giziew.org

ባልንጀራዬ ማንኛውም የእግዚአብሔር ቤተሰብ ነው

ለሰዎች ደኅንነት ኃላፊነት የተሰጣቸው ካህኑና ሌዋዊው በሞትና በህይወት መካከል ወድቆ የነበረውን ሰው አይተው ያለምንም ሃዘኔታ ገለል ብለው ሲያልፉ...
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ሰው ባልንጀራዬ የሚለው አብሮ አደግ ጓደኛውን ወይም የትምህርት ቤት ጓደኛውን ወይም በሀሳብ የሚግባባውን ስለርሱ በጎ የሚያስበውንና ፍልስፍናውን የሚጋራውን ብጤውን ነው።

ክርስቶስ ግን በሉቃስ 10፡30 ላይ “ባልንጀራዬ ማነው?” ብሎ ለጠየቀው ህግ አዋቂ የሰጠው መልስ ከዚህ እጅጉን ለየት ያለ እንደ ሆነ እናያለን። ምላሹ በቅርቡ በዚያ አካባቢ በተከሰተው አሳዛኝ ክስተት ላይ የተመሰረተ ነበር፤ ጠያቂው ክርስቶስን ያገኘው በኢያሪኮ ሲሆን በዚህው አካባቢ ትኩስ ወሬ የነበረው አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲሄድ ወንበዴዎች ስላደረሱበት ጉዳት ነበር። ወንበዴዎቹ ከደበደቡትና ልብሱን ከገፈፉት በኋላ በሞትና ህይወት መካከል ትተውት ሄዱ፤ ይህ ሰው ማንነቱ ያልታወቀ፤ አብሮት ተጓዥ ባልንጀራ ያልነበረው፤ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ በመጓዝ ላይ የነበረ ከመሆኑ ባለፈ ተጨባጭ አድራሻው እንኳን የማይታወቅ ሰው ነበር። ጌታም ያንን አጋጣሚ በመጠቀም የህግ አዋቂውን ጥያቄ መለሰ።

መድኃኒዓለም በምድር ላይ በቆየበት ጊዜ ሲያስተምርም ሆነ ጥያቄዎች ሲቀርቡለት ሰዎች ሊያስተውሉት በሚችሉት፤ በአካባቢያቸው በሚያዩትና በሚለማመዱት ነገር ያስተምራቸው ነበር።

ወደ ህግ አዋቂው ጥያቄ ስንመጣ ክርስቶስ ያደረገው በታሪኩ ውስጥ የተካተቱትን የካህኑን፣ የሌዋዊውንና የሣምራዊውን ድርጊቶች በመግለጥ፣ ጠያቂው ጥያቄውን ለራሱ እንዲመልስ በማድረግ ነበር።

በሉቃስ 10፡31 “ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ አይቶትም (የተጎዳውን ሰው) ገለል ብሎ አለፈ” ይላል። ገለል ብሎ ማለፍ፣ አይቶ እንዳላየ መሆን ነው። ግድየለሽነትና የራስ ምቾት እስካልተነካ ድረስ ለሌላው ችግርና መከራ ደንታቢስ መሆን ነው። በቁጥር 32 ላይ “እንዲሁ ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ሥፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ” ይላል። ይህ ሌዋዊ ከካህኑ በትንሹ ለየት የሚለው መንገድ አሳብሮ ባለመሄድ ሲሆን ለማወቅ ካደረበት ጉጉትም ሊሆን ይችላል “ወደዚያ ሥፍራ መጣ” ይላል። ግን እርሱም እንደካህኑ “ገለል ብሎ አለፈ” ይላል።

በቁጥር 33 ላይ ግን “አንድ ሣምራዊ ሲሄድ ወደርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት” ይላል። ለሣምራዊው ያ አካባቢ የራሱ ያልሆነ እንግዳ አካባቢ ነው። በመሆኑም ከካህኑና ከሌዋዊው የበለጠ ለደኅንነቱ ሊፈራና ራሱን ሊከላከል የሚገባው ሣምራዊው ነበር። ምክንያቱም ችግሩ የአይሁዶች በመሆኑ ሣምራዊያን ደግሞ በአይሁዶች የተናቁና የተጠሉ በመሆናቸው ነው። ሣምራዊው ግን የተጎጂው ሁኔታ ስላሳዘነው ሊደርስበት የሚችለውን እያወቀ ያንን በወንበዴዎች እጅ የወደቀውን ሰው ሊረዳ ወሰነ።

ቀጥሎም ያደረጋቸው ነገሮች በዚያ ስጋት ባለበት አካባቢ እንዲቆይ የማያደርጉት ቢሆንም ለራሱ ደኅንነት ሳያስብ ዕቃውን ፈትቶ የዘመኑን የመጀመሪያ ዕርዳታ ካደረገለት በኋላ በአህያ ላይ አስቀምጦ ወደ እንግዶች ማደሪያ ወሰደው። የሚገርመው በቁጥር 34 ላይ “ጠበቀውም” የሚለው ቃል ነው። ወዲያው በዚያ ትቶት እንዳልሄደ ነገርግን ባጠገቡ ሆኖ እዚያው እንደቆየ ያሳያል። ከእንግዶች ማደሪያ ባለቤት ጋር ያደረገው ስምምነትና የከፈለው ገንዘብ የራሱን ሥራና ምቾት ወደጐን አድርጐ ለዚያ ለማያውቀው የተጐዳ መንገደኛ ያደረገው በጐነት “ባልንጀራዬ ማነው?” ለሚለው ጥያቄ የሱስ የሰጠው መልስ ነው።

ይህንን ክስተት ለህግ አዋቂው ጠያቂ ከተረከለት በኋላ ጌታችን በቁጥር 36 ላይ “እንግዲህ ከእነዚህ ከሦሥቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል?” ብሎ ከጠየቀውና ከህግ አዋቂው አፍ “ምህረት ያደረገለት” እንደሆነ ከሰማ በኋላ በቁጥር 37 ላይ “ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ” አለው።

ካህኑ፣ ሌዋዊና ሣምራዊው የሚመሳሰሉበት መንገድ ሦስቱም የተጐዳውን ሰው ያገኙት በድንገት መሆኑ ነው። ይህ ያላሰቡትና ያልጠበቁት ክስተት ነበር። ሦስቱም ይጓዙ የነበሩት ሥራቸውን ለመሥራት ነበር፤ ካህኑና ሌዋዊ በቤተመቅደስ ለማገልገል ሲሆን ሳምራዊው ደግሞ አህያውን ጭኖ ወደ ንግዱ ይሄድ ነበር። የሚለያዩትና የማይመሳሰሉበት መንገድ ደግሞ ለተጐዳው ሰው ባደረጉትና ባላደረጉት ነው።

ለሰዎች ደኅንነት ኃላፊነት የተሰጣቸው ካህኑና ሌዋዊው በሞትና በህይወት መካከል ወድቆ የነበረውን ሰው አይተው ያለምንም ሃዘኔታ ገለል ብለው ሲያልፉ ከማያምኑት አህዛብ ወገን የሆነው ሣምራዊ ግን አዝኖለት ያደረገው በጐነት ነው።

ትምህርቱ ጥልቅና ታሪኩም በሦስቱ ላይ ብቻ ተወስኖ የማይቀር የእያንዳንዱን አንባቢ ህይወት የሚነካ ነው – ባልንጀራዬ ማን ይሆን? በቤተክርስቲያን ሁሌ ባጠገባችን የሚቀመጠው ይሆን? ወይስ አብረን የምንጫወተው ይሆን? ምሥጢር የምናወራው ይሆን? ወይስ ብቸኝነት የሚያጠቃው ብቻውን ሲወጣና ሲገባ የምናየው? ችግሩን የሚያወያየው ሰው የሌለው? ወዘተ ማነው ባልንጀራችን?

ህግ አዋቂው ጌታችን በነገረው ታሪክ መልዕክት አገኘ፤ ለጥያቄውም ተገቢ መልስ።

ሰው ባልንጀራው እርዳታውን የሚፈልግ ሰብዓዊ ፍጡር ሁሉ ነው። ለየሱስ ጥያቄ የህግ አዋቂው መልስ “ምህረት ያደረገለት ነው” የሚል ነበር። ጌታም “ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ” አለው (ቁ. 37)። በሌላ አነጋገር እውነተኛ ባልንጀራህን ለማወቅ ከፈለግህ ሂድና የሣምራዊውን ሥነምግባር ተለማመድ ወይም እንደርሱ አድርግ ማለቱ ነበር። በያዕቆብ 1፡27 “ንፁህ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸው ልጆች፣ ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ … ነው” ይላል።

እንግዲህ በዚህ ችግርና መከራ በበዛበት ዓለም ውስጥ እስካለን ድረስ የችግርና የመከራ ሰለባዎች የሆኑትን ሰዎች ስናይ ባልንጀሮቻችን እነርሱ መሆናቸውን እንድናውቅና የሣምራዊውን መልካም ሥነምግባር በመለማመድ አለብን። ብቸኝነት ላጠቃቸው ጓደኛ፣ ላዘኑ መፅናኛ፣ ተስፋ ለቆረጡ የብርታት ምክንያቶች መሆን እንዲያስችለን አሁን በፀሎት ወደ እግዚአሔር እንቅረብ፤ እግዚአብሔር ሊሰማውና ሊመልሰው የሚወደው ፀሎት ይህ ነውና።

ፓ/ር አገኘሁ ወንድም


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *