በሰው ልጅ የሃይማኖት ታሪክ ውስጥ እንደ መዳን ያለ አወዛጋቢ ርዕሰ ጉዳይ አለ ለማለት ያስቸግራል። ከኃጢአት እንዴት እድናለሁ? የዘላለምንስ ሕይወት እንዴት እወርሳለሁ? የሚለው ጉዳይ የየቤተ እምነቱ ምዕመናን የኅልውና ጥያቄ ነው።
የመዳን አስተምህሮ፣ የኃይማኖት አስተምህሮ ሁሉ መመ’ሥረቻ መሠረት ነው። መዳንን የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት “የሰው ከኃጢአት ኃይልና ተጽዕኖ መዳን/መትረፍ” ሲሉ ፍች ይሰጡታል። በብሉይ ኪዳን “መዳን” ከብዙ በጥቂቱ ከአደጋ፣ ከአስጨናቂ ሁኔታ፣ ከጠላት፣ ከግብጽ ባርነት (ዘጸ. 14፡13፣ 15፡2)፣ ከባቢሎን ምርኮ (ኢሳ. 46፡13፣ 52፡10-11)፣ ከባላጋራ (መዝ. 106፡10)፣ ከሽንፈት (ዘዳ. 20፡4)፣ ወይም ከጭቆና ነጻ መሆንን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል።
በአዲስ ኪዳን ደግሞ ከስቃይ፣ ከበሽታ፣ ከህመም፣ ከእርኩስ መንፈስ፣ ከሞት (ማር. 5፡34፣ ያዕ. 5፡15) ጋር መዳንን ሲያቆራኘው እናነባለን። ቃሉ ከሕክምና ጋርም ግንኙነት ኖሮት ይታያል። የቃሉ መንፈሳዊ ይዘት ያለው ፍችና በመጽሐፍ ቅዱስ ጎልቶ የሚታየው ግን “የሰው ከኃጢአት ኃይልና ተጽዕኖ መዳን/መትረፍ” የሚለው ነው። በሰብዓዊ ዘር የመዳን ታሪክም ክርስቶስ “… የመዳን ራስ …” ተብሎ ተጠርቷል (ዕብ. 2፡10)። በዚህች አጭር ፅሁፍ ስለ መዳን በአጭሩ እንመለከታለን።
- ኃጢአት በየት ተጀመረ?
“አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ? አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቈረጥህ? አንተን በልብህ፦ ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፥ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍአደርጋለሁ፥ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ፤ ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ” (ኢሳ. 14፡12-14)።
ኃጢአት የተጀመረው በሰማይ በሉሲፈር/ሳጥናኤል አማካኝነት ነው። “ሉሲፈር” ብርሃን ተሸካሚ የነበረው መልአክ ሲፈጠር ፍጹም ነበር። በልቡ ውስጥ ክፋት ሲገባ ግን “ሰይጣን” ሆነ፤ የእግዚአብሔር ቀንደኛ ጠላት። ዙፋኑን ከእግዚአብሔር ዙፋን በላይ ለማድረግ ተመኘ፤ እግዚአብሔርን በሃሰት ከሰሰው፤ ከመላዕክትም ሢሦውን በማሳሳት ከሰማይ እንዲባረሩ አደረጋቸው (ራዕ. 12፡4)። ክርስቶስ ስለ እርሱ ሲናገር እንዲህ ይላል፤ “… ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና” (ዮሐ. 8፡44)።
2. ኃጢአት እንዴት ወደ ምድር ገባ?
“እባብም ለሴቲቱ አላት፦ ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ (ከፍሬዋ) በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ። ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ” (ዘፍ. 3፡4-6)።
የመጀመሪያዎቹ የሰብዓዊ ዘር ወላጆች በእግዚአብሔር ላይ በማመጻቸው ምክንያት ነው ኃጢአት ወደ ምድር የገባው። በኤድን ገነት ሔዋን የፈጸመችውን የመጀመሪያውን ኃጢአት ስንመለከት አለማመን ጎልቶ ይታይበታል። የአንድ ዛፍ ፍሬ ወስዶ ከመብላት በላይ በእግዚአብሔር ላይ እምነትን ማጣት ይንጸባረቅበታል። ይህም ማለት እግዚአብሔር ለልጆቹ መልካሙን ሁሉ የሚያውቅ፣ የሚመኝና የሚያደርግ ቸር አባት ሆኖ ሳለ ክፉው ግን ለሔዋን እግዚአብሔርን እንደ ክፉ፣ ጨካኝ፣ ራስ ወዳድና የልጆቹን ነጻነት የሚነፍግ አምላክ አድርጎ አቀረበላት። እርሷም የክፉውን ቃል አመነች፤ አምላኳንም አልፈልግህም አለች። በእያንዳንዱ ኃጢአት ውስጥ እግዚአብሔርን አለማመን፣ አለመፈለግ እንዲሁም ራስን ማስቀደም አለ። እኔነት የኃጢአት ሁሉ ሥር ነው።
3. መድኃኒዓለም ምን ሊያደርግ ወደ ምድር መጣ?
“የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቷልና አለው” (ሉቃ. 19፡10)። “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው” (ዮሐ. 1፡18)። መድኃኒዓለም ወደ ምድር ከመጣባቸው ምክንያቶች አንዱ እግዚአብሔርን ሊገልጥልን ነው። ሰይጣን ስለ እግዚአብሔር ማንነት ለሰው ልጆች የሰጠው ፍች ፍጹም ሀሰት ስለሆነ እግዚአብሔርን በትክክል ማወቅ ለሰው ልጆች ቀላል አይሆንላቸውም። ስለሆነም አብ አባታችን በልጁ በሙላት ራሱን ገለጠ። “ኢየሱስም አለው፦ አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ፦ አብን አሳየን ትላለህ?” (ዮሐ. 14፡6)።
4. ክርስቶስ ኃጢአተኛውን አዳነው ስንል ምን ማለታችን ነው?
“እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥ ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው” (ሮሜ 3፡25፣26)።
ኃጢአት በሰው ልጅ ላይ ያመጣው መዘዝ ብዙ እንደመሆኑ የመድኃኒዓለም የማዳን ሥራም ብዙ አቅጣጫዎችን ይዳስሳል። ሐዋሪያው ጳውሎስና ሌሎቹ የወንጌል ጸሐፊዎች እንዳስቀመጡት መድኃኒዓለም ለኃጢአተኛው እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ ካለው ቁጣ ሥርየትን፣ ከኃጢአት ባርነት መዋጀትን፣ ከኃጢአት መቀጮና ኩነኔ መጽደቅን (ነጻ ነህ መባልን)፣ ከአምላኩ ጋርም መታረቅን አመጣ። እነዚህ በአዲስ ኪዳን ላይ ተዘውትረው የተጻፉ ቃላት የሚያስተላልፉት የየራሳቸው መልዕክት አለ።
ሥርየት፤ የዚህ ቃል ትርጉም “ስጦታ በመስጠት ቁጣን መመለስ” የሚል ፍች እንዳለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ይናገራሉ። እግዚአብሔር ፍጹምና ጻድቅ ስለሆነ ኃጢአትን ሊታገስ አይችልም። በኃጢአት ላይም ቁጣውን ይገለጣል። በዚህ ክፉ የኃጢአት በሽታ ልጆቹ ሲማቅቁ መመልከት ደግሞ በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ጥልቅ ሐዘንን ይፈጥራል። ለዚህ መፍትሔ ይሆን ዘንድ ልጁን ላከ፤ የሥርየት መስዋዕትም አድርጎ አቀረበው፤ ኃጢአተኛውንም ከኩነኔ አነጻ፤ በኃጢአት ላይም ቅንና ጻድቅ ፍርዱን ፈረደ።
አንዳንዶች በብሉይ ኪዳን የተገለጠው አምላክ ክፉና ጨካኝ፣ በአዲስ ኪዳን የተገለጠው አዳኝ ደግሞ አዛኝና ርኅሩኅ አድርገው ለማሰብ ይዳዳሉ። ምናልባትም እግዚአብሔር አስፈሪና በኃጢአተኛው ላይ ስህተትን ፈላጊ፤ እንከንን ባገኘ ጊዜ ደግሞ በመቅጣት ደስ የሚሰኝ፤ በአንጻሩ ጌታችን ኢየሱስ ደግሞ ልቡ የሚራራ ድካማችን የሚገባውና የሚፈቀር ስብዕና ያለው አድርግው የሚያስቡም አይጠፉም። እግዚአብሔር ሰብዓዊ ዘርን በጥልቅ ፍቅር ስለሚወድ ልጁን ላከ። በልጁ ሞት ምክንያት ኃጢአት በሰው ልጅ ላይ ያመጣው ፍርድ ተነሳ።
ቀራኒዮ በእግዚአብሔር ባህርይ ላይ ያመጣው ምንም ለውጥ የለም። ይልቁንም ባህርዩን ፍንትው አድርጎ ገለጠው እንጂ። ሥርየቱ ጸጋ እንዲመጣ አላደረገም፤ ጸጋው ሥርየቱን አመጣልን እንጂ። እግዚአብሔር ሰውን የወደደው በልጁ ሞት ምክንያት አይደለም፤ ይልቁንም ሰውን ስለወደደ ልጁን እስከሞት አሳልፎ ሰጠ እንጂ። ፍቅሩ ሁሉን ይቀድማል። በብሉይ ኪዳን ዘመንም ይሁን በአዲስ እግዚአብሔር ፍቅር ነው (ዘጸ. 34፡6)። ለኃጢአት ያለው ጥላቻም ያው ነው። በመለኮት ውስጥ የባህርይ መለያየት ከቶውንም የለም።
አፍቃሪው ክርስቶስም በኃጢአት ላይ ቁጣው ይገለጣል። “ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና። እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል” (2ተሰ. 1፡7፣8)።
መዋጀት፤ የቃሉ ትርጉም “እንደገና መግዛት” ማለት ሲሆን በጥንት ዘመን በጦር ሜዳ ውሎ የተማረከን ወታደር ገንዘብ ከፍሎ ማስመለስና ባሪያን ነጻ ማውጣት በመሰሉ ኩነቶች ጋር ተያይዞ ቃሉ ጥቅም ላይ ይውል ነበር። የሚከፈለው ገንዘብም “ቤዛ” ይባላል። መድኃኒዓለም ራሱን “ቤዛ” በማድረግ ሰብዓዊ ዘርን ከኃጢአት ባርነት ዋጀው፣ ነጻ አወጣው። በራሱም ደም ገዛው።
“እንዲሁ የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” (ማር. 10፡45)። “አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፥ ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበረ” (1 ጢሞ. 2፡5፣6)። “በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን” (ገላ. 3፡13)።
መጽደቅ፤ የቃሉ ትርጉም በፍርድ ችሎት ፊት “ጻድቅ ነህ”፣ “ነጻና ትክክል ነህ” ተብሎ መጠራትን ያመለክታል። በሮሜ 3፡23 እንደተጻፈው “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤” የዘላለም ሞትም ተፈርዶባቸዋል (ሮሜ 6፡23)። የምሥራቹ ግን “በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ” (ሮሜ 3፡24)። ኃጢአተኛው በደሙ ቤዛነት ከዘላለም ሞት ነጻ ሊያወጣው የሚችለውን አዳኝ ሲያምን ያኔ የአዳኙ ጽድቅ እርሱ እንዳደረገው ተደርጎ ተቆጥሮ በእግዚአብሔር ፊት “ነጻና ጻድቅ ነህ” ተብሎ ይነገርለታል። ጽድቅ የኩነኔ ተቃራኒ ነው። ጽድቅ ማለት ከበደል፣ ከኩነኔና እሱ ከሚያስከትለው ቅጣት “ነጻ ነህ” ብሎ ማወጅ ነው። ኃጢአተኛው በአዳኙ ሲያምን እንደ ጻድቅ ይቆጠራል።
መታረቅ፤ የቃሉ ትርጉም “ግንኙነትን ማደስ፣ ተቋርጦ የነበረን ግንኙነት/ኅብረት እንደገና መመለስ” የሚል ሲሆን በኃጢአት ምክኒያት ከእግዚአብሔር ቤተሰብ ኮብልሎ የጠፋው ኃጢአተኛ እንደገና ወደ አባቱ ቤት በአዳኙ ቤዛነት ተመለሰ፤ ከአባቱም ጋር ታረቀ (ሉቃስ 15፡10-32)።
“ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን” (ሮሜ 5፡10)። “እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና” (ቆላ. 1፡20)። በመስቀሉ የሰው ልጅ ከአምላኩ ጋር ሲታረቅ ውጤቱ ኃዋሪያው ጳውሎስ እንደጻፈው ከእግዚአብሔር ጋር “ሰላም”፣ እርሱን የማግኘት ዕድል፣ ቤተሰባዊ ኅብረት፣ ወዘተ ናቸው።
5. በመዳን ሂደት ውስጥ ኃጢአተኛውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ (መካከለኛ) ሰው ያስፈልገዋልን?
“ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔርጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን” (2ቆሮ. 5፡18-20)።
የጥያቄው አጭር መልስ “አያስፈልገውም” ነው። በኃጢአቱ ምክንያት የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ተለይቶ የእግዚአብሔር ጠላት ነበር። እግዚአብሔርም በዘላለማዊ ፍቅሩ ልጁን ልኮ ከራሱ ጋር አስታረቀው። በብዙ ሃይማኖቶች ለእግዚአብሔር የሚሰጠው ምስል፣ በአማላጅና በሽማግሌ የሚለመን ከብዙ ውትወታ በኋላ ፊቱን ወደ ኃጢአተኛው የሚመልስ ተደርጎ ነው። በዚህም ሂደት የሰው ልጅ እግዚአብሔርን በመፈለግ ሂደት ሲባዝንና ደጅ ሲጠና እንዲሁም ከርሱ የተሻለ ጽድቅ አላቸው ብሎ የሚያስባቸውን ቅዱሳንና መላዕክትን ጭምር ለምልጃ ወደ አምላኩ ሲልክ ይስተዋላል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህንን የሃይማኖት እሳቤ ይቃረነዋል።
ከላይ ያነበብነው ጥቅስ እግዚአብሔር ከሰው ልጆች ጋር ታረቀ አይልም። ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ታረቀ እንጂ። ገና ከመጀመሪያው ሰው የአምላኩ ጠላት ነበር እንጂ እግዚአብሔር የሰው ጠላት አልነበረም። በአንዳንድ ቤተ እምነቶች የአማልክትን ቁጣ ለማብረድና ለማስታገስ “ምስ” ማቅረብ፣ የጣዖቱን ፊት ማፍካትና ከዚያም ግንኙነትን ማደስ የተለመደ ነው። የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ግን የሰውን ልጅ በጥልቅ ፍቅር እንዲሁ በነጻ የሚወድ፤ የጠፋውን ፈላጊ አምላክ ነው። ስለሆነም ሰው እንዲድንና ከአምላኩ ጋር እንዲስማማ፤ የዘላለምንም ሕይወት እንዲወርስ ካለበት የሚፈለግ፣ የሚለመን፣ ምናልባትም አስታራቂ የሚላክበት በኃጢአቱ ምክንያት የጠፋውና ከእግዚአብሔር ራሱን የለየው የሰው ልጅ ነው እንጂ ፈጣሪ አይደለም።
6. ሰው የሚድነው በእግዚአብሔር ጸጋ ነው ወይስ ህግን በመጠበቅ? የሁለቱስ ግንኙነት ምንድን ነው?
“ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም” (ኤፌ. 2፡8-9)። “ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና” (ሮሜ 3፡20)።
ሰው የሚድነው በእግዚአብሔር ጸጋ ነው። ብዙዎች የእግዚአብሔር ጸጋና ህግ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ሁለት የተለያዩ ነገሮች አድርገው ይመለከቷቸዋል። ይህንን ውጥረት ለማርገብም አንዳንዶች የማስታረቂያ ሃሳብ በሚል የብሉይ ኪዳኑ አስፈሪ አምላክ በአዲስ ኪዳን ደግና ርኅሩኅ ሆኗል (ወይም በየዘመናቱ እግዚአብሔር ሰውን የሚያድንበት መንገድ የተለያየ ነው) የሚለውን የ“ዲስፐንሴሽናሊዝምን” ትምህርት ያቀርባሉ። ለዚህም አስረጂ እንዲሆን መድኃኒዓለም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፣ በቀራኒዮ መስቀል ሥጋውን ቆርሶ፣ ደሙን አፍስሶ፣ የሰውን ልጅ ከኃጢአት እስኪያድነው ድረስ መዳን “ህግን በመጠበቅ” ነበር፤ ከዚያ በኋላ ግን በአዲስ ኪዳን የሰው ልጅ የመዳኛው መንገድ “ጸጋ” እንዲሆን ተደረገ የሚል አስተምህሮ ነው። ቅዱሳት መጻህፍት እንደሚሉን ግን እግዚአብሔር የሰውን ልጅ የሚያድንበት መንገድ ሁሌም አንድ ነው። እርሱም ጸጋው ነው። መዳን ከእግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሚሰጥ ነጻ ስጦታ ነው። ምንም ያህል ጻድቅና ቅዱስ ቢሆን ሰው ራሱንም ሆነ ሌሎችን ማዳን አይችልም። የሰውን ልጅ የሚያድነው የሞተለት መድኃኒዓለም ብቻ ነው።
የእግዚአብሔር ህግ በመዳን ሂደት ውስጥ ያለው ሚና ኃጢአተኛውን መኮነን ነው። ማንም በራሱ ጥረት ጻድቅ ሊሆን እንደማይችል፤ የሰው ልጅ ሁሉ ኃጢአተኛ እንደሆነና ሞት እንደሚገባው በመኮነን ከዚህ ሞት ሊያስመልጠው ወደሚችለው መድኅን ይጠቁመዋል። ህግ ማንነታችንን ፍንትው አድርጎ የሚነግረን መስታወታችን ነው። በኃጢአት ምክንያት ሞት የተገባን መሆናችንን ከማርዳት ባሻገር ከሞት የምናመልጥበት የመዳኛው መንገድ ክርስቶስ መሆኑንም ያበስረናል። የእግዚአብሔር ጸጋና ህጉ የሚቃረኑ ሳይሆኑ እርስ በርሳቸው ተመጋጋቢ ናቸው።
7. የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ጸጋ በማመን የሚድን ከሆነ ተጨማሪ ሥራ ከርሱ ይጠበቅብሃል መባሉ አፍራሽ አይሆንም?
“በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና” (ገላ. 5፡6)። ከሰው ልጅ ሥራ መጠየቁ ፀጋን የሚያፈርስ አይሆንም። የሰው ልጅ የተዘጋጀለትን ጽድቅ የሚቀበልበት መንገድ እምነት ነው። የመድኃኒዓለም ሥራ ወይም በጎ ተግባር በክርስቶስ ከማመን ተለይቶ የሚታይ አይደለም። ሥራና እምነት በመዳን ውስጥ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ማመን ማለት በመድኃኒዓለም መልካምነት ሙሉ በሙሉ ማረፍ ነው፤ ሁለንተናን በእርሱ ላይ በመጣል በእርሱ መደገፍ ማለት ነው። እንዲሁ ክርስቶስ ያድናል ብሎ በአእምሮ ከመስማማት ያለፈ ቁምነገርን ይይዛል። አንድ በጌታችንና በመድኃኒታችን ያመነና ህይወቱን ለእርሱ የሰጠ ሰው በጎ ተግባር ማድረግ የክርስትናው መገለጫ ባህርይ ነው። በመዳኑ ላይ የሚጨምረው ምንም ነገር የለም፤ ድኗልና። መንፈስ ቅዱስ በህይወቱ ሲያድር የመንፈስ ፍሬዎች ሁሉ መታየት ይጀምራሉ። እነዚህ መልካም ባህሪያት በመዳኑ ላይ ምንም ሚና ባይኖራቸውም መዳኑን ግን ያሳያሉ። ይህ ደግሞ የቅድስና ህይወት ይባላል፤ (ገላ 5፡22፣23)።
8. አንድ ጊዜ የዳነ ሰው ሁል ጊዜ የዳነ ነው?
“… እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” (ማቴ. 10፡22)። አንድ ጊዜ የዳነ ሁልጊዜ የዳነ ነው የሚል ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ የተደገፈ አይደለም። እግዚአብሔር የነጻነትና የምርጫ አምላክ ነው። በመድኃኒዓለም አምኖ የጸደቀ ሰው እንደገና በአዳነው ጌታ የነበረውን እምነት ጥሎ የራሱን የኃጢአት መንገድ ከተከተለ የሚጠብቀው የዘላለም ሞት ነው። ኃጢአተኛው እምነቱን በአዳኙ ላይ አድርጎ እርሱን እስከተከተለ ድረስ ግን ጻድቅ ሆኖ እንዲቆጠር ያደረገው ጸጋ በዘመኑ ሁሉ ያዳነውን ጌታ እንዲከተል ኃይልን ይሰጠዋል። ቃሉ እንደሚለው “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል”።
9. እውን ለእግዚአብሔር ህግ ባንገዛ እንጠፋለን?
“እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ ከሰጣቸው” (2ኛ ጴጥ. 2፡4)። “እግዚአብሔር የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል፤ ኃጢአተኞችንም ሁሉ ያጠፋል” (መዝ. 145፡20)። “እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤ በዚያም ቀን በቅዱሳኑ ሊከብር፥ ምስክርነታችንንም አምናችኋልና በሚያምኑት ሁሉ ዘንድ ሊገረም ሲመጣ፥ ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ” (2ኛ ተሰ. 1፡8-10)።
እነዚህ ጥቅሶች ሁሉ የሚነግሩን ግልጽ ቃል ለማስፈራራት የተጠቀሱ ሳይሆን ዲያቢሎስና መላእክቱን ጨምሮ የማይታዘዙት ሁሉ እንደሚጠፉ በማያሻማ መልኩ ለማስረዳት ነው። ይህ የሚሆነው ግን እግዚአብሔር እንዲጠፉ ስለሚጨክንባቸው ወይም ለማጥፋት ቁርጥ ውሳኔ ስላደረገ ሳይሆን ለመዳን የተሰጣቸውን አማራጮች በሙሉ “አንፈልግም” በማለት ውድቅ ስላደረጉ ነው። በበሽታ የተያዘ ሰው ለመዳን የሚችልበትን አንድና ብቸኛ መድኃኒት አልወስድም ቢል መሞቱ አይቀሬ ይሆናል። የሚሞተው በበሽታው ስለተለከፈ ሳይሆን መድኃኒቱን “አልወስድም” ብሎ አሻፈረኝ በማለቱ ነው። ምክንያቱም ከዚያ በፊት በተመሳሳይ በሽታ የተለከፉ ብቸኛውን መድኃኒት በመውሰድ ተፈውሰዋል።
10. ታዲያ ለሰብዓዊ ዘር የእግዚአብሔርን ህግ መታዘዝ ይቻለዋልን?
“በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል” (ማቴ. 19፡26)። “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” (ፊሊ. 4፡13)። “ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን” (2ቆሮ. 2፡14)።
ሰብዓዊ ዘር በራሱ ምንም ሊያደርግ አይቻለውም። በእግዚአብሔር ጸጋ ታግዞ ግን ከርሱ የሚጠበቁትን ሊያደርግ ይችላል። ጥሪው አሁንም ግልጽ ነው፤ ሕግን ጠብቅ፣ ወይም ይህንን አድርግና አታድርግ አይደለም። ከዚያ ይልቅ የፍቅር ጥሪው እንዲህ ይላል፤ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” (ማቴ.11፡28-30) ስለዚህ የአምላካችን ጥሪ ተሸከሙ፣ ታዘዙ፣ ተገዙ ሳይሆን “እናንተ ደካሞች” ከነድካማችሁ፣ ከነሸክማችሁ ወደኔ ኑ! እኔም አሳርፋችኋለሁ የሚል ነው። አንባቢ ሆይ፤ እንዲህ ላለው የወዳጅ ጥሪ ምላሽዎ ምንድን ነው?
ቅንብር፤ ፋንታሁን መላኩ