giziew.org

ቤተሰብና ትዳር

ትዳር የተለየ እንክብካቤን የሚጠይቅ የሁለት ሰብዓዊ ፍጡሮች አንድነት ነው
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

የቤተሰብ መሰረት ትዳር ነው። ትዳር ደግሞ የአንድ ወንድ እና የአንዲት ሴት አብሮ ለመኖር እና ባልና ሚስት ለመሆን መወሰን እና ቃልኪዳን መለዋወጥ ነው። ይህ በእግዚአብሔር አምሳል ለተፈጠረ ሰው በጣም አስፈላጊ የሆነ ውህደት እንደሆነ እግዚአብሔር ራሱ “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት” በማለት የትዳርና የቤተሰብን አስፈላጊነት ተናግሯል (ዘፍጥረት 2፡18)። እግዚአብሔር መልካም ነው ያለው መልካም ነው። በተቃራኒው መልካም አይደለም ያለውም መልካም አይደለም። ትዳርን በተመለከተ መልካም አይደለም የተባለው ብቸኝነት ነው። አዳም ከትዳር በፊት ብቸኝነት ያጠቃው ሰው ነበር። የሚበላ፣ የሚጠጣ ለዓይን የሚያስደስት ነገር ከብቦት እያለ ደስተኛ አልነበረም። ለሰው የትዳርን በረከት ምንም ነገር ሊተካው አይችልም፤ ስልጣን፣ ገዢነት፣ የበላይነት ሊተካው አይችልም። ያ ቢሆን ኖሮ አዳም የፍጥረታት ጥበቃ ኃላፊነት ስለነበረው ደስተኛ በሆነ ነበር።

ሀብትም ትዳርን ሊተካ አይችልም። ለአዳም በኤደን ገነት የነበረ ምግብና ለኑሮ የሚያስፈልገው ሁሉ በእጁ ስለነበረ ደስተኛ በሆነ ነበር፤ አዳም ደስተኛነትን የተለማመደው እግዚአብሔር የትዳር ጓደኛን በሰጠው ጊዜ ነበር። “ይህቺ አጥንት ከአጥንቴ ስጋም ከስጋዬ ናት” አለ (ዘፍጥረት 2፣23)፤ ይህ የእኔነት ስሜት የሚባለው ነው። ሰው የእኔ ነው የሚለው ያስፈልገዋል። ይህንንም ጥማቱን የሚያረካለት ትዳር ነው።

ትዳር የሚመሰርት ሰው ከብቸኝነት ይላቀቃል። በመጀመሪያ ከትዳር ጓደኛው ጋር ካለው ቅርርብ እና መተሳሰብ፣ አብሮ መሰራት፣ አብሮ መፀለይ፣ አብሮ የኑሮን ግድድሮሽ መጋጠም የተነሳ ብቸኝነቱ ይቀረፋል፣ ከዚያም ባለፈ ከትዳር ጓደኛ ወላጆች፣ ወንድሞችና እህቶች፣ እንዲሁም በሁለቱም በኩል ካሉት ቤተዘመዶች ጋር የመቀራረብ እና የመተሳሰብ ግንኙነታቸው የማህበራዊ ህይወታቸውን አድማስ እያሰፉ በትዳር ህይወታቸውም ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች በረከት የሚሆኑበትን የአገልግሎት በር ይከፍትላቸዋል። ይህ ሁሉ እውን የሚሆነው አስቀድመው ሁለቱ የትዳር ጓደኛሞች ከሚኖራቸው አንድነት እና የእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሰረተ ፍቅርና መደጋገፍ ላይ ተነስቶ ስለሆነ ከሁሉ በፊት አንዱ ለሌላው በረከት የሚሆንበትን የትዳር ህይወት መኖር እንዳለበት ማወቁ እና መተግበሩ በጣም አስፈላጊ ነው።

በትዳር ለሚጣመሩ ወንድና ሴት የእርስ በርስ ባህርያቸውን ማወቅ፣ ደካማና ጠንካራ ጎኖቻቸውን መለየት እና ደካማ ጎኖቻቸውን አስወግደው በጠንካራ ጎኖቻቸው ላይ የበለጠ ለመገንባት መሥራት ለትዳር ህይወታቸው እድገት እና ለማህበራዊ ህይወታቸው ክንውንን ያስገኝላቸዋል። የትዳር መፍረስ ዱብ እዳ ወይም በድንገት ሳያውቁት የሚከሰት ነገር አይደለም። ለትዳር ጓደኛ ትኩረት ከመከልከል ይጀምራል፣ ለትዳር ጓደኛ ደግነትን ከማሳየት ድክምት የተነሳ ብዙ ትዳሮች ለአደጋ ተጋልጠዋል፤ ከስራ ብዛት የተነሳ ለትዳር ጓደኛ አለማሰብ ወይም በግል ችግር ላይ በማተኮር የትዳር ጓደኛን ችግር አለማየት ወዘተ በትዳር ላይ አሉታዊ ተፅእኖ አላቸው።

ትዳር የተለየ እንክብካቤን የሚጠይቅ የሁለት ሰብዓዊ ፍጡሮች አንድነት ነው። ስለሆነም እንክብካቤ እንደሚደረግለት ቡቃያ ወይም ጥሩ ጥንቃቄ እንዳለው ህፃን ተመጣጣኝ ዕድገትን ማሳየት አለበት። ትዳር የማይመረቁበት ትምህርት ቤት እንደመሆኑ መጠን በየጊዜው ከስህተቶቻቸው ተምረው ስህተቶቻቸውን የሚያሸንፉበት፣ ስለእርስ በርስ የበለጠ እያወቁ የሚሄዱበት እና ተቻችለው እና ተገነባብተው መኖርን የሚማሩበት ትምህርት ቤት ነው። አንዲት ወጣት ከሶስት ዓመት የትዳር ህይወት በኋላ ስለ ባሏ እንዲህ አለች “እውነቱን ለመናገር ባለቤቴ የመጨረሻ ግትር፣ የሰውን ሀሳብ የማይቀበል ሰው ነው። ነገር ግን አብሬው መኖርን እየተማርኩ ነው፤ እንዲህ አስቸጋሪ ከሆነ ሰው ጋር የምኖር አይመስለኝም ነበር ግን አሁን በጣም እወደዋለሁ።”

በነዚህ ባለትዳሮች ህይወት የምናየው መተዋወቅን እና መቻቻልን፤ መቀባበልን እና መፈቃቀርን ነው። በጥቅሉ የምንመለከተው በትዳር ህይወት ማደግን ነው። ሌሎች ባለትዳሮች ደግሞ ስለገጠማቸው ችግር የትዳር አማካሪያቸውን ምክር ሊጠይቁ ሄዱ። ከተጋቡ 19 ዓመት ሆኗቸዋል። አማካሪያቸው ችግራቸውን በትኩረት ከሰማ በኋላ “በትዳር 19 ዓመት የቆያችሁ ብትሆኑም የ19 ዓመት ልምድ አላገኛችሁም። ያደረጋችሁት የመጀመሪያ ዓመት ልምዳችሁን 19 ጊዜ ደገማችሁት” አላቸው። በነዚህ ባለትዳሮች ህይወት ደግሞ የምናየው በትዳር ህይወታቸው አለማደግን፣ ከትዳር ህይወት ገጠመኞቻቸው አለመማርን፣ ስህተቶቻቸውን ደጋግመው መስራትን ነው። በትዳር ትምህርት ቤት ገብተው ለ19 ዓመት ምንም አልተማሩም፤ አንድም ክፍል አላለፉም ማለት ነው። በቀለም ትምህርት ዓለም ቢሆን ይህ በጣም አሳሳቢ ነው። በትዳርም አሳሳቢነቱ ከዚያ ያላነሰ ነው።

የትዳር ስኬት የተወሳሰበ አይደለም ሌላውን ሥራችንን ጠንክረን የምንሰራውን ያህል ለትዳራችን ብንሰራ ትዳራችን የተሳካ ይሆናል። ስራችንን በስልትና በቀና አስተሳሰብ እንሰራለን። ይህ በቢሮ ስራም ሆነ በሌላው በጣም አስፈላጊ ነው። ሁሉም ለማደግ ያንን ለማድረግ ይጥራል፤ ስልጠናም ይሰጥበታል። በትዳር ህይወትም ስልት ያስፈልጋል። በትዳር ስልት ማለት ትክክለኛውን ነገር በትክክለኛው ጊዜና በትክክለኛው መንገድ ማድረግ ነው። ለምሳሌ በትዳር ስልት ማለት መናገር ብቻ ሳይሆን በንግግር ወቅት የድምጽ አወጣጥንም ይጨምራል። ቀና አስተሳሰብም ሌላውን ለማስተዋል ፈቃደኛ መሆን ነው። እነዚህ ሁለቱ የቆሰለውን ልብ ይጠግናሉ። ትዳርንም ከአደጋ ያድናሉ። መሳሳትና ማጥፋት ያለ ነገር ነው። ይህን ችግር ጋብቻ ከመመስረት የሚያግድ አይደለም። ብዙዎች ትዳር ወዲያውኑ ከልጅነት ጀምሮ የተጠናወታቸውን ችግር የሚያጠፋላቸው ይመስላቸዋል። አንድ የኮሌጅ ተማሪ ገና ኮሌጅ ሲገባ ከጓደኞቹ ጋር ለመግባባት ጊዜ ይወስድበታል። የቫዮሊን ወይም የፒያኖ ተማሪም መሳሪያውን እንደያዘ የወጣለት ፒያኒስት ሊሆን አይችልም። ቀስ በቀስ መለማመድ መማር አለበት፣ ትዳርንም ከዚህ ለይተን ማየት የለብንም።

ህይወትን እንዳለ ስንቀበለው፤ የትዳር ጓደኛችንንም ከነችግሩ ስንቀበለው ወደ ደስተኛ ቤትና ትዳር ጉዞ እንጀምራለን። ትክክለኛ ሰው በትዳር ችግርን መለማመዱ አይቀርም። አንዳንድ ሰዎች ከትዳር ጓደኛዬ ጋር ተጣልተን አናውቅም ይላሉ። እንዲህ የሚሉት ለጠባቸው ሌላ ስም አውጥተውለት ይሆናል፣ ጠብ ማለት መደባደብ ብቻ አይደለም አለመደማመጥ፣ አለመረዳዳት፣ አለመከባበር፣ መጨቃጨቅ ወዘተ ከዱላ ያላነሰ ጉዳትን ያደርሳል። አንድ አባወራ ስለትዳሩ ለፓስተሩ ሲናገር “በሰላሳ ዓመት ትዳራችን ከሚስቴ ጋር ተጨቃጭቀን አናውቅም ግን ጎረቤቶቻችን እስኪሰሙ ድረስ ሞቅ ያለ ክርክር እናደርጋለን” አለው። ጎረቤት እስኪሰማ ሞቅ ያለ ክርክር ባለበት ተከራካሪውን የመጉዳት አደጋ እንዳለ ማወቅ አያዳግትም። ሀቁ እያንዳንዱ ትዳር ችግርን መለማመዱ አይቀሬ ነው። የአንዱ ችግር ከሌላው የበለጠ ወይም ያነሰ ሊሆን ይችላል ባለትዳሮች ይህንን በማወቅ ትኩረታቸውን በችግሮቻቸው ላይ በማድረግ መንስኤውን መመርመርና መፍትሄውን ለማግኘት በፀሎትና በእግዚአብሔር ኃይል መስራት አለባቸው።

በመጨረሻም፤ በመጽሐፈ ምሳሌ 31፡10-29 ላይ የተከናወነለት ቤተሰብ የስኬቱ ምክንያት የሆኑትን ቁም ነገሮች እናያለን።

በቁጥር 11 ላይ ልባም የተባለችውን ሴት ሲገልጻት “የባልዋ ልብ ይታመንባታል” በማለት የተናገረው ቃል በትዳር ጓደኛ ላይ መተማመን የትዳር ጓደኛን ለመልካም ነገር ማበረታታት እንደሆነ እናያለን። በምላሹ በቁጥር 12 ላይ “ዕድሜዋን ሙሉ መልካም ታደርግለታለች ክፉም አታደርግም” ይላል ለዚህ ባህርይዋ የባልዋ በርስዋ መተማመን አስተዋፅዎ እንዳለው ያሳያል።

በቁጥር 15 ላይ “ለቤትዋ ሰዎች ምግባቸውን ለሰራተኞችዋም ተግባራቸውን ትሰጣለች” የሚለው ይህች ልባም የምታደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በትክክለኛው ጊዜና በትክክለኛው መንገድ (በስልት) የምታከናውን እንደሆነች ያሳያል። ጥሩ አሠሪ ነች፤ ለቤትዋ ሰዎች ምግባቸውን ከሰጠች በኋላ ሥራቸውን እንዲሰሩ ታደርጋለች። ይህ ተግባርን በቅደም ተከተልና በስርዓት መፈፀም ነው።

በቁጥር 20 ላይ “እጅዋን ወደ ደሃ ትዘረጋለች” የሚለው በጎ አድራጊነትዋን ያሳያል። የትዳር ወይም የቤተሰብ ክንውን በባለትዳሮች ወይም በቤተሰቡ ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን ለሌሎችም የሚተርፍ ነው። በቤትዋ ሰዎች የጀመረችው በጎነት ለሌሎችም ይተርፋል።

በቁጥር 23 ላይ “ባልዋ በሀገር ሀገር ሽማግሌዎች መካከል በተቀመጠ ጊዜ የታወቀ ይሆናል” ይላል። ለባልዋ መታወቅ ምክንያቱ እርሷ ነች፤ የሀገር ሽማግሌ የሚባሉት በማህበረሰቡ ውስጥ የተከበሩ፣ ቤተሰባቸውን በትክክል የሚይዙ የትዳር ጓደኞቻቸው በጥሩ ሥነ-ምግባር የታወቁ ናቸው። እንዲህ ያሉት የሀገር ሽማግሎች በአደባባይ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ ፍርድ ለጎደለባቸው የመፍረድን ስራ ይሰራሉ። የዚህ ሁሉ ክንውን ምሥጢር የቤተሰቡ መተማመንና መተሳሰብ ነው።

ከቁጥር 28-29 “ልጆችዋ ይነሳሉ ምስጋናዋን ይናገራሉ ባሏም እንዲህ ብሎ ያመሰግናታል መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጪያለሽ” ይላታል ይላል። ይህ ደግሞ ለተሳካለት ቤተሰብና ትዳር በጣም አስፈላጊውን ነገር ያሳያል። መመሰጋገን አንዱ ላደረገው በጎ ነገር እውቅና መስጠት የበለጠ በጎ ስራን እንዲያደርግ ይረዳዋል። ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት የተሳካ ትዳርና ቤተሰብ ስነምግባሮች በቤተሰቡ ላይ ተወስነው የሚቀሩ አይደሉም። የዚያ ቤተሰብ አባሎች በሚሄዱበት ሁሉ መልካም ስነ-ምግባርን የሚያሳይ ህብረተሰብን የማፍራት ዕድላቸው ሰፊ ይሆናል። ይህ በእግዚአብሔር ምሪት በሰለሞን የተፃፈው የምሳሌ መጽሐፍ በሰለሞን የመጀመሪያ የንግሥና ታሪክ ጊዜ የተፃፈ ነው። በዚያን ጊዜ ሰለሞን ወደ አምላኩ በጣም የቀረበ፤ በፍፁም ልቡም ለእግዚአብሔር መንፈስ የሚታዘዝ ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር ስለ መልካም ትዳርና ቤተሰብ የፃፈው።

ይህ በምሳሌ 31፡10-31 የተፃፈው ዘመን የማይሽረው የመልካም ትዳርና ቤተሰብ ምሳሌና መመሪያ ሆኖ ይኖራል። እኛም ይህንን ጽሁፍ የምናነብ ባለትዳሮችና ቤተሰቦች የትዳራችንና የቤተሰባችን መለኪያና መመሪያ አድርገን እንድንጠቀምበት እግዚአብሔር ይርዳን።

ፓ/ር አገኘሁ ወንድም


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *