giziew.org

ኢየሱስ በርባን ወይስ ኢየሱስ ክርስቶስ?

Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ጥናቱ ትንሽ ቆየት ያለ ነው፤ ውጤቱ ግን ብዙ የሚናገረው አለ። አጥኚዎቹ እንደሚሉት አንድ እንግሊዛዊ (ለሌሎችም ሊውል ይችላል) በአማካይ የሕይወት ዘመኑ 773,618 ውሳኔዎችን ያሳልፋል። ከእነዚህ ውስጥ 143,262 ያህሉ የሚጸጸትባቸው ውሳኔዎች ናቸው። ይህም ከአምስቱ ውሳኔዎቹ አንዱ ማለት ነው። ውሳኔና ምርጫ የተጋመዱ ናቸው። እኛም በተለምዶ “የምርጫ ጉዳይ ነው” እንላለን። ውጤቱ ግን ቀላል አይደለም፤ ጥሩ ውሳኔ ከሆነ በረከቱ፤ መጥፎ ከሆነ መዘዙ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ነው።

ወቅቱ ጭቆና እጅግ የሰፈነበት ነበር፤ የአይሁድ ሕዝብ በጨካኙ የሮም አገዛዝ ሥር የወደቀበት፣ ሃይማኖቱ የረከሰበት፣ መብቱ የተረገጠበት፣ ነጻ አውጪ የናፈቀበት፣ መሢሕ የተመኘበት ዘመን! መሢሕ ይመጣል የሚለውን ትንቢት ተከትሎ ዘመኑ በርካታ ሰዎች “እኔ መሢሕ ነኝ” ብለው የተነሱበት ነበር።

“የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” ሆኖ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣበት ዘመን የአይሁድ ሕዝብ በየወገኑ ተከፋፍሎ ነበር። የእግዚአብሔርን ሕግ ተጠንቅቀው የሚውቁና የሚጠብቁ፣ በየምኩራቡ የሚያስተምሩ፣ የአይሁድን ወግ አጥብቀው የሚከተሉ፣ ከሕዝቡ ጋር ቅርብ ግንኙነት ያላቸው ፈሪሳውያን ነበሩ። “ፈሪሳዊ” ማለት ከሌሎች ልዩ የሆነ፣ የተለየ ማለት ነው። ታዋቂው የዘመኑ ታሪክ ጸሐፊ ጆሲፈስ እንደሚለው በኢየሩሳሌም ብቻ በዚያን ወቅት ከስድስት ሺህ በላይ ፈሪሳውያን ነበሩ።

ሌሎች ደግሞ ከሮም ጋር ተመቻምቸው መኖርን የመረጡ፤ ቤተ መቅደሱን በበላይነት የሚመሩ፣ የሊቀ ክህንነት ቦታ የወሰዱ፣ ሮም ሥልጣናቸውን እንድታስጠብቅላቸው የሚጠየቀውን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ የማይሉ፣ በዘመናችን ቋንቋ “ልሒቃን” የሚባሉት፣ በሃብትም የበለጸጉ ናቸው የሚባልላቸው ሰዱቃውያን ነበሩ። ሥልጣናቸው እስከተጠበቀ ድረስ የአይሁድ ሥርዓትና ወግ ለእነርሱ ምናቸውም አይደለም።

ከሁለቱም ወገን ያልሆኑ በተለይ ፈሪሳውያንን “ተበርዘዋል” የሚሉ፣ ንጹሑ የአይሁድ ሃይማኖት ተበላሽቷል፣ በትክክለኛው መንገድ መጠበቅ አለበት የሚሉ፣ አንዳንዶቹ ራሳቸውን ከማኅበረሰቡ ለይተው እንደ ቁምራን ባሉ ቦታዎች የሚኖሩ፤ ሌሎቹ ደግሞ ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅለው ግን ሃይማኖታዊ ንጽሕናቸውን ጠብቀው ኤሲንስ የሚባሉ ነበሩ።  

ከእነዚህ ሁሉ የሚለዩና የተነጠቅነውን መብት በኃይል እናስመልሳለን የሚሉ ቀናተኛ ተብለው የሚጠሩ ነበሩ። ከእነርሱ ውስጥም በጣም ጽንፈኛና በሽብር ሥራ የተሰማሩ፣ የሮም ወታደሮችንም ሆነ ሹሞች እንዲሁም ለሮም የሚያገለግል ማንኛውንም ሰው (ለምሳሌ ቀራጭ ወይም ቀረጥ የሚቀርጥ አይሁድ) በተገኘበት ቦታ ለመግደል ጩቤ ይዘው የሚዞሩና “ሲካሪ” ወይም “ባለ ጩቤዎቹ” የሚባሉ ነበሩ። በርባን የዚህ ቡድን አባል ነበር በሚለው በርካቶች ይስማማሉ።

ከእነዚህ ቡድኖች፣ ከዚህ በፊት “ኢየሱስ ነኝ” ብለው ከተነሱት፣ በወቅቱ ከነበሩት፣ ሁሉ ፍጹም የተለየ ነበር። ትምህርቱ ልዩ የሆነ፤ ጠላትህ አጥፋው፣ ግደለው በሚባልበት ዘመን “ጠላትህን ውደድ”፤ “የሚረግሙአችሁን መርቁ፣ ለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ፣ ቀኝ ጕንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጕንጭህን ደግሞ አዙርለት። እጀ ጠባብህን ሊወስድ ለሚፈልግ ካባህን ጨምረህ ስጠው። አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል የሚያህል ርቀት እንድትሄድ ቢያስገድድህ ዕጥፉን መንገድ አብረኸው ሂድ” እያለ የሚያስተምር ልዩ መምህር ነበር ኢየሱስ ክርስቶስ። ሌሎቹን እንኳን ብንተው ይህ ዓይነቱ ትምህርት ቀናተኞቹ እንዴት ሊቀበሉት ይችላሉ? ፈጽሞ ያልተጠበቀ መሢሕ ነበር።

በርባን በአራቱም ወንጌላት ተጠቅሷል። “በዐመፅ የታወቀ … እስረኛ ነበር” ይለዋል ማቴዎስ 27፡16፤ “በዐመፃ ተነሣሥተው ነፍስ ከገደሉ ዐመፀኞች ጋር የታሰረ በርባን የሚባል አንድ ሰው ነበረ” በማለት በማርቆስ 15፡7 ተጠቅሷል። ሉቃስ (23፡19) ደግሞ ሲጽፍ “በርባንም በከተማ ውስጥ የሕዝብ ዐመፅ በማነሣሣትና በነፍስ ግድያ የታሰረ ሰው ነበር” ይላል። ጲላጦስ “ማንን ልፍታላችሁ?” እያለ ሲጠይቅ “በርባንን” የሚል ምላሽ ማግኘቱን ዮሐንስ ከጠቀሰ በኋላ ስለ በርባር ሲናገር “በርባን ግን ወንበዴ ነበር” ይላል (ዮሐንስ 18፡40)። ሐዋርያው ጴጥሮስ ደግሞ “ቅዱሱን ጻድቁንም ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩን ሰው ይሰጣችሁ ዘንድ ለመናችሁ” በማለት ጲላጦስ ምርጫ ሲያደርግላቸው ነፍስ አዳኙን ይሰቀል ብለው ነፍስ ገዳዩን ነጻ እንዲለቀቅ መምረጣቸውን ያስታውሳል (የሐዋርያት ሥራ 3፡14)።

በዚያን ዘመን በርካታ ሰዎች “ኢየሱስ” የሚል የግል መጠሪያ ስም ነበራቸው። ከእነርሱም መካከል በርባን አንዱ ነበር። በማቴዎስ 27፡17 ጲላጦስ “ማንን ልፍታላችሁ?” በማለት ያቀረበውን ጥያቄ NIV, NET, NRSV የተሰኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “(ኢየሱስ) በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን?” በማለት ጽፈውታል። ቀደምት አባቶች ይህንኑ እንደሚደግፉ የተናገሩ ሲሆን ምሑራንም የበርባን ሙሉ ስሙ “ኢየሱስ በርባን” ነበር በማለት ይናገራሉ። “በርባን” የአረማይስጥ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም “የአባቱ ልጅ” ማለት ነው።

በወቅቱ የቀረበው ጥያቄ ማንን ትመርጣላችሁ? የሚል ነበር። ኢየሱስ በርባንን ወይስ ኢየሱስ ክርስቶስን!? ኢየሱስ የአብን ልጅ ወይስ ኢየሱስ የአባቱን ልጅ!? ለጥቂት ነው የሳቱት ልንል እንችላለን። ሌላም ምክንያት መደርደር ይቻላል። በዘላለም ሕይወት ምርጫ ግን “ለጥቂት መሳት” የሚባል ነገር የለም። በጭፍን፣ በብዙ፣ በጥቂት መሳት በሙሉ መሳት ነው። ምርጫው ሊመሳሰል ይችላል፤ ምርጫውን የሚሰጠው አምላካችን ግን በምርጫው እንዳንሳሳት ግልጽ አድርጎ ነው የሚያቀርበው።

ያለንበት የመጨረሻ ዘመን ማሳሳቻው እጅግ የበዛበት ነው። ጌታችን ሲናገር “ብዙዎች፦ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። … ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ” (ማቴዎስ 24፡5፣11)። ሐሰተኞቹ “ጥቂቶች” ናቸው አላለም፤ በተደጋጋሚ “ብዙዎች” በማለት ነው የጠቀሳቸው። የቁጥር መብዛት ብቻ ሳይሆን የዓይነትም ጭምር ነው። ስለዚህ የዘመናችን የማሳሳቻ መንገዱ እጅግ የረቀቀና በርካታዎችን የሚያስት ነው። ስለዚህ አለ ጌታችን ክርስቶስ ሲናገር “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ” (ማቴዎስ 24፡4)።

ሐዋርያው ጳውሎስም በመጨረሻው ዘመን “ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን” እንደሚለውጥ አገልጋዮቹም “የጽድቅ አገልጋዮች ለመምሰል ራሳቸውን” እንደሚለውጡ ይነግረናል (2ኛ ቆሮንቶስ 11፡14-15)። ለመለየት የሚያዳግት የሚመስል ትልቅ ተመሳስሎ ነው። አሳቹ ዲያቢሎስ ግን በዚህ ሳይገታ እሳት እንኳ ሳይቀር ከሰማይ በማውረድ ታላላቅ ድንቅና ተዓምራት እንደሚያደርግም ተጽፎልናል (ራዕይ 13፡13)።

አይሁድ ምርጫ ሲቀርብላቸው ከኃጢአት ነጻ የሚያወጣቸውን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመምረጥ ይልቅ ከሮም ነጻ ያወጣናል ብለው ያሰቡትን ኢየሱስ በርባንን መረጡ። እኛስ ዛሬ ማንን ነው የምንመርጠው? ክርስቶስ ወይስ በርባን ተብሎ ላይቀርብልን ይችላል፤ ምክንያቱም የማሳሳቻው ሥልት ተቀይሯል። ጥያቄው ለመወሰን መሥፈርት የምናደርገው ምንድነው የሚለው ላይ ነው። ምክንያቱም መሥፈርታችን ምርጫችንን ይወስናል። ለአይሁድ መሥፈርታቸው ከሮም ነጻ መውጣት ነበር፤ ለእኛስ?

ዛሬስ ማንን ትመርጣለህ? ኢየሱስ ክርስቶስ የአብን ልጅ ወይስ ኢየሱስ በርባን የአባቱን ልጅ?  

ጥበበሥላሴ መንግሥቱ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *