giziew.org

“ነጣቂ ተኵላዎች” – የዘመኑ ነቢያትና ሐዋርያት

“የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ”
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃሰተኛ ነቢያትንና በእርሱ ስም የሚያጭበረብሩትን ጠንከር ባለ ቃል ብቻ ሳይሆን የጠራቸው በክፉ አውሬም መስሏቸዋል። “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ” ማቴዎስ 7፡15።

ሃዋርያው ጳውሎስ እንዲሁ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች የመሰናበቻ ንግግር ባደረገ ጊዜ ከእርሱ በኋላ ስለሚመጡ ክፉ መምህራንና መሪዎች ሲናገር “ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ” ብሎ ነበር (ሐዋ. 20፡29)።

ከላይ በተጠቀሰው የጌታችን ንግግር ላይ “ነጣቂ” ተብሎ የተጠቀሰው ቃል “ቀማኛ” ከሚለው ጋር አብሮ የሚጠቀስ ነው (ሉቃስ 18፡11)። ሐሰተኛ ነቢያት ከቀማኝነታቸው በተጨማሪ ይህንን ባህርያቸውን ደብቀው እንደሚመጡና ሲታዩ እንደ በግ የዋህና ለሌላው ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው ለመስጠት የተዘጋጁ አድርገው እንደሚቀርቡ ጥቅሱ ይናገራል። በዚህ ብቻ ሳያበቃ “ተጠንቀቁ” በማለት ጉዳዩ ጥንቃቄ የሚያሻው እንደሆነ አጽንዖት ሰጥቶታል።

ሃዋርያው ጳውሎስ ደግሞ “ጨካኞች ተኩላዎች” በማለት ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን ደቀመዛሙርትን ወይም ተከታዮችን እንደሚሰበስቡ፤ ተከታይ ለማፍራት ደግሞ እውነትን አጣምመው እንደሚናገሩ ይገልጻል። እዚህ ላይ ሁለት ነገሮች ግልጽ ናቸው፤ አንደኛው እነዚህ ሰዎች የሚከተሏቸው እንደሚኖሩ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በማጭበርበር ወይም ነገርን በማጣመም ሰዎችን እንደሚያታልሉ ነው።

የተኩላ ባህርያት

ተኩላዎች በውሻ ቤተሰብ ውስጥ የሚመደቡ ሲሆን ከዚያ ቤተሰብ ውስጥ ትልቁ እንስሳ ተኩላ ነው። አስተዋይ ወይም ብልህ ከሚባሉት እንስሳት መካከል ተኩላ አንዱ ነው። ወደ ላይ ቀጥ ያሉት ጆሮዎች፣ ስለታም ጥርሶች፣ ወደፊት የሾጠጠው አፍ፣ ሰርጾ ገብ ዓይኖች ይህንን ብልህ የሚባለውን የተኩላ ባህርያትን የሚያመለክቱ ናቸው። ከዚህ ሌላ የሙቀት መጠኑ እስከ -40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በወረደ ቀዝቃዛ ቦታ መኖር ይችላል።

ተኩላዎች ከሚታወቁባቸው ነገሮች አንዱ በጩኸታቸው ወይም በሚያላዝኑበት ድምጽ ነው። ይህንንም እርስበርስ ለመግባባት የሚጠቀሙበት ነው። ብቸኛ የሆነ ተኩላ ትኩረት ለመሳብ ማላዘን ሊጀምር ይችላል። በማኅበር ውስጥ ያለ ደግሞ እንዲሁ ሊያላዝን ይችላል፤ ነገርግን የእርሱ ድምጽ ማሰማት ዋናው ምክንያት “እዚህ ነው ያለሁት፣ ድንበሬን እንዳትጥሱ” የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል ነው።

በአገራችን ከምናውቃቸው ሌላ የተለያዩ ዓይነት ተኩላዎች በዓለማችን ላይ ይገኛሉ። ሁሉንም የሚያመሳስላቸው ባሕርይ የሚያሰሙት ድምጽ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም በርካታ ባህርያት አሉ። ተኩላዎች በደንብ የተደራጀ ማኅበራዊ መዋቅር አላቸው። ይህም በተለይ ለአደን በሚወጡበት ጊዜ ድንበራቸውን በማስጠበቅና እንደልብ በመነጋገር የተሳካ አደን ለማድረግ ያስችላቸዋል።

ተኩላዎች ለአደን በሚወጡበት ጊዜ ሰፋ ያለ ቦታ ያካልላሉ፤ በአብዛኛው የሚጓዙትም በምሽት ጨለማን ተገን በማድረግ ነው። አንዳንድ ጊዜ በአንድ ቀን ብቻ እስከ 20 ኪሎ ሜትር ይጓዛሉ። የሚፈልጉትን አድነው እስኪያገኙ የማይሄዱበት ቦታ የለም፤ በዚህም በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ የሚታወቁ ሆነዋል።    

አመጋገብን በተመለከተ ተኩላዎች ሲያድኑ በቡድን ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ በግልም ለአደን ይወጣሉ። ለአደን በሚወጡበት ጊዜ አድነው የያዙትን ማንኛውንም ነገር የመብላት ባህርይ አላቸው። ሥጋ ብቻ በሊታ ሲሆኑ የሚያድኑት ለጨዋታ ወይም ለስፖርት ሳይሆን የመኖር ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ ነው። ያደኑትንም አምጥተው ለልጆቻቸው በመስጠት ይመግቧቸዋል። ይህንንም የሚያደርጉት የበሉትን ከሆዳቸው መልሶ በማውጣት ወይም ትኩስ ሥጋ በአፋቸው ይዞ በመምጣት ነው።

ለአደንና ለመብል የሚጠቀሙበት 42ቱም ጥርሳቸው በጣም ጠንካራ በሆነ የመንጋጋ ጡንቻ የተደገፈ ሲሆን ከዚሁ ጋር ከፍተኛ ብቃት ያለውን የማሽተት ችሎታቸውን በመጠቀም ታዳኙ ያለበትን ቦታ ለማወቅና ወደ ጥቃት ለመሄድ በቀላሉ ይችላሉ።

ተኩላዎች አንድ መንጋ ውስጥ ገብተው ከማደናቸው በፊት “የሞት ውይይት” በሚባለው ጉዳይ ውስጥ ይገባሉ። ይህም ተኩላውና ታዳኙ ተፋጥጠው ለተወሰኑ ደቂቃዎች የሚተያዩበት ድምፅ አልባ ንግግር ነው። በዚህ “የሞት ውይይት” ተኩላው ታዳኙን እንስሳ “አሳድጄ ልያዘው ወይስ እንደ ተላላፊ መንገደኛ ቆጥሬ ልተወው” በማለት ውሳኔ ላይ የሚደርስበት ክስተት ነው ተብሎ ይታመናል።    

ሌላው የሚገርመው የተኩላዎች ባህርይ ከሚያድኑት እንስሳ መንጋ ውስጥ የሚበሉት በተለይ የታመሙትን፣ ደካማዎችን፣ ልጆችን፣ ወይም ለአደጋ የተጋለጡትን መርጠው መሆኑ ነው። ይህ ግን ጤነኛውን አይነኩትም ማለት ሳይሆን ቀዳሚው ምርጫቸው ግን አይደለም። ልጆቻቸውን ለአደን በሚያዘጋጁበትም ወቅት የሚጠቀሙት አንዱ ስልት ሚዳቋ እንዲያሳድድ ማድረግ ነው። በዚህ ልምምድ ወቅት ዋናው ዓላማ የአደን ክህሎትን ማዳበር ስለሆነ  ልጅ ተኩላዎች ሚዳቆዎቹን ማሳደድ እንጂ መግደል አይፈቀድላቸውም።     

ተኩላዎች በኅብረት በሚሆኑበት ጊዜ የበላይ ወይም አለቃ የሚባለውን ለይቶ ለማወቅ ብዙም አይከብድም። በኅብረቱ ውስጥ ግጭት ለመቀነስ ከሁሉም የበላይ የሆነው ቀጥ ብሎ ይቆማል፤ ጥርሱን እያሳየ፣ ጸጉሩ እንደቆመ ዓይኖቹን ገልጥጦ በመክፈት ከፍ ብሎ ሲታይ ሌሎቹ ታዛዥ ተኩላዎች ደግሞ ጆሯቸውን ወደኋላ በመሸምጠጥ፣ መሬት ላይ ለጥ ብለው፣ ጭራቸውን በእግሮቻቸው መካከል አድርገው፣ አፋቸውን ዘግተው ዓይኖቻቸውን ጨለም ጨለም በማድረግ በሆዳቸው መሬቱን በመንካት ታዛዥነታውን ይገልጻሉ።

ነጣቂ፣ ጨካኝ ተኩላ

ጌታም እንዲህ አለ፤ “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ” ማቴዎስ 7፡15።

ጌታችንን ይህንን ማስጠንቀቂያ የተናገረው በተራራው ስብከቱ ወቅት ሲሆን ሐሰተኛ ነቢያቱን “ነጣቂ ተኩላ” በሚል ስዕላዊ መግለጫ ነው ያብራራቸው። ከላይ እንደተገለጸው ይህ “ነጣቂ” የሚለው ቃል “ቀማኛ” ከሚለው ቃል ጋር በተመሳሳይ የሚጠቀስም ነው። በሌላ ቦታ ደግሞ ይኸው ቃል “ኃይልን በመጠቀም መንጭቆ መውሰድ”፣ “መንጠቅ” የሚለውንም ሃሳብ የሚጠቀልል ነው። ለዚህም ነው ጌታችን “ተጠንቀቁ” በማለት የተናገረው። ምክንያቱም በንቃት ካልጠበቅን ትልቅ ችግር ውስጥ ልንገባ እንችላለን። ሆኖም “ተጠንቀቁ” ከማለት በተጨማሪ “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” በማለት ዘርዘር ያለ የመፍትሔ ሃሳብንም ሰጥቷል (ማቴዎስ 7፡16-20)።

ከላይ በመግቢያው እንደተጠቀሰው ሃዋርያው ጳውሎስ እነዚህን የተኩላ ባህርይ ያላቸውን ሰዎች “ጨካኞች” ይላቸውና ሲቀጥል “ከእናንተው መካከል እንኳ የራሳቸውን ደቀ መዛሙርት ለማፍራት እውነትን የሚያጣምሙ ይነሣሉ። ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ሦስት ዓመት ሙሉ ሌሊትና ቀን ምንም ያህል ሳላቋርጥ በእንባ እያንዳንዳችሁን እንደ መከርኋችሁ አስታውሱ” ይላል (ሐዋ. 20፡29-31)። እዚህ ላይ ጌታችን ኢየሱስም ሆነ ሃዋርያው ጳውሎስ የተናገሯቸው ተመሳሳይ ቃላት “ነጣቂ ተኩላ” እና “ተጠንቀቁ” የሚሉት እንደሆኑ ልብ ይሏል።

በጥንት ዘመን እረኞች የሚለብሱት የበግ ለምድ ነበር። ይህም ከበግ ጸጉር የተሠራና የክረምቱን ብርድ፣ የሌሊቱን ቁር ለመከላከል የሚለበስ ነው። እውነተኛው እረኛ ከበጎቹ ጋር ተመሳስሎ፤ ከእነርሱ እንደ አንዱ ሆኖ፤ የእነርሱን ዓይነት ቆዳ ለብሶ ነው ጥበቃ የሚያደርግላቸው። ከዚህ ሌላ እውነተኛው እረኛ በአገራችን እንደምናውቀው ከበጎቹ ኋላ ሆኖ እየገረፈ ራሱ ወደፈለገው አቅጣጫ መንጋውን የሚመራ ሳይሆን ከፊት ሆኖ አቅጣጫ እያስያዘ፣ እየመራ፣ የሚመጣውን ማንኛውንም አደጋ ከፊት ሆኖ እየተጋፈጠ መንጋው እንዲከተለው የሚያደርግ ነው።

በጎች በተፈጥሯቸው ከመንጋው ተነጥሎ የመሄድ፤ የመንከራተት ባህርይ አላቸው። ይህም ለአደጋ የሚያጋልጣቸውና ለጠላት አሳልፎ የሚሰጣቸው ክስተት ሲሆን ብዙ ጊዜ ይታያል። በጎች ካላቸው የዋህነት አኳያ ጠፍተው ባሉበት ጊዜ እንኳ መጥፋታቸውን ወዲያውኑ አያስተውሉም፤ ተመልሰው ወደ መንጋው እንዴት እንደሚቀላቀሉም አያውቁም። ከዚህ ሌላ ደግሞ መንጋውን መከተል ወይም አንዱ በመራው መከተል የበጎች ባህርይ ነው። ይህም በራሱ ለጠላታቸው ተኩላ ተጋላጭ ሲያደርጋቸው ይታያል።

ጌታችን ሲናገር እንዲህ አለ፤ “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል፤ ተቀጣሪው እረኛ ግን በጎቹ የእርሱ ስላልሆኑ፣ ተኵላ ሲመጣ ጥሎአቸው ይሸሻል፤ ተኵላውም በጎቹን ይነጥቃል፤ ይበትናቸዋልም” (ዮሐንስ 10፡11-12)።   

ተኩላ በጎችን ለማጥቃት ሲመጣ በተቻለው መጠን ራሱን ከእረኛው ጋር ለመመሳሰል ይሞክራል። ቢገኝም የበግ ቆዳ ለብሶ፤ አስፈሪ ጥርሶቹን ደብቆ “እኔኮ በግ ነኝ” በማለት ለመቀላቀል ቢሞክር የሚደንቅ አይደለም። ነገርግን አንዴ ከመንጋው መኻል ገብቶ ማተራመስ ሲጀምር ሁኔታዎች ፈጽሞ ይቀየራሉ።

በአገራችን ለቁጥር የሚያታክቱት ነቢያትና ሐዋርያት ብዙ የተኩላ ባህርያት ይታዩባቸዋል። ሲጀምሩ በግ ይመስሉና በኋላ ግን የተኩላ ባህርያቸውን ያወጡታል። በአፈጮማነት መጽሐፍ ቅዱሱን ሲጠቅሱ፣ ለምዕመን እየተጉ መሆናቸውን ሲያሳዩ ማንም ተኩላ ባህርያቸውን በፍጥነት ሊያየው አይችልም። በኋላ ግን የሰዎችን አመኔታ ማግኘታቸውን ሲያረጋግጡ እንደ አለቃ ተኩላ ጥርሳቸውን ሲያፏጩ ሌላው በተገዢነት ለጥ ብሎ እንዲሰግድላቸው ቀጥ ብለው ይቆማሉ።

በእነዚህ ነጣቂ ተኩላዎች ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሲናገሩ እንደሚደመጡት ነቢይ/ሐዋርያ ብለው ራሳቸውን የሾሙ ያደረሱባቸው ግፍ ደግሞ ለመናገር የሚያሳዝንና እጅግ የዘቀጠ ነው። አንዳችም የክርስቲያን ባሕርይ ሳያሳዩ እንዴት የረቀቁ ግፎችን እንደፈጸሙ የሚሰማው ዘግናኝ ዘገባ የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ አይደለም የካደው እንኳን የሚደፍረው አይደለም። መልካሙ እረኛ የሆነው ጌታችን አለምክንያት አይደለም “ነጣቂ ተኵላዎች” በማለት የጠራቸው።

ከላይ እንደተጠቀሰው የተኩላ ባሕርይ፤ እነዚህ ራሳቸውን በተለያየ ቅዱስ ስም የሰየሙ “ነጣቂ ተኩላዎች” ለጥቅማቸው የማይጓዙት ርቀት የለም። ታዳኞቻቸው በሁሉም ቦታ እንደሚኖሩ ስለሚያውቁ ከአገር ውስጥ አልፈው በውጪ አገራት በስደት የሚገኘውን ሕዝባችንንም የጥቃት ሰለባ አድርገውታል። እንዲያውም ከዳያስፖራው የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ አገር ውስጥ በብር ከሚያገኙት የላቀ በመሆኑ ቅድሚያ ለእነርሱ እንደሚሰጡ ራሳቸው በአንደበታቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ።

ከዚህ ሌላ ከውጭ የሚመጡትን ከአውሮጵላን ማረፊያ በመኪና ተቀብለው ወደ እንግዳ ማረፊያ በመውሰድ “የቪ.አይ.ፒ. የጸሎትና የፈውስ አገልግሎት” እንደሚሰጡ፤ የአገር ውስጡ ተገልጋይ ግን በየቀኑ በጸሐይና በሌት ቁር እየተሰቃየ፣ በየቤተ እምነቶቹ ጥበቃዎች እየተንገላታ፣ ለቀናት እንደሚጠብቅ በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።   

“አብረኸኝ እንድታገለግል ጌታ ተናግሮኛል” በማለት በአስመሳይ ትህትና እና “በመንፈሳዊነት” ጥሩ የገቢ ምንጭ ያላቸውን በመቅረብ የእነርሱ አገልጋዮች እንዳደረጓቸው፤ ከዚያም አልፎ ንብረታቸውንና በሺዎችና ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘባቸውን ዘርፈው ሙልጫቸውን እንዳስቀሯቸው የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም። እነዚህ ሰለባዎች ጉዳዩ መንፈሣዊ አገልግሎት እንዳልሆነ በሚረዱበት ወቅት ገንዘባቸውና ንብረታቸው እንዲመለስላቸው በሚጠይቁበት ጊዜ የሰማይ ስባሪ በሚያክሉ ወጠምሻዎች ድብደባ እንደደረሰባቸው፤ ለጉዳዩ ዕልባት ለማግኘት የሚሠሩ ሽማግሌዎችም ከባድ ማስፈራሪያ እንደሚሰጣቸውና ሽምግልናውን እንዲያቆሙ እንደሚገደዱ ግፉዓኑ ይናገራሉ።

ከዚህ ሌላ የተቀደሰ ዘይት ነው፤ የተጸለየበት ውሃ ነው፤ በሚል በብዙ ሺዎች የሚሸጠውና ይህንንም የሚወስዱ ከበሽታቸው ወዲያውኑ እንደሚፈወሱ እየተነገራቸው መድኃኒታቸውን በማቆም ለሞት እንደተዳረጉ የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም። ለዚህ ዓይን ያወጣ ወንጀል አንድም ነቢይ ወይም ሃዋርያ ነኝ የሚል ወደ ሕግ ቀርቦ የተጠየቀበት ሁኔታ አለመኖሩ አሁንም በ“ነጣቂ ተኩላነት” ያለተጠያቂነት ያገኙትን እያደኑ እንዲኖሩ ፈቃድ ሰጥቷቸዋል።

ስለዚህ ምን እናድርግ?

የእነዚህን “ለመንጋው የማይራሩ ነጣቂ ተኩላዎች” ጸረ-መንፈሣዊ የግፍ ድርጊት ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም። ከሁሉ በላይ እጅግ ርኅሩኅና ፍጹም አፍቃሪ በሆነው አምላክ ስም እንዲህ ያለውን ተግባር በመፈጸም የእግዚአብሔርን ቅዱስ ስምና ባሕርይ እንዲጎድፍ በማድረግ ረገድ የጠላት ወኪል መሆናቸው ሕዝባችን ሊገነዘብ ይገባዋል።

ከዚህ ግንዛቤ ሌላ እያንዳንዱ ምዕመን ለእግዚአብሔር ቃል ቀዳሚ ትኩረት በመስጠት ማጥናት ይገባዋል። “ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል” ይላል ቃሉ (ሆሴዕ 4፡6)። ስለዚህ ሕዝባችን በቅድሚያ የቃሉ ዕውቀት ያስፈልገዋል።

ወደ እነዚህ “ነጣቂ ተኩላዎች” የምሄደው ለምንድነው ብሎ መጠየቅ ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ነው። በርካታው ሰው የተኩላዎቹ ሰለባ የሚሆነው ሃብት ለማግኘት፣ ከበሽታ ለመፈወስ፣ ከችግር ለመላቀቅ፣ ወዘተ በሚል እንደሆነ እሙን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፈውስ፣ ከችግር ስለመዳን፣ ስለ ብልጽግና እና መሰል ጉዳዮች ምን ይላል ብሎ ማጥናት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል። ሲቀጥል ስለ ሃሰተኛ ነቢያትና ሐዋርያት ቃሉ ምን ያስተምራል ብሎ ጊዜ ወስዶ ማጥናት ሌላው ሥራ መሆን አለበት። “ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል” (ያዕቆብ 1፡5)።

ሌላውና በጣም ወሳኝ የሆነው ነገር “በእርግጥ አምላካችን እንዲህ ማንም ሊቀርበው የማይችል፤ በአማላጅና ነቢያት ነን በሚሉ ካልሆነ በስተቀር እያንዳንዳችን በቀጥታ ልናገኘው የማንችል ነው?” የሚለው መጠየቅና መመለስ ያለበት ጉዳይ ነው። ጌታችንና መድኃኒታችን ሲናገር “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል” ብሏል (ዮሐንስ 16፡ 23)። አምላካችንን እንደፈቃዱ የለመነውን ሁሉ ሊሰጠን ፈቃደኛ ነው።

በመቀጠልም በዚሁ ዮሐንስ ምዕራፍ 16 ላይ ጌታችን ይህንን አስደናቂ ነገር ተናገረ፤ “በዚያ ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ ይህም በእናንተ ፈንታ አብን እለምናለሁ ማለቴ አይደለም፤ ስለ ወደዳችሁኝና ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ ራሱ ይወዳችኋል” (ቁጥር 16-17)።

ጌታ ኢየሱስ በእነዚህ ቁጥሮች ከላይ በቁጥር 23 የተናገረውን ነው ያብራራው። በሌላ አነጋገር ጌታችን ያለው በእኔም ስም መለመን አያስፈልጋችሁም፤ ለእግዚአብሔር አብ በቀጥታ፣ ራሳችሁ፣ ጥያቄያችሁን ማቅረብ ትችላላችሁ። እኔን የሚወደኝ አብ እናንተንም ይወዳችኋል። በመካከል ምንም አማላጅ፣ ነብይ፣ ሐዋርያ፣ ወዘተ አያስፈልጋችሁም ምክንያቱም “አብ ራሱ ይወዳችኋል” እያለን ነው ያለው።

እግዚአብሔር አምላካችን “እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው” (ያዕቆብ 5፡11)። እንዲህ ያለ አምላክ እያለን ለምን ወደሌላ ቦታ፣ ለመንጋው ወደማይራሩ ጨካኝና ነጣቂ ተኩላዎች ለመሄድ እንፈልጋለን?* 

“ምሕረትን እንድንቀበልና በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ፣ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ” (ዕብራውያን 4፡16)።                                        

ጥበበሥላሴ መንግሥቱ

* በእነዚህና መሰል ርዕሰ ጉዳዮች በቀጣይ የሚወጡ ጽሁፎች ይኖራሉ


2 thoughts on ““ነጣቂ ተኵላዎች” – የዘመኑ ነቢያትና ሐዋርያት”

 1. “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል” ብሏል (ዮሐንስ 16፡ 23)። አምላካችንን እንደፈቃዱ የለመነውን ሁሉ ሊሰጠን ፈቃደኛ ነው።
  በመቀጠልም በዚሁ ዮሐንስ ምዕራፍ 16 ላይ ጌታችን ይህንን አስደናቂ ነገር ተናገረ፤ “በዚያ ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ ይህም በእናንተ ፈንታ አብን እለምናለሁ ማለቴ አይደለም፤ ስለ ወደዳችሁኝና ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ ራሱ ይወዳችኋል” (ቁጥር 16-17)።
  ጌታ ኢየሱስ በእነዚህ ቁጥሮች ከላይ በቁጥር 23 የተናገረውን ነው ያብራራው። በሌላ አነጋገር ጌታችን ያለው በእኔም ስም መለመን አያስፈልጋችሁም፤ ለእግዚአብሔር አብ በቀጥታ፣ ራሳችሁ፣ ጥያቄያችሁን ማቅረብ ትችላላችሁ። እኔን የሚወደኝ አብ እናንተንም ይወዳችኋል። በመካከል ምንም አማላጅ፣ ነብይ፣ ሐዋርያ፣ ወዘተ አያስፈልጋችሁም ምክንያቱም “አብ ራሱ ይወዳችኋል” እያለን ነው ያለው። ውድ ጸሃፊ ከላይ የተገለጸው ሃሳብ በእውነትም ክርስቶስ አማላጅ አለመሆኑን የሚያሳ ነው ወይ?

  1. ውድ Solomon ለመልዕክትህ በጣም እናመሰግናለን፡፡
   አንተ የጠቀስሃቸው ጥቅሶች ለጥያቄህ በቂ ምላሽ የሚሰጡ ይመስለናል፡፡ ተጨማሪ ሌላ ጥያቄ ካለህ ልታሳውቀን ትችላለን፡፡
   መልካም ጊዜ፡፡
   አርታኢ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *