giziew.org

ታላቁ ውዝግብ፡ ጦርነት በሰማይ

"በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ ... ድል ተመቱ"
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

በአንድ ወቅት በሰማይ ጦርነት እንደተካሄደ መፅሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ራእይ 12:7)። ጦርነቱን ያስነሳው ውዝግብ ምንድነው?

ሰማይ የአምላክ መኖሪያ ነው (ኢሳ. 66:1)። ጥንት ምድር ከመፈጠሯ በፊት መላእክት ከእግዚአብሔር ጋር መተማመን በሞላው ደስታ ይኖሩ ነበር። አምላክ ሙሉ ነፃነትና ብዙ ጥበብ የሰጣቸው መላእክት ፈጣሪን የሚያመልኩት ተገደው ሳይሆን ፍቅር በሚያመነጨው ደስታ ነበር። ሆኖም አንድ ቀን ይህንን ደስታ የሚያደፈርስ ነገር መጣ። ታይቶ የማይታወቅ፣ ሰላማዊ መፍትሄ የሌለው የሃሳብ ልዩነት በሰማይ ቤተሰብ ውስጥ ገብቶ መላእክትን ያስጨንቅ ጀመረ።

በሰማይ የተፈጠረው አለመግባባት መላእክትን ለሁለት እንደከፈለ ባለ ራእዩ ዮሐንስ ይናገራል (ራእይ 12:7)። አንደኛው የመላእክት ቡድን በሚካኤል አመራር ስር ሆኖ ለውጊያ ሲሰለፍ ተቃራኒው ሰራዊት ደግሞ በሰይጣን ዕዝሥር ሆነ።

ሚካኤል ማለት “እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው?” ማለት ነው። በመላእክት ላይ ባለው ስልጣንም የፈጣሪን ማንነት ማስከበር ስሙም ግብሩም መሆኑ ዮሐንስ ስለ ጦርነቱ በሰጠው ዘገባ ላይ ጎልቶ ይታያል።

ሰይጣን ማለት ተገዳዳሪ ማለት ነው። ይህ ብዙ መላእክትን ወደ አመፅና ጦርነት የመራው የመላእክት አለቃ አሳሳችና ከሳሽ መሆኑን ዮሐንስ ይናገራል (ራእይ 12:9-10)። ቀድሞ መልካም የነበሩትን መላእክት በማሳሳት ከፈጣሪያቸው ጋርና እርስበእርስ የነበራቸውን ግንኙነት አበላሸ።

በጥበብ ከታላላቅ አዋቂ ሰዎች የሚልቁትን መላእክት ሰይጣን እንዴት አሳሳተ? ከነርሱ የረቀቀ ፍጡር ቢሆን ነው። ንግግሩ፣ ውበቱና የሃሳቡ አድማስ በአንጋፋ መላእክት የሚደነቅ ባይሆን እንዴት የጥበብ ምንጭ ከሆነው አምላክ ጋር ሊያጣላቸው ቻለ?

ሰይጣን ወደ ክፋት ከማዘነበሉ በፊት ፈጣሪው በሰጠው የክብር ቦታ ማገልገል ዘወትር ደስታው ነበር (ሕዝ. 28:14፣15)። ድንቅ አድርጎ ከፈጠረው የብርሃን አምላክ ጋር እጅግ የቀረበ ግኑኝነት ስለነበረው ስሙ “የንጋት ኮከብ” ተባለ – “ሉሲፈር” ማለት ትርጉሙ ይኽው ነው (ኢሳ. 14:12)። ይህ ስሙ ከፍጥረታት ሁሉ በሚቀድም መንገድ የአምላክን ክብር ማንፀባረቁን ያስገነዝባል።

ያለ አንዳች ምክንያት ይህ ኃያል መልአክ ለአምላኩ የሚገባውን ክብር ለራሱ መመኘት ጀመረ (ኢሳ. 14:13-14)። ውበቱና ረቂቅ የሆነው አእምሮው ከፈጣሪ የተገኙ ስጦታዎች መሆናቸውን እያወቀ የጌታውን ትሁት ፍቅር በንቀት ዘነጋው። የመመለክ ጥማት በፅኑ ያዘው። ከፍ ባለ ቦታ ተቀምጦ የመላእክትን አምልኮ በጌትነት እርካታ መቀበል ሕልሙ ሆነ። አልፎ ተርፎም እግዚአብሔር ራሱ ሊሰግድለት እንደሚገባ የማሰብ እብደት ውስጥ ገባ (ኢሳ. 14:13-14)። የሰማዩ ሉሲፈር እርኩሱ ሰይጣን ሆነ።

ሰይጣን እነዚህን እንግዳ ሃሳቦች ወደ መላእክት ይዞ ቢሄድ ፈጣን ተቃውሞ እንደሚገጥመው ያውቅ ነበር። መላእክት የአምላክን በጎነትና ጥበብ እንዲጠራጠሩ የሚጋብዝ ምንም ምክንያት አልነበራቸውም። ስለ ፈጣሪ አባታቸው ባሰቡ ጊዜ ሁሉ ልባቸው ሊገለፅ በማይችል ምስጋና ተሞልቶ በስግደት ይዘምሩ ነበር። ይህንን የሚያውቀው ዲያብሎስ የልቡን ፍላጎቱን በስልት ለመጋረድ ዘዴ ወጠነ። ውሸት ተወለደ (ዮሐ. 8:44)።

እናታችን ሔዋንን ባሳሳተበት ዘዴ አንደበቱን በውሸት አስውቦ ወደ መላእክት ሄደ። የመብታቸው ተቆርቋሪ መስሎ ቀረበ። ፈጣሪን እንዲጠራጠሩ ጥያቄዎች ሰነዘረ። አድማጮች ሲያገኝ ደግሞ አስደንጋጭ የውሸት ክሶችን በማራባት ጣቱን በፈጣሪ ላይ መቀሰር ጀመረ።

ውሸቱን ላመኑ መላእክት ያለ ፈጣሪ አዲስ ሕይወት በመመስረት አማልክት የመሆን ታላቅ ተስፋ እንዳላቸው ልብ በሚሰርቅ ምላስ ተናገረ። ይህ ተስፋ እንዳይፈፀም እንቅፋት የሆነባቸው፣ አምልኮን ለራሱ ብቻ የሚፈልገው እግዚአብሔር እንደሆነ በሚደንቅ ድፍረት ተናገረ።

ቀጥሎም ወደ አዲሱ ሕይወት እነዚህን መላእክት የሚመራቸው መሪ ማስፈለጉ ግልፅ ሲሆን አማፅያኑ ያለማንገራገር የሰይጣንን ምሪት እንደሚፈልጉ ወሰኑ። ለፈጣሪ መገዛት ባርነት እንደሆነ ታወጀ። የአምላክ ሕግ ረቂቅ አእምሮ ለሌላቸው እንጂ የምጡቅ መላእክት መመሪያ ሊሆን እንደማይችል ሰይጣንና አጋሮቹ ሰበኩ። ዲያቢሎስ ተሳካለት። ባልንጀሮቹ ትኩረታቸውን ከፈጣሪ ላይ በጥላቻ አዙረው እርሱን እንደ ነፃ አውጪ ጀግና እንዲመለከቱት አሳመናቸው።

የፍቅር አምላክ “ስልጣኔ እንዴት ተነካብኝ?” ብሎ እንደማይበቀለው ሰይጣን ያውቅ ነበር። ሊሰግዱለት የማይፈልጉትንም አንኳን እንደማያስገድድ ያውቃል (2 ቆሮ 9:7)። በተጨማሪም እንደ ሰይጣን ፍላጎቱን ለማሟላት እንደማይዋሽ ያውቃል። ስለሆነም የጌታ ፍቅር በሰማይ ለንስሃ የሰጠውን ሰፊ ጊዜ ዲያብሎስ ተከታዮችን ለማፍራት ተጠቀመበት። የአምላክን በጎ ባህሪዎች እንደ ድክመት ቆጥሮ እርኩስ ስራውን ለማፋጠን ተጋ።

ሰይጣን ተሹሞ የሚመለክበትን ቤተመቅደስ በሰማይ ለማቋቋም ነበር የፈለገው። በአንድ ቤት ውስጥ ሁለት ተቃራኒ መመሪያዎች አብረው መኖር እንደማይችሉ ሁሉ የአምላክ እውነትና የሰይጣን ውሸትም ተቻችለው መኖር ይሳናቸዋል (ማቴ. 6:24)። ፍቅርና ራስወዳድነት ህብረት የላቸውም። የሀሜት ክሶችና የምስጋና ቃላት አብረው መሰንበት አይችሉም። ስለዚህም ፈጣሪና ሰይጣን ሥልጣን ተከፋፍለው ሰማይን ማስተዳደር እንደማይችሉ ግልፅ ሆነ።

መላእክት በታላቁ ውዝግብ ውስጥ ውሳኔ ላይ መድረስ ግድ ሆነባቸው። ምርጫቸውን አሳወቁ። የዲያቢሎስ መላእክት ሰማይን ከፈጣሪ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት ተሰለፉ። ይህንን ያልፈለጉ መላእክት ግን “እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው?” በማለት በሚካኤል ሥር ተሰባሰቡ።

“በሰማይም ጦርነት ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም መልሰው ተዋጓቸው፤ ነገር ግን ድል ተመቱ፤ በሰማይም የነበራቸውን ስፍራ ዐጡ። ታላቁ ዘንዶ፣ የጥንቱ እባብ ተጣለ፤ እርሱም ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው፣ ዓለምን ሁሉ የሚያስተው ነው፤ እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።” ራእይ 12:7-9

በጦርነቱ የተሸነፉት ሰይጣንና ተከታዮቹ መላእክት ከሰማይ ተባረሩ። የአምላክን ቤት ሰላም አደፍርሶት የነበረው እንግዳ ጭቅጭቅም ፀጥ አለ። ስለዚህም በሰማይ የቀሩት መላእክት በደስታ ዘመሩ።

ከሰማይ የተባረሩት መላእክት (አጋንንት) ተስፋ ያደረጉትን ነፃነት አላገኙም። ቀድሞ በሰማይ ክብር ተሞልቶ የነበረው ሃሳብና ንግግራቸው ነውረኛ ሆነ። የብቸኝነት ፅልመትና የሞት ስጋት አስደነገጣቸው። ለደረሰው ጥፋት እርስበእርሰ ተወነጃጀሉ። የቀራቸው እርኩስ ተስፋ ሌሎችን የኪሳራቸው ተካፋይ ማድረግ ሆነ። ስለሆነም ወደ ምድር መጡ።

“ታላቁ ዘንዶ፣ የጥንቱ እባብ ተጣለ፤ እርሱም ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው፣ ዓለምን ሁሉ የሚያስተው ነው፤ እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ” (ራዕይ 12፡9)።

ድርባ ፈቃዱ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *