በቤተሰብ ምሥረታ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር በእግዚአብሔርና በመላእክት እንዲሁም በታዳሚዎች ፊት ቆመው ሁለቱ ሙሽሮች የተለዋወጡትን ቃልኪዳን መጠበቅ ነው። የትዳር መፍረስና የቤተሰብ መበተን ወይም ማንኛውም በትዳር የሚከሰት ችግር የሚመጣው ይህንን ቃልኪዳን ባለመጠበቅ ነው። በማቴዎስ 24፡12-13 “ከአመፃም ብዛት የተነሳ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች፤ እስከመጨረሻ የሚፀና ግን እርሱ ይድናል” የሚለው የክርስቶስ አባባል ሁለንተናዊ ጠቀሜታ አለው። ቤተሰብን በተመለከተም ታላቅ ትምህርት ያለበት ነው። ብዙጊዜ ቃልኪዳንን ማፍረስ የሚመጣው የሠርግ ጋጋታው አልፎ ወደ ትዳር ዓለም ዘልቀው ከገቡ በኋላ ነው። አዲሶቹ ተጋቢዎች ዕለት ዕለት በእግዚአብሔር ተመርተው ካልኖሩ ፍቅራቸውን የሚያቀዘቅዙና ቃልኪዳናቸውን የሚያስረሱ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል።
ስለ ሁለት ወጣቶች የጋብቻ ታሪክ ሞሪስ ቬንደን “To Know God” በሚል ርዕስ በፃፉት መጻሐፍ ላይ ይህ ይነበባል፤ “(አዲሶቹ ተጋቢዎች በጣም ይዋደዱ ነበር) ባል ሚስቱን ‹ከሴቶች ሁሉ በውበትም በባህሪም የበለጠች ፍጡር ነች› ይል ነበር። ሚስትም በምላሹ ‹ባለቤቴ በዓለም የሚስተካከለው የሌለ መልከ መልካም ነው› ብላ ታስብ ነበር። ትዳራቸው በዚህ ዓይነት ተጀመረ። በየጠዋቱ ባል ለሥራ ሲወጣ ሚስቱን ይሰናበታታል፤ እርሷም በበር ላይ ቆማ እጇን እያወዛወዘች ከዓይኗ እስኪሰወር ትሰናበተዋለች። ከሥራ መልስ የመስኮቷን መጋረጃ ገለጥ አድርጋ ከሩቅ ትጠብቀዋለች፤ በበርም ሆና ትቀበለዋለች።
“ጊዜ ቀናትና ሳምንታት እያለፉ ሲሔዱ ግን የፍቅራቸው ግለት እየቀዘቀዘ ሄደ። ባል ጠዋት ይነሳና በጠረጴዛው ላይ ያለውን ቁርሱን በልቶ፤ ሻዩን ፉት ፉት አድርጎ በችኮላ ይወጣል። ሚስትም ባሏ ማታ ከሥራ መልስ ሲመጣ በቤት ውስጥ ሥራ ተጠምዳ ታየውና ‹ለካ መጥተሃል የያዝኩትን ልጨርስና እራት አቀርባለሁ› ትለዋለች። የባሰው ግን አሁንም ገና ነው። ብዙ ሳይቆይ አንድ ቀን በቤት ሆና እየሠራች ቀኑ ወደ ምሽት ሲቀየር የባሏን መምጣት እየጠበቀች ነበር፤ አልመጣም። ራት አቀረበች፤ ጠበቀች፤ አልመጣም። ብቻዋን ቀርባ ቀማምሳ በሳሎኗ ሶፋ ላይ ጋደም አለች። በዚያ ቀን ወደ ቤት ሳይመጣ አደረ፤ ቀኑንም ውሎ ማታ መጣ።
“ሚስት፤ ‹የት ነበርክ?›
“ባል፤ ‹ምን ማለትሽ ነው?›
“ሚስት፤ (ድምጽዋን ከረር አድርጋ) ‹የት ነበርህ?›
“ባል፤ (የበለጠ በመገረም) ‹የት እንደነበርኩ ለማወቅ ለምን ፈለግሽ? በየምሽቱ ቤት እንድመጣ መጠበቅ የለብሽም› በማለት ልብ የሚነካ ምላሽ ይሰጣል። ሲቀጥልም ‹በሺዎች የሚቆጠሩ ባለትዳሮች በተለያየ ቦታ ይኖራሉ፤ እኔ አልፎ አልፎ ባልመጣ አያስገርምም፤ ስለትዳራችን ይህንን ያህል አክራሪዎች መሆን የለብንም፤ ትላንት ማታ ቤት መምጣት አላሰኘኝም፤ የምሠራው በጣም አስፈላጊ ሥራ ነበረኝ፤ (እንደምታውቂው) ብዙ ጊዜ ማታ እገባለሁ፤ ያ አይበቃም እንዴ?›
“ሚስት፤ (ሳግ እየተናነቃት) ‹አይበቃም!› አለች፤ እንባዋን አፈሰሰች።”
ስለዚህ ትዳር ፍፃሜ ለማወቅ ብዙ ምርምር የሚጠይቅ አይደለም። ከዚህ በኋላ እነዚህ ባለትዳሮች በደስታ አብረው ሊኖሩ አይችሉም። ምክንያቱም ትዳር በቃልኪዳን ላይ የተመሰረተ ነው። ቃልኪዳን ሲፈርስ የባለትዳሮች ግንኙነት እየላላ ይሄድና መጨረሻው መለያየት ይሆናል። ቃልኪዳኑ በማቴዎስ 19፡5 መሠረት ሁለት ቁምነገሮችን ያካተተ ነው። የመጀመሪያው መተው ሲሆን ሁለተኛው መጣበቅ ነው። ስለዚህ “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይጣበቃ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” ባልም ሆነ ሚስት ከሁሉ በፊት የሚያውቁት አባታቸውንና እናታቸውን ነው። ከወላጆቻቸው የሚቀርባቸው ምንም ነገር የለም። ስለዚህ ከትዳር ጓደኛቸው ጋር አንድ ለመሆን እናታቸውንና አባታቸውን ከተዉ፤ የማይተውት ነገር የለም ማለት ነው! በጋብቻ ጊዜም የሚገቡት ቃልኪዳን በዚህ እውነት ላይ የተመሠረተ ነው።
መጣበቅ የሚያካትታቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? የሚለውን ስንወስድ በጣም ጎልቶ የሚታየው አብሮ መሆን ነው። ይህም ማለት በአካልና በመንፈስ አብሮ መሆን ማለት ነው። ነገርግን በዚህች ምድር አልፎ አልፎ በአካል አብሮ መሆን የማይቻልበት የተለያዩ ምክንያቶች ይኖራሉ። ሆኖም ሰዎች በተለይም ባለትዳሮች አብረው በሚሆኑበት ጊዜ መልካም ወሬዎችን እያነሱ ይጫወታሉ፤ ይስቃሉ፣ ይደሰታሉ፣ የሕይወትን ግድድሮሽ አብረው ይጋፈጣሉ፤ አብረው የእግዚአብሔርን ቃል ያጠናሉ፣ ይፀልያሉ፣ ወዘተ …።
ብዙ ጊዜ የባለትዳሮችን አብሮ መሆን የሚጋፋው ክፉ ምክንያት ሥራ ነው። ሥራ በራሱ መልካም ነው። ነገር ግን ባለትዳሮች አብሮ የሚሆኑበትንና የሚዝናኑበትን ጊዜ የሚያሳጣ መሆን የለበትም። በመክብብ 3፤1 ላይ “ከሰማይ በታች ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው፤” ይልና በቁጥር 3 ደግሞ “ለመሥራትም ጊዜ አለው” ይላል። ስለዚህ ባለትዳሮች በዚህ የእግዚአብሔር ቃል መሠረት ተግባራቸውን የሚያከናውኑበትንና አብሮ የሚሆኑበትን ጊዜ ለይተው በማወቅ መኖር አለባቸው።
ባለቤቱን ለማስደሰት ራሱን በሥራ የጠመደ ባል እንዲህ አለ፤ “ሚስቴን ለማስደሰት ብዙ ጥረት አደርጋለሁ፤ የቤት ውስጥ ሥራ ሳይቀር እሠራለሁ፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜዬን አጥፍቼ የምሠራው ሥራ ብዙ ዎጋ አስከፍሎኛል። የምግብ ሳህኖችን ሳጥብ በጣም ውድ ሳህኖቻችንን ሰብሬያለሁ፤ የሚስቴን ልብስ ስተኩስ የምትወደውን ቀሚሷን በጋለ ካውያ አቃጥያለሁ፤ ቤት ሳጸዳ የተሳሳተ የወለል ሰም በመቀባት አበላሽቼ እንደገና ያንን ለማስለቀቅ ወለሉን በመፋቅ ብዙ ጊዜ አባክኛለሁ፤ ባለቤቴ ግን ከሁሉ በላይ የምትፈልገው ቁጭ ብለን እንድናወራ፣ አብረን በመሆን ጊዜ
እንድናሳልፍ ነው። እኔ ግን ብዙ የምሠራው ስለነበረኝ አልቻልኩም።’’ ብዙ ባለትዳሮች አብሮ በመሆን የሚያሳልፉትን ጊዜ መስዕዋት በማድረግ በሚሠሩት ሥራ ቤተሰባቸውን የጠቀሙ ይመስላቸዋል። አንዳንዶችም ከትዳር ጓደኛቸው ጋር አብረው ማሳለፍ ያቃታቸውን ጊዜ ሥራ በመሥራት ለማካካስ ይሞክራሉ። እውነቱ ግን ጥቅም ሳይሆን ጉዳት ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉም ጊዜ አለው ባለው መሰረት ለመስራትም ሆነ ከትዳር ጓደኛ ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ አልፎም እንደቤተሰብ በአንድነት ተሰባስበው ለመደሰት ለመወያየት ለመማማር ለመፀለይ ጊዜያቸውን ቢጠቀሙ በስራ የተከናወነላቸው ይሆናሉ ትዳራቸውም የተባረከ ይሆናል የቤተሰብ ቅርርባቸውም አስደሳች ይሆናል፣ ቃልኪዳን መለዋወጡ፣ አስፈላጊ የሆነውን ያህል ቃልኪዳንን ጠብቆ መገኘት የበለጠ አስፈላጊ ነው ይህንን በትዳር ሕይወታችን እንድንለማመደው እግዚአብሔር ይርዳን።
ፓ/ር አገኘሁ ወንድም