የቫይታሚን ሲ እጥረትን መከላከል የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል ዓቅም እንደሚያዳብር ለበርካታ ዓመታት ሲነገር ቆይቷል። በቅርቡ በቻይና ዜንዡ ዩኒቨርሲቲ በተደረገ ጥናት የቫይታሚን ሲ መጠን በተገቢው መገኘት የአጥንት መሰበርን፣ መሰንጠቅን እንደሚከላከል ተነግሯል። ለዚህ ደግሞ ዋንኛ ምንጭ የሆነው ብርቱካን መመገብ ጠቃሚ እንደሆነ አብሮ ተገልጾዋል።
ይህም ማለት በቀን አንድ መካከለኛ መጠን ያለው ብርቱካን መመገብ ወይም አዲስ የተጨመቀ የአንድ ብርጭቆ 1/4ኛ የብርቱካን ጭማቂ መጠጣት የአጥንት ስብራት በመከላከል ዓይነተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋል። በጠኑን በእጥፍ መጨመር ጉዳቱን በግማሽ መከላከል እንደሚያስችል ጥናቱ ጠቁሟል።
ቫይታሚን ሲ ከብርቱካን ሌላ በብዛት በቲማቲም፣ በእንጆሪ እና በእንግሊዝኛ ኪዊ እና ብሮኮሊ በሚባሉት አትክልትና ፍራፍሬዎች ውስጥ ይገኛል።
በእንግሊዝ፣ በዌልስና በሰሜን አየርላንድ በዓመት 65ሺህ ሰዎች በዳሌ አጥንት መሰበር ወይም መሰንጠቅ ይሰቃያሉ። በተለይ ከዕድሜ መግፋት ጋር በተያያዘ አጥንት ውስጡ እንደ እንጀራ ቀዳዳ በመሥራት በቀላሉ ተሰባሪ ይሆናል። ይህም ኦስቲዮፖሮሲስ የተባለውን የአጥንት ህመም ያስከትላል።