giziew.org

አማኑኤል – እግዚአብሔር ከእኛ ጋር!

ምድርን ሰማይ ለማድረግ ከሰማይ ወደ ምድር ወረደ። ያጣነውን ሰማያዊ ቤት ዳግም ሊሰጠን ቤት አልባ ሆኖ በበረት ተወለደ! አምላክ ከሰው ጋር አደረ! አማኑኤል – እግዚአብሔር ከእኛ ጋር!
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ኃጢአት ወደዚህች ምድር ሲገባ ሰው ከአምላኩ ጋር የነበረው ቀጥተኛ ግንኙነት ተቋረጠ። አዳምና ሔዋን በኤድን ገነት መቅደስ ከአምላካችው ጋር ፊት ለፊት ይገናኙ ነበር። ጀምበር ስታዘቀዝቅ ቀጠሮ አክባሪው አምላክ በሰዓቱ ሲመጣ ድምጹን ሰምተው ወደእርሱ ይሄዱ ነበር። ኃጢአት ጣልቃ ሲገባ ግን ሁሉ ተበላሸ።

ለወትሮ አምላካቸው በገነት ሲመላለስ ሰምተው ወደ እርሱ ይሄዱ የነበሩ ጥንዶች አሁን ግን ድምፁን በገነት ዛፎች መካከል ሲሰሙ ፈርተው ተሸሸጉ። የሚናፍቁት የአምላካቸው ድምፅ የሚያስፈራቸው ሆነ – የመጎብኘታቸው ጊዜም የፍርሃትና የመንቀጥቀጥ!  

ጌታም አዳምን ወዴት ነህ ብሎ ጠራው፤ አዳምም መለሰ ድምፅህን ስሰማ ፈራሁና ተደበቅሁ! ናፍቆት በፍርሃት ተለወጠ፤ የመገናኘት ደስታ በፍርሃት ተዋጠ! ጨለማ በብርሃን ላይ በረታ። ሰው ከአምላኩ ተለየ! በሰውና በአምላክ መካከል ትልቅ የልዩነት ገደል ሆነ!

በምሕረቱ ባለጸጋ የሆነው አምላካችን ወዲያውኑ መፍትሔ አበጀ። በኃጢአት በወደቀው የሰው ዘር አማካኝነት መድኃኒት አመጣ። የአሳቹን ዲያቢሎስ ራስ የሚቀጠቅጥ በአንቺ ዘር አማካኝነት ይወለዳል አላት ለሔዋን። እንዲህም አላት ካንቺ ዘር ዓለምን የሚያድን መድኃኒት ይመጣል። እናንተ ሞትን መርጣችሁ ብትለዩኝም እኔ ግን አልተዋችሁም፤ አልለያችሁም አላቸው።

እግዚአብሔር እንደገና ከሰው ጋር የሚሆንበትን ጊዜ አባቶች ሲጠብቁ እጅግ ብዙ ዓመታት አለፉ። በተስፋ በርቀት እያዩት ተሳለሙት። አባታችን አብርሃም የመሢሑን መገለጥ ለማየት ተመኘ፤ በራዕይም አየና አንቀላፋ። ሌሎችም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መቼ ነው የሚሆነው” እያሉ ተስፋቸውን ትኩር ብለው እያዩ አለፉ፤ ተስፋ ለጨለመባቸው ግን ነቢያት ትንቢትን ተናገሩ፤ “እነሆ ድንግል ትጸንሳለች” ብለው የኤድን ገነትን ተስፋ እንደገና ሕይወት ዘሩበት።

አዳምና ሔዋንን በቀጠሮው ሰዓት ሲጎበኝ የነበረው የሰማይ ጌታ ግን እንደገና ከሰው ጋር የሚሆንበትን ቀጠሮ አልረሳም። በቀዳሚት ሔዋን ያጣነውን በዳግሚት ሔዋን እንደምናገኝ የተናገረውን ፈጸመ። ጊዜው በደረሰ ጊዜ በቤተልሔም ከድንግል ተወለደ። ቤዛ ኲሉ ዓለም ወደ እኛ መጣ! መድኅናችን ተወለደ! አማኑኤል! እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ።

ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ በእኛ አደረ። እንደገና ልጆች እንሆነው ዘንድ እግዚአብሔር ልጁን ላከልን። ከሕግም በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ ከሕግ በታች የተወለደውን ልጁን ሰጠን! በልጁ አማካኝነት የአብን ክብር አየን! ጸጋና እውነት በመድኃኒዓለም እውን ሆነ!

ምድርን ሰማይ ለማድረግ ከሰማይ ወደ ምድር ወረደ። ያጣነውን ሰማያዊ ቤት ዳግም ሊሰጠን ቤት አልባ ሆኖ በበረት ተወለደ! ሰማይን ቤታችን ሊያደርግ ምድርን ቤቱ አደረገ! አምላክ ከሰው ጋር አደረ! አማኑኤል – እግዚአብሔር ከእኛ ጋር!

የዘመናት ምኞት፣ የቅዱሳን ተስፋ፣ የአባቶች ናፍቆት በገሃድ ታየ! በጨለማ ተወልዶ ጨለማውን ብርሃን አደረገው! ብርሃንም በጨለማ በራ! ጨለማውም አላሸነፈውም! በጨለማም የሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃንን አየ! በሞት ጥላ ምድር የሚኖር ሕዝብ የጽድቅ ጸሐይ ወጣለት! ሃሌሉያ!

ስለዚህ ነፍሴ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ መንፈሴም በመድኃኒቴ በእግዚአብሔር ሐሴት ታደርጋለች፤ የእሥራኤል አምላክ ይባረክ፤ ሕዝቡን ጎብኝቷልና፤ በቅዱሳን ነቢያት አፍ የተናገረውን ፈጽሟልና፤ ምሕረቱን ያሳየን፤ ለአባቶቻችን የገባውን ቃል የፈጸመ፤ ቅዱስ ኪዳኑን ያልረሳ፤ መሐላውን ያሰበ፤ የንጋት ጸሐይ ያወጣልን፤ እግሮቻችንን በሰላም መንገድ ያቀና፤ ያለፍርሃት እናገለግለው ዘንድ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ ያቆመን፤ ማደሪያውን በሰዎች መካከል ለዘላለም ያደረገ፤ ልዑል እግዚአብሔርን ነፍሴ ለዘላለም ታወድሰዋለች! ሃሌሉያ!

“ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም፣ ሰላምም እርሱ ለሚወድዳቸው ሰዎች በምድር ይሁን!” አማኑኤል – እግዚአብሔር ከእኛ ጋር!

ወስብሃት ለእግዚአብሔር

ጥበበሥላሴ መንግሥቱ

ዘፍጥረት 3፡8፣15፤ ማቴዎስ 4፡16-17፤ ሉቃስ 1፡46-79፤ 2፡14፤ ዮሐንስ 1፡1-14፤ ገላትያ 4፡4


Christmas, Ethiopian Christmas, Genna, ገና

3 thoughts on “አማኑኤል – እግዚአብሔር ከእኛ ጋር!”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *