ስለ ሰው ተፈጥሮ ጥናት የሚያደርጉ ሰዎች ከሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ “የሰው ተፈጥሮ ምን ምን ያካተተ ነው?” የሚለው ነው። ታዲያ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሦስት የተለያዩ አመለካከቶችን ያቀርባሉ። አንደኛው ምልከታ በ1ኛ ተሰ. 5፡23 ላይ የሚመረኮዝ ሲሆን ይህም፤ ሰው መንፈስ፣ ነፍስና ሥጋ (አካል) የተባሉ ሦስት ክፍሎችን የያዘ ነው የሚለው ነው። ይህ አመለካከትም ትራይኮቶሚ (ሦስትነት) በመባል ይታወቃል።
ሁለተኛው አመለካከት ደግሞ በዘፍ. 2፡7 ላይ የተመሠረተው ሲሆን ይህም ሰው ከአፈርና ከእግዚአብሔር እስትንፋስ በመሠራቱ ሁለት ነገሮችን ያካተተ ነው ይለናል። እነዚህም ማቴሪያላዊ (ቁሳዊ) የሆኑና ያልሆኑ በመባል ይከፈላሉ። ቁሳዊ በመባል የሚታወቀው ክፍል እንደ ደም ሥር፣ ኩላሊት፣ ጭንቅላት፣ እጅ፣ እግርና የመሳሰሉትን የሚያካትት ሲሆን ቁሳዊ ያልሆነው ክፍል ደግሞ ነፍስ፣ መንፈስ፣ አእምሮ፣ ኅሊና፣ ፈቃድ የመሳሰሉት ናቸው ይላል። ይህ ዓይነት የሰው ተፈጥሮ አገላለጽ ደግሞ ዳይኮቶሚ (ሁለትነት) በመባል ይታወቃል።
ሦስተኛው የሰውን ተፈጥሮ የሚገልጸው ሃሳብ በተመሳሳይ መልኩ መነሻ ጥቅሱ ዘፍ. 2፡7 ሲሆን ነገር ግን የሰውን ተፈጥሮ እንደ ሁለት ማየት ትቶ እንደ አንድ ውኁድ አድርጎ የሚያይ ነው። ይህም አመለካከት ሰው መንፈስም፣ ነፍስም፣ ሥጋም ልብም ሆነ ኅሊናም ቢኖረውም፤ እነዚህ አንዱ ከሌላው ተነጣጥለው ኅልውና የሌላቸው ናቸው፤ ስለዚህ ሰው ተነጣጥለው ኅልውና የሌላቸው ክፍሎች ውህድ ውጤት ነው ይላል። በዚህ ምክንያት ይህ አመለካከት ሞኒዝም (አንድ-ነት) በመባል ይታወቃል።
እነዚህ ሦስት አመለካከቶች ልዩነታቸው ጎልቶ የሚወጣው “ሰው ሲሞት ምን ይሆናል?” የሚለውን ጥያቄ በምንጠይቅበት ጊዜ ነው። የትራይኮቶሚና የዳይኮቶሚ ሃሳብ አራማጆች ሰው ሲሞት ነፍሱ ከሰውነቱ ተለይታ ኅልውና እንዳላት ሲያስተምሩ፤ የሞኖይስት ሃሳብ አራማጆች ደግሞ ነፍስ ከሰውነት ተነጥላ ኅልውና ሊኖራት አይችልም፤ ነፍስ ማለት ሰው ነው፤ ስለዚህ ሰው ሲሞት ነፍስም ትሞታለች በማለት ያስተምራሉ።
ሁላችንም እንደምናውቀው ሞት እጅግ ከማይስተዋሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው። ለብዙዎች ሞት በምሥጢር የተሸፈነ፣ ፍርሃትንና ተስፋ መቁረጥን የሚጭርና በሕይወት እርግጠኛ ባለመሆን መዋለልን የሚፈጥር ጉዳይ ነው። የሚገርመው አንዳንዶች የሚወዷቸው ሰዎች ቢሞቱም እንዳልሞቱ፤ እንዲያውም በሆነ መንገድ አብረዋቸው እንደሚኖሩ ያስባሉ። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ በሥጋ፣ በነፍስና በመንፈስ መካከል ያለው ግንኙነትና ልዩነት ተምታቶባቸዋል።
በዘመናችን ሰይጣናዊ የሆኑ የተለያዩና በርካታ ማታለያዎች ተስፋፍተው ስላሉ ሞትን በተለመከተ እያንዳንዳችን የምንወስደው አቋም ወሳኝነትና አስፈላጊነት ስላለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረዳት ማግኘት እጅግ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ለግምታዊ አስተሳሰብ ምንም ክፍተት ሳንሰጥ ሰው ሲሞት ምን ይሆናል? የሚለውንና ሌሎች ተያያዥ ርዕሰጉዳዮችን እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ የገለጠውን ለመረዳት በጸሎት መንፈስ እናጥና። ከሰው አፈጣጠር እንጀምር፤
1. ሰው በምድር ላይ እንዴት ተፈጠረ?
“እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወሰዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ” (ዘፍ. 2፡7)። በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰውን ከምድር አፈር ወስዶ ካበጀውና የራሱን የአምላክን “እስትንፋስ እፍ” ካለበት በኋላ ሰው ሕያው ነፍስ ሆነ። ይህ የሆነው የአምላክ የህይወት እስትንፋስ ከአፈር ከተሠራው በድን የሰው አካል ጋር ሲደመር ነው፤ ማለትም ሁለቱ (የአምላክ እስትንፋስና ከአፈር የተሠራው የሰው አካል) ሲደመሩ፣ ሲጣመሩ ሰው ሕያው ነፍስ ሆነ።
2. ሰው ሲሞት ምን ይሆናል?
“ዐፈር ወደ መጣበት መሬት ሳይመለስ፣ መንፈስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ፣ ፈጣሪህን አስብ” (መክብብ 12፡7)። እዚህ ላይ የምንረዳው ሰው ሲሞት አካሉ ወደ አፈር (መሬት)፣ እስትንፋሱ ደግሞ ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር እንደሚመለስ ነው፤ ይህ ክስተት የሚፈጸመው በዚህ ምድር ላይ በሚገኙ ኃጢአንም ሆነ ጻድቃን ላይ ልዩነት ሳያደርግ ነው። እዚህ ላይ በተጨማሪ ልብ ማለት ያለብን ከላይ የተጠቀሰውን “ሳይመለስ” የሚለውን ቃል ነው። ከቃሉ በምናገኘው መረዳት መሠረት ሞት ማለት ሁሉ ነገር ቀድሞ ወደ ነበረበት ሁኔታ መመለስ ማለት ነው፤ ሞት ዐፈሩን (የሰውን አካል) ወደ መሬት፤ እስትንፋሱን ደግሞ ወደ ሰጠው እግዚአብሔር ይመልሳልና። ለምሳሌ በኬምስትሪ ትምህርት መሠረት ውሃ የሁለት እጅ ሃይድሮጅንና የአንድ እጅ ኦክስጅን ውህደት ውጤት ነው። እነዚህ ሁለት ንጥረነገሮች ሲዋሃዱ ውሃ ይፈጠራል፤ ሲለያዩ ደግሞ ውሃ አይኖርም። የሰውም በሕይወት መኖር የአምላክ እስትንፋስና የምድር ዐፈር ውህደት የፈጠረው ሲሆን ሰው ሞተ ስንል ደግሞ የእነዚህ ሁለት ነገሮች ተነጣጥለው ወደ መጡበት መመለስ ነው።
3. ሰው ሲሞት ከእርሱ ወጥቶ ወደ እግዚአብሔር የሚሄደው እስትንፋስ ምንድነው?
“ከመንፈስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ ከሥራም የተለየ እምነት የሞተ ነው” (ያዕ. 2፡27)። “በውስጤ የሕይወት እስትንፋስ፣ በአፍንጫዬም ወስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ እስካለ ድረስ” (ኢዮብ 27፡3)። በመጽሐፍ ቅዱስ አነጋገር ከሰው ወደ እግዚአብሔር የሚመለሰው መንፈስ የሕይወት እስትንፋስ ነው። ይህ እስትንፋስ ወይም መንፈስ ከአካል ተለይቶ የሟቹን ግለሰብ የሚወክል ጥበብ ወይም እውቀት ሆነ ስሜት ወይም ማንነት እንዳለው የሚያስረዳ አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የለም።
4. ታዲያ ነፍስ ማለት ምን ማለት ነው?
ከላይ በተጠቀሰው ዘፍጥረት 2፡7 መሠረት “ነፍስ” ማለት የሕይወት እስትንፋስ ከአፈር ከተሠራው አካል ጋር ሲገናኝ የሚፈጠረው ሕይወት ያለው ፍጡር ነው። ይህ ነፍስ ወደ ኅልውና የመጣው እስትንፋስና አካል ተገናኝቶ ወይም ተደምሮ በመሆኑ ሁለቱ በተለያዩ ቀን የነፍስ ኅልውና ያከትማል። ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ “ነፍስ” ተብሎ እንደሚጠራ እናነባለን። በቀላሉ “አምስት ሰዎች” ያሉበት ቦታ “አምስት ነፍሳት” ያሉበት ሊባል ይቻላል።
5. ነፍስ ይሞታል?
“ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች” (ሕዝ. 18፡20)። “በባሕርም ከሚኖሩት ሕይወት ያለበት ነፍስ ሁሉ ሞተ” (ራዕይ 16፡3)። እንደ እግዚአብሔር ቃል አገላለጽ ነፍስ ይሞታል። ምክንያቱም የአምላክ እስትንፋስና የአፈር ውኁድ የሆነው ሰው ነፍስ ነው፤ ነፍስ (ሰው) ደግሞ ይሞታል፤ ስለዚህ ሰዎች ሁሉ ሟች ናቸው (ኢዮብ 4፡17)። የማይሞተው እግዚአብሔር ብቻ ነው (1ጢሞ. 6፡15፣16)። ይህ በመሆኑም ሰው ሲሞት ተለይታ የምትወጣ የዘላለማዊ ነፍስ (የማይሞት ነፍስ) አለች የሚለው ጽንሰሀሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም።
6. መልካም ሰዎች ሲሞቱ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ?
“በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉ ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ” (ዮሐ. 5፡28፣29)። “ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። … ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና” (የሐዋ. 2፡29፣34)። ሰዎች ሲሞቱ ወደ ሰማይም ሆነ ወደ ገሃነም አይሄዱም። ይልቁኑ እስከ ትንሳዔ ቀን ድረስ በመቃብራቸው ሆነው እንደ ዳዊት የትንሣኤን ቀን ይጠብቃሉ።
7. ሰው ከሞተ በኋላ ምን ያህል ያስተውላል?
“ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቷልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም። ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ጠፍቶአል፥ ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘላለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም። … አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ” (መክብብ 9፡5፣6፣10)። “አቤቱ፥ ሙታን የሚያመሰግኑህ አይደሉም፥ ወደ ሲኦልም የሚወርዱ ሁሉ” (መዝ. 115፡17)። በእነዚህ ጥቅሶች መሠረት ሙታን አንዳች አያውቁም።
8. ሙታን ሕያዋን የሚሠሩትን ያውቃሉ? ከሕያዋን ጋር መገናኘት፣ መነጋገር ይችላሉን?
“ሰውም ተኝቶ አይነሣም፤ ሰማይ እስኪያልፍ ድረስ አይነቃም፥ ከእንቅልፉም አይነሣም። … ልጆቹ ቢከብሩ አያውቅም፤ ቢዋረዱም አያይም” (ኢዮብ 14፡12፣21)። “ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘላለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም” (መክብብ 9፡6)። ሙታን በዚህ ምድር ላይ በሚፈጸመው ማንኛውም ነገር ላይ ተሳትፎ የላቸውም። ስለዚህ ማንኛውንም ሕያው ሰው አያናግሩም፤ በዚህ ምድር ላይ የሚፈጸምን አንዳች ነገር አያውቁም፤ ሃሳባቸው ሁሉ ጠፍቷል (መዝ. 146፡4)።
9. በዮሐ 11፡11-14 ላይ ክርስቶስ ሞትን በእንቅልፍ መስሎታል። ታዲያ ሙታን ለምን ያህል ጊዜ ያንቀላፋሉ?
“ሰውም ተኝቶ አይነሣም፤ ሰማይ እስኪያልፍ ድረስ አይነቃም፥ ከእንቅልፉም አይነሣም” (ኢዮብ 14፡12)። “የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ” (2 ጴጥ. 3፡10)። ሙታን በመቃብራቸው ውስጥ በእንቅልፍ የሚቆዩት ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን እስከሚደርስና ሰማያት እስከሚያልፉ ድረስ ነው። እስከዚያ ድረስ ግን አንዳች የሚያውቁት ሳይኖር በመቃብራቸው ውስጥ ይቆያሉ።
10. ክርስቶስ ዳግመኛ በሚመጣበት ጊዜ የሞቱት ጻድቃን ምን ይሆናሉ?
“ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤… እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን” (1ተሰ. 4፡16፣17)። “እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን።…ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና”(1ቆሮ. 15፡51-53)።
ሙታን በትንሳኤ ቀን በማይሞት ሥጋ ይነሳሉ። ጌታን በአየር ላይ ለመገናኘት ወደ ሰማይ ይነጠቃሉ። ሽልማታቸውን ይቀበላሉ (ራዕይ 22፡12)። እንግዲህ ሰዎች እንደሞቱ ወደ ሰማይ የሚሄዱ ቢሆን ኖሮ መጽሐፍ ቅዱስ የትንሳኤን አስፈላጊነት ይህን ያህል አጉልቶ አይናገርም ነበር።
11. በዚህ ምድር ላይ የመጀመሪያው የሰይጣን ውሸት ምንድን ነበር?
“እባብም ለሴቲቱ አላት፦ ሞትን አትሞቱም” (ዘፍ. 3፡4)። “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ” (ራዕይ 12፡9)። በኤድን ገነት ሔዋንን ያሳታት “እባብ” ተብሎ የተጠቀሰው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ ራዕይ 12፡9 ተርጉሞታል። በወቅቱም ሰይጣን በእባብ ተመስሎ ለሔዋን ያላትና የመጀመሪያው ውሸት “አትሞቱም” የሚለው ነበር፤ እግዚአብሔር ግን “ከፍሬዋ በበላችሁ ጊዜ ሞትን ትሞታላች” ብሎ ነበር። አሁንም ከዋንኞቹ የሰይጣንን ማሳሳቻ ትምህርቶች አንዱ “አትሞቱም” የሚለው ሲሆን ይህም ማለት ሰው ሲሞት ነፍሱ ወደ ገነት ወይም ወደ ሲዖል ትሄዳለች፣ ነፍስ አትሞትም፣ ከሙታን ጋር እናገኛለን፣ ወዘተ የሚባሉት የክርስትናን ካባ የደረቡ ትምህርቶች ናቸው። (ለምሳሌ የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ማንበብ ይጠቅመናል፤ የግብፅ አስማተኞችና ጠንቋዮች—ዘፀ. 7፡11፤ በዓይንዶር የምትገኘዋ መናፍስት ጠሪ—1ሳሙ. 28፡3-25፤ የባቢሎን ጠንቋዮች—ዳን. 2፡2፤ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት አንዲት ሴት—ሐዋ. 16፡16-18)።
12. በርግጥ አጋንንት ተአምራትን ይሠራሉ?
“… ምልክት (የሚያደርጉ) የአጋንንት መናፍስት ናቸውና፥” (ራዕይ 16፡14)። “ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ” (ማቴ. 24፡24)።በርግጥ ሰይጣን አስደናቂ የሚባሉ ተአምራቶችን ይሠራል፤ “… በሰዎቹም ፊት እሳት ከሰማይ ወደ ምድር እስኪያወርድ ድረስ ታላላቅ ምልክቶችን አደረገ” (ራዕ 13፡13፣14)። “ሰይጣን የብርሃን መልአክ እስኪመስል ድረስ ራሱን ይለውጣል” (2ቆሮ.11፡14)። ክርስቶስ ነኝ ብሎ ራሱን ይገልጣል (ማቴ. 24፡23፣24)።
13. ታዲያ የእግዚአብሔር ሕዝብ በሰይጣን ማታለያዎች እንዳይሳሳት ምን ያስፈልገዋል?
“እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና፦ ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ” (የሐዋ ሥራ 17፡11)። “ወደ ሕግና ወደ ምስክር ሂዱ! እንዲህም ያለውን ቃል ባይናገሩ (ወይም በእነዚህ ላይ ተመሥርተው የማይናገሩ ከሆነ) ንጋት አይበራላቸውም” (ኢሳ. 8፡20)። የእግዚአብሔር ልጆች መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠኑ ሙታን በርግጥ የሞቱ እንጂ በህይወት የሌሉ መሆናቸውን ይረዳሉ። የሚወዷቸውን የሞቱ ሰዎች መስሎ የሚታይ ማንኛውም ነገር ወይም መንፈስ የሰይጣን እንጂ የአምላክ መንፈስ አለመሆኑን ይረዳሉ።
14. ጻድቃን በትንሳኤ ከሞት ከተነሱ በኋላ እንደገና የመሞት አደጋ አለባቸውን?
“ያን ዓለምና ከሙታን ትንሣኤ ሊያገኙ የሚገባቸው እነዚያ ግን አያገቡም አይጋቡምም፥ እንደ መላእክት ናቸውና፥ ሊሞቱም ወደ ፊት አይቻላቸውም፥ የትንሣኤም ልጆች ስለ ሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው” (ሉቃ. 20፡35፣36)። “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ”(ራዕ. 21፡4)። “ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ፦ ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል” (1 ቆሮ.15፡54)።
ሰይጣን – እንደ ብርሃን መልአክ፤ ሰይጣንና መላዕክቱ እጅግ በርካታ የሆኑ ሰዎችን ለማታለል ከዚህ በፊት የሞቱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ነብያትን፣ ሐዋርያትንና ቅዱሳንን በመምሰል የብርሃን መልአክ መስሎ ይገለጻል፤ “…ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋውጣል” (2ቆሮ.11፡13)። ሰይጣን ሰዎችን ለማታለል የሚጠቀምበት አንዱ መንገድ “እኔ ኢየሱስ ነኝ” በማለት ነው። ከዚህም ሌላ ልክ ጌታችንና መድኃኒታችን ከቃና ዘገሊላ ጀምሮ በርካታ ተዓምራትና ድንቅ ያደርግ እንደነበረው ሰይጣንም እንዲሁ በተዓምራት ሰዎችን ለመጥለፍ በረቀቀ መልኩ ይጠቀማል። የተለያዩ በሽታዎችን “ፈውስ” አስመልክቶ “ተዓምራት” ከማድረግ ጀምሮ ሙታንን ያስነሳ እስኪመስል ድንቆችን ያደርጋል። በመሆኑም “ሙታን በሆነ መልኩ በሕይወት አሉ” ብለው የሚያምኑ ሰዎች በእንደዚህ አይነቱ የሰይጣን ማታለያ ተጠልፎ ለመውደቅ በጣም ቅርብ ናቸው።
ቅንብር፤ ፓስተር መስፍን ማንደፍሮ