እንደ አሁኑ ዘመን ሠርግ በተጋቢዎቹ ቀኑ ተቆርጦ፣ ታዳሚ ተሰብስብቦ፣ ሰዓቱ ተወስኖ በተንጣለለ አዳራሽ ይካሄድ ባልነበረበት ዘመን ጥንዶቹ ከተጫጩ በኋላ ሙሽራው የሚመጣበትና ሠርጉ የሚካሄድበት ቀን ወዲያውኑ አይታወቅም ነበር። እንዲያውም በአገራችንም እንደተለመደው በመጀመሪያ ወላጆች “ልጅህን ለልጄ” ተባብለው ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ። ቀጥሎም ልጅቷ አድጋና ተሞሽራ፤ ልጁም ራሱን ችሎና ቤተሰብ ለመምራት የሚችልበት ዕድሜ እስከሚደርስ ልጅቷ በልጁ እናት ጥበቃ ሥር በእንክብካቤ ትቀመጣለች።
በመካከለኛው ምሥራቅ በነበረው ልማድ መሠረት የሠርጉን ቀን የሚያውቀውና የሚወስነው የሙሽራው አባት ነው። ሙሽራው ቤት ለመምራት፣ ትዳር ለመመሥረት ብቁ መሆኑን እና አስፈላጊ ዝግጅት ማድረጉን አባቱ ሲያረጋግጥ የሠርጉ ቀን እየታወቀ ይመጣል። እስከዚያ ድረስ ግን ሙሽሪት ሙሽራው ባሏ አንድ ቀን መጥቶ እንደሚወስዳት የተቆረጠ ቀን እንዳለ እንጂ ቀኑ መቼ እንደሚሆን አታውቅም። ሙሽራውም “መቼ ነው ሠርግህ?” ተብሎ ቢጠየቅ “እኔ ቀኑን አላውቅም፤ አባቴ ነው የሚወስነው” በማለት ይመልሳል። ሁለቱም ቀኑን እስከሚያውቁት ድረስ በየጊዜው እየተዘጋጁ በናፍቆት ይጠብቃሉ።
“ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” ገላትያ 4፡4።
በኤድን ገነት አዳምና ሔዋን በደል እንደፈጸሙ ነበር አዳኝ መሢሕ እንደሚላክላቸው ተስፋ የተሰጣቸው (ዘፍጥረት 3፡15)። እነርሱም የመጀመሪያ ልጃቸው ከተዘፈቁበት የኃጢአት አረንቋ ነጻ የሚያመጣቸው የተስፋው መሢሕ አድርገው ቢጠብቁ ተሳስተዋል ሊባሉ አይችሉም።
ግን አልሆነም። ተስፋ የተጣለበት እንዲያውም የመጀመሪያው ነፍሰ ገዳይ ሆነና የወንድሙን ሕይወት አጠፋ (ዘፍጥረት 4)። ተስፋቸው ግን አብሮ አልጠፋም። ዘመናት ተቆጠሩ። የታሰበው ተስፋ ዕውን ሳይሆን እነርሱ አለፉ። ይባስ ብሎ በምድር ላይ የሚሠራው ርኩሰት ከመብዛቱ የተነሳ የሰው ዘር ከመጥፋቱ በፊት እግዚአብሔር ምድርን በውሃ አጸዳትና በኖህ አማካኝነት ሕይወት ቀጠለ (ዘፍጥረት 6)።
በመሣፍንትና ነቢያት ዘመንም የመሢሑ መምጣት በናፍቆት ተጠበቀ፤ ግን ሳይሳካ በርካታ አበውና ነቢያት ተስፋውን ትኩር ብለው በማየት በተስፋ አሸለቡ። ሌሎች ግን ተስፋቸው ሲርቅ፣ መከራቸው ሲበዛ “ዘመኑ ረዝሞአል ራእዩም ሁሉ ጠፍቶአል” ወደማለት ደርሰው ነበር (ሕዝቅኤል 12፡22)።
እግዚአብሔር ግን በአሠራሩ አይዘገይም፤ አይቸኩልምም። በሰማይ ላይ የምናያቸውና የማናያቸው ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ከዋክብት አንዲት ሥንዝር ሳያዛንፉ የጉዞ መስመራቸውን ተከትለው እንደሚሄዱ ሁሉ የእግዚአብሔርም ዕቅድ እንዲሁ ሳይፈጥንም ሳይዘገይም በጊዜው ይፈጸማል።
ቃሉን የማያጥፍ አምላክ ከብዙ ዘመናት በፊት ለአብርሃም በእሣትና በጢስ ውስጥ የገባውን አስደናቂ ቃልኪዳን ማንም ሊያከሽፈው ወይም ሊያስቀረው የሚችል አልነበረም (ዘፍጥረት 15:14)። በዚህ ቃልኪዳን እስራኤል በግብፅ ምድር ለበርካታ ዓመታት እንደሚሰቃዩና በኋላ ግን ከባርነት ነጻ እንደሚወጡ የሰጠውን ቃል እብሪተኛው ፈርዖን የሚችለውን ሁሉ ቢጥርም አላከሸፈውም። ልክ ያቺ ለአብርሃም የተነገረችው ዘመን ስትፈጸም እስራኤል ከግብፅ ምድር ባርነት ነጻ ወጣ (ዘጸአት 12፡41)።
በተመሳሳይ ሁኔታ ጌታችንና አምላካችን ሰው ሆኖ የሚወለድበት ጊዜ ሲደርስ ሰማይ ዝግጁ ሆነ። “ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” (ገላትያ 4፡4)። አምላክ በምሥጢረ ሥጋዌ ወደ ምድር በሚገለጥበት ጊዜ የምድር ሰዎች ነገር ዓለሙን ሁሉ ረስተው፣ በዕለታዊ ኑሯቸው ተጠምደው፣ በዓላትን እያከበሩ “የሰላም ሕይወት” እየመሩ ነበር።
ለአራት ሺህ ዓመታት “ይመጣል” ተብሎ የተጠበቀው መሢሕ በቤተልሔም ሲወለድ፤ መላእክት ምድርን በሰበር ዜና ለማናወጥ በናፍቆት በተዘጋጁበት ጊዜ ዓለማችን ግን በሌላ “ዓለም” ውስጥ ነበረች። ከጥቂት እረኞች፣ ከእስራኤል ወገን ያልሆኑ ከሩቅ አገር ከመጡ ሰብዓ ሰገልና ሁለት በኢየሩሳሌም መቅደስ ሲያገለግሉ ከነበሩ አዛውንት በስተቀር (ሉቃስ 2፡25 – 38) እነ አብርሃም የናፈቁትን መሢሕ ለመቀበል ምድር ጊዜ ብቻ ሳይሆን ቦታም ስላልነበራት የዓለም ቤዛ በከብቶች በረት መወለድ ግድ ሆነበት።
መድኃኒዓለምም “እንኳን ደህና መጣህ” ብላ ባልተቀበለችው ምድር 33 ዓመታት በማሳለፍ በዘፍጥት 3፡15 ላይ ለአዳምና ሔዋን የተሰጠውን ተስፋ በመፈጸም የእባቡን ጭንቅላት ቀጥቅጦ ወደ ሰማይ በሄደ ጊዜ መላእክት ለደቀመዛሙት የሰጡት ቃል ነበር። “የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው” (የሐዋርያት ሥራ 1፡11)።
ጌታችን “ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ … ሥፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” በማለት ተስፋ ከሰጠን ሁለት ሺህ ዓመታት አልፈዋል (ዮሐንስ 14፡ 1 – 3)።
ዓለማችን ግን ዳግም መጥቶ የሚፈውሳትን ሙሽራ ለመቀበል ከመናፈቅ ይልቅ በማያቋርጥ የኑሮ አዙሪት ተጠምዳ በደመነፍስ እየተሸከረከረች ነው። ሌሎች “ዘመኑ ረዝሞአል ራእዩም ሁሉ ጠፍቶአል” የሚሉና ራሳቸው ሰንፈው ሌሎች እንዳይዘጋጁ የሚያሳንፉ ዘባቾች ደግሞ አሉ። “ከሁሉ አስቀድሞ ይህን ዕወቁ፤ በመጨረሻው ዘመን የራሳቸውን ክፉ ምኞት የሚከተሉ ዘባቾች እየዘበቱ ይመጣሉ። እነርሱም፣ “‘እመጣለሁ’ ያለው ታዲያ የት አለ? አባቶች ከሞቱበት ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ሁሉም ነገር እንዳለ ይኖራል” ይላሉ” (2ኛ ጴጥሮስ 3፡3-4)።
“እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ። ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል” (2ኛ ጴጥሮስ 3፡8-9)።
ቃሉን የሰጠው አምላካችንም “አዎን (በእርግጥ) በቶሎ እመጣለሁ” ብሏል (ራዕይ 22፡20)። ይህንን የሠርግ ቀን በታላቅ ናፍቆት ሲጠባበቅ ከነበረው ባለራዕዩ ዮሐንስ ጋር እኛም “አሜን፤ ጌታ ኢየሱ ሆይ ና” በማለት “በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት” እየኖርን “ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ከእርሱ ጋር በሰላም” ለመገናኘት እየተጋን “ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት” እንጠብቅ (2ኛ ጴጥሮስ 3፡11 – 13)።
ጥበበሥላሴ መንግሥቱ