ዛሬ ዛሬ የፖለቲካው አለም ካሳደረብን ተፅዕኖ የተነሳ ስለ ብሔር፣ ጎሳ፣ ነገድ ወይም ቋንቋ በቤተክርስቲያን ውስጥ አንስተን ማውራት እንደ ነውር ወይም እንደ ዘረኝነት መቁጠር ተይዟል። ለእኔ ግን ይህ አካሄድ የተለያዩ ጥያቄዎችን በአዕምሮዬ ውስጥ ይፈጥራል። “ዘረኝነት ምንድነው?” “ዘረኛስ ማነው?” “መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ብሔር፣ ጎሳ ነገድ ቋንቋ ምን ይላል?” የዚህ ፅሑፍ ዓላማ ዘረኝነት ምን እንደሆነ እና ዘረኛ ማን እንደሆነ ለማብራራት ባይሆንም ካነሳሁት አይቀር የተወሰነ ነገር ብዬ ማለፍ ይኖርብኛል ብዬ አሰብኩ።
በእኔ አረዳድ “ዘረኝነት” የሚለውን አባባል በውል ሳንገነዘብ በመለጠጥ የምንጠቀም መስሎ ይታየኛል። በዚህ ዓለም ላይ ብሔር፣ ጎሳ ወይም ቋንቋ የሌለው ማንም የለም (1ቆሮ. 14፡10) የማንም ሰው ብሔር ወይም ቋንቋ ከሌላው ብሔር እና ቋንቋ ስለሚለይ ብቻ አንድ ሰው ዘረኛ አይደለም። ወይም ደግሞ አንድ ሰው በአፍ መፍቻ ቋንቋው መግባባት ስለሚወድ ብቻ ዘረኛ አይሆንም። የማናችንም ተፈጥሮ ወደዚያ ያጋድላል። ይልቁንም አንድን ሰው ዘረኛ የሚያሰኘው ምንድን ነው ከተባለ ከራሱ ብሔር ወይም ቋንቋ ውጪ ለሌላው እውቅና የማይሰጥ ከሆነ፤ የራሱን ከፍ፣ የሌላውን ዝቅ የሚያደርግ ከሆነ፤ ከራሱ ውጪ የሌላውን መስማት የሚያንገሸግሸው ከሆነ፤ ወይም ደግሞ የራሱን ማልማት የሌላው ማጥፋት ሥራ ላይ ከተሰማራ ያ ሰው ዘረኛ ሊባል ይችላል።
ከዚያም ሁሉ በላይ የሚገርመኝ ደግሞ ማንም ሰው ራሱን እኔ ዘረኛ ነኝ ሲል ሰምቼም ሆነ አንብቤ አለማወቄ ነው። አንዱ ስለሌላው ሲናገር “እገሌ ዘረኛ ነው” ይላል፤ “ዘረኛ” የተባለው ደግሞ “ዘረኛ” ስላለው ሲናገር “እንቶኔኮ ዘረኛ ነው” በማለት ይተቻል። የማንም ዓይን ወደ ውጪ (ወደ ሌላው) እንጂ ወደ ውስጥ (ወደ ራስ) ስለማያይ አንዱ ሌላውን እየወቀሰ ይኖራል። ያ ግን መፍትሄ ካለመሆኑ በላይ መፅሐፍ ቅዱስ ዕውቅና የሰጠውን ዕውቅና መንፈግ ይሆናል።
ከብሉይ ኪዳን ጊዜ ጀምሮ በአጠቃላይ ይህ ዕውቅና የተንፀባረቀ ሲሆን በአዲስ ኪዳን ውስጥ ደግሞ በተደጋጋሚ የተጠቀሰ፤ በልዩነት ያለ አንድነት ነው። ምናልባት ሁላችን በቃል ከምናውቀው ከዮሐንስ ወንጌል 3፡16 ብንጀምር “በእርሱ የሚያምን ሁሉ” እንደሚድን ይነግረናል። “ሁሉ” በሚለው ቃል ውስጥ እኔም፣ አንተም ወይም አንቺም የተጠቃለልን ብቻ ሳይሆን ሁሉም ብሔር፣ ጎሳ እና ቋንቋ ተካቷል።

ታላቁ ተልዕኮ በመባል የሚታወቀውን የማቴዎስ ወንጌል 28፡18-20 ስናነብ “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለሁሉም ስበኩ” ይለናል። ወንጌል የራሱ የሆነ ብሔር ወይም ቋንቋ የለውም። ወይም ደግሞ ለወንጌል ብቻ የተለየ ቅዱስ የሚባል ቋንቋ የለውም። የክርስቶስ ወንጌል ለሁሉም በነፃ የተሰጠ ስጦታ ነው። ሌሎቹን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ስናጠና ተመሳሳይ ነገር የምናገኝ ቢሆንም የራዕይ መጽሐፍ ደግሞ በተለየ ሁኔታ ፍንትው አድርጎ አስቀምጦታል። በዚህ መጽሐፍ ብቻ ስለነገድ እና ቋንቋ በአምስት ምዕራፎች ውስጥ ተጠቅሶ እናገኛለን። በዚህ አጭር ጽሑፍም የያዝነውን ርዕስ ጉዳይ በራዕይ መነፅር ቀርበን እንደሚከተለው እንመለከታለን ፡-
1. በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ያልተዋጀ ነገድ ወይም ቋንቋ የለም
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ደሙን ያላፈሰሰለት አንድም ሰው፤ አንድም ብሔር ወይም አንድም ቋንቋ የለም። እንዲያውም ዮሐንስ ሲመሰክር “ይገባሃል” ያለበት ዋናው ምክንያት ይህ ነው። “መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኀተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፤ ታርደሃልና፤ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብም ሁሉ፣ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥት እና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው በምድር ላይ ይነግሣሉ እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ” (ራዕይ 5፤9-10)።
2. ስለ ክርስቶስ መከራ የማይቀበል ነገድ ወይም ቋንቋ የለም

“ከዚህ በኋላ አየሁ እነሆ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከህዝብ እና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ። ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊ በእጃቸው ይዘው በዙፋኑ እና በበጉ ፊት ቆሙ” (ራዕይ 7፡9)። በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 14 ላይ ደግሞ እነዚህ ስለ ክርስቶስ መከራ የተቀበሉ ናቸው ይለናል፤ “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ።” ስለዚህ ምንም እንኳ በነገድ እና በቋንቋ ብንለያይም ስለክርስቶስ መከራን በመቀበላችን አንድ እንሆናለን። ራዕይ 11፡9ን በዚህ መነፅር ማየት ይቻላል።
3. በጦርነቱ ውስጥ የማይሳተፍ ነገድ ወይም ቋንቋ የለም
ራዕይ 11፡9 እና 13፡7 አንድ ላይ አድርገን ስንመለከት ከአውሬው ጋር በሚደረግ ጦርነት ውስጥ በሁለቱም ጎራ ሁሉም ነገድ እና ሁሉም ቋንቋ ይኖራል። ስለዚህ ለእውነት በመቆማቸው የሚገደሉም ሆነ ከአውሬው ጋር በመተባበር ለእውነት ታማኝ የሆኑትን የሚያሳድዱም ይኖራሉ።
4. በ3ቱ መላዕክት መልዕክት ያልተካተተ ነገድ ወይም ቋንቋ የለም
ቤተክርስቲያናችን በራዕይ 14 ላይ ያለውን ከማቴዎስ 28፡18-20 ጋር በማገናዘብ የተልዕኮዋ ማዕከል ያደረገችው ይህን የ3ቱን መላዕክት መልዕክት ነው። ይህ በጣም ወሳኝ የሆነው መልዕክት በምድር ላይ ከሚኖሩት መካከል ማንንም ያገለለ አይደለም። በዚህ ጥሪ ውስጥ ሁሉም ነገድ እና ቋንቋ ተካትተዋል። “በምድርም ለሚኖሩ ለህዝብም፣ ለነገድም፣ ለቋንቋም፣ ለወገንም ሁሉ ይሰበክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ በታላቅ ድምፅም የፍርዱ ሰዓት ደርሷልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት ሰማይንና ምድርንም ባህርንም የውሃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት አለ” (ራዕይ 14፡6-7)።
ውድ አንባቢ፤ አንድ ማናችንም መካድ የማንችለው እውነት አለ፡- በብሔር፤ በነገድ፣ በጎሳ እና በቋንቋ እንለያያለን። ነገር ግን በፖለቲካው ዓለም ልዩነቱ እየሰፋ የሚሄድ ቢሆንም በወንጌል ዓለም ግን ልዩነቱ እየጠበበ ነው መሄድ የሚገባው። የፈጠረን አንድ እግዚአብሔር፤ የሞተልን አንድ ጌታ፤ የሚመራን አንድ መንፈስ ከመሆኑም አልፎ ስለእምነታችን የምንቀበለው መከራ አንድ መሆኑ እና መዳረሻችን አንድ ሰማይ መሆኑን ማስተዋል በእጅጉ ያስፈልገናል።
ከዚህ በተጨማሪ በልዩነታችን ላይ ማተኮር የጋራ ተልዕኳችንን እንድንዘነጋ ያደርገናል፤ ስለዚህ በልዩነት ውስጥ አንድ ሆነን የሦስቱን መላዕክት መልዕክት ለህዝብ፣ ለነገድ እና ለቋንቋ ሁሉ ለማድረስ እንትጋ።
ፓ/ር ገመቺስ ጃፌ










