም በቀጥታ ወደ አማርኛ ስንመልሰው እንደሚከተለው ሆኖ ሊተረጎም ይችላል።

እና ኤሎሂም ያህዌ ሰውን ከምድር አፈር አበጀው። እና በአፍንጫው የሕይወት እስትንፋስ ተነፈሰበት። እና ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ።

ስለዚህ እነዚህን መረጃዎች በመመልከት “ሕያው ነፍስ ሆነ” የሚለው የዘፍጥረት 2፡7 ቃል ሰው ሕይወት ያለው ፍጡር ወይም “ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ” ተብሎ በእርግጠኛነት መተርጎም ይችላል ማለት ነው።

  1. ነፍስ ይሞታል?

አዎ ይሞታል! ምክንያቱም ነፍስ ማለት ሰብዓዊ ፍጡር ነው። “ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች” (ሕዝ. 18፡20)። “በባሕርም ከሚኖሩት ሕይወት ያለበት ነፍስ ሁሉ ሞተ” (ራዕይ 16፡3)። እንደ እግዚአብሔር ቃል አገላለጽ ነፍስ ይሞታል። ምክንያቱም የአምላክ እስትንፋስና የአፈር ውኁድ የሆነው ሰው ነፍስ ነው፤ ነፍስ (ሰው) ደግሞ ይሞታል፤ ስለዚህ ሰዎች ሁሉ ሟች ናቸው (ኢዮብ 4፡17)። የማይሞተው እግዚአብሔር ብቻ ነው (1ጢሞ. 6፡15፣16)። ይህ በመሆኑም ሰው ሲሞት ተለይታው የምትወጣ የማትሞት ዘላለማዊ ነፍስ አለች የሚለው ጽንሰሀሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም።

  1. መልካም ሰዎች ሲሞቱ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ?

“በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉ ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ” (ዮሐ. 5፡28፣29)። “ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። … ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና” (የሐዋርያት ሥራ 2፡29፣34)። ሰዎች ሲሞቱ ወደ ሰማይም ሆነ ወደ ገሃነም አይሄዱም። ይልቁኑ እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስ በመቃብራቸው ሆነው እንደ ዳዊት የትንሣኤን ቀን ይጠብቃሉ።

  1. ሰው ከሞተ በኋላ ምን ያህል ያስተውላል?

“ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቷልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም። ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ጠፍቶአል፥ ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘላለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም። … አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ” (መክብብ 9፡5፣6፣10)። “አቤቱ፥ ሙታን የሚያመሰግኑህ አይደሉም፥ ወደ ሲኦልም የሚወርዱ ሁሉ” (መዝሙር 115፡17)። ጥቅሶቹ እንደሚነግሩን ሙታን አንዳች አያውቁም።

  1. ሙታን ንቃተኅሊና አላቸው? ከሕያዋን ጋርስ መገናኘት፣ መነጋገር ይችላሉን?

“ሰውም ተኝቶ አይነሣም፤ ሰማይ እስኪያልፍ ድረስ አይነቃም፥ ከእንቅልፉም አይነሣም። … ልጆቹ ቢከብሩ አያውቅም፤ ቢዋረዱም አያይም” (ኢዮብ 14፡12፣21)።“ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘላለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም” (መክብብ 9፡6)። ሙታን በዚህ ምድር ላይ በሚፈጸመው ማንኛውም ነገር ላይ ተሳትፎ የላቸውም። ስለዚህ ማንኛውንም ሕያው ሰው አያናግሩም፤ በዚህ ምድር ላይ የሚፈጸምን አንዳች ነገር አያውቁም፤ ሃሳባቸው ሁሉ ጠፍቷል (መዝሙር 146፡4)።

  1. በዮሐንስ 11፡11-14 ላይ ክርስቶስ ሞትን በእንቅልፍ መስሎታል። ታዲያ ሙታን ለምን ያህል ጊዜ ያንቀላፋሉ?

“ሰውም ተኝቶ አይነሣም፤ ሰማይ እስኪያልፍ ድረስ አይነቃም፥ ከእንቅልፉም አይነሣም” (ኢዮብ 14፡12)። “የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ” (2 ጴጥሮስ 3፡10)። ሙታን በመቃብራቸው ውስጥ በእንቅልፍ የሚቆዩት ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን እስከሚደርስና ሰማያት እስከሚያልፉ ድረስ ነው። እስከዚያ ድረስ ግን አንዳች የሚያውቁት ሳይኖር በመቃብራቸው ውስጥ ይቆያሉ።

  1. ክርስቶስ ዳግመኛ በሚመጣበት ጊዜ የሞቱት ጻድቃን ምን ይሆናሉ?

“ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤… እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን” (1ኛ ተሰሎንቄ 4፡16፣17)። “እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን። … ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና”(1ቆሮ. 15፡51-53)።

ሙታን በትንሣኤ ቀን በማይሞት ሥጋ ይነሳሉ። ጌታን በአየር ላይ ለመገናኘት ወደ ሰማይ ይነጠቃሉ። ሽልማታቸውን ይቀበላሉ (ራዕይ 22፡12)። እንግዲህ ሰዎች እንደሞቱ ወደ ሰማይ የሚሄዱ ቢሆን ኖሮ መጽሐፍ ቅዱስ የትንሣኤን አስፈላጊነት ይህን ያህል አጉልቶ አይናገርም ነበር።

  1. በዚህ ምድር ላይ የመጀመሪያው የሰይጣን ውሸት ምንድን ነበር?

“እባብም ለሴቲቱ አላት፦ ሞትን አትሞቱም” (ዘፍጥረት 3፡4)። “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ” (ራዕይ 12፡9)። በኤድን ገነት ሔዋንን ያሳታት “እባብ” ተብሎ የተጠቀሰው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ ራዕይ 12፡9 ተርጉሞታል። በወቅቱም ሰይጣን በእባብ ተመስሎ ለሔዋን የነገራት የመጀመሪያው ውሸት “አትሞቱም” የሚለው ነበር፤ እግዚአብሔር ግን “ከፍሬዋ በበላችሁ ጊዜ ሞትን ትሞታላች” ብሎ ነበር። አሁንም ከዋንኞቹ የሰይጣን ማሳሳቻ ትምህርቶች አንዱ “አትሞቱም” የሚለው ሲሆን ይህም ሰው ሲሞት ነፍሱ ወደ ገነት ወይም ወደ ሲዖል ትሄዳለች፣ ነፍስ አትሞትም፣ ከሙታን ጋር እናገናኛለን፣ ወዘተ የሚባሉት የክርስትናን ካባ የደረቡ ትምህርቶች ናቸው። (ለምሳሌ የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ማንበብ ይጠቅመናል፤ የግብፅ አስማተኞችና ጠንቋዮች—ዘጸአት 7፡11፤ በዓይንዶር የምትገኘዋ መናፍስት ጠሪ—1ሳሙኤል 28፡3-25፤ የባቢሎን ጠንቋዮች—ዳንኤል 2፡2፤የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት አንዲት ሴት—የሐዋ. ሥራ  16፡16-18)።

  1. በርግጥ አጋንንት ተዓምራትን ይሠራሉ?

“… ምልክት (የሚያደርጉ) የአጋንንት መናፍስት ናቸውና፥” (ራዕይ 16፡14)። “ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ” (ማቴዎስ 24፡24)። በርግጥ ሰይጣን አስደናቂ የሚባሉ ተአምራቶችን ይሠራል፤ “… በሰዎቹም ፊት እሳት ከሰማይ ወደ ምድር እስኪያወርድ ድረስ ታላላቅ ምልክቶችን አደረገ” (ራዕይ 13፡13፣14)። “ሰይጣን የብርሃን መልአክ እስኪመስል ድረስ ራሱን ይለውጣል” (2ኛ ቆሮንቶስ 11፡14)። ክርስቶስ ነኝ ብሎ ራሱን ይገልጣል (ማቴዎስ 24፡23፣24)።

  1. ታዲያ የእግዚአብሔር ሕዝብ በሰይጣን ማታለያዎች እንዳይሳሳት ምን ያስፈልገዋል?

“እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና፦ ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ” (የሐዋ. ሥራ 17፡11)። “ወደ ሕግና ወደ ምስክር ሂዱ! እንዲህም ያለውን ቃል ባይናገሩ (ወይም በእነዚህ ላይ ተመሥርተው የማይናገሩ ከሆነ) ንጋት አይበራላቸውም” (ኢሳይያስ 8፡20)። የእግዚአብሔር ልጆች መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠኑ ሙታን በርግጥ የሞቱ እንጂ በሕይወት የሌሉ መሆናቸውን ይረዳሉ። የሚወዷቸውን የሞቱ ሰዎች መስሎ የሚታይ ማንኛውም ነገር ወይም መንፈስ የሰይጣን እንጂ የአምላክ መንፈስ አለመሆኑን ይረዳሉ።

  1. ጻድቃን በትንሣኤ ከሞት ከተነሱ በኋላ እንደገና የመሞት አደጋ አለባቸውን?

“ያን ዓለምና ከሙታን ትንሣኤ ሊያገኙ የሚገባቸው እነዚያ ግን አያገቡም አይጋቡምም፥ እንደ መላእክት ናቸውና፥ ሊሞቱም ወደ ፊት አይቻላቸውም፥ የትንሣኤም ልጆች ስለ ሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው” (ሉቃስ 20፡35፣36)። “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ”(ራዕይ 21፡4)። “ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ፦ ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል” (1ኛ ቆሮንቶስ 15፡54)።

ሰይጣን – እንደ ብርሃን መልአክ፤ ሰይጣንና መላዕክቱ እጅግ በርካታ የሆኑ ሰዎችን ለማታለል ከዚህ በፊት የሞቱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ነብያትን፣ ሐዋርያትንና ቅዱሳንን በመምሰል የብርሃን መልአክ መስሎ ይገለጻል፤ “…ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋውጣል” (2ኛ ቆሮንቶስ 11፡13)። ሰይጣን ሰዎችን ለማታለል የሚጠቀምበት አንዱ መንገድ “እኔ ኢየሱስ ነኝ” በማለት ነው። ከዚህም ሌላ ልክ ጌታችንና መድኃኒታችን ከቃና ዘገሊላ ጀምሮ በርካታ ተዓምራትና ድንቅ ያደርግ እንደነበረው ሰይጣንም እንዲሁ በተዓምራት ሰዎችን ለመጥለፍ በረቀቀ መልኩ ይጠቀማል። የተለያዩ በሽታዎችን “ፈውስ” አስመልክቶ “ተዓምራት” ከማድረግ ጀምሮ ሙታንን ያስነሳ እስኪመስል ድንቆችን ያደርጋል። በመሆኑም “ሙታን በሆነ መልኩ በሕይወት አሉ” ብለው የሚያምኑ ሰዎች በእንደዚህ ዓይነቱ የሰይጣን ማታለያ ተጠልፎ ለመውደቅ በጣም ቅርብ ናቸው።

ቅንብር፤ ፓስተር መስፍን ማንደፍሮ

ስለ ሞት ተጨማሪ ጥያቄዎች

አሁንም ያልተመለሱ ተጨማሪ ጥያቄዎች አሉኝ፤ ለምሳሌ …

  1. ከጌታችን ጋር ተሰቅሎ የነበረውን ሌባ “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፤ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ነበር ክርስቶስ ያለው (ሉቃ. 23:42፣43)። ስለዚህ የሁለቱም ነፍስ ወደ ሰማይ አርጓል ማለት አይቻልም?
ፊል. 2፡6-7 ግጥምጥም ብሎ በግሪክ የተጻፈ ነው

አይቻልም! ጌታችን ክርስቶስ በሞተበት ቀን ወደ ሰማይ አላረገም። ለዚህ ማስረጃው በትንሣኤው ቀን ለመግደላዊት ማርያም የሚከተለውን መናገሩ ነው፤ “ኢየሱስም፣ ‘ገና ወደ አብ ስላላረግሁ፣ አትንኪኝ … አላት’” (ዮሐንስ 20:17)። ጌታችን እግዚአብሔር አብ ወዳለበት ሰማይ ያረገው ከትንሣኤው በኋላ ነው (የሐዋ. ሥራ 1:9-10)። ከዚህ የተነሳ በስቅለቱ ቀን ቀድሞ ገነት ደርሶ በእርሱ ያመነበትን ሌባ አስተናገደ የሚለው ነገር ትክክለኛ አይደለም።

ይህን ሃሳብ ጥያቄው ላይ ከቀረበው ጥቅስ ጋር ለማስታረቅ ስለ አዲስ ኪዳን አጻጻፍ ማወቅ ያለብን ነገር አለ። አዲስ ኪዳን ሲጻፍ ሥርዓተ ነጥብ (punctuation) አልነበረውም። ይህ ብቻ ሳይሆን በቃላት መካከል ወይም በዓረፍተ ነገሮች መካከል ምንም ዓይነት ክፍት ቦታ ሳይኖር ግጥምጥም ብሎ (or continuous script) ነበር የተጻፈው (በስተቀኝ  የተቀመጠውን ፎቶ ፊል. 2፡6-7 ግጥምጥም ብሎ በግሪክ የተጻፈ ነው)። ለምሳሌ ይህን አናባቢ የሌለውን በእንግሊዝኛ ፊደል የተጻፈ ጽሑፍ እንዴት ያነቡታል? “CMPTRNTWRK” ይህ እንግዲህ “computer network” ወይም “come Peter into work?” ሊሆን ይችላል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የምንባቡን ዐውድ በሚገባ በማስተዋል ይህንን ዓይነት ስህተት ከመፈጸም ተቆጥበዋል። ስለዚህ ሥርዓተ ነጥቦችን አስመልክቶ ግን የተፈጸሙ ግድፈቶች እንዳሉ ይህ የሉቃስ 23፡43 ጥቅስ አንዱ ማስረጃ ነው።

  1. ግን ታዲያ ጌታችን ለሌባው “ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሎት ክርስቶስ ግን በዚያኑ ቀን ወደ ሰማይ ካልሄደ የጥቅሱ ትርጉም ምንድነው?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለ ቀን ለሌባው የተናገረውን ከዐውዱ በመረዳት ለማርያም ከተናገራት ጋር የሚጣጣም ዓረፍተነገር ማግኘት ይቻላል። ሥርዓተ ነጥብ የተከተለው የጥቅሱ እውነተኛ አቀማመጥ የሚከተለው ነው፤ “እውነት እልሃለሁ ዛሬ (አሁን ተሰቅዬ ሳለሁ)፤ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ (ትድናለህ)።” ጌታችን ክርስቶስ ለሌባው ሊያረጋግጥለት የፈለገው ነገር “ዛሬውኑ” ገነት እንደሚገባ ሳይሆን የመዳኑ ጉዳይ “ዛሬውኑ” ወይም በዚያ እየተሰቀለ ባለበት ቀን እርግጠኛ መሆኑን ነው። ሌላው መታወቅ ያለበት ጉዳይ ጌታችን በስቅለተ ዓርብ ዕለት ሲሞት ሁለቱ ሌቦች ግን ገና ስላልሞቱ ጭናቸውን ሰብረው ከመስቀል እንዳወረዷቸው ዮሐንስ 19፡30-33 ላይ እናነባለን። በወቅቱ አዲስ ኪዳን ከተጻፈበት ሁኔታ በተጨማሪ ሌባው ዓርብ ዕለት አለመሞቱ በዚያን ቀን ገነት ላለመግባቱ ሌላው ማስረጃ ነው። መቼም ገነት ገብቷል ብሎ ለማመን ቢያንስ መሞት ይጠበቅበታል። ስለዚህ “ዛሬ” የሚለው ቃል አረዳድ ይህ ነው።

  1. እንደሱ ከሆነ እንደ ሌባው አምነው የሞቱ የሚነሱት መቼ ነው?       

በክርስቶስ አምነው ስለሞቱ ሰዎች መነሳት ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፤ “በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህን ነው፤ እኛ በሕይወት ያለንና ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉትን አንቀድምም፤ ጌታ ራሱ በታላቅ ትእዛዝ፣ በመላእክት አለቃ ድምፅና በእግዚአብሔር የመለከት ድምፅ ከሰማይ ይወርዳልና። በክርስቶስ የሞቱትም አስቀድመው ይነሣሉ። ከዚያም በኋላ እኛ የቀረነው፣ በሕይወትም የምንኖረው ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ በዚህም መሠረት ለዘላለም ከጌታ ጋር እንሆናለን” (1ኛ ተሰሎንቄ 4:15-17)። በቅድስና ኖረው የሞቱ ሁሉ እስከ ታላቁ ትንሣኤ ቀን ከሞት አይነሱም። እነዚህ ቅዱሳን በዚያ ቀን በትንሣኤ የሚነሱት ሟች አካል ይዘው ሳይሆን ዘላለማዊ ሆነው ነው። “ይህም የሚሆነው የመጨረሻው መለከት ሲነፋ ድንገት በቅጽበተ ዐይን ነው። መለከት ይነፋል፤ ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተውም የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ፣ “ሞት በድል ተዋጠ” ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል” (1ቆሮንቶስ 15:52-54)።

  1. መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን ምን ብሎ ነው የሚጠራው?

መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን በእንቅልፍ ይመስለዋል። ለምሳሌ ስለ ዳዊት ሞት ሲናገር እንዲህ ይላል፤ “ከዚያም ዳዊት ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ” (1ነገሥት 2:10)። ሞት ዕንቅልፍ መሆኑ የሚናገሩ 54 ተጨማሪ ጥቅሶች አሉ፤ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡ ዘዳግም 31፡16፤ በተለይ በሁለተኛ ነገሥት እና በሁለተኛ ዜና መዋዕል ነገሥታቱ ሲሞቱ “አንቀላፋ” የሚለው ቃል 25 ጊዜ ያህል ተጠቅሷል፤ ክርስቶስም ማቴዎስ 9፡24፤ ማርቆስ 5፡39፤ ሉቃስ 8፡52፤ ዮሐንስ 11፡11 ሞትን “ዕንቅልፍ” ብሎታል። በዚህ ምክንያት ጳውሎስም “ያንቀላፉት” ብሎ የሚጠራው ሟቾችን እንደሆነ ማወቅ ይቻላል። እንደ ሐዋርያው አገላለፅ አምነው የሞቱ ከሞት እንቅልፍ የሚቀሰቀሱበት ታላቅ የትንሣኤ ቀን ይመጣል። ያ ጊዜ ጌታ ከሰማይ የሚወርድበት መሆኑን ይነግረናል። ያኔ ነው ክርስቶስን አምነው የሞቱት ተነስተው በሕይወት ጌታን ከሚቀበሉት ጋር በመሆን ወደ ሰማይ የሚነጠቁት። ነፍሳቸው ሳትሞት ከእነርሱ ተለይታ የነበረች ከሆነ ታዲያ ትንሣኤ ለምን ያስፈልጋል?

  1. ይህ ከሆነ ሙታን አሁን የት ናቸው?

በመቃብራቸው! ሙታን እንደ ሕያዋን አለመሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁምና” (መክብብ 9:5)።

በተጨማሪ ሙታንን አስመልክቶ ቃሉ እንዲህ ይላል፤ “ዐፈር ወደ መጣበት መሬት ሳይመለስ፣ መንፈስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ፣ ፈጣሪህን አስብ” (መክብብ 12:7)። ይህ ጥቅስ እንደሚጠቁመው ሰው ሲሞት ዐፈር (አካሉ) ወደ መሬት፣ መንፈሱ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንደሚሄድ ነው። እንዲሁም አዳም ከበደለ በኋላ በኃጢአት ምክንያት አዳም የሚያገኘውን ሞት አስመልክቶ እግዚአብሔር ሲናገር ይህንን ብሏል፤ “ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ … አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህና” (ዘፍ 3፡19)። ከአፈር የተፈጠረው ሰው ሲሞት አፈር ይሆናል።

  1. መንፈስ ምንድነው?

መንፈስ ከሥጋ ተለይቶ ሕያው ሆኖ የሚኖር ነገር አይደለም። ቃሉ እንደሚለው “ከመንፈስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ ከሥራም የተለየ እምነት የሞተ ነው” (ያዕቆብ 2:26)። ሰው ውስጥ ስላለው መንፈስ ምንነት ቃሉ ሲተነትን እንዲህ ይላል፤ “በውስጤ የሕይወት እስትንፋስ፣ በአፍንጫዬም ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ እስካለ ድረስ …” (ኢዮብ 27:3)። ይህ የሚያሳየው መንፈስ የተባለው ነገርና የሕይወት እስትንፋስ አንድ መሆናቸውን ነው።

የሕይወት እስትንፋስ ከአምላክ የተቀበልነው ስጦታ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። “እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ” (ዘፍጥረት 2:7)። ጌታ እፍ ያለው ነገር በራሱ የሚያስብና የሚንቀሳቀስ የሰው ምናብ ወይም ማንነት አለመሆኑ ግልፅ ነው። ፍጥረት የሚያሳየው የምድር አፈርና የአምላክ እስትንፋስ ሰውን “ሕያው ነፍስ” እንደሚያደርጉት ነው። እስትንፋስና አካል የነፍስ ወይም የሰው ኅልውና መሥራቾች ናቸው። ተለያይተው የግል ኑሮ አይኖሩም፤ አንድ ሕያው ሰው ማለት አንድ ነፍስ ነው። ከመንፈስ የተለየ አካል (ሥጋ) ሙት ነው።

         (ሰው)ነፍስ = የአምላክ እስትንፋስ + አፈር
  1. በሉቃስ 16:19-31 ላይ ያለው ምሳሌ ያልዳኑ ሙታን በሲኦል እሳት እየተሰቃዩ የሚኖሩ መሆኑን አያስተምርም?

አያስተምርም! በቅድሚያ መታወቅ ያለበት ጉዳይ በሉቃስ 16:19-31 የተጠቀሰው ምሳሌ እንጂ በትክክል የተፈጸመ ታሪክ አለመሆኑ ነው። ምሳሌውም የሚናገረው በሕይወት ሳለ በድሃ ባልንጀራው ላይ ይጨክን ስለነበረ ሃብታም ሰው ነው። ይህ ሃብታም ሰው ሲሞት በገሃነም እሳት መሰቃየት ጀመረ። በአንፃሩ ደግሞ ዓልአዛር የተባለው ድሃ ባልንጀራው ሲሞት በአብርሃም ጉያ በምቾት ተቀመጠ። ይህ በእግርጥ የተከሰተ ሳይሆን ምሳሌ ነው።

ጌታችን ክርስቶስ ነገሮችን በምሳሌ የመናገር ባህርይ ነበረው። ለምሳሌ “እውነተኛው የወይን ተክል እኔ ነኝ፤ አትክልተኛውም አባቴ ነው” ብሏል (ዮሐንስ 15:1)። ይህን ቃል አንብቦ ክርስቶስን ፍለጋ ወደ ወይን እርሻ የሚሄድ የዋህ የለም። አባቱም ቢሆን በየቀኑ እንደምናያቸው ዓይነት አትክልተኞች አለመሆኑ ግልፅ ነው።

ነገር በምሳሌ እንዲባል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፉት ምሳሌያዊ አነጋገሮች ዋና ዓላማ ሰዎች በሚረዷቸው ነገሮች አዳዲስ ትምህርቶችን በቀላሉ ለማስተማር ነው። ሰዎች የወይን ግብርናን ያውቁ ስለነበር ጌታችን ክርስቶስ ማንነቱን በወይን ግንድ አማካይነት ገለፀ። ቅርንጫፎች በወይን ግንድ ላይ ተደግፈው ፍሬያማ እንደሚሆኑ ሁሉ እኛም ጌታችንና መድኃኒታችንን ተደግፈን የባሕርይ ለውጥ ለማድረጋችን ምስክር የሆኑትን የቅድስና ፍሬዎች እናፈራለን። ገበሬ የወይን አትክልቱን እንደሚገርዝና እንደሚኮተኩት እኛንም እግዚአብሔር እየቀጣ ወደ ቀናው መንገድ ያደርሰናል። ምሳሌው ይህ ነው።

ሉቃስ 16 ላይ ያለው ምሳሌም በዚሁ መንገድ ሊታይ ይገባል። ዋና ትኩረታችንን መሳብ ያለበት ከምሳሌው ጀርባ ያለው ትምህርት ወይም ምሳሌው የተጻፈበት ዐውድ እንጂ ትምህርቱ የተላለፈበት ምሳሌያዊ አነጋገር አይደለም። ይህ ምሳሌ በተጻፈ ጊዜ የነበረው ዋንኛ አስተምህሮ ሰው ድሀ የሚሆነው ስለተረገመ፤ ሃብታም የሚሆነው ደግሞ ስለተባረከ ነው የሚል ነበር። ምዕራፉን ከቁጥር አንድ ጀምሮ ማንበብ ዋናው ዐውድ ይህንኑ የሚያስተምር እንደሆነ ለመረዳት ያስችላል።

ጌታችን ኢየሱስ በምሳሌው ሊያስተላልፍ የፈለገው ትምህርት ምድራዊ ሀብትና ዝና በቅድስና ካልተያዘ በፈጣሪ ዘንድ ክብር የሌለው መሆኑን ነው። በአንፃሩ ምስኪን ድሃ ሆኖ በምድር ክብር የተነፈገ ነገርግን በእግዚአብሔር የሚያምን ሁሉ በአምላክ ዘንድ ታላቅ ክብር እንዳለውና ለአብርሃም የተሰጠው ክብር እንደሚጠብቀው ይጠቁማል።

በዚህ ምሳሌ የተጠቀሱትን መቃጠል፣ ሲዖል፣ የእሳት ነበልባል፣ ወዘተ ትክክል እንደሆኑ አድርገን ቀጥታ የምንወስድ ከሆነ ቁጥር 22 ላይ “ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት” የሚለውንም እንዲሁ በቀጥታው መውሰድ አለብን። ይህ ደግሞ በአብርሃም ዕቅፍ ውስጥ ስንት ሰው ነው መግባት የሚችለው? ወይም አብርሃም ስንቱን ነው ማቀፍ የሚችለው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። “የአብርሃም ዕቅፍ” ምሳሌ ነው ካልን ሌላውንም ጉዳይ በምሳሌነት መውሰድ ግድ ይሆንብናል። ሌላው በምሳሌው ሃብታሙ ሲናገር “በዚህ ነበልባል እሰቃያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ ምላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ” ይላል። ይህ እውነት ነው እንበልና እንዴት ነው በእሣት ነበልባል እየተሰቃየ ያለ ሰው ጠብታ ውሃ ስቃዩን የሚያበርድለት? እና ይህ ደግሞ እንዴት ነው ለዘላለም የሚቀጥለው? እንደ አብርሃም ያሉና ሌሎች የዳኑ ጻድቃን ይህንን ስቃይ እያዩ እንዴት ነው ደስ ብሏቸው “እግዚብሔር ፍቅር ነው” እያሉ ለዘላለም የሚኖሩት? በፊልም ትወና እንኳ የሰውን ስቃይ ስናይ ወይ ፊልሙን ወደፊት እናሳልፈዋለን ወይም አብረን እየተጨነቅን እንሰቃያለን። እንዴት ነው የገሃነምን ስቃይ ለዘላለም እያየንና ከሚሰቃዩት ልጆቻችንና ዘመዶቻችን ጋር እየተነጋገርን ለዘላለም የምንኖረው? ሌላው በምድር ላይ አንድ ሰው ሲኖር 100 ዓመት በማትሞላ ዕድሜው ለሚሠራው ኃጢአት እንዴት ሆኖ ነው ለዘላለም እየተቀጣ የሚኖረው? ይህ በምድራዊ ፍርድ እንኳን ፍርደ ገምድልነት ወይም ከወንጀል ጋር ያልተመጣጠነ ብያኔ አይሆንም? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው የፍርድ ብያኔ የሚሰጠው ሰዎች ሲሞቱ ሳይሆን ክርስቶስ ሲመጣ ነው፤ “እነሆ፤ ቶሎ እመጣለሁ፤ ዋጋዬ በእኔ ዘንድ አለ፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍለዋለሁ” (ራዕይ 22፡12)።

  1. በዚሁ በራዕይ መጽሐፍ 14:11 ላይ ስለ ሙታን ሲናገር “የሥቃያቸውም ጢስ ከዘላለም እስከ ዘላለም ወደ ላይ ይወጣል። … ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም” የሚለው ሙታን በስቃይ እንደሚኖሩ አያሳይም?

ይመስላል እንጂ አያሳይም! ከዚህ ጥቅስ የአገላለፅ ዘይቤ ጋር የሚመሳሰል ጥቅስ በይሁዳ መፅሐፍ ላይ የሚከተለውን እናገኛለን፤ “እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል” (ይሁዳ 7)።

ተቃጥላ የወደመችው የሰዶም ከተማ

ሰዶሞና ገሞራ ከጠፉ ከሶስት ሺህ ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። ታዲያ እንዴት ነው አሁን ድረስ “በዘላለም እሳት እየተቀጡ” ነው ማለት የሚቻለው? እግዚአብሔር በሰዶም ላይ የወሰደው እርምጃ ዘላለማዊ ውጤት ያለው ነው። ሟች ሁሉ ያለ ተስፋ ወደ መቃብር አይወርድም። በጌታችን ክርስቶስ የሚያምኑ ከሞት ይነሳሉ። ከኃጢአት አንላቀቅም ብለው መዳንን ችላ ያሉ ግን መመለሻ በሌለው ዘላለማዊ ሞት ለዘላለም ይጠፋሉ፤ ወይም ጠፍተው ይቀራሉ። እሣቱ የሚነደው የሚቃጠለው ነድዶ ዓመድ እስከሚሆን ነው።

የሰዶምና ገሞራ ከተሞች ግን ዛሬ በጥፋት እሳት እየነደዱ አይደለም። አንዴ ተቃጥለው ጠፍተዋል። ጥቅሱ ግን “በዘላለም እሳት እየተቀጡ ለሚሰቃዩት ምሳሌ ሆነዋል” ይላል። ይህ ማለት በሰዶምና የገሞራ ዕልቂት የሞቱት ዓመድ እንደሆኑ ሁሉ ወደፊት በእሳት የሚቀጡትም ተቃጥለው ሲያልቁ ውጤቱ ዘላለማዊ ይሆናል ማለት ነው።

በራዕይ ላይ የተጠቀሰው እሳት ምንነት እዚያው መፅሐፍ ውስጥ ተፈትቷል፤ “ከዚያም በኋላ ሞትና ሲኦል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ፤ የእሳቱ ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው” (ራዕይ 20:14)። በጥቅሱ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው በእሳቱ ሞትና ሲኦልም እንደሚቃጠሉ ተፅፏል። ይህ ማለት ሞት፣ ሲዖል እና ስቃይ ለዘላለም አይኖርም ማለት ነው። ኃጥአን፣ ሰይጣንና ተከታዮቹ ለዘላለም በእሣት እየተሰቃዩ ሞትና ሲኦል ግን ተቃጥለዋል ማለት ፈጽሞ አይቻልም።

በተጨማሪ ጌታ እንዲህ ይላል፤ “እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና” (ራዕይ 21:4)። በአዲሱ ሰማይና ምድር ድብቅ የስቃይ ጓዳ አይኖርም። ተፈጥሮ ሁሉ ከጣዕርና ከሞት የፀዳ ይሆናል። ይህ ሊሆን የሚችለው ሰይጣንና ግብረአበሮቹ ልክ እንደ ሰዶምና ገሞራ ለዘላለም ዓመድ ሆነው ሲጠፉ፤ ከመኖር ወደ አለመኖር ሲሄዱ ነው። ለዘላለም መቃጠል ማለትም ይኸው ነው፤ ለዘላለም አለመኖር፤ ፍጹም ተቃጥሎ መጥፋት ማለት ነው።

  1. ግን ታዲያ በኢሳይያስ 66፡24 ላይ “ትላቸው አይሞትምና፥ እሳታቸውም አይጠፋምና ይላል። እሳቱ ካልጠፋ ለዘላለም እየተቃጠሉ አይደል የሚኖሩት?

በጭራሽ! በመጀመሪያ ልንረዳ የሚገባን ነገር ግልጽ ያልሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን የምንፈታው ግልጽ በሆኑ ጥቅሶች ነው። ስለዚህ ስለ ሞት የተጻፉ ግልጽ የሆኑ፣ ትርጉማቸው የማያሻማና ትንታኔ የማያሻቸው ጥቅሶች አሉ። እስካሁን ባጠናነው አዳም ሲፈጠር የተሠራው ከአፈርና ከሕያው የእግዚአብሔር እስትንፋስ መሆኑን እና የእነዚህ ሁለቱ ድምር ሰው ወይም ሕያው ነፍስ እንደሚባል በግልጽ ተረድተናል። ስለዚህ ሰው ሲሞት ከውስጡ የምትወጣ የሆነች እርሱን የምትወክል ሚጢጢ ሰው ወይም ነፍስ የምትባል ነገር የለችም። ሰው ሲሞት ያንቀላፋል፤ ከአፈር የተፈጠረ ነውና ሲሞት ወደ አፈር ይመለሳል (ዘፍጥረት 3፡19)።

በኢሳይያስ 66፡24 ላይ ትሉ የማይሞትበትና እሳቱ የማያንቀላፋበት ተብሎ የተጠቀሰውን ሃሳብ የሚመስል ተመሳሳይ ሃሳብ ጌታችንም በወንጌል ተናግሯል። “ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት ወደ ገሃነም ወደማይጠፋ እሳት ከመጣል አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል” በማለት በማርቆስ 9፡48 የተናገረው ክርስቶስ ነው። ይህንን የተናገረው እግዚአብሔርን ከመታዘዝ የሚያሰናክሉንን ነገሮች ቆርጠን የመጣል ያህል ወሳኝ እርምጃ መውሰድ እንዳለብን ለማስተማር ነው። ሲቀጥልም ሙሉ ሰውነትህን ይዘህ ገሃነም ከምትገባ እጅና እግርህ ተቆርጦ ገነት ብትገባ ይሻልሃል ይላል (ማርቆስ 8፡43-48)። ይህንን ሲል ግን ገነት ውስጥ የሞሉት የተቆራረጡ ሰዎች ናቸው ማለቱ አይደለም። ምክንያቱም በገነት ሰዎች አዲስ ሙሉ አካል እንደሚለብሱ፣ ይህ የሚሞተው ደካማ ሥጋችን ወይም አካላችን እንደሚቀርና ዘላለማዊ አካል እንደምንለብስ፤ ሕመምና ሞት እንደማይኖር፤ ሁሉ ነገር አዲስ እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (1ኛቆሮንቶስ 15፡51-54፤ ራዕይ 21፡4-5)።

በተለምዶ “ሲዖል” የሚባለው ቃል “ገሃነም”፣ አንዳንዴም “መቃብር” ተብሎ እንደሚጠራ መጽሐፍ ቅዱስ ስናነብ እናገኛለን። በአዲስ ኪዳን “ገሃነም” የሚለው ቃል 12 ጊዜ ተጠቅሶ የምናገኝ ሲሆን የግሪኩ ቃል “ጌሄና (Gehenna)” የሚል ነው (ማቴ. 5፡22፤ 29-30፤ 10፡28፤ 18፡9፤ 23፡15፣33፤ ማር. 9፡43-47፤ ሉቃ.12፡5፤ ያዕ.3፡6)። “የገሃነም ሸለቆ” ተብሎ የሚጠራው “የሄኖም ሸለቆ” በመባል 13 ጊዜ በብሉይ ኪዳን ተጠቅሷል (ኢያሱ 15፡8፤ 18፡16፤ 2ነገ. 23፡10፤ ወዘተ)። የታሪክ ምሁራን ይህ የገሃነም ሸለቆ (የሄኖም ሸለቆ) ቦታ በጥንታዊው የኢየሩሳሌም ግምብ ደቡብ ምዕራብ የሚገኝ ሸለቆ እንደሆነ ይናገራሉ፤ በኢያሱ 15፡1፣8 ለይሁዳ ነገድ በተሰጠው ግዛት ውስጥ እንደሚገኝና ከቄድሮን ሸለቆ ጋር እንደሚገጥም ተጽፏል።   

አካዝ የተባለ በጣዖት አምልኮ የተለከፈ የይሁዳ ንጉሥ በሄኖም ሸለቆ ልጆቹን መሠዋቱን (2ኛ ዜና 28፡1-3)፤ በኋላ ላይ የእግዚአብሔርን መንገድ የተከተለው ንጉሥ ኢዮስያስ “ማንም ሰው ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን ለሞሎክ በእሳት እንዳያሳልፍ በሄኖም ልጆች ሸለቆ የነበረውን ቶፌትን (እሣት የሚነድበትን) ቦታ” የረከሰ መሆኑን ማወጁን እናነባለን (2ነገሥት 23፡10)። ከዚህ በኋላ በታሪክ እንደምናነበው ይህ ከኢየሩሳሌም በታች የሚገኝ ሸለቆ ያለማቋረጥ የቆሻሻ ክምር (የሞቱ ወንበዴዎች፣ የሞቱ እንስሳት ጨምሮ ማንኛውም ቆሻሻ) የሚቃጠልበት ቦታ ሆኖ ቀጥሏል።

ሆኖም ንጉሥ ኢዮስያስ ከሞተ በኋላ ይሁዳ እንደገና ወደ ጣዖት አምልኮ ተመልሶ የሰው መስዋዕት የሚቀርብበት ቦታ በመደረጉ የሄኖም ሸለቆ/ቶፌት የመጨረሻው ፍርድ የሚደረግበት “የዕርድ ሸለቆ” እንደሚሆን ኤርምያስ ተንብዮ ነበር፤ “እኔ ያላዘዝኋቸውን፣ ከቶም ያላሰብሁትን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት አቃጥለው ለመሠዋት በሄኖም ልጅ ሸለቆ የቶፌትን መስገጃ ኰረብቶች ሠሩ። ስለዚህ አስተውሉ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ስፍራ እስከማይገኝ ድረስ ሙታንን በቶፌት ስለሚቀብሩ፣ የዕርድ ሸለቆ እንጂ ከእንግዲህ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ተብሎ የማይጠራበት ጊዜ ይመጣል። የዚህም ሕዝብ ሬሳ ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ሲሳይ ይሆናል፤ የሚያባርራቸውም አይኖርም” (ኤርምያስ 7፡31-33)።

በሌሎችም የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች ይህ የሄኖም ሸለቆ/ቶፌት የተባለው ቦታ የማይጠፋ እሣት የሚቃጠልበት ቦታ ተብሎ በተደጋጋሚ ተጠቅሶ እናነባለን። እሣቱ የማይጠፋበት ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀሱ እሣቱ የማይጠፋ ሆኖ ሳይሆን የሚቃጠል ነገር እስካለ ድረስ እንደሚነድና እየነደደ የሚቆየውም ሁሉም ዐመድ እስኪሆን ለመግለጽ ነው። “አስቤስቶስ ፑር” የሚለው የግሪኩ ቃል ትርጉምም ይህንኑ የሚገልጽ ነው።

ለምሳሌ በኢሳይያስ 34፡8-10 ኤዶም በእግዚአብሔር ፍርድ እንደምትጠፋ “በሌሊትና በቀንም አትጠፋም፤ ጢስዋም ለዘላለም ይወጣል” ይላል። ኤዶም ግን እስካሁን እየጤሰች አይደለም። ሙሉ በሙሉ ተቃጥላ እስክትጠፋ ድረስ ብቻ ነው የጤሰችው። በኤርምያስ 17፡27 እስራኤላውያን ሰንበትን ባለማክበራቸው የኢየሩሳሌም በሮች እንደሚቃጠሉ ሲናገር “በበሮችዋ ላይ እሳትን አነድዳለሁ፥ የኢየሩሳሌምንም አዳራሾች ትበላለች፥ አትጠፋም” ይላል። የኢየሩሳሌም አዳራሾች እስካሁን እየነደዱ አይደሉም፤ ነገርግን “ትበላለች” የሚለውን በሌላ መልኩ ሲገልጸው “አትጠፋም” ብሎታል። በእሣት የሚበላ ነገር ምንም የሚተርፍለት የለም፤ ሁሉ ነገሩ ነው የሚነድደው።  በተጨማሪ ሕዝቅኤል 20፡47-48፤ አሞጽ 5፡6 ያንብቡ።

ከእነዚህ የብሉይ ኪዳን ሃሳቦች በመነሳት ነበር በቅድሚያ ዮሐንስ መጥምቁ በኋላም ጌታችን ከላይ በተጠቀሱት ወንጌላት እሣቱ ስለማጠፋበት ገሃነም በምሳሌ የተናገሩት። ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ ሲናገር “ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል” ይላል (ማቴዎስ 3፡12)። ገለባ በማይጠፋ እሳት ለዘላለም ሲቃጠል አይኖርም። ስንዴውም፣ ገለባውም ምሳሌያዊ አባባል እንደመሆኑ “የማይጠፋ እሳት” የተባለውም እንዲሁ ምሳሌያዊ ነው። ስለዚህ በኢሳይያስ 66፡24 ላይ “ትላቸው አይሞትምና፥ እሳታቸውም አይጠፋምና” የሚለው በዚህ ምሳሌያዊ መነጽር ሊተረጎም ይገባዋል።   

  1. በመግቢያው የተጠቀሰው 1ኛ ተሰሎንቄ 5፡23 “የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም” የሚለው ነፍስን ጠቅሶ ይናገር የለ?

እርግጥ ነው ነፍስ የሚለው ቃል ተጠቅሷል፤ ነገር ግን በቅድሚያ የተጠቀሰበትን ዐውድ ማስተዋል ይገባል። ሐዋርያው ይህንን ያለው ስለ ነፍስ ለማስተማር ሳይሆን ስለ ቅድስና ለመናገር ነው። “ሁለንተናችሁን ይቀድስ” ካለ በኋላ ስለ መንፈስ፣ ነፍስና ሥጋ የተናገረበትን ምክንያት ሲገልፅ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ” ይላል። ቅድስና ሁለንተናን የሚካትት ነው። የማንነታችን መገለጫ የሆኑት ሦስቱም (መንፈሳዊነት፣ አእምሮ እና አካል) ሳይዛነፉ ካልተቀደሱ ወደ መንግሥቱ ለመግባት አንችልም። ይህ ቅድስና ነው ሙሉ ለውጥ በሕይወታችን የሚያመጣው። ጥያቄውን ለመመለስ፤ በጥቅሱ “ነፍሳችሁን” ተብሎ የተጠቀሰው የግሪክ ቃል “ሱኼ” የሚል ሲሆን ይህም “ትንፋሽ” ወይም “ሕይወት” የሚል ትርጉም አለው። ስለዚህ ጳውሎስ እየነገራቸው ያለው ሁለንተናችሁ እግዚአብሔር ይቀድስና እርሱን ለማየት ያብቃችሁ ነው።

  1. በ2ኛ ቆሮንቶስ 5፡8 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ “ከሥጋ ተለይተን ከጌታ ጋር መኖርን እንደምንመርጥ ርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁ” ይላል። በሥጋ ስንሞት ከክርስቶስ ጋር ነፍሳችን እንደምትሆን እየተናገረ አይደል?

አይደለም! ከዚህ በፊት እንዳጠናነው አዳም የተፈጠረው ከአፈርና ከእግዚአብሔር እስትንፋስ ነው (ዘፍጥረት 2፡7)። ስለዚህ ሰው ሞተ የምንለው አፈር (አካሉ) እና እስትንፋሱ ሲለያዩ ነው። ሰው ሲሞት እስትንፋሱ ወደ እግዚአብሔር እንደሚመለስና አካሉ አፈር እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ዘፍጥረት 3፡19)። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ቦታዎች የሰዎችን ሞት ወይም መጨረሻ ዓመድ ወይም አፈር መሆን ነው ብሎ የሚጠቅሰው ለዚህ ነው (ሚልክያስ 4፡3)። ይህንን ሃሳብ ሳይንስም ይደግፋል። ከዚህ አንጻር በጥያቄው ላይ የተጠቀሰውን የጳውሎስ ሃሳብ ከተጻፈበት ዐውድ አንጻር ስናጤነው መልሱን ቁጥር 7 ላይ እናገኛለን። “ስለዚህ ሁልጊዜ በመታመን እንኖራለን፤ በሥጋ እስካለን ድረስ ከጌታ ርቀን እንደምንገኝ እናውቃለን፤ ምክንያቱም የምንኖረው በእምነት እንጂ በማየት አይደለም” (ቁጥር 6 እና 7)።

ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ በጻፋቸው ሌሎች መልዕክቶቹ ያለ አካል ወይም ከሥጋ ተለይተን ከክርስቶስ ጋር እንኖራለን አይልም (ለማስረጃነት 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡51-55 ያንብቡ)። በትንሣኤ የሚኖረን አካል ጌታችን ከተነሳ በኋላ እንደነበረው የሚታይና የሚዳሰስ አካል እንጂ መንፈስ እንደማንሆን ጳውሎስ ያስተምራል (ፊል. 3፡21)። አሁን የምንኖረው መከራና ሥቃይ በበዛበት የዚህ ምድር ሕይወት እና አዲስ አካል በምናገኝበት በታላቁ የክርስቶስ ዳግም ምፅዓት መካከል ነው። ይህ በሁለቱ ጊዜያት መካከል ያለውን ጊዜ ሐዋርያው ጳውሎስ “ራቁት” የምንሆንበት ማለትም ያለ አካል የምንቆይበት ጊዜ ነው ይለዋል (2ኛ ቆሮንቶስ 5፡3)። ይህንን የራቁትነትን ጊዜ አይደለም ጳውሎስ የሚመኘው፤ ይልቁንም “በዚህ ድንኳን እስካለን ድረስ ከብዶን እንቃትታለን፤ ምክንያቱም ሟች የሆነው በሕይወት እንዲዋጥ ሰማያዊውን መኖሪያችንን ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ አንፈልግም” ይላል (ቁጥር 4)። ጳውሎስ መጪውን ዘላለማዊ ሕይወት በማይታይ አካል የሚኖርበት አድርጎ አይደለም የሚገልጸው፤ ዘላለማዊነት በትንሣኤ ከሚገኝ አዲስ ሕይወት ጋር የተቆራኘ ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 15፡51-55)።

ስለዚህ ለአንድ ክርስቲያን በሥጋ መኖር ማቆም ማለት ወደ አፈር መመለስ ነው፤ ወደ ሞት (ወደ አፈር) የሚሄድ አማኝ ደግሞ በቀጣይ የሚመኘውና የሚያስበው በትንሣኤ ከጌታ ጋር መሆንን ነው። ምክንያቱም አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ቀጥሎ የሚጠብቀው የፍርድ ብያኔን ነው፤ በሌላ አነጋገር አንድ ክርስቲያን ሲሞት ክርስቶስ መጥቶለታል ማለት ነው፤ ስለዚህ ወደፊት የሚመጣውን ትንሣኤ ተስፋ በማድረግ ሥቃይ ሲበዛበትና ሞት ሲመጣበት እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “ከጌታ ጋር መኖርን” እመርጣለሁ ይላል። ሌላው መረዳት የሚገባን ሃሳብ “ከጌታ ጋር ልሁን” የሚለውን የጳውሎስን ጥቅስ የነፍስ አትሞትም ትምህርት መደገፊያ አድርጎ ማቅረብ በሌሎቹ መልዕክቶቹ ጳውሎስ በግልጽና በማያሻማ ማስረጃ ስለ ትንሣኤ በተለይ በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፡51-55 እና 1ኛ ተሰሎንቄ 4፡13-18 በዝርዝር የተናገረውን የሚጻረር ይሆናል።  ጳውሎስ ሰው ሲሞት አፈር እንደሚሆን እና ጌታ ዳግም ሲመለስ ደግሞ ይህ የሚሞተው የማይሞተውን፤ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን እንደሚለብስ የሚያምን ክርስቲያን ነው።        

  1. “ነፍስ አትሞትም” የሚለው ፅንሰ ሃሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ካልሆነ እንዴት በክርስትናው ዓለም ተቀባይነትን አገኘ?

ሰው በተፈጥሮው ሞትን መቀበል አይፈልግም። ሕልምና ተስፋው ከተቀበሩ ወዳጆቹ ጋር መገናኘትና መነጋገር ነው። ይህ ስለሆነ ከጥንት ጀምሮ በዓለም ያሉ ኃይማኖቶችና አምልኮዎች ከሞት በኋላ ባለው ተስፋ ላይ ያጠነጥናሉ። በጥንት ዘመን የግብፅ ነገሥታት ሲሞቱ ነፍሳቸው ከሥጋ ተነጥሎ ወደ አዲስ ኑሮ እንደሚሸጋገር ያምኑ ነበር። ለዚህም ሽግግር ታላቅ ዝግጅት ይደረግ ነበር። እንዲሁም በእስያ ያሉ ሂንዱዎች፣ ቡዲስቶች፣ ዳዊስቶችና ሺንቶዎች ከሞት በኋላ ነፍስ ከሥጋ ተነጥሎ ወደ ተሻለ ሕይወት እንዲሻገር ብዙ ትግልና ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ያስተምራሉ። በአገራችንም ያሉ አንዳንድ መናፍስት ጠሪዎች ከሙታን ጋር መነጋገር እንደሚችሉ ይታመናል። 

ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ የራቀ አስተሳሰብ በምዕራቡ ዓለምም በተለይም በግሪክ ፈላስፎች ሲስተጋባ ቆይቷል። ነፍስ ቅዱስ፤ ሥጋ ደግሞ ክፉ ስለሆኑ ነፍስ ነጻ መውጣቷ ተገቢ ነው ብለው ያምኑ ነበር። በአጠቃላይ ነፍስ አትሞትም፣ ነፍስ ዘላለማዊ ናት የሚለው ዓለማቀፋዊ፣ ሥር የሰደደና ጥንታዊ እምነት ነው። ከዚህ የተነሳ ግብፃውያንና ግሪኮች የክርስትናን እምነት ሲቀበሉ ይህንን ባዕዳዊ አስተሳሰብ እንደተሸከሙ ተጠመቁ፤ ወደ ክርስትና ይዘውት ገቡ። በፊትም ከሰዎች አስተሳሰብ፣ ምኞትና ፍልስፍና ጋር የተጣጣመ ስለነበር ወደ ክርስትና ሰርጎ ሲገባ ብዙ ተቃውሞ የገጠመው አይመስልም።

ሆኖም እውነት በሰዎች ፍላጎትና ጥንታዊ ፍልስፍናዎች የሚወሰን አይደለም። የእግዚአብሔር ቃል ስለ ሞት የሚናገረው እውነት ለትዕቢተኛው ልባችን መራራ ነው። ገና ከውልደታችን ጀምሮ እጅግ በርካታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ትምህርቶችን ስንሰማና ስንማር ስለቆየን እውነተኛውን ትምህርት ለመቀበል ሊያዳግት ይችላል። ሆኖም መታወቅ ያለበት ዋንኛው ጉዳይ “የክፉ ሰው ነፍስ ለዘላለም እየተቃጠለች ትኖራለች” የሚለው አስተሳሰብና አስተምህሮ ከአፍቃሪ አምላክ ባህርይ ጋር ፈጽሞ የሚጣጣም አለመሆኑ ነው። በእርግጥ አፍቃሪው አምላካችን ሰዎችን ለዘላለም በማቃጠል የሚደሰት ነውን? የሰው ልጅ እንኳን ሊፈጽመው የማይችለው ይህ ዓይነቱ ጭከና እንዴት ነው ልጁን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለምን ሁሉ የወደደው እግዚአብሔር ዘንድ ሊኖር የሚችለው? እንዴት ነው አንድ ሰው በአማካይ በሕይወት በሚኖራት 60 እና 70 ዓመት ለሠራው መጥፎ ሥራ ለዘላለም በመቃጠል የሚቀጣው? እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን በመጠየቅ ይህን ወሳኝ ጉዳይ በጥልቀት እንዲመረምሩ ልናሳስብዎ እንወዳለን።

ድርባ ፈቃዱ እና ጥበበሥላሴ መንግሥቱ

ይህንን ጽሑፍ ሙሉውን በፒዲኤፍ (PDF) ለማንበብም ሆነ ለማተም እዚህ ላይ በመጫን ወይም ከታች Download የሚለውን በመጫን ማውረድ ይቻላል።


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *