ጌታችንና መድኃኒታችን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ተወልዶ የሰው ሥጋ ለብሶ በኖረባት ምድር የፅድቅን መንገድ አስተምሮ ሥራውን ሲፈጽም ስቅለተ አርብ “ተፈጸመ” በማለት የማዳን ሥራውን በማጠናቀቅ ወደ መቃብር ወረደ። ጌታችን ቀዳሚት ሰንበትን በመቃብር ከማረፉ በፊት የነበረውን ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “ወዐርብ ውእቱ ዕለት አሜሁ ከመ ይጽባሕ ሰንበት” (“አርብ ቀንም ነበር፤ የሰንበትም አጽቢያ ነበር”) ይላል (ሉቃስ 23፡54)። በቀደምት ዘመናት ቀን የሚጀምረው ፀሐይ ስትገባ በመሆኑ ሰንበት ከፀሐይ ግባት እስከ ፀሐይ ግባት ይከበር ነበር (ዘሌ. 23፡32)። በመሆኑም የጌታችንን አካል ሽቱና ቅባት ሊቀቡ የመጡት ሴቶች ሰንበት በመጀመሩ ምክንያት ሥራቸውን ሳያከናውኑ ስለመመለሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “ከገሊላም ከእርሱ ጋር የመጡት ሴቶች ተከትለው መቃብሩን ሥጋውንም እንዴት እንዳኖሩት አዩ። ተመልሰውም ሽቱና ቅባት አዘጋጁ። በሰንበትም እንደ ትእዛዙ ዐረፉ” ይላል (ሉቃ. 23፡55-56)።
የሰማይና የምድር ፈጣሪ የሆነው አምላካችን በስድስተኛው ቀን (አርብ) ሰውን በመልኩና በምሳሌው ከፈጠረ በኋላ ለስድስት ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን የመፍጠር ተግባር አጠናቀቀ። “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ” (ዘፍ. 1፡31)። ምድር ተውባ ተሠራች፤ ለቀንና ለማታ የሚያገለግሉ ብርሃናት ተሰየሙ፣ በውስጧ የሚኖሩት ሁሉ በድንቅ ሁኔታ ተፈጠሩ፣ የምድር እንስሳትና የሰማይ አእዋፋት በተመደበላቸው ቦታ ሰፈሩ፣ ባሕሩ በረቂቅ ፍጡራን ተሞላ፣ ይህ “እጅግ መልካም” ሆኖ የተሠራው የአምላክ ውብና ድንቅ የእጅ ሥራ ሰውን በመፍጠር ተጠናቀቀ፤ “ሰማይና ምድር ሠራዊታቸውም ሁሉ ተፈጸሙ”፣ ሁሉ ተጠናቀቀ፣ እንከን አልባ ሆኖ ተከናወነ፣ አንዳች የሚጨመርበት፣ አንዳችም የሚቀነስበት ሳይኖር ፍጹም ሆኖ ተሠራ፣ ፍጥረት ተፈጸመ!
በዚህ ዓይነት ሁኔታ ፍጥረት ከተጠናቀቀ በኋላ የተከሰተው ቀን ሰንበት ነው፤ “ሰማይና ምድር ሠራዊታቸውም ሁሉ ተፈጸሙ። እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ፤ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ። እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና” (ዘፍ. 2፡1-3)። አዳምና ሔዋን ገና ሳይፈጠሩ ለእነርሱ የሚያስብ አምላክ ሳይጠይቁ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ፍጹም አድርጎ አዘጋጀላቸው። ስለዚህ ያለ ሃሳብና ያለ ጭንቀት መኖር የጀመሩት በማረፍ ነበር – ሥጦታውን በምስጋና በመቀበል። ያለ ሃሳብ እንዲያርፉ ያደረጋቸው ደግሞ የሰማይና የምድር ፈጣሪ የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ሥራቸውን ሁሉ አስቀድሞ ስላጠናቀቀላቸው ነበር። ህይወት በሰንበት ዕረፍት ተጀመረ።
ይህንን ነጻ ሥጦታ የራሳቸው አድርገው መጠበቅ ያቃታቸው የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በአለመታዘዛቸው ከኤድን ሲባረሩ ያለ ተስፋ አልነበረም። ከወጡበት ኤድን ገነት እንደገና የሚመልሳቸው መሢሕ ከሰማያተ ሰማይ በመውረድ ወደዚህች ምድር መጥቶ እንደሚሞትላቸው ተስፋ ተሰጥቷቸው ነበር (ዘፍ. 3፡15)። ተስፋው መቼ እንደሚፈጸም በመጠበቅ ዘመናት ቢያልፉም ቃልኪዳኑን የሙጥኝ ያሉ ግን ተስፋውን ለልጅ ልጆቻቸው በማስተላለፍ በእምነት አለፉ።
ይህንን ታላቅ ተስፋ የሰነቁት የአብርሃም ልጆች ከግብፅ ባርነት ነጻ ወጥተው ወደ ተስፋዪቱ ምድር ሲሄዱ እግዚአብሔር የሚተዳደሩበትን ሕግ በሲና ተራራ ላይ ሰጣቸው። “ዐሥርቱ ትዕዛዛት” ብለን ከምንጠራቸው መካከል አራተኛው ትዕዛዝ “ተዘከር ዕለተ ሰንበት አጽድቆታ” (“የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ”) የሚል ተስፋ ያዘለና በረከት የሞላበት ነበር (ዘጸ. 20፡10)። “ተዘከር” ወይም “አስብ” የተባለበት ምክንያት ይህ ትዕዛዝ አዲስ ትዕዛዝ አለመሆኑን ለማሳሰብ ነው። ሰንበት በሲና ተራራ ላይ ሳይሆን የተሰጠው “ተፈጸመ ሰማይ ወምድር” (ሰማይና ምድር ተፈጸሙ፤ ዘፍ. 2፡1) ብሎ እግዚአብሔር ከተናገረ በኋላ ነው። ሰንበት የተሰጠው በኤድን ገነት ገና ኃጢአት ሳይገባ ነው። ስለዚህ ነበር በሲና ተራራ ላይ ሕጉን ሲሰጥ ጌታችንና መድኃኒታችን ሰንበትን ዘክር፣ አትርሳ፣ አስታውስ፣ አስብ በማለት ለሕዝቡ የተናገረው።
ይህም የሆነበትን ምክንያት ሲገልጽ፤ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ፈጥሮ በሰባተኛው በማረፉ ነው ይላል (ዘጸ. 20፡11)። ይኸው ሕግ በዘዳግም 5፡1-21 ላይ ሲደገም ስለ ሰንበት የተነገረው ላይ እንዲህ የሚል የተለየ ዐርፍተ ነገር አለው፤ “ወተዘከር ከመ ገብር አንተ በምድረ ግብጽ” (“አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ አስብ”) ይልና እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ከዚያ ባርነት ነጻ እንዳወጣቸው ይናገራል። በመሆኑም ከዚያን ዘመን ጀምሮ ቀዳሚት ሰንበት የፍጥረት መዘከሪያ ቀን ብቻ ሳትሆን “እግዚአብሔር በጸናች እጅና በተዘረጋች ክንድ” ከባርነት ነጻ ያወጣቸው መሆኑን የሚያስቡበት ቀንም ሆና ስትከበር ቆይታለች።
ስለዚህ እንደ ቀድሞዎቹ አባቶቻችን ለዚህ ዘመን ሰዎች ደግሞ ሰንበት የፍጥረት ማስታወሻችን ነች። ከዚህ በተጨማሪ እንደ አብርሃም ልጆች ከአካላዊ ባርነት ሳይሆን ከኃጢት ባርነት ነጻ በመውጣት የምናስባት ቀን ሆናልናለች። እነዚህን ታላላቅ እውነታዎችን ያካተተችው የሰንበት ቀን በሰው ፈቃድ የመጣች ሳትሆን በእግዚአብሔር ትዕዛዝ የተፈጠረች ናት። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ከሆነ የሰንበት ቀን የእግዚአብሔር የራሱ ናት፤ የ“ተቀደሰ(ች)ው ቀኔ” በማለት ይጠራታል (ኢሳ. 58፡13)።
“እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” ይላል (ሚል. 3፡6፤ ዘኁ. 23፡19፤ ዕብ. 13፡8)፤ የቃሉ ባለቤት የማይለወጥ ከሆነ ቃሉም አይለወጥም። ፍጥረትን ሲያጠናቅቅ ቅዳሜን ሰንበት አድርጎ የሰየማት አምላክ ሃሳቡን ቀይሮ ቀዳሚት ሰንበትን በሌላ አይተካትም፤ እርሱ ዘላለማዊ እንጂ በየጊዜው ሃሳቡን የሚለዋውጥ አምላክ አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ሰንበት ዘላለማዊ ናት፣ በአዲሲቱ ምድር እግዚአብሔርን ለማምለክ በየሰንበቱ እንሰበሰባለን (ኢሳ. 66፡23)። ስለዚህ በእግዚአብሔር ቃል ላይ መጨመርም ሆነ ከቃሉ መቀነስ ወይም ቃሉን መለወጥ ሁሉን በሚችል አምላክ ፊት የሚያስጠይቅ ተግባር መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ “እኔ ያዘዝኋችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትጠብቃላችሁ እንጂ ባዘዝኋችሁ ቃል ላይ አትጨምሩም፥ ከእርሱም አታጎድሉም” (ዘዳ. 4፡2፤ ራዕ. 22፡18፣19)።
ፍጥረትን ሲያጠናቅቅ “ተፈጸመ” በማለት ወደ ሰንበት ዕረፍት የገባው ጌታችንና አምላካችን የመዳንን ዕቅድ በማያሻማ መልኩ ባጠናቀቀበት ጊዜ በመስቀል ላይ ሆኖ “ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ፦ ተፈጸመ አለ” (ዮሐ.19፡30)። ይህንን በማለት ምንም ተስፋና ትንሣኤ የሌለውን የዘላለም ሞት በመሞት ለእኛ የዘላለም ህይወት ሰጠን። ለኃጢአት የተጠየቀውን መስዋዕትነት ፍጹምና ነቁጥ አልባ ህይወት በመኖር ከፈለ። የሰይጣንን ርኩስ አሠራር ለፍጥረተ ዓለም በማጋለጥ የእግዚአብሔርን ጻድቅነት ከጥግ እስከ ጥግ በማያሻማ መልኩ አሳየ። ይህንን በሚገባ በማጠናቀቁ ነበር “ተፈጸመ” ያለው።
ፍጥረትን ድንቅ አድርጎ ሲያጠናቅቅ “ተፈጸመ” ያለው ጌታ የመዳንን ጉዳይ እንዲሁ አንዳች የሚጨመርበትና የሚቀነስበት እንዳይኖር በማድረግ ሲያጠናቅቅ “ተፈጸመ” አለ። ለአዳምና ሔዋን ሁሉን አዘጋጅቶ በአምላካቸው በፍጹም በመተማመን እንዲኖሩ ህይወታቸውን በሰንበት ዕረፍት እንዲጀምሩ ያደረገው መድኃኒዓለም ለሰው ልጅ መዳን የሚጠየቀውን ፍጹም መስዋዕትነት በመክፈል ማንኛውም የኃጢአት ሸክም ያለበት ሁሉ ወደ እርሱ በመምጣት ነጻነት በማግኘት ህይወቱን በፍጹም ዕረፍት ለመኖር ይችል ዘንድ በቀራንዮ መስቀል ላይ ሁሉ በማጠናቀቅ ፈጸመ። የሰውን ልጅ ከኃጢአት ወቀሳ ነጻ በማውጣት ዕረፍትን ሲያጎናጽፍ የራሱንም አካል በሰንበት ቀን በመቃብር አሳረፈ። በቀዳሚት ሰንበት በመቃብር ማረፉ የሰንበትን ዘላለማዊነት ብቻ ሳይሆን የትንሣኤንም እውን መሆን ያረጋገጠበት ነው። መድኃኒዓለም ስለ መዳናችን የሚገባውን ሥራ ሁሉ ዕለተ አርብ ፈጽሞ በሰው ልጆች የመዳን ጉዳይ ላይ ማኅተሙን ሲያኖር በእርሱ ሞት ዘላለማዊ ህይወትን የምንቀበል መሆናችንን አስረግጦ፣ የዘንዶውን ራስ ቀጥቅጦ፣ ከሞት የመነሳቱን ጉዳይ ለአባቱ አስረክቦ ነው በፍጹም ዕረፍት በቀዳሚት ሰንበት በመቃብር ያረፈው (ሐዋ. 2፡32፤ ገላ. 1፡1)።
በተፈጥሮ ላይ አዳምና ሔዋን የሚጨምሩት ወይም የሚቀንሱት ሳይኖር የፍጥረትን ፍጽምና በመቀበል በነጻ የተሰጣቸውን (ጸጋ) በአምላካቸው በመተማመን እንደተቀበሉ ሁሉ ጽድቅን ለማግኘት የሰው ልጅ የሚሠራው አንዳች እንደሌለ ጌታችን በቀራንዮ መስቀል “ተፈጸመ” ሲል በአዋጅ ተናግሯል። ስለዚህ በፍጥረት ላይ የምንጨምረው እንደሌለ ሁሉ መዳናችንን በተመለከተ “አሜን” ብለን ከመቀበል በቀር የምንጨምረው የፅድቅ ሥራ አለመኖሩን መስቀል ላይ በገሃድ አሳይቷል።
ስለዚህ ቀዳሚት ሰንበትን የእግዚአብሔር ቀን አድርገን ስናከብር ሁለት ነገሮችን እንመሰክራለን። አንደኛው ጌታችንና አምላካችን በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን ሁሉ ፍጹም አድርጎ የፈጠረ አምላክ መሆኑን ለፍጥረተዓለም (ዩኒቨርስ) ሁሉ እንመሰክራለን። ሁለተኛው ደግሞ ይኸው አምላክ ለኃጢአት ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የማያዳግም መልስ በመስጠት እስራኤልን ከግብጽ ባርነት እንዳወጣ እኛንም ከኃጢአት ባርነት ያወጣን፤ ሁሉን አስተካክሎ የፈጸመ፤ ጸጋን ያጎናጸፈን መሆኑን የምንመሰክርበት ቀን ነው። ፍጥረትን አከናውኖ ሲያበቃ ያረፈው አምላክ የመዳንን ጉዳይ ለዩኒቨርስ በማሳየት የቀደመውን እባብ የሰይጣንን ራስ በመቀጥቀጥ ድል አድርጎ በሰንበት በመቃብሩ ሲያርፍ እኛንም ምንም ሳንዋጋ ባለድሎች በማድረግ ወደ ዕረፍቱ ያስገባን አምላክ መሆኑን የምናውጅበት ቀን ነው ሰንበት።
በመፍጠር አምላካችን ሆነ፤ በማዳንም እንዲሁ ጌታችን ሆነ! ስለዚህ “እኛ (ይህንን) ያመንን ወደ ዕረፍቱ እንገባለን” (ዕብ. 4፡3)። አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር።
ጥበበሥላሴ መንግሥቱ