ለሥራ ጉዳይ ሩቅ ቦታ ሄደው፣ ሰውነትዎን መታጠብ ሳይችሉ ቀርተው፣ ሁኔታው ምቾት አልሰጥ ብሎዎት፤ መለቃለቂያ ያለበት ቦታ ለመድረስ ጓጉተው ያውቃሉ? ከታጠቡ በኋላስ ምን ተሰማዎት? አልቀለለዎትም? እንደዚሁ በተናገሩት ውሸት ኅሊናዎ ቆሽሾ፣ የሚወዷቸውን ሰዎች በመጉዳትዎ ተጸጽተው፣ አንዳንድ የፈጸሟቸው ተንኮሎችና የድፍረት ኃጢአቶች ትዝ ብለዎት፣ የውስጥ ሰውነትዎ እንደቆሸሸ የተሰማዎት ጊዜ የለምን? ንጉሡ ዳዊት እንደዚህ ተሰምቶት ያውቃል፤ ስለዚህ ሲፀልይ እንዲህ አለ፤ “አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ። ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤ እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና። አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥ በነገርህም ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ።… በሂሶጵ እርጨኝ፥ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ፥ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ” (መዝ. 51፡1-4፣7)። ዛሬ እኛም ለእርስዎ የሚሆን የምሥራች አለን።
ልክ ለዳዊት እንዳደረገው፤ እግዚአብሔር እነዚህን ዕረፍት የሚነሱ የኃጢአት ትውስታዎችንና ኃጢአትዎን ሁሉ በክርስቶስ ይቅር ብሎ “ከበረዶ ይልቅ ነጭ” ሊያደርግዎት ዛሬም ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤ “ንጹሕ ውሃ እረጫችኋለሁ፤ እናንተም ንጹሕ ትሆናላችሁ”(ሕዝ. 36፡25)። ጌታ ክርስቶስን የግል አዳኝዎ አድርገው ሲቀበሉ፤ እግዚአብሔር የቀድሞ ኃጢአትዎን ሁሉ ይቅር ይልዎታል፤ ሕይወትዎንም ይለውጣል። የከዚህ በፊት የኃጢአት ልምምድዎን ለማሸነፍ የሚያስችል የመንፈስ ኃይል ይሰጥዎታል። ለመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መስቀል 28 ጊዜ፣ ጥምቀት ደግሞ 97 ጊዜ መጠቀሱን ያውቃሉ? እንግዲህ ይህ የሆነበት ምክንያት ጥምቀት እጅግ አስፈላጊና በክርስቶስ ያገኘነውን አዲስ ሕይወት የሚወክል በመሆኑ ነው። ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥምቀት ምን ይላል? እስቲ የሚያስተምረውን እናጥና፤
1. በውኑ ጥምቀት ይህን ያህል አስፈላጊ ነው?
“ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል” (ማር. 16፡16)። አዎ! ጥምቀት አስፈላጊ ነው። እንግዲህ በጥቅሱ ከተገለጸው በላይ እንዴት ግልጽ መሆን ይቻላል? መጠመቅ ወሳኝ ተግባር ነው።
2. በመስቀል ላይ የነበረው ወንበዴ አልተጠመቀም፤ ታዲያ እኛ ለምን እንጠመቃለን?
“ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፥ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ” (መዝ. 103፡14)። በመስቀል ላይ የነበረው ሌባ በሕዝቅኤል 33፡15 ላይ እግዚአብሔር እንደተናገረው የሰረቀውን ለመመለስ እንኳን ዕድል አላገኘም። እግዚአብሔር የአቅማችንን ውስንነትና አፈር መሆናችንንም ይገነዘባል፤ እርሱም እኛን ተጠያቂ የሚያደርገን ማድረግ በምንችለው ነገር ነው። ከአቅማችን በላይ የሆነን ነገር አይጠይቅም። አንድ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ነገር ሌባው ከመስቀል ላይ በሰላም ወርዶ ቢሆን ኖሮ ለመጠመቅ የማያንገራግር ለመሆኑ ነው። ምክንያቱም በዚያ አስቸጋሪ ሰዓት መድኃኒዓለምን ፈጣሪና አዳኝ አድርጎ ለመቀበል ከወሰነ ለመጠመቅ ብዙም አይከብደውም። ስለዚህ ማንኛችንም ከመጠመቅ ወደኋላ ማፈግፈግ የለብንም።
3. የተለያዩ የጥምቀት ዓይነቶች አሉ፤ ታዲያ የተጠማቂዎች ልብ ቅን እስከሆነ ድረስ በየትኛውም መልኩ ቢጠመቁ ምን ችግር አለው?
“አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት” (ኤፌ. 4፡5)። የትኛውም ዓይነት ጥምቀት ተቀባይነት የለውም። እውነተኛ ጥምቀት አንድ ብቻ ነው። “ጥምቀት” ተብለው የሚጠሩ ሌሎች እውነተኛውን የሚመስሉ ማሳሳቻዎች አሉ። “ጥምቀት” የሚለው ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ በግሪክኛ “ባፕቲዝማ” ከሚል የተወሰደ ነው። ትርጉሙም “ወደ ውስጥ መንከር፣ ማጥለም ወይም ማስመጥ” የሚል ነው። በግሪክኛ በተጻፈው አዲስ ኪዳን የፈሳሽን አጠቃቀም የሚገልጹ ስምንት አይነት ቃላት ጥቅም ላይ ውለዋል። እነዚህ የተለያዩ ቃላት ስንጠቀልላቸው መርጨት፣ ማፍሰስ ወይም ማጥለም የሚሉት ፍቺ የሚሰጡ ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ ጥምቀትን በሚገባ የሚገልጸው ማጥለም የሚለው ቃል ብቻ ነው።
በአንድ ወቅት የተነገረ ማሳሳቻ እንዲህ ይላል፤ “በየትኛውም የጥምቀት ዓይነት መጠመቁ ዋና ነገር ስላይደለ በወደድከው የአጠማመቅ ዓይነት መጠመቅ ትችላለህ፤ ወሳኝነት ያለው ነገር መንፈሱ በአንተ ላይ ማረፉ ነው”። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱሳችን የሚነግረን “አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት” ብሎ ነው። በተጨማሪም “እኔ የምነግርህን የእግዚአብሔርን ቃል እባክህ፥ ስማ፤ ይቀናሃል ነፍስህም በሕይወት ትኖራለች” ይለናል ቃሉ (ኤር. 38፡20)።
4. ኢየሱስ በየትኛው የጥምቀት ዓይነት ነው የተጠመቀው?
“በዚያ ወራትም ኢየሱስ ከገሊላ ናዝሬት መጥቶ ከዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ። ወዲያውም ከውኃው በወጣ ጊዜ ሰማያት ሲቀደዱ መንፈስም እንደ ርግብ ሲወርድበት አየና፦ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅ ከሰማያት መጣ” (ማር. 1፡9፣10)። ኢየሱስ የተጠመቀው በጥልቅ ነው። “ከውኃው በወጣ ጊዜ” የሚለው አገላለጽ ይህንን እውነታ በግልጽ ያሳያል። ኢየሱስ የተጠመቀው አንዳንዶች እንደሚያስቡት ከወንዙ ዳር ውሃ በመርጨት ወይም ውሃ ራሱ ላይ በማፍሰስ ሳይሆን በዮርዳኖስ ውስጥ በመጥለቅ ነው። ስለ መጥምቁ ዮሐንስም መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና ያጠምቅ ነበር” ይላል (ዮሐ. 3፡23)። ይህ የሆነበት ምክንያት የሚያጠምቃቸውን ሰዎች በሚገባ ሙሉ ሰውነታቸውን ለማጥለም እንዲያመቸው ነበር። መጽሐፍ ቅዱሳችንም የኢየሱስን ምሳሌ እንድንከተል ይመክረናል (1ጴጥ. 2፡21)።
5. የመጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የማጥመቁን ዓይነት ቀይረው ይሆን?
“ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም። ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፥ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና” (የሐዋ. ሥራ 8፡38፣39)። የቀድሞ ቤ/ክ መሪዎች ሥርዓቱን አልቀየሩትም! ከመጀመሪያዎቹ መሪዎች አንዱ የሆነው ፊሊጶስ፤ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ያጠመቀው ልክ መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን እንዳጠመቀው ብዙ ውሃ በሚገኝበት ቦታ በማጥለቅ ነበር። አንድ ግልጽ ማድረግ ያለብን ነገር ማንም ሰው በቤተክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛ የሥልጣን ቦታ ቢኖረውም እንኳ ይህንን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ መለወጥ አይችልም።
6. በጥልቀት ከመጠመቅ የተለየ የአጠማመቅ ዘዴ ወደ ቤተክርስቲያን ያስገባው ማን ነው?
“የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል” (ማቴ. 15፡9)። የእግዚአብሔርን ቃል በተሳሳተ መንገድ የተረጎሙ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩ የአጠማመቅ ዓይነቶችን ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገብተዋል። መድኃኒዓለም ግን “እናንተስ ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ምን ትተላለፋላችሁ? … ስለ ወጋችሁም የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ” ብሏቸዋል (ማቴ. 15፡3፣6)። የሰውን ትምህርት በመከተል የሚፈጸም አምልኮ ከንቱ ነው። መዘዙ ትንሽ እንደሆነ በመገመት፤ ሰዎች በዚህ በተቀደሰ የጥምቀት ሥርዓት ውስጥ የራሳቸውን ግምታዊ አስተሳሰብ በመጨመር የመጽሐፍ ቅዱሱን ትምህርት አዛብተዋል። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንደዚህ በማለት ያስጠነቅቀናል፤ “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ” (ይሁዳ 3)።
7. አንድ ሰው ራሱን ለጥምቀት ለመዘጋጀት ምን ማድረግ አለበት?
ሀ. እግዚአብሔር በቃሉ ያዘዘው ምን እንደሆነ መማር፤ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ. 28፡19፣20)።
ለ. የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኝነት ማመን፤ “ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል” (ማር. 16፡16)።
ሐ. ንስሐ በመግባት ከኃጢአት መመለስና መለወጥ፤ “ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።” (የሐዋ. 2፡38)። “ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም” (የሐዋ. 3፡19)።
8. ለመሆኑ የጥምቀት ትርጉም ምንድን ነው?
“እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን። ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤ ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና” (ሮሜ 6፡4-6)።
ጥምቀት ራሳችንን ከክርስቶስ ሞት፣ ቀብርና፣ ትንሳኤ ጋር አንድ ማድረግ ማለት ነው። እንደዚህ የጠለቀ ትርጉም አለው። በጥምቀት ጊዜ ልክ እንደ ሞተ ሰው ዓይናችንን እንጨፍንና መተንፈስ እናቋርጣለን። በመቀጠልም በውሃ ውስጥ ተቀብረን በክርስቶስ አዲስ ህይወት ለመኖር በመወሰን ከውሃ መቃብር ውስጥ በትንሳኤ ምሳሌ እንነሳለን። በትንሳኤ ምሳሌ ከውሃ ውስጥ ከወጣን በኋላም ዓይናችን ተከፍቶ በመተንፈስ ከወዳጆቻችን ጋር እንቀላቀላለን። ክርስትና ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ሲነጻጸር ያለው ትልቁ ልዩነት የክርስቶስ ሞት፣ መቀበርና ትንሳኤ ነው። እግዚአብሔር እነዚህን ሦስት ዋና እውነቶች በሃሳባችን ታትመው እንዲጸኑና እስከ ዘመን መጨረሻ እንድናስታውሳቸው ይህንን የጥምቀት ስርዓት ፈጠረ። ስለዚህ ትክክለኛው የጥምቀት ዓይነት በሮሜ 6፡4-6 የተገለጸው በውሃ ውስጥ በመጥለቅ የሚደረገው ብቻ ነው።
9. ከመጠመቃችን በፊት ኃጢአት መሥራት ማቆም መቻላችንን እርግጠኛ መሆን አለብን?
“ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” (1ዮሐ. 2፡1)። ይህ ጥያቄ አዲስ የተወለደ ህፃን ለመራመድ ሲሞክር አይንገዳገድ ወይም አዳልጦት አይውደቅ እንደ ማለት ነው። እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ መንገዳገድም መውደቅም አይቀርም። ክርስቲያን አሁን በክርስቶስ እንደተወለደ አዲስ ህፃን ማለት ነው። ለዚህ ነው የክርስትና ልምምድ “እንደገና መወለድ” ተብሎ የሚጠራው። ሰው በክርስቶስ እንደገና ሲወለድ ድሮ የሠራው ኃጢአት ሁሉ ይቅር ተብሎ ተረስቷል። ጥምቀትም የዚያ የድሮ ኃጢአተኛ ሕይወቱና ምኞቱ የመቀበር ምሳሌ ነው። እኛም ይህንን የክርስትና ሕይወት ስንጀምረው እንደ ሕፃን ሆነን እንጂ እንደ አዋቂ ሆነን አይደለም። እግዚአብሔርም የሚፈርድብን በሕይወታችን በያዝነው አቅጣጫና ዝንባሌያችን እንጂ እንዳልበሰሉ ክርስቲያኖች በፈጸምናቸው ውድቀቶችና ድርጊቶቻችን አይደለም።
10. ወደ እግዚአብሔር ልቡን ለመለሰ ሰው መጠመቅ አስፈላጊና አስቸኳይ የሚሆንበት ምክንያት ምንድን ነው?
“አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ” (የሐዋ ሥራ 22፡16)። ጥምቀት አንድ ሰው ከኃጠአቱ የመመለሱ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአቱ ይቅር የመባሉና የመንጻቱን ልምምድ በሕዝብ ፊት በማወጅ የሚመሰክርበት ነው (1ዮሐ. 1፡9)። ከእንግዲህ ወዲህ የድሮ ኃጢአታችን የተረሳ ነው። ሰው ከተመለሰ በኋላ እርሱን ሊያስጠይቅ የሚችል ምንም ዓይነት የመክሰሻ ጉዳይ አይኖርም። ዛሬ ሰዎች በከባድ የኃጢአትና የበደለኝነት ሸክም ሥር እየተንገላቱና እየታገሉ ይገኛሉ። ይህ ሸክም ለማስወገድና ይቅርታን ለማግኘት ሲሉ ሰዎች ማንኛውንም ርቀት ይሄዳሉ። ነገር ግን እውነተኛ ዕርዳታ የሚገኘው “እወዳለሁ፥ ንጻ” ብሎ በመናገር ወደሚፈውሰው ኢየሱስ በመምጣት ነው (ማቴ. 8፡3)። እግዚአብሔር ከኃጢያት ማንጻት ብቻ ሳይሆን በውስጣችን የሚገኘውን የድሮውን የኃጢአት ተፈጥሮ ይሰቅለዋል። ይህንን አስደናቂውን የኢየሱስ ጸጋ በሕዝብ ፊት መቀበላችንን የምናሳየው በጥምቀት በመሆኑ ጥምቀትን እጅግ አስፈላጊ ያደርገዋል።
ስለዚህ አንድ ሰው ልቡን ወደ እግዚአብሔር ሲመልስ፤ እግዚአብሔር፤ (ሀ) ኃጢአቱን ይቅር ይለውና ይረሳለታል፤ (ለ) አዲስ መንፈሳዊ ህይወት በመስጠት በየጊዜው ይለውጠዋል፤ (ሐ) ልጁ አድርጎ ይቀበለዋል።ክርስቶስ የሰው ልጆችን ሕይወት በመለወጥ ለሠራው ተዓምር በሕዝብ ፊት የሚሰጥ ግልጽ ምስክርነት ቢኖር ጥምቀት ነው። ስለዚህ በርግጥ ልቡን ወደ እግዚአብሔር የመለሰ ሰው ለመጠመቅ ጭራሽ ማዘግየት የለበትም።
11. አንድ ሰው ከመጠመቁ አስቀድሞ ምን ያህል ዝግጅት ያስፈልገዋል?
ይህ ጉዳይ ከሰው ሰው ሊለያይ ይችላል፤ ምክንያቱም አንዳንድ ሰው ቶሎ የመረዳት ዓቅም ሲኖረው ለሌሎች ደግሞ ጊዜ ይወስድባቸዋል። ይሁን እንጂ ለጥምቀት የሚያስፈልገውን ዝግጅት ማሳጠር ይቻላል። የሚከተሉትን ምሳሌዎች እንመልከት፤ (ሀ) ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ (ሐዋ. 8፡26-39) የተጠመቀው በተመሰከረለት የዚያኑ ቀን ነበር። (ለ) በፊልጵስዩስ ከተማ የነበረው የእስር ቤት ጠባቂውና ቤተሰቡ የእውነትን ቃል በሰሙበት በዚያች ሌሊት ተጠመቁ (ሐዋ. 16፡23-34)። (ሐ) የተርሴሱ ሳኦል (ጳውሎስ) የተጠመቀው ኢየሱስን በደማስቆስ መንገድ ላይ ከተገናኘ ሦስት ቀን በኋላ ነበር (ሐዋ. 9፡1-18)። (መ) ቆርኔሊዮስ የተጠመቀው የእውነትን ቃል በሰማበት ዕለት ነበር (ሐዋ. 10)።
12. ልቡን ወደ እግዚአብሔር በንስሐ መልሶ በሚጠመቅ ሰው እግዚአብሔር ምን ያህል ደስተኛ ነው?
አብ በልጁ የጥምቀት ቀን “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ” (ማቴ. 3፡17)። ጌታን የሚወዱ ሁልጊዜ እርሱን ለማስደሰት ይጥራሉ። (1ዮሐ. 3፡22፤ 1 ተሰ. 4፡1)። በእውነት ወደ እግዚአብሔር በተመለሰች ነፍስ በሰማይ ደስታ አለ።
13. አንድ ሰው የቤ/ክን አባል ሳይሆን እውነተኛ የጥምቀት ልምምድ ሊኖረው ይችላልን?
አይችልም! መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን በግልጽ ያስረዳናል። የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ ይበሉ፤
(ሀ) ሁላችን የተጠራነው ወደ አንድ አካል ነው። “በአንድ አካልም የተጠራችሁለት” (ቆላ. 3፡15)። (ለ) ይህ አካል ቤተ ክርስቲያን ነች። “እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤” (ቆላ. 1፡18)። (ሐ) ወደዚህ አካል የምንጨመረው በጥምቀት ነው። “እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና” (1ቆሮ. 12፡13)። (መ) ልባቸው ወደ እግዚአብሔር የተመለሱ ሁሉ ወደ ቤተክርስቲያን ይጨመራሉ። “… ጌታም የሚድኑትን በቍጥራቸው ላይ ዕለት በዕለት ይጨምር ነበር” (የሐዋ ሥራ 2፡47)።
14. ጥምቀት ሊፈጽማቸው የማይችሉ የሚከተሉትን አራት ነገሮች ልብ ይበሉ
አንደኛ፤ መጠመቅ በራሱ የማንንም ልብ አይለውጥም፤ ይልቁንም ጥምቀት በሕይወታችን ለውጥ የመምጣቱ ማሳያ ነው። ነገር ግን ማንም ሰው እምነት ሳይኖረው፣ ንስሐ ሳይገባና አዲስ ልብ ሳይኖረው ሊጠመቅ ይችላል። እንዲያውም እንደ ኢየሱስ በጥልቅ ሊጠመቅም ይችላል። ነገር ግን ይሄ ሁሉ እርሱን ደረቅ የነበረውን እርጥብ ኃጢአተኛ ከማድረግ ውጪ የሚጠቅመው አንዳች ነገር አይኖርም—ምክያቱም አሁንም እምነት የለውም፣ ንስሐ አላገኘም፣ አዲስ ልብንም አልተቀበለም። ጥምቀት በራሱ ማንንም አዲስ ሰው አያደርግም፣ አይለውጥምም። ልባችንን ሊለውጥልን የሚችል ኃይል የሚገኘው ከመንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው። ሰው ከውሃ ብቻ ሳይሆን ከመንፈስም መወለድ አለበት የተባለው ለዚህ ነው (ዮሐ. 3፡5)።
ሁለተኛ፤ ጥምቀት የማንንም ሕይወት የተሻለ ሆኖ እንዲሰማን አያደርግም። ስሜታችንንም የሚቀይር ነገር አይደለም። ይህንን የምንልበት ምክንያት አንዳንድ ሰዎች ከጥምቀት በኋላ የተለየ ስሜት ስላልተሰማቸው ብቻ ተስፋ የሚቆርጡ ስላሉ ነው። መዳን የእምነትና የመታዘዝ ጉዳይ እንጂ የስሜት ጉዳይ አይደለም።
ሦስተኛ፤ መጠመቅ የህይወት ፈተናን አያስወግድም። አንድ ሰው ስለተጠመቀ ሰይጣን ከዚያ ወዲያ አይፈትነውም ማለት አይደለም። ጌታችን ክርስቶ ከተጠመቀ በኋላ ሊፈተን ወደ በረሃ እንደ ሄደ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል (ማቴ. 3፡15-17፤ 4፡1-11)። ስለዚህ ከጥምቀት በኋላ ፈተና ሊኖር ይችላል፤ ምናልባትም እጅግ የበረታ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ኢየሱስ የተጠመቀውን ሰው “አልለቅህም፤ ከቶም አልተውህም ብሎአልና” በማንኛውም ጊዜ አብሮት ይሆናል (ዕብ. 13፡5)። ይህ የማይለወጥ የተስፋ ቃል ነው። ስለዚህ ምንም ዓይነት ፈተና ቢገጥመን መውጫ መንገዱን አምላክ ያዘጋጃል። የተስፋ ቃሉ አያረጅም (1ቆሮ. 10፡13)።
አራተኛ፤ ጥምቀት ለመዳናችን ዋስትና የሚሰጥ አስማታዊ ስርዓት አይደለም። መዳን ከኢየሱስ ክርስቶስ የምናገኘው ነፃ ስጦታ ነው። አንድ ሰው እንደገና መወለድን ሲለማመድ የዚያን ጊዜ ጥምቀቱ በእውነት የመለወጡ ምልክት ይሆንለታል። ስለዚህ መለወጥ ከጥምቀት በፊት ካልቀደመ የመጠመቅ ሥርዓት ብቻውን ትርጉም የሌለው ነው።
15. ኃጢአትዎ እንደታጠበ ምልክት ይሆን ዘንድ እርስዎም እንዲጠመቁ ኢየሱስ ይጠይቅዎታል፤ ይህንን የተቀደሰ ሥርዓት በቅርቡ ለማድረግ ውሳኔዎ ነውን?
ውሳኔዎን በተመለከተ ሊያነጋግሩን ካሰቡ ልንረዳዎት ዝግጁ ነን። ከአድራሻችን በአንዱ ይጻፉልን፣ ይደውሉልን። በፍጥነት ምላሽ እንሰጣለን።
ቅንብር፤ ፓስተር መስፍን ማንደፍሮ