giziew.org

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ”

“የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ”
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ጌታችንና አምላካችን ክርስቶስ የመልዕክቱ ፍሰት ሳይቋረጥ ከተናገረባቸው ስብከቶች በቀዳሚነት የሚጠቀሰው በተለምዶ “የተራራው ስብከት” የሚባለው ነው። በዚህ ስብከቱ እጅግ በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሰው ጌታ፤ “ብሩካን” በማለት በማቴዎስ ምዕራፍ 5 ንግግሩን ጀምሮ ምዕራፍ 7 ላይ ሲደርስ አንድ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጠ። እንዲህም አለ፤ “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን?” (ማቴ 7፡15-16)።

በአገራችን የደቡብ ክፍል የሚነገር አንድ ተረት አለ፤ ጥንቸል፣ ቀበሮና ተኩላ በስምምነት ተላምደው ይኖሩ ነበር። ቀበሮውና ተኩላው ከሚመገቡት ሥጋ ጀምሮ የባህርይም ተመሳስሎ ስለነበራቸው ይግባቡ ነበር። ጥንቸሉ በአመጋገቡ ከእነርሱ የሚለይ ቢሆንም ፈጣን መልዕክተኛ በመሆኑ በአገልግሎቱ ተስማምተው ለመኖር ቀጠሉ።

ሆኖም ቀበሮውና ተኩላው ሲያስቡት ከጥንቸሉ ጋር በዚህ መልኩ መኖራቸው አልተስማማቸውም። እናም ሲነጋገሩ ይህንን ጥንቸል ብንበላው፤ አንዳችን እግሩን፣ ሌላችን ደግሞ ሌላውን ይዘን ብንጎትተው በቀላሉ ልንገነጣጥለውን እንችላለን፤ መጠኑ ትንሽ በመሆኑ ለምሳ የሚበቃን ባይሆንም ለቁርስ ምንም አይልም ተባባሉ።

ከተላከበት ሲመለስ ሁኔታው ያላማረው ጥንቸል፤ ተኩላው ጥርሱን ሲያፋጭ በድንገት ተመልክቶ “ምን ሆናችኋል፤ ሰላም አይደለም?” ብሎ ጠየቃቸው። ችግር እንደሌለ ቢነግሩትም ከባህርያቸው ማንነታቸውን አሳምሮ የሚያውቀው ብልጡ ጥንቸል ቀስ ብሎ ሾልኮ አመለጠ።

በጉዳዩ የተናደዱት ተኩላና ቀበሮ ጥንቸሉን አባብሎ የመያዝ ወጥመድ በቀጣይ ዘረጉ። ተኩላው ሕመምተኛ በመምሰል ይተኛል፤ ቀበሮው ጥንቸሉ ወዳለበት ይሄድና የተኩላውን በጽኑ መታተም ይነግረዋል፤ ጥንቸሉም ስለ ቀድሞው ወዳጅነታቸው በሚል ተኩላውን ለመጠየቅ ሲመጣ አፈፍ ያደርገውና ከቀበሮ ጋር ይካፈለዋል።       

ድራማው ተቀናበረ፤ ጥንቸል በሚመጣበት መንገድ ቀበሮው ጠብቆ የተኩላን መታመም ነገረው። ጥንቸልም ተኩላን ለመጠየቅ ወደቤቱ ሄደ። ሆኖም ዓይኖቹን ጨፍኖ (ሽፋሽፍቱ ግን ይርገበገብ ነበር)፣ አፉን ዘግቶ የተኛውን ተኩላ ጥንቸሉ ሲያይ የሆነ ወጥመድ የተዘጋጀለት መሰለውና በጣም ተጠራጠረ። ጥቂት አሰበና “ተኩላ እኮ ሲሞት ዓይኑ በቶሎ ሲከደን አፉን ግን ይከፍታል” አለ። ይህንን የሰማው ተኩላም ዓይኑን ግጥም አድርጎ በመጨፈን አፉን ሲከፍት ጥንቸሉ ሳይታይ ሮጦ አመለጠ።

ጌታም እንዲህ አለ፤ “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ”። ከተኩላ እንዴት እንጠበቃለን ብለን ከጠየቅን በታሪኩ እንደተገለጸው ጥንቸል ብልህ በመሆንና አርቆ በማሰብ፣ በጸሎትና በቃል ጥናት ነው።

በዚህ የጊዜው መጽሔት ልዩ ዕትም በዘመናችን በተለይም በአገራችን የበግ ለምድ ለብሰው ምዕመኑን እያምታቱ ስላሉት “ተኩላዎች” ሰፊ ትንታኔ ተሰጥቷል። የቀረቡት ጽሁፎች ዓላማና ይዘት የሰዎችን ስም እየጠሩ ስህተታቸውን ለማጋለጥ አይደለም። ይልቁንም ጽሁፎቹ ትኩረት ያደረጉት ስለ ተኩላ ባሕርያት፣ ጌታችን “ተጠንቀቁ” ሲልና “ተኩላ” ብሎ ሲጠራቸው ምን ማለቱ እንደሆነእውነተኛ ነቢይን በምን እንደምንፈትንየዱሮና የአሁኑን ነቢያትና ሐዋርያት ንጽጽራዊ ትንታኔ እንዲሁም ስለ ተዓምራትና ስለ ልሳን ትርጉምና አጠቃቀም ነው።

በዘመናችን በየሚዲያው እንደምንመለከተው እነዚህ የሃሰት ነቢያትና ሐዋርያት ክርስቶስ እንዳለው “የበግ ለምድ” መልበስ የሚያስፈልጋቸው አይመስሉም። ሃማይኖቱን እንተወውና ሰብዓዊነት በጎደለው ሁኔታ የእግዚአብሔርን ስም በመጥራት የሚከተላቸውን ምዕመን እንዴት እንደሚያሰቃዩ መስማት ለአእምሮ የሚከብድ ነው። ከሁሉ በላይ ግን ይህንን የሚያደርጉት በእግዚአብሔር ስም በመሆኑ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አንገት የሚያስድፋም ነው። ይህ፤ እጅግ የከበረውና ለምህረቱና ርኅራኄው ወሰን የሌለውን አምላክ ስም እጅግ የሚያጠለሽ ብቻ ሳይሆን በክፉ እንዲነሳ የሚያደርግ እኩይ ተግባር ነው።

ጌታችን ስለተኩላዎች ሲናገር “ተጠንቀቁ” ቢለንም ዋናው ዓላማ ግን ዕድሜልካችንን የተኩላዎችን ድርጊት ስንከታተልና የሠሩትን መጥፎ ተግባራት ስንኮንን እንድንኖር አይደለም። ይልቁንም ዋና ትኩረታችን “መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል” (ዮሐንስ 10፡11) በማለት የተናገረውን የመልካሙን እረኛ የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ባህርያት ጠንቅቆ ማወቁ ላይ ነው። የዚህ ልዩ ዕትም ዋና ዓላማም ይኸው ነው።

መልካም ንባብ።


2 thoughts on ““ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ””

  1. It is wonderful website , iI’m going to order the spritual books and I will enjoy my soul.
    God bless you for your sharing the word of God to others Thank you and God bless your Ministry🙏🏽

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *