giziew.org

የእውነተኛ ነቢይ መለኪያ መሥፈርቶች

ሐዋርያው ጳውሎስም “ትንቢትን አትናቁ ሁሉን ፈትኑ መልካሙን ያዙ” በማለት ይመክረናል። በዚህ መሠረት እውነተኛ ነቢያትን ከሐሰተኞቹ የምንለይባቸውን መሥፈርቶች እናጠናለን
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ነቢያት በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ዘመን ትልቅ ሚና ይጫወቱ ነበር። በዘመናችንስ ነቢያት ያስፈልጋሉ? የትንቢት ስጦታ አስፈላጊነት ምን ያህል ነው? በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ነቢያት ብቻ ናቸው ትንቢትን ይናገሩ የነበሩት ወይስ እስከ ምድር ታሪክ መጨረሻ ድረስ እግዚአብሔር ነቢያትን ያስነሳል? እውነተኛውንና ሐሰተኛውን ነቢይ እንዴት ነው መለየት የምንችለው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረጉ መልሶችን በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ይዘን ቀርበናል።

የትንቢት ስጦታ አስፈላጊነት

በአንድ ወቅት የይሁዳ ንጉስ ኢዮሣፍጥ በጭንቀት ላይ ነበር። በጠላት ወታደሮች በመከበቡ ምክንያት የነበረበት ሁኔታ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆኖ ሳለ “ኢዮሣፍጥ እግዚአብሔርን ሊፈልግ ፊቱን አቀና በይሁዳም ሁሉ ፆም አወጀ” (2ዜና 20፡3)። ሕዝቡም ከእግዚአብሔር ምህረትንና ድልን ለማግኘት ወደ ቤተ መቅደስ ለጸሎት ይጎርፉ ጀመር።

በጸሎትም ሰዓት ኢዮሣፍጥ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። ከደረሰበትም ችግር እንዲያወጣው ስለፈለገ እንዲህ ብሎ ጠየቀው “አቤቱ የአባታችን አምላክ ሆይ በሰማይ ያለህ አምላክ አንተ አይደለህምን? የአሕዛብንስ መንግሥት ሁሉ የምትገዛ አንተ አይደለህምን? ኃይልና ችሎት በእጅህ ነው ሊቋቋምህ የሚችል የለም” (ቁ. 6)። በመቀጠልም “አምላካችን ሆይ አንተ አትፈርድባቸውምን? ይህን የመጣብንን ታላቅ ወገን እንቃወም ዘንድ አንችልም፣ የምናደርገውን አናውቅም ነገር ግን ዓይኖቻችን ወደ አንተ ናቸው” (ቁ. 12) ብሎ የምር ጸሎት አቀረበ።

በዚያን ጊዜ መላው ይሁዳ በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ሳሉ የሕዚኤል የሚባል አንድ ሰው ተነሳና በፍርሃት ይንቀጠቀጥ የነበረውን ሕዝብ አበረታታ እንዲህም አላቸው፡- “ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው እንጂ የእናንተ አይደለምና አትፍሩ፣ አትደንግጡም … እናንተ በዚህ ሰልፍ የምትዋጉ አይደላችሁም … ተሰለፉ ዝም ብላችሁ ቁሙ፣ የሚሆነውንም የእግዚአብሔርን መድኃኒት እዩ፣ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፣ አትደንግጡም (ቁ. 15-17)።

በነጋታውም ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ወታደሮቹን ለማበረታታት እንዲህ አለ፣ “… በአምላካችን በእግዚአብሔር ታመኑ ትፀኑማላችሁ በነቢያቱም እመኑ ነገሩም ይሰላላችኋል (ይሳካላችኋል)” (ቁ. 20)።

ንጉሥ በነብዩ በየሕዚኤል ቃል ከመተማመኑ የተነሳ በጦርነቱ ላይ በግንባር ቀደምነት የታወቁትን ጀግና ወታደሮቹን በማድረግ ፈንታ የእግዚአብሔርን ክብርና ቅድስና ከፍ ከፍ የሚያደርጉትን መዘምራን እንዲቀድሙ አዘዘ። እነዚህም መዘምራን እምነት የሞላባቸውን መዝሙሮች በሚያሰሙበት ጊዜ እግዚአብሔር የይሁዳን ጠላቶች እርስ በእርሳቸው እንዲጨፋጨፉና አንዱ የራሱን ወገን እንዲገድል አደረገ። የታሪኩም መጨረሻ እንደሚነግረን “… ያመለጠ ሰው አልነበርም” (ቁ. 24)።

በኢዮሣፍጥ ዘመን ነቢዩ የሕዚኤል የእግዚአብሔር አፍ ነበር። በመፅሐፍ ቅዱስ አባባል “ነቢይ” ማለት ከእግዚአብሔር መልዕክትን ተቀብሎ ለሕዝቡ የሚያስተላልፍ ሰው ማለት ነው። ነቢያት ትንቢት ይናገሩ የነበረው በራሳቸው ሥልጣን ተነሳስተው አልነበረም። “ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ” (2ጴጥ. 1፡21)።

በተጨማሪም ስለ ነቢያት በ1ኛ ሳሙኤል 9፡9 ላይ እንዲህ የሚል ጥቅስ እናገኛለን፡- “ዛሬ ነቢይ የሚባለው ቀድሞ ‘ባለራዕይ’ ይባል ነበርና አስቀድሞ በእስራኤል ዘንድ ሰው እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሲሄድ፡- ‘ኑ ወደ ባለራዕይ እንሂድ’ ይል ነበር”፣ “ጌታ እግዚአብሔር ምስጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም” (አሞጽ 3፡17)።

በአዲስ ኪዳንም ውስጥ የትንቢት ስጦታ ከመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አንዱ በመሆን አስፈላጊውን ቦታ ይዞ እናገኘዋለን (ሮሜ 12፣6፤ 1ቆሮ 12፡28፤ ኤፌ. 4፡11)። ምዕመናን በተለይ ይህንን ስጦታ ለማግኘት እንዲጥሩ ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “… መንፈሳዊ ስጦታን ይልቁንም ትንቢት መናገርን በብርቱ ፈልጉ” (1ቆሮ. 14፡1) በማለት ይመክራል።

በአዲስ ኪዳን ዘገባ መሠረት የትንቢት ስጦታ የተሰጣቸው ነቢያት፡-

  1. ቤተክርስቲያንን በመገንባት ተካፋይነት ነበራቸው (ኤፌ. 2፡20)፤
  2. ቤተክርስቲያን ወንጌልን እንድታስፋፋ ያደፋፍሯት ነበር (ሐዋ. 13፡1-2፣ ሐዋ. 16፡6-10)፤
  3. ቤተክርስቲያንን ያንፁ ነበር (1ቆሮ. 14፡3-4፣ ኤፌ. 4፡12)፤
  4. ቤተክርስቲያንን ከሃሰት ትምህርት ይጠብቋት፣ የምዕመናንንም አንድነት ያጠነክሩ ነበር(ኤፌ.4፡14)፤
  5. ምዕመናንን ወደፊት ከሚደርሱባቸው ችግሮች ያስጠነቅቁ ነበር (የሐዋ. ሥራ 11፡27-30፣ ሐዋ. 21፡4፣ 10፣ 14)፤
  6. በቤተክርስቲያን ውስጥ መሠረታዊ ትምህርቶችን በተመለከተ ክርክር ሲኖር እውነተኛውን ትምህርት ግልፅ በማድረግ ውሳኔ ያስተላልፉ ነበር (ሐዋ. 15፡32)፤

ሁሉን ፈትኑ፣ መልካሙን ያዙ

የምድር ታሪክ የሚገባደድበት የመጨረሻው ዘመን ሲደርስ፣ ማለትም ጌታ ኢየሱስ ቃል በገባበት መሠረት ዳግም የሚመለስበት ጊዜ ሲቃረብ፣ ብዙ “እኔ ክርስቶስ ነኝ” ባዮች በኢየሱስ ስም እንደሚመጡና ብዙዎችን እንደሚያስቱ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል፤ “ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፣ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፣ ብዙዎችንም ያስታሉ” (ማቴ. 24፡4-5)። እነዚህ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ እንደሚያሳዩም የናዝሬቱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽ ተናግሯል (ማቴ. 24፡24)።

የእነዚህ ሐሰተኞች ነቢያት ተአምር፣ ምልክትና ድንቅ ነገሮች የማሳየት ችሎታ እውነተኛ ነቢያት ስለመሆናቸው አያረጋግጥም። “እውነተኛ ነቢያትንና ሐሰተኛ ነቢያትን እንዴት መለየት እንችላለን?” የሚለው ጥያቄ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ አንገብጋቢና ወቅታዊ የሆነበት ዘመን ላይ እንገኛለን። ደግነቱ፣ እጅግ በጣም የሚወደን አምላክ፣ በጠላት ወጥመድ ውስጥ እንዳንገባ ስለፈለገ “እነሆ አስቀድሜ ነገርኋችሁ” በማለት ክፉውንና በጎውን፣ እውነቱንና ሐሰትን፣ ከጌታ የሆነውንና ከዲያቢሎስ የሆነውን የምንለይበትን መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል። እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ በየዕለቱ በውስጣችን እንዲሆን ስንጋብዘው፣ ወደ እውነት ሁሉ እንደሚመራን የተስፋ ቃል ሰጥቶናል።

ሐዋርያው ጳውሎስም “ትንቢትን አትናቁ ሁሉን ፈትኑ መልካሙን ያዙ” በማለት ይመክረናል። ማለትም፣ በዘመናት ሁሉ ነቢያቶች ይኖራሉ ነገር ግን እነርሱ በርግጥ ከእግዚአብሔር ይሁኑ ወይም አይሁኑ ፈትኑ ማለቱ ነው። በመሆኑም፣ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረጉ፣ እውነተኛ ነቢያትንና ሐሰተኛ ነቢያትን የምንለይባቸውን መሥፈርቶች ከዚህ በታች በዝርዝር እንመለከታለን፡-

1. ነቢዩ የሚናገረው ትንቢት ሁልጊዜ ይፈጸማል፡- “ነገር ግን ስለ ሰላም ትንቢት የተናገረ ነቢይ እግዚአብሔር በእውነት እንደላከው የሚታወቀው የተናገረው ትንቢት ሲፈጸም ነው” (ኤር. 28፡9)። “አንተም በልብህ፣ ‘እግዚአብሔር ያልተናገረውን መልእክት እንዴት ማወቅ እንችላለን?’ ብትል፣ ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም የተናገረው ካልተፈጸመ ወይም እውነት ሆኖ ካልተገኘ፣ መልእክቱ እግዚአብሔር የተናገረው አይደለም። ያ ነቢይ በድፍረት ተናግሮታልና እርሱን አትፍራው” (ዘዳ. 18፡21-22)። እዚህ ላይ ነቢዩ ዮናስ “በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች” በማለት የተናገረው ትንቢት አለመፈጸሙን ልብ ይሏል (ዮናስ 3፡4)። ትንቢቱ ያልተፈጸመው ዮናስ ሃሰተኛ ነቢይ ስለነበር ሳይሆን የነነዌ ሰዎች ኃጢአታቸውን ስለተናዘዙ ነው።

2. እውነተኛ ነቢይ ራሱን ሳይሆን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ያደርጋል፣ ክብሩን ለራሱ ለነቢዩ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ይሰጣል፡- “የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ ከራሱ አይናገርም፤ የሚሰማውን ብቻ ይናገራል፤ እንዲሁም ወደ ፊት ስለሚሆነው ይነግራችኋል፤ የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ በማድረግ ያከብረኛል” (ዮሐ. 16፡13-14)። “ዮሐንስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል … እርሱ ሊልቅ፣ እኔ ግን ላንስ ይገባል” (ዮሐ. 3፡30)።

3. እውነተኛ ነቢይ፣ የእግዚአብሔርን ቃል የበለጠ ለማስረዳት/ለማስተማር፣ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ ጥቅስን ከጥቅስ ጋር እያጣቀሰ ያስተምራል እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃልን በዘፈቀደ ወይም ራሱ እንደተመቸው አይተረጉምም፡- “ከሁሉ አስቀድሞ ይህን ልታውቁ ይገባችኋል፤ በመጽሐፍ ያለው የትንቢት ቃል ሁሉ ማንም ሰው በገዛ ራሱ መንገድ የሚተረጒመው አይደለም፤ ምክንያቱም ትንቢት ከእግዚአብሔር የተላኩ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩት እንጂ ከቶ በሰው ፈቃድ የመጣ አይደለም“ (2ኛ ጴጥ. 1፡20-21)።

4. እውነተኛ ነቢይ ኃጢአትን አያደባብስም፣ ኃጢአትን በስሙ ጠርቶ ይገስጻል፡- “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሕዝቤን የሚያስቱ ነቢያት፣ ሰው ሲያበላቸው፣ ‘ሰላም አለ’ ይላሉ፤ ሳያበላቸው ሲቀር ግን፣ ጦርነት ሊያውጁበት ይነሣሉ። … እኔ ግን፣ ለያዕቆብ በደሉን፣ ለእስራኤልም ኃጢአቱን እነግር ዘንድ ኃይልን፣ በእግዚአብሔር መንፈስ፣ ፍትሕና ብርታት ተሞልቻለሁ“ (ሚክያስ 3፡5፣8)። “በኃይል ጩኽ፤ ምንም አታስቀር፤ ድምፅህን እንደ መለከት አሰማ፤ ለሕዝቤ ዐመፃቸውን፣ ለያዕቆብም ቤት ኃጢአታቸውን ተናገር“ (ኢሳ. 58፡1)። “መጥምቁ ዮሐንስም ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሃ ግቡ’ እያለ ህዝቡን ወደንስሃ ሲያድም ነበር። ሕዝቡም ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ይጠመቁ ነበር“ (ማቴ. 3፡1፣2፣6)።

5. እውነተኛ ነቢይ የፍርድ ሰዓት እንደደረሰ (እንደተቃረበ)፣ ሰዎች ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ ያስጠነቅቃል፡- “ምድር እንደ ሰካራም ዞረባት፤ ነፋስ እንደሚወዘውዘውም ጐጆ ሆነች፣ የዓመጿ ሸክም ከባድ ስለ ሆነ ትወድቃለች፤ እንደ ገናም አትነሣም። በዚያ ቀን እግዚአብሔር፣ በላይ በሰማያት ያሉትን ኀይሎች፣ በታችም በምድር ያሉትን ነገሥታት ይቀጣቸዋል” (ኢሳ. 24፡20-21)።

6. እውነተኛ ነቢይ ቤተክርስቲያንን ያንጻል፣ ያበረታታል፣ ያነቃቃል፣ በመንፈሳዊ ሕይወት እንድታድግ ያግዛታል፡- “ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽ፣ ለማበረታታትና ለማጽናናት ለሰው ይናገራል። በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል፤ ትንቢትን የሚናገር ግን ቤተ ክርስቲያንን ያንጻል“ (1ኛ ቆሮ. 14፡3-4)።

7. የእውነተኛ ነቢይ መልእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፈው ቃል ጋር ይስማማል እንጂ አይቃረንም፡- “ወደ ሕጉና ወደ ምስክር ቃሉ ሂዱ! እነርሱም እንዲህ ያለውን ቃል ባይናገሩ የንጋት ብርሃን አይበራላቸውም” (ኢሳ. 8፡20)። በሌላ አነጋገር የአግዚአብሔርን ሕግና ምስክር የሚያቃልል ነቢይ ከእግዚአብሔር የተላኩ ነኝ ማለት አይችልም። እንዲያው ጥቅሱ የሚለው በእግዚአብሔር ሕግና ምስክር መሠረት የማይናገሩ ከሆነ ብርሃን በውስጣቸው ስለሌላቸው ነው። በእንግሊዝኛ እንዲህ ይላል “To the law and to the testimony! If they do not speak according to this word, it is because there is no light in them” (NKJV).

8. እውነተኛ ነቢይ ክርስቶስ በሥጋ እንደተገለጠ ይናገራል፣ ያስተምራል፡- “ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና። የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥ ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ” (1ኛ ዮሐ. 4፡1-3)። ስለዚህ ነቢያት ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ ወደ ምድር እንደሚመጣ ማመን፣ እንዲሁም ስለ እርሱ መስበክና ማስተማር አለባቸው።

9. እውነተኛ ነቢይ ትሁት ነው ራስወዳድ አይደለም፤ ይህም በፍሬው ይታወቃል:- “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን?” (ማቴ. 7፡15-16)። የነቢያት ሕይወት (ፍሬ) ከመጸሐፍ ቅዱስ ጋር መስማማት ይኖርበታል (ማቴ 7፡1 8-21 እና ገላ 5፡19-23)። “የትንቢት ስጦታ አለኝ” የሚል ማንኛውም ሰው እነዚህን መለኪያዎች ካሟላ፣ በርግጥ መንፈስ ቅዱስ ለእርሱ የትንቢት ስጦታን እንደሰጠው ማመን፣ በመልዕክቱም መታመን ይቻላል።

10. እውነተኛ ነቢይ ለእግዚአብሔር ቃልና ለእግዚአብሔር ሕግ ይታዘዛል፡- “ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፥ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል” (ዘዳ. 18፡18)። “እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፥ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው” (ሐዋ. 5፡32)።

11. እውነተኛ ነቢይ የነቢይነት አገልግሎትን በነጻ ይሰጣል፣ ገንዘብ አይቀበልም፡- “ዳንኤልም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ ‘ስጦታዎችህን ለራስህ አድርግ፤ ሽልማቶችህንም ለሌላ ሰው ስጥ፤ ይሁን እንጂ ጽሕፈቱን ለንጉሡ አነባለሁ፤ ትርጒሙ ምን እንደሆነም እነግረዋለሁ’” (ዳንኤል 5፡17)። “ወዮላቸው፣ በቃየን መንገድ ሄደዋል፤ ለገንዘብ ሲስገበገቡ በበለዓም ስሕተት ውስጥ ወድቀዋል፤ በቆሬም ዐመፅ ጠፍተዋል” (ይሁዳ 1፡11)።

ማጠቃለያ

አንድ ማስተዋል የሚገባን ነገር አለ። ከላይ በተዘረዘሩት በእነዚህ መሥፈርቶች በአንዱ ወይም በሁለቱ ብቻ አንድን ሰው ትክክለኛ ወይም ሃሰተኛ ነብይ ነው ማለት አንችልም። ለምሳሌ ዮናስ ከእግዚአብሔር የተላከ ነቢይ ነበር። የተሰጠውም መልዕክት “በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች” የሚል ነበር (ዮናስ 3፡4)። ነገር ግን የነነዌ ሰዎች ንሰሐ በመግባታቸውና ኃጢአታቸውን በጾምና ጸሎት በመናዘዛቸው ከሚመጣባቸው ቁጣ ዳኑ። ዮናስ የተናገረው ትንቢት ያልተፈጸመው በዮናስ ሃሰተኛ ነቢይነት ምክንያት ሳይሆን በአምላክ ቸርነትና ምህረት ነው። ስለዚህ ይህ ነቢዩን ሃሰተኛ አያስብለውም።  

እንግዲህ ውድ አንባቢያን፡- በዚህች አጠር ባለች ጽሁፍ አማካኝነት የእውነተኛ ነቢይ መለያ መስፈርቶች ምን እንደሆኑ በመጠኑም ቢሆን እንዳስተዋላችሁ ተስፋ አለኝ። መጽሐፍ ቅዱስ “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ” (ኢሳ. 54፡13) ስለሚል፣ እናንተ እራሳችሁ በግላችሁ ቃሉን የበለጠ በመመርመር በዘመናችን እንደ አንበጣ የተስፋፉትን ሐሰተኛ፣ አታላይ እና ዘራፊ ነቢያት እንድትለዩ እንዲሁም ከእነርሱ እንድትጠበቁ በትህትና እና በወንድማዊ ፍቅር እማጸናችኋለሁ። ተጨማሪ ጥያቄዎች ካላችሁ በገጽ 3 ላይ በሚገኘው አድራሻችን ልትልኩልን ትችላላችሁ።

ዳዊት መሐሪ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *