በሐዋርያት ምስክርነት ምክንያት የአማኞች ቁጥር በኢየሩሳሌም በፍጥነት ባደገበት ወቅት አስጨናቂ ስደት በቤተክርስቲያን ላይ ደርሶ እንደነበረ ቃሉ ይናገራል። በስደቱ ምክንያት ከኢየሩሳሌም ከሸሹት አንጋፋ ሰዎች አንዱ ፊልጶስ ነበር። ይህ መንፈሳዊ መሪ “ወደ ሰማርያ ወርዶ ክርስቶስን ሰበከላቸው። ብዙ ሕዝብም ፊልጶስ የተናገረውን ሲሰሙና ያደረገውንም ተዓምራዊ ምልክቶች ሲያዩ፣ አንድ ልብ ሆነው ያዳምጡት ነበር። ርኵሳን መናፍስትም እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ወጡ፤ ብዙ ሽባዎችና አንካሶችም ተፈወሱ፤ ከዚህ የተነሣም በከተማዪቱ ታላቅ ደስታ ሆነ” (ሐዋ. 8:5-8)።
ለሰማርያ ሰዎች ክርስቶስ ተሰበከላቸው። ከስብከቱም ጋር ተዓምራዊ ምልክቶች ታዩ። የፊልጶስ ስብከትና ተዓምራት የሕያው አምላክ መንፈስ ሥራዎች ስለነበሩ ሕዝቡ ጉዳዩን በአግራሞት ይከታተል ነበር፤ በከተማዪቱም ታላቅ ደስታ ሆነ። ይህን ታላቅ ደስታ ያመጣው የኃጢአት መድኃኒትና የበሽታ ሁሉ ሐኪም የሆነውን ጌታ ኢየሱስን ማግኘታቸው ነው።
ቃሉ በመቀጠል እንዲህ ይላል፤ “ነገር ግን ከዚህ ቀደም ሲል በከተማዪቱ ውስጥ እየጠነቈለ የሰማርያን ሰዎች ሁሉ ያስገረመ፣ ሲሞን የሚሉት አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ራሱን እንደ ታላቅ ሰው ይቈጥር ነበር። ከታናሽ እስከ ታላቅ ያለው ሰው ሁሉ፣ ‘ይህ ሰው “ታላቁ ኀይል” በመባል የሚታወቀው መለኮታዊ ኀይል ነው’ በማለት ከልብ ያዳምጡት ነበር” (ሐዋ. 8:9-10)።
የሲሞን ጥንቆላ እንደ ፊልጶስ ተዓምራት የሰማርያን ሰዎች ሁሉ ያስገረመ ነበር። የመተተኛው ሲሞን ባህርይ ግን ከቅዱስ ፊልጶስ የተለየ ነበር። ፊልጶስ ለዲቁና አገልግሎት የተቀባ፣ ድሆችን ለመርዳት የተዘጋጀ ትሁት ሰው ነበር (ሐዋ. 6፡5)። ሲሞን ግን በጥንቆላው ምክንያት “ራሱን እንደ ታላቅ ሰው ይቆጥር ነበር”። ከሰማርያም አድናቆትና አምልኮ ተቀበለ።
አንድ ሰው ራሱን እያወቀ “ታላቁ ኃይል” በመባል የሚታወቀው መለኮታዊ ኃይል አንተ ነህ ሲባል እንዴት ሳይፈራ ይቀበላል? የሰማርያ ሰዎች ብዙ ያላስተዋሉት መንፈሳዊ እውነት ቢኖርም፤ ሙሴ በጻፋቸው የኦሪት መጽሐፍት ያምኑ ስለነበር ሲሞንም ይህ አጠራር ትክክል እንዳልሆነ ያውቅ ነበር፤ ነገርግን ለዚህ ነውሩ ከድፍረት ሌላ ምንም ምክንያት አልነበረውም። ኅሊናውን ለጥንቆላ ሽጦ፣ ተሰባሪ ሸክላ መሆኑን ረስቶ፣ አዳፋ ማንነቱን በቅዱስ አምላክ ዙፋን ላይ ለማስቀመጥ የተንጠራራ ሰው ነበር።
ሲሞን ሲናገር ሰዎች ከልብ ያዳምጡት ነበር፤ ሰባኪም ነበር ማለት ነው። ሲሞን በጥንቆላው ብዙ እንደቆየበትና ትኩረት ሰጥተው የሚከተሉት በርካታዎች እንደነበሩ ቃሉ ይመሰክራል (ሐዋ. 8:11)። ስለምን ሰብኮ ይሆን? ራሱን እንደ ታላቅ ሰው ቆጥሮ የፈጣሪን ምስጋና የሚቀበል አታላይ ስለ አምላክ ታላቅ ርኅራኄና እውነት እንዴት መስበክ ይችላል? በአፈጮሌነት ለሰዎች የሚፈልጉትን በመናገር እንደመሰጣቸው መገመት አያዳግትም። በተለይ የእርሱን ሕይወት ከፊሊጶስ ጋር ስናነጻጽረው ምላሹን እናገኛለን።

የፊልጶስ ስብከት ከሲሞን የላቀ ለመሆኑ ማሳያው ፍሬው ነው፤ ውጤቱ ነው። “ነገር ግን ፊልጶስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም የሰበከላቸውን አምነው በመቀበላቸው ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ፤ ራሱ ሲሞን እንኳ ሳይቀር አምኖ ተጠመቀ” (ሐዋ. 8:12-13)።
የእግዚአብሔር መንግሥት ለሁሉም ክፍት መሆኑ፣ በክርስቶስ ስም የኃጢአት ይቅርታና የልጅነት መብት መገኘቱ ከስብከት ሁሉ የላቀ መልዕክት ነው። የአንድ መተተኛ ተዓምራት፣ ድንቆችና ራስን ብቻ ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ከንቱ ትምህርቶች ከወንጌል ኃይል ጋር ፈጽሞ መፎካከር አይችሉም። ስለሆነም ብዙዎች ሲጠመቁ እርሱም ተቀላቅሎ ተጠመቀ።
ሲሞን የተጠመቀው ደንግጦ ነው። የሰከነ ስብዕና አልነበረውም። በሰማርያ ያገኘው ዝና የውሸት ውጤት ነበር፤ ጥንቆላ የአጭበርባሪ ልቡ ሽፋን ነበር። ራሱን እንደ ታላቅ ሰው ቢቆጥርም የሰዎች አምልኮ ሲሸሸው የሕዝቡን አግራሞት ከርሱ ወደነጠቀው ጉዳይ ዞሮ በመመሳሰል የቀድሞ ክብሩን ለመጎናፀፍ ፈለገ። ዋና ሙያው ማስደነቅና ማስገረም ነበር። ይህ ደግሞ ተለዋዋጭና አዳዲስ ስልቶችን ማዳበር ስለሚጠይቅ የአግራሞት ነፋስ ወደነፈሰበት መሮጡ ግድ ሆነበት። ስለዚህም “ፊልጶስንም ተከትሎ ሄደ፤ የሚደረገውን ምልክትና ታላቅ ታምራት አይቶም ተገረመ” (ሐዋ. 8:13)።
በሰማርያ ብዙዎች ማመናቸውን ሐዋርያት ሰምተው ጴጥሮስና ዮሐንስን ወደ እነርሱ ላኳቸው። “እነርሱም ሰማርያ በደረሱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ለሰማርያ ሰዎች ጸለዩላቸው፤ … ስለዚህ ጴጥሮስና ዮሐንስ እጃቸውን ጫኑባቸው፤ እነርሱም መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ (ሐዋ. 8:15፣17)።
በሐዋርያትና በፊልጶስ ውስጥ የሠራው ኃይል መንፈስ ቅዱስ ነው። ይህ ኃይል ደግሞ ለአማኞች ሁሉ በነጻ የሚሰጥ እንጂ እንደ ሲሞን ባሉ ጥቂት ንፉጎች የሚወሰን አይደለም። የእግዚአብሔር ሥራ ድንቅና ብርቅ ነው። ይህ የአምላክ ስጦታ በአንዳንድ “የተለዩ” ግለሰቦች ሕይወት ውስጥ ብቻ እየታየ ብዙሃኑ ከርቀት በመገረምና በመቋመጥ እንዲከታተል የሚጋብዝ አይደለም። በፊልጶስ ላይ የነበረው መንፈስ በሰማርያ አማኞችም ላይ ወረደ። ይህ ደግሞ አጋጣሚ የፈጠረው ክስተት ሳይሆን ጥንት የተተነበየ መለኮታዊ ዕቅድ ነው።

“ከዚህም በኋላ፣ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁ ሕልም ያልማሉ፤ ጒልማሶቻችሁም ራእይ ያያሉ። በእነዚያ ቀናት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ እንኳ፣ መንፈሴን አፈሳለሁ” (ኢዮኤል 2:28-29)። ይህ የአምላክ ጸጋ ውሱንነት የሌለው፣ ለተወሰኑ “ምርጦች” ብቻ የተፈቀደ ሳይሆን ለሁሉም የተሰጠ ስጦታ ነው።
በአንፃሩ ሲሞን የበላይነቱን ለማስቀጠል የሚፈለግ በዘመናችን እንዳሉት የወንጌል ነጋዴዎች እንደነበረ ቃሉ ያስተምራል። “ሲሞንም ሐዋርያት እጃቸውን በሚጭኑበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጥ አይቶ፣ ገንዘብ አመጣላቸውና እንዲህ አላቸው፤ ‘እጄን የምጭንበት ሰው ሁሉ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበል ይህን ሥልጣን ለእኔም ስጡኝ’” (ሐዋ. 8:18-19)።
ለመተተኛው ሲሞን መንፈሳዊ ኃይል ግላዊ ጥቅም የሚያግበሰብስበት መሳሪያ ነበር። እምነቱም ከአጋንንት እምነት የተለየ አልነበረም። “አንድ እግዚአብሔር እንዳለ ታምናለህ፤ መልካም ነው፤ አጋንንትም ይህንኑ ያምናሉ፤ በፍርሀትም ይንቀጠቀጣሉ” (ያዕ. 2:19)።
ፊልጶስና ሐዋርያት ውስጥ ሲሠራ ያየው ኃይል የላቀ መሆኑን ስላመነ ነው ሲሞን እጅ የመጫን ሥልጣን የተመኘው። በመሆኑም አዲሱን ኃይል ተቀብሎ በሰማርያ ላይ መሠልጠኑን ሊቀጥልበት ፈለገ። የተሻለ የንግድ አጋጣሚ ተመለከተና ቢሳካለት የሚያገኘውን አስካሪ ክብር በምናቡ አሸትቶ ሕልሙን እውን ለማድረግ ቸኮለ። ስለሆነም ይህ ርኩስ ሰው የሕይወት ሁሉ መገኛና መድኃኒት የሆነውን መንፈስ ቅዱስ አላፊ ጠፊ በሆነው ገንዘብ ለመግዛት አሰበ።
“ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፤ ‘የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ ለመግዛት አስበሃልና፣ አንተም ገንዘብህም አብራችሁ ጥፉ! ልብህ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ስላልሆነ፣ አንተ በዚህ አገልግሎት ድርሻ ወይም ዕድል ፈንታ የለህም’” (ሐዋ. 8:20-21)።
አንተም ገንዘብህም አብራችሁ ጥፉ! ራስን መውደድ ዝና ወደማሳደድ አጣድፎ የሚወስድ ሰይጣናዊ ወጥመድ ነው። ሰዎች በመለኮታዊ ድንቆች የመገረም ተፈጥሯዊ ዝንባሌ ስላላቸው ዲያብሎስ የዝና አፍቃሪዎቹን ወደ ቤተክርስቲያን መድረኮች በብዛት ይልካቸዋል። በራስ ፍቅር የጦዙትን የተጠሙትን ዕውቅና አጠጥቶ “ታላቁ ኀይል” በማስባል ለመለኮት ብቻ የሚገባውን ኀይል ያሸክማቸዋል። በተዓምራትና በድንቅ የሰዎችን ትኩረት በመሳብ ብዙ ታማኝ ተከታዮችን ያፈራላቸዋል።
ለመሆኑ ሲሞን ለሐዋርያት መስጠት የፈለገውን ገንዘብ ከየት አመጣው? ሙያው ጥንቆላ ከነበረ ከተከታዮቹ ነው ያገኘው ብሎ መገመት ስህተት አይሆንም። ሐዋርያትን ከርሱ እንደተሻሉ ጠንቋዮች አድርጎ ስለቆጠረም ነው አዲሱን መንፈሳዊ ኃይል በገንዘብ ለመግዛት የፈለገው። ይህ ግን ርኩስ ሃሳብ ነው። የዝና ፍቅር ከገንዘብና ከአጋንንት ታምራዊ ኃይል ጋር ተደምሮ ጥፋት እንደሚያመጣ አምላክ በጴጥሮስ አማካይነት ነገረው።
መንፈሳዊ ኃይል ከአምላክ በነፃ የሚታደል ሥጦታ ነው። ማንም ሰው ይህን ኃይል ተቀብሎ መንፈስ ቅዱስ በሕይወቱ ውስጥ ድንቅና ታምራት ሲሠራ ማየት ይችላል። ነገር ግን በአማኞች ሕይወት ውስጥ የሚታየውን የድንቅ ዓይነት የሚወስነው ራሱ መንፈስ ቅዱስ እንጂ የሰው ሥጋ አይደለም።
መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ልብ ውስጥ የሚያፈራው ታምራዊ ፍሬ ምንድነው? “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው።” (ገላ. 5:28)
ከሁሉም በላይ ምድራችን የሚያስፈልጋት ታላቅ ኃይል ሥርነቀል የባሕርይ ለውጥ የሚያመጣ መንፈስ ነው። ታዲያ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት በጠፉበት ዘመን ድንቅ የሚሠሩ ነቢያትና ሐዋርያት መብዛታቸውን እንዴት እናየዋለን?
አብዛኛዎቹ የመፅሐፍ ቅዱስ ታላላቅ አባቶችና ነቢያት በተዓምራዊ ሥራዎች የታወቁ አልነበሩም። ሔኖክና አብርሃም ድንቅ ሠሪዎች አልነበሩም። ለአምላክ ስለታዘዙ ግን ታሪክ ለዘላለም ያመሰግናቸዋል። ኤርምያስና ሕዝቅኤል ከታላላቅ ነቢያት ውስጥ ይመደባሉ። በሕይወት ሳሉ ግን ዝነኛ አልነበሩም፤ ድንቅና ተዓምራት ሠሪዎችም አልነበሩም። እንዲያውም ዘመናቸውን የጨረሱት በድህነት፣ በስደትና ለንስሐ የጠሩት ሕዝብ እምቢ በማለቱ የመጣውን ጦስ ምክራቸውን አልቀበልም ካለው አንገተ ደንዳና ሕዝብ ጋር አብሮ በመቀበል ነበር።
“ሌሎቹ ደግሞ … መትረፍን ንቀው ለሞት ለሚዳርግ ሥቃይ ራሳቸውን ሰጡ፤ ከዚህም ነጻ ለመውጣት አልፈለጉም። አንዳንዶቹ መዘባበቻ ሆኑ፤ ተገረፉ። ሌሎቹ ደግሞ ታስረው ወደ ወህኒ ተጣሉ፤ በድንጋይ ተወገሩ፤ በመጋዝ ለሁለት ተሰነጠቁ፤ በሰይፍ ተወግተው ሞቱ፤ እየተጐሳቈሉ፣ እየተሰደዱና እየተንገላቱ የበግና የፍየል ቈዳ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም ለእነርሱ አልተገባቻቸውምና። በየበረሓውና በየተራራው፣ በየዋሻውና በየጒድጓዱ ተንከራተቱ” (ዕብ. 11: 35-38)።

በአንጻሩ የዛሬዎቹ ነቢያት ራሳቸውን ሳይሆን ተከታዮቻቸውን ለሞት ለሚዳርግ ሥቃይ አሳልፎ መስጠቱን ያውቁበታል። የታመሙና የተቸገሩትን እንደ ጉም ፈጥኖ በሚጠፋ ተስፋ ሸብበው ወደ ሲዖል አፍ ይገፏቸዋል። እንደ መተተኛው ሲሞን “ታላቅ ኃይል” ተብለው ሲጠሩ በይገባኛል መንፈስ “አሜን” የሚሉ ናቸው። ከአማኞች በግፍና በአጋንንታዊ ስልት በተቀነባበረ ተዓምራዊ ተንኮል ባገኙት ገንዘብ የሚገዙት ልብስ ዕድሜያቸውን በመንከራተት እንዳሳለፉት ቅዱሳን “የበግና የፍየል ቆዳ” አይደለም። እንደቀድሞዎቹ ነቢያት በየዋሻውና በየጒድጓዱ እያንከራተተ የሚያኖር ተቃውሞ አጠገባቸውም አይደርስ።
በአገራችን የፈሉት የአሁኖቹ “ሐዋርያት” እና “ነቢያት” “ሲሞናዊ” ግርማ ሞገስ አላቸው። ምቾት በተትረፈረፈበት ፈገግታ ያጌጡ ምስሎቻቸው በትልልቅ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች በየከተማው ጎልቶ ይታያል። እንደ ሲሞን በየመድረኩ ይደመጣሉ፤ ድርጊቶቻቸው አስደናቂና ተዓምራዊ ስለመሆናቸው የሚመሰክሩ ብዙዎች ናቸው። ሆኖም ከመተተኛው ሲሞን የማይለዩ፣ የማይጠረቁ፣ ገብጋባ የወንጌል ነጋዴዎች ለመሆናቸው በርካታ ማሳያዎች አሉ።
አይሁዳዊው ፊልጶስ ወደ ሰማርያ መሄዱ ድንቅ ነው፤ ምክንያቱም “አይሁድ ከሳምራውያን ጋር ስለማይተባበሩ ነው” (ዮሐ. 4:8)። የሰማርያ ሰዎች ወደ ወንጌል የተሳቡት ፊልጶስ ዘረኝነት በልቡ አለመኖሩን በተግባር ስላሳየ ነው። መንፈስ ቅዱስ በልቡ ያፈራው የፍቅርና የርኅራኄ ፍሬ ከሲሞን ሰይጣናዊ ታምራት እጅግ የላቀ ድንቅ ነበር። ስለሆነም የሰማርያ ሰዎችን ዓይን ጋርዶ የነበረው ሲሞናዊ ጥንቆላ ሲጋለጥ የእግዚአብሔርን እውነተኛና ታላቅ ኃይል ዓይተው ተደነቁ። ማኅበራዊም ሆነ መንፈሣዊ ችግሮቻቸውን ማስወገድ ያልቻለውን ውሸታሙን ሲሞን ተዉት፤ ሲሞንም ሲሞንነቱ እንደማያዋጣው ተገንዝቦ አዲሱን ኃይል ተመኘ።

“ነቢያት”ና “ሐዋርያት” በበዙባት ኢትዮጵያ ዘረኝነት እንደ መዥገር ተጣብቆብን ያበጠው ለምን ይሆን? ብዙ ደዌ እንፈውሳለን የሚሉት እነዚህ “መንፈሣዊያን” ይሄኛውንም ጥገኛ በሽታችንን ጊዜ ሰውተው ቢያክሙት በታሪካችን ላይ ትልቅ የፈውስ አሻራ ጥለው ማለፍ በቻሉ ነበር። በርካታ ሕዝብ ሰብስበው በተዓምሮቻቸው በማስጮህና ማስለቀስ እንችላለን የሚሉት ነቢያት አገራችን ውስጥ ለተስፋፋው ምግባረ-ብልሹነት ተከታዮቻቸውን ለምን በንስሐና ምልጃ አያስለቅሱም?
የዘመኑን ነቢያት አስመልክቶ ጌታ ጥንት ተንብዮ ነበር፤ “በውስጣቸው ነጣቂ ተኵላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው መካከላችሁ በመግባት ከሚያሸምቁ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ፤ ከእሾህ ቍጥቋጦ ወይን፣ ከኵርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁም ጥሩ ዛፍ ሁሉ ጥሩ ፍሬ፣ መጥፎ ዛፍ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል። … በሰማይ ያለውን ያባቴን ፈቃድ ሳይፈጽም ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም። በዚያ ቀን ብዙዎች፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህ አጋንንት አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ታምራት አላደረግንምን?’ ይሉኛል። በዚያ ጊዜ፣ ‘ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንት ክፉዎች፤ ከእኔ ራቁ’ ብዬ በግልጽ እነግራቸዋለሁ” (ማቴ. 7:15-17, 21-23)።
የዛሬ ተዓምር ሠሪዎች ምን ዓይነት ፍሬ አፍርተዋል? በአስደንጋጭ ፍጥነት የተገኘ ገንዘብ፣ እጅግ ውድ የሆኑ በርካታ ልብሶች፣ ያማሩ ቤቶችና ውብ መኪናዎችን መዘርዘር ይቻላል። በመንፈስ ፍሬ አለመበልፀጋቸው ግን በእነርሱና በየዋህ ተከታዮቻቸው ብልሹ ሥራዎች ላይ በየቀኑ ይታያል።
ታዲያ መፍትሄው ምንድነው? ጴጥሮስ ለጠንቋዩ ሲሞን የሰጠው ተግሳፅ ለዛሬዎቹም “ነቢያት”ና “ሐዋርያትም” ፍቱን ምክር ነው፤ “አሁንም ስለዚህ ክፋትህ ንስሓ ግባ፤ ወደ ጌታም ጸልይ፤ ምናልባት ይህን የልብህን ሐሳብ ይቅር ይልህ ይሆናል” (ሐዋ. 8:22)።
ሁላችንም ወደ ጌታ ተመልሰን የልባችንን ሃሳብ እንዲለውጥ መፀለይ ይገባናል። ከራስወዳድነት፣ ከዝናና ከገንዘብ ፍቅር ተላቀን እውነተኛ መንፈሳዊ ፍሬ ማፍራት እንድንችል ጌታ አምላክን መማፀን አለብን። አውቀንም ይሁን በየዋህነት የምንከተላቸውን “ነቢያት” እና “ሐዋርያት” እነዚህ የመንፈስ ፍሬዎች የሚታዩባቸው እንደሆነ እንመርምር። በቸልተኛነት ከተቀመጥን ግን ሰይጣን በሚቀባቸው ሲሞኖች ተወናብደን፣ ድንቆች የምንከተል ሞኞች እንሆናለን። አወዳደቃችንም እጅግ የከፋ ይሆናል።
ድርባ ፈቃዱ










