giziew.org

“ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ”

ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች፦ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ።
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ጌታችንና መድኃኒታችን በምድር የነበረውን አገልግሎት ወደመፈጸሙ በተቃረበበት ወቅት የእርሱን የፍቅር ጥሪ ስትቃወም ለነበረችው ኢየሩሳሌም “ዶሮ ጫጩቶቿን እንደምትሰበስብ ልጆችሽን” ለመሰብሰብ ብሞክርም ስላልወደዳችሁ “ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል” በማለት አለቀሰላት፤ በመቀጠልም “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም” በማለት ከመቅደሱ ወጥቶ ሄደ (ማቴ. 23፡37-39)።

ሁኔታው ያስጨነቃቸው፣ የቤተመቅደሱ ጉዳይ ያሳሰባቸው፣ የዓለም ፍጻሜ እንዴት ይሆን የሚል ጥያቄ የጫረባቸው ደቀመዛሙርት ወደ ጌታችን በመቅረብ “ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት” (ማቴ. 24፡3)። ጌታችን ጥያቄያቸውን ሲመልስ በመጀመሪያ የተናገረው “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ” የሚል ነበር (ማቴ. 24፡4)። ቀጥሎም ይህንን የመሳት (የመታለል) ጉዳይ በማቴዎስ ምዕራፍ 24 ላይ አራት ጊዜ በመደጋገም ማስጠንቀቂያውን አጸናው (ቁጥር፤ 5፣11፣13 እና 24)።

ለምን ይሆን ጌታችን ስለ መታለል እንዲህ በአጽንዖት የተናገረው? ለምንስ ይሆን የመታለል ጉዳይ ከሃሰተኛ ነቢያትና ከሃሰተኛ ተዓምራት ጋር በማያያዝ የተናገረው?

አንድን ሰው ለማሳሳት ቀላሉ መንገድ ውሸትን መንገር አይደለም። ይልቁንም ውሸትን ከእውነት ጋር በመቀላቀል፤ የእውነትን አሠራርና መንገድ በሃሰት በመደባለቅ፤ በብዙ ውሸት ውስጥ አንዲት ጠብታ እውነት ጣል በማድረግ ሰዎችን በቀላሉ ማታለል ይቻላል። ይህ ደግሞ የሠይጣን ዓይነተኛ መሣሪያ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።

እናታችን ሔዋን በኤድን ገነት ከባሏ አዳም ተለይታ ባለችበት ወቅት ሠይጣን በእባብ ተመስሎ ወደ እርሷ በመቅረብ የነገራት ውሸት ብቻ አልነበረም። ትንንሽ የእውነት ጠብታዎችም ነበሩበት። የማታለያ ወጥመዱንም ሲዘረጋ ለስለስ ብሎ በስልት “በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን?” አላት። ሔዋንም አምላክ እንደዚያ እንዳላዘዘ ማብራሪያ ከሰጠች በኋላ መብላት የሌለባቸው ፍሬ እንዳለና ከዚያ ከበሉ እንደሚሞቱ ስትናገር እባቡ “ሞትን አትሞቱም” በማለት አወዛገባት።

በመቀጠልም በማር የተለወሰ መርዙን ሰጣት፤ ከእውነት ጋር የተቀላቀለውን ውሸት ቀስ ብሎ በማቅረብ ፍሬውን “በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው” አትብሉ ያላችሁ በማለት የበለጠ አወሳሰበባት። ይህንን ከእውነት ጋር የተቀየጠውን ውሸት እንደ እውነት አድርጋ ሔዋን በመውሰድ ፍሬውን በመብላት የእግዚአብሔር አምላኳን ሕግ ተላለፈች (ዘፍ. 3፡1-6)።

ዓይኗም ተከፈተ፤ መልካምና ክፉውን አወቀች፤ ነገርግን ፍሬውን ሳትበላ እግዚአብሔርን ብቻ በመታዘዝ ዓይኗ ይከፈት ነበር፤ ክፉውንም ለማወቅ የግድ አለመታዘዝ አልነበረባትም፤ ለእውነት በመታዘዝ የክፉውን ማንነት በቀላሉ መረዳት ትችል ነበር። ሆኖም እውነትን በተላበሰ ውሸት ተታልላ ሕይወቷ ለውድቀት ተዳረገ። “የተታለለም አዳም አይደለም፥ ሴቲቱ ግን ተታልላ በመተላለፍ ወደቀች” ይላል መጽሐፍ ቅዱስ(1ጢሞ. 2፡14)።

ይህ ውሸትን ከእውነት ጋር እየቀላቀሉ የማቅረብ ስልት ሠይጣን ለዘመናት ቀጥሎበት እስራኤላውያንም በዚሁ ወጥመድ በተደጋጋሚ ሲወድቁ እናነባለን።

አክዓብ የእስራኤል ንጉሥ በነበረበት ጊዜ ጣዖት አምላኪ የነበረችው ሚስቱ ኢልዛቤል ምድረ እስራኤልን በጣዖት አምልኮ ሞላችው (1ነገ. 18)። አገሩ ሁሉ በርኩሰት መሞላቱን የተመለከተው ነቢዩ ኤልያስ ለንጉሡ አንድ ግድድሮሽ አቀረበለት። የቀረበውንም ተግዳሮት በመቀበል አክዓብ አራት መቶ በላይ የሚሆኑትን የብኤል ነቢያትን ወደ ቀርሜሎስ ተራራ አስጠራቸው።

“እናንተም የአምላካችሁን ስም ጥሩ፥ እኔም የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ፤ ሰምቶም በእሳት የሚመልስ አምላክ፥ እርሱ አምላክ ይሁን” በማለት ኤልያስ ለጣዖት አምላኪ ነቢያቱና ለሕዝቡ ጥሪ አደረገ። ለመስዋዕትም የተዘጋጁት ወይፈኖች ታርደው ቀረቡ። ቅድሚያው ለብኤል ነቢያት ተሰጥቶ አማልክቶቻቸውን በእሣት እንዲመልሱ ዕድሉ ተሰጣቸው።

“ስለዚህ የተሰጣቸውን ወይፈን ወስደው አዘጋጁት። ከዚያም ከጧት እስከ እኩለ ቀን የብኤልን ስም ጠሩ፤ “ብኤል ሆይ ስማን” እያሉ ጮኹ፤ ድምፅ ግን የለም፤ የሚመልስ አልነበረም፤ በሠሩት መሠዊያ ዙሪያም እየዘለሉ ያሸበሽቡ ነበር። … እየጮኹ እንደ ልማዳቸው ደማቸው እስኪፈስ ድረስ ሰውነታቸውን በሰይፍና በጩቤ ያቈስሉ ነበር። እኩለ ቀን ዐለፈ፤ እነርሱም የሠርክ መሥዋዕት እስኪቀርብ ድረስ የሚዘላብድ ትንቢት ይናገሩ ነበር፤ አሁንም ድምፅ የለም፤ የመለሰና ከቁም ነገር የቈጠረውም አልነበረም።

“ከዚያም ኤልያስ ሕዝቡን በሙሉ፣ “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እርሱም ፈርሶ የነበረውን የእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ። … በመሠዊያውም ዙሪያ ዐሥራ አምስት ሊትር ውሃ የሚይዝ ጒድጓድ ቈፈረ፤ ዕንጨቱን ረበረበ” የተዘጋጀውን የወይፈን ሥጋ ካቀረበ በኋላ “በዕንጨቱ ላይ አኖረው። ከዚያም፣ “ውሃ በአራት ጋን ሞልታችሁ፣ በመሥዋዕቱና በዕንጨቱ ላይ አፍስሱ” አላቸው። ደግሞም፣ “እንደ ገና ጨምሩበት” አላቸው፤ እነርሱም ጨመሩበት። “ሦስተኛም ጨምሩበት” ሲል አዘዛቸው፤ እነርሱም ለሦስተኛ ጊዜ ጨመሩበት። ውሃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ጒድጓዱንም ሞላው”።

ከዚያም ኤልያስ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ስም ጠራ፤ “የአብርሃም፣ የይስሐቅና የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የእስራኤል አምላክ መሆንህ፣ እኔም የአንተ አገልጋይ መሆኔና ይህን ሁሉ በትእዛዝህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይታወቅ። ይህ ሕዝብ፣ አንተ አምላክ እግዚአብሔር እውነተኛ መሆንህንና ልባቸውን የመለስኸው አንተ መሆንህን ያውቁ ዘንድ እባክህ ስማኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህ መልስልኝ” በማለት ወደ አምላኩ ልመናውን አቀረበ።

“ከዚያም የእግዚአብሔር እሳት ወርዳ መሥዋዕቱን፣ ዕንጨቱን፣ ድንጋዩንና ዐፈሩን ፈጽማ በላች፤ በጒድጓዱ ውስጥ ያለውንም ውሃ ላሰች። ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲያዩ፣ በግንባራቸው ተደፍተው፣ “አምላክ እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ ነው! እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው!” አሉ። እውነተኛው አምላክ በእሣት መለሰ (1ነገሥት 18)።

እሣት ከሰማይ ማውረድ የእውነተኛው አምላክ መገለጫ ሆነ። የአምላክን አሠራር በመኮረጅ ሰዎችን በስህተት መንገድ መምራት ልዩ ክህሎት ያለው ሠይጣን ባለንበት ዘመን ይህንን እሣት የማውረድ፣ ተዓምር የመሥራት፣ ድንቅ የማድረግ ክስተት ብዙዎችን ለማታለል የመጠቀሚያ መሣሪያ እያደረገው ይገኛል። በኤልያስ ዘመን እሣት ከሰማይ ማውረድ የትክክለኛነት ማረጋገጫ ሆኖ ስለታየ በተለይ በመጨረሻው ዘመን ያንኑ መድገም ሰዎችን ለማሳት ዓይነተኛ መንገድ ሆኖ እናገኘዋለን።

ባለራዕዩ ዮሐንስ በኋለኛው ዘመን የሚሆነውን ሲናገር ጌታችን ለደቀመዛሙርቱ “ሐሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ” በማለት የተነበየውን ለየት ባለ መልኩ ያቀርበዋል። በራዕይ 13 ላይ በአውሬ የተመሰለውና ከባህር (በትንቢታዊ ፍቺው ከብዙ ሕዝብ መካከል ራዕይ 17፡15) የሚወጣው አውሬ፤ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ መልክ በመያዝ ዓለምን እንደሚቆጣጠር ይናገራል (ራዕይ 13፡3፣8)። በተለይ ደግሞ ዘንዶው ወይም የቀደመው እባብ የተባለው ሰይጣን (ራዕይ 12፡9) ለዚህ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ የበላይነት ላለው ኃይል ሥልጣን ስለሰጠው አውሬውን ማን ሊዋጋው ይችላል? እያሉ በምድር ያሉ እንደሚሰግዱለት ይናገራል (ራዕይ 13፡4፣8)።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለራዕዩ ሌላ አውሬ ከምድር ሲወጣ እንደተመለከተና ይህ ኃይል ደግሞ ለቀደመው ከባህር ለወጣው ኃይል በምድር የሚኖሩ እንዲሰግዱለት እንደሚያደርግ ይናገራል (ራዕይ 13፡12)። ይህንን ስግደትም ለማስፈጸም እሣትንም እንኳን ሳይቀር ከሰማይ እንደሚያወርድ፤ ታላላቅ ምልክቶችን፣ ድንቆችንና ተዓምራቶችን እንደሚያደርግ፤ በዚህም ድርጊቱ በምድር የሚኖሩትን እንደሚያስት ይተነብያል (ራዕይ 13፡14)።

በዚህ ሳያቆም ዘንዶው (የቀደመው እባብ ወይም ሠይጣን)፣ ከባህር የወጣው አውሬ (ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ሥልጣንን አጣምሮ የያዘው ኃይል) እና ከምድር የወጣው አውሬ (ሃሰተኛው ነቢይም ይባላል) አስመሳይ የሥላሴ ዓይነት ጥምረት በመፍጠር ምድርን ሁሉ በድንቅና ተዓምራት እንደሚያታልሉ ይናገራል። “ከዘንዶውም አፍና ከአውሬው አፍ ከሐሰተኛውም ነቢይ አፍ ጓጕንቸሮች የሚመስሉ ሦስት ርኵሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ፤ ምልክትን የሚያደርጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸውና” ይላል (ራዕይ 16፡13-14)።

ጌታችን ክርስቶስ በመጨረሻው ዘመን “ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ” ያለው ያለምክንያት አልነበረም። የሚነሱት ነቢያት ጥቂቶች፤ የሚያስቱትም ሕዝብ ጥቂት ነው አላለም። ይልቁንም የሃሰተኛ ነቢያቱ ቁጥር ብዙ እንደሆነና እርሱን በመከተል የሚስቱትም ሰዎች ብዙዎች መሆናቸውን ነው ጌታችን የተናገረው። ባለንበት የመጨረሻ ዘመን እየሆነ ያለውም ይኸው ነው።

ባለፉት ሁለት ዐሥርተ ዓመታት በአገራችን ብቻ እየሆነ ያለውን ብንመለከት በየቦታው፣ በየማኅበራዊ ሚዲያው፣ “ነቢይ”፣ “ሐዋርያ”፣“የእግዚአብሔር ሰው”፣ “ኧፖሰትል”፣ “ፕሮፌት”፣ “ማን ኦቭ ጎድ”፣ … እየተባሉ የሚጠሩ ወንዶችም ሴቶችም ከቁጥር በላይ በርክተዋል። የእነዚህ አብዛኛዎቹ አካሄድ ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን በርካታ ሕዝብ በመሰብሰብ፤ ሰዉ መስማት የሚፈልገውን ነገር በመንገር፤ በአብዛኛው የፈውስና መሰል ፕሮግራሞችን ማካሄድ ነው።

አንዳንዶቹ ተጠንተው ሌሎቹ ደግሞ በግምት የሚደረጉት “ትንቢቶች” እና “ፈውሶች” ብዙዎችን ወደ መታለል እየወሰዱ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ከመታለል ባሻገር እነዚህን የሃሰት ትንቢቶች እንደ እውነት በመቀበል ከሥራቸው የተፈናቀሉ፣ ከትዳራቸው የተለያዩ፣ ኑሯቸው የተመሰቃቀለ፣ ገንዘባቸውን የተበሉ እንዲያውም ሕይወታቸውንም ያጡ እንዳሉ የጉዳቱ ሰለባዎች ይናገራሉ። 

በአፍሪካ አህጉር ባጠቃላይ ያለው ሁኔታ ይህንኑ የሚሳይ ሆኖ እናየዋለን። ጥቂት የማይባሉ በአገራችን ላይ በነቢይና በሐዋሪያነት የሚጠሩ ዘመናዮች ልምምዳቸውን የቀሰሙት በሌሎች የአፍሪካ አገራት (እንደ ናይጄሪያ ካሉ) ከሚገኙ “አባቶቻቸው” እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፤ ራሳቸው ሰዎቹም ሲናገሩ ይደመጣሉ። በርካታ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ የሚንጣት አፍሪካም ሆነች አገራችን፤ ዜጎቿ ላለባቸው ለዚህ አንገት የሚያስደፋ ችግር መፍትሔው በክርስቶስ ስም የብልጽግና ወንጌል የሚሰብኩላቸው “ሐዋሪያት”ና “ነቢያት” ሆነዋል።

መበልጸግ በራሱ ምንም ችግር ያለበት ጉዳይ አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ በርካታ ሰዎች ባለጸጎች እንደነበሩ እናነባለን። ኢዮብ አንዱ ነው፤ “ሀብቱም ሰባት ሺህ በጎች፥ ሦስት ሺህም ግመሎች፥ አምስት መቶም ጥማድ በሬ፥ አምስት መቶም እንስት አህዮች ነበረ፥ እጅግ ብዙም ባሪያዎች ነበሩት፤ ያም ሰው በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ታላቅ ነበረ” (ኢዮብ 1፡2)። ይህንን ሃብት በዚህ ዘመን ባለው ዋጋ ብናሰላው ኢዮብ በቀላሉ ባለብዙ ሚሊዮነር ነበር። ነገርግን ይኸው ኢዮብ ሃብቱ ሁሉ ወድሞ ሙልጩን በቀረበት ጊዜ “እነሆ፥ ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤ ነገር ግን መንገዴን በፊቱ አጸናለሁ” በማለት ነበር በአምላኩ ላይ የነበረውን ፍጹም መተማመን የተናገረው (ኢዮብ 13፡15)። በዘመናችን ሲሆን የምናየው ግን እንደዚያ አይደለም። 

“ችግር ከቤትህ ተወግዷ፣ በመሥሪያ ቤትህ የተነሳብህ የጠላት አሠራር ፈርሷል፣ በጎረቤትህ አካባቢ ያለው የምቀኝነት ምሽግ ድባቅ ተመትቷል፣ ወደ ከፍታ ነው የምትጓዘው፣ ለታላቅነት ተጠርተሃል፣ ከሁሉ በላይ ከፍ ስትል ይታየኛል፣ ቅባቱ ባንተ ላይ ፈስሷል፣ ከዚህ በኋላ ሃብትና ብልጽግና ካንተ አይለይም፣ ወዘተ” የመሳሰሉ የሰዎችን ስነልቡና በቀላሉ የሚሰርቁና ከዕለታዊ የኑሮ ተግዳሮት ጋር የተያያዙ “ትንቢቶችንና መገለጦችን” ከመድረክ ይሰማሉ። የጉዳቱ ሰለባዎች እንደሚናገሩት ከሆነ ሐሰተኛ ነቢያቱ “የሚያገለግሉት” በመረጃ ነው፤ ይህም ምዕመኑን በእንግዳ ማረፊያ (ገስት ሃውስ) በሺዎች የሚቆጠር ብር ከፍሎ እንዲቀመጥ በማድረግ፣ ወይም በሌላ ስልት አስቀድሞ ችግሩን እንዲናገር በማድረግና ቀጥተኛ መረጃ ከራሱ በመሰብሰብ ነው።

ይህንንም በረቀቀ ስልት ወደ “ነብዩ” በማስተላለፍ፤ “ነብዩም” “ጌታ ነው የተናገረኝ” በማለት በሕዝብ ፊት መልሶ በመናገርና ተሰብሳቢውን በማስደመም በሚደረግ ዓይን ያወጣ የማጭበርበር “አገልግሎት” ነው። ይህንን ግልጽ ውንብድና እንደ እውነተኛ መልዕክት በመቀበል እያወቀ የሚታለለውና ሳያውቅ በስህተት መንገድ ላይ ያለው ሕዝብ ለዕለታዊ የኑሮና የጤና ችግሩ ማርገቢያ የሚሆን ተስፋ አዘል “ትንቢት” መስማት በመፈለግ በየቦታው በብዛት ተሰብስቦ ይታያል። ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉም ነገሩ ለአንዳንዶች እንደ ሱስ እንደሆነባቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ። ይህ አስገራሚና አስደንጋጭ ሁኔታ ጌታ ኢየሱስ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ” የሚለውን የትንቢት ቃል በጥንቃቄ እንድንመለከተው የሚያደርግ ነው።

ከእነዚሁ ስሜትን ከሚኮረኩሩ የብልጽግና ወንጌል ትምህርቶች ጋር በተያያዘ የፈውስ አገልግሎቶችም ይካሄዳሉ። የሰውን ስብዕና እጅግ በሚነካ፤ የእህቶችን ማንነት እጅግ በሚያዋርድ መልኩ ሰዎች እየተገፈተሩ ይጣላሉ፤ በደረታቸው መሬት ላይ እንዲነጠፉ ይደረጋል፤ በአየር ካራቴ ይመታሉ፤ በቡጢ ይነረታሉ፤ አዛውንት አባቶችና እናቶችም ሳይቀሩ የዚሁ ሰለባ ሲሆኑ ማየት የዕለት ተዕለት ክስተት ሆኗል።

በፈውስ ስም ደግሞ “የተጸለየበት” ነው እየተባለ የሚቸበቸበው “ዘይት” ለሃሰተኛ ነቢያቱ ቀላል የገቢ ምንጭ ሆኖላቸዋል። የምግብ ዘይት ዋጋ እጅግ በናረበትና ጥራቱን የጠበቀ ዘይት ለማግኘት አስቸጋሪ በሆነበት አገር፤ “እፈወሳለሁ” በማለት በትንሽ ብልቃጥ የተሞላች ዘይት እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ ለመግዛት የሚሰለፈው ሰው መብዛቱ “ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ” የሚለውን የጌታ ኢየሱስን ቃልና በራዕይ ላይ ከምድር የወጣው ኃይል በድንቅና በተዓምራት እንዲሁም በምልክት ብዙዎችን ያስታል ያለውን ደግመን እንድናሰላስልበት የሚያደርገን ነው።

በኤልያስ ዘመን ጸሎትን ሰምቶ በእሣት የመለሰው ኃያሉ ጌታ እግዚአብሔር እውነተኛ አምላክ መሆኑ ተረጋግጦ ነበር። ይህም የእውነተኛ አምልኮ ማሳያ ተደርጎ ሲወሰድ ቆይቷል። በኤልያስ ዘመን ሰምቶ በእሣት መመለስ ባለመቻሉ የተዋረደው አሳቹ ሰይጣን፤ ባለንበት የመጨረሻ ዘመን የከሰረውን ታሪኩ ለማስተካከልና እውነተኛ አምላክ እርሱ መሆኑን ለማሳየት እሣትን ከሰማይ እንደሚያወርድ ዮሐንስ በራዕዩ ተመልክቷል (13፡13)። ሃሰትን ከእውነት ጋር በመቀላቀል ሰዎችን በቀላሉ በማታለል የሚታወቀው ሰይጣን፤ በዚህ ዘመን ይህንኑ ስልት ሰዎችን ለማሳሳቻ፣ ለማታለያ ሲጠቀምበት ይታያል። ወደፊት ደግሞ መጠኑን በመጨመር “የእግዚአብሔር እሣት ወረደች” በማስባል ብዙዎችን ያሳስትበታል። ጌታችን ግን ያለው “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ” ነው።

እጅግ ብዙ ሰዎችን በቀላሉ ወደሚፈለግበት አቅጣጫ ለመንዳት የሚቻለው ለአእምሯቸው ሳይሆን ለስሜታቸው ደስ የሚላቸውን በመንገር ነው። በዘመናችን ያሉቱ የሚጠቀሙት ስልት ከዚህ የተለየ አይደለም። ጠንከር ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነታ፣ አስተምህሮ (ዶክትሪን)፣ ወዘተ ለምዕመናቸው ማስተማር የማይፈልጉት የዘመናችን “መምህራን፣ ነቢያት፣ ኧፖስትሎች፣ ፕሮፌቶች፣ …” በዚህ መስመር ላይ ያለ አንዳች ችግር ሲመላለሱ እየታዩ ነው። ራሱን ለዕርድ እንደሚያቀርብ በግ በየቀኑ ወደ ጥፋት በሚወስደው ሰፊ ጎዳና ላይ እየተጓዘ ያለው ሕዝብም ቆም ብሎ “ምን እየሆነ ነው?” ብሎ መጠየቅ ይገባዋል። 

ጌታችን በምድር በነበረበት ጊዜ እጅግ በርካታ ተዓምራትን አድርጓል፤ ሐዋሪያቱም እንዲሁ። ችግሩ ያለው ድንቅና ተዓምራትን ማድረግ ላይ ሳይሆን፤ ድንቅ የተደረገለት ሰው በቀጣይ ሕይወቱ ወዴት ይሄዳል? የሚለው ነው። ወደ እግዚአብሔር ቃል ጥናትና የተረጋጋ ሕይወት? ወይስ ወደ ሌላ ተጨማሪ ተዓምራት ፍለጋ? ከዚህ ጋር ተያይዞ “ነቢይና ሐዋሪያ” ነን የሚሉትን ግለሰቦች ሕይወት መመርመር አስፈላጊ ነው። ምን ዓይነት ፍሬ ነው በሕይወታቸው የሚታየው የሚለውን መጠየቅ እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።

“ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ” (ማቴ. 7፡21-23)።

እነዚህ ራሳቸውን የሾሙ የሃሰት ነቢያት የሚኖሩት ኑሮ ሊጤን የሚገባው ነው። ተዓምራትና ፈውስን ለመቀበል ከመጣው ሕዝብ በተለያየ ስልት በሚወስዱት ገንዘብ ጥግ የደረሰ ዓለማዊ ሕይወት የሚኖሩት እነዚህ “ነቢያት”፤ በጉባዔ ፊት በግልጽ የተቃወሟቸውን እንደ ግል ጠባቂ በቀጠሯቸው ጡንቸኞች ዝም እንዲሉ ከመናገር እስከ መደብደብና እንደሚያጠፏቸው እስከማስፈራራት እንደሚደርሱ የችግሩ ሰለባዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ። ከፍሬ ማወቅ ማለት አንዱ ይህ ነው። ጌታችን ስለሁላችን ተደበደበ፣ ተተፋበት፣ ተገረፈ፣ ተሰቃየ እንጂ ማንንም በክፉ ቃል እንኳን አልተናገረም። እንዴት የእርሱ አገልጋይ ነኝ የሚል ፈጽሞ ተጻጻሪ ነገር እያደረገ “የጌታ መልዕክተኛ ነኝ” ይላል? ስለዚህ ልንነቃ ይገባናል፤ ግልጽ የሆነውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምናውቅበት ዋንኛው መንገድ ድንቅ፣ ተዓምራትና መገለጥ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናትና ራስን አዋርዶ በአምላክ ፊት በመቅረብ ነው። 

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጌታችን በግልጽ እንዳስቀመጠው በኋለኛው ዘመን “ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት” እንደሚነሱና “ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ” በማለት የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት የተናገረውን በጥንቃቄ ማስተዋሉ ከጥፋት ለመጠበቅ ያስችላል (ማቴ. 24፡24)።

በዚህ ሁሉ ወጀብ ውስጥ በድል አድራጊነት ለመውጣትና ለመዳን የሚችለው “እስከ መጨረሻ የሚጸና” መሆኑን አምላካችን አብሮ መፍትሔውንም አስቀምጧል። ይህንን እስከመጨረሻ መጽናት የምንችልበትን ኃይል የምናገኘው ከጌታ ቃል ብቻ ነው። “እኔን ስሙኝ” ባዩ በበዛበት፤ የሃሰተኛው ቁጥር የጻድቃንን ሊውጥ ባለበት ዘመን በብርሃን መጓዝ የምንችልበትን ዘዴ አለ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ለእግራችን መብራት፤ ለመንገዳችን ብርሃን ስናደርገው ብቻ ነው (መዝ. 119፡105)።

ቃሉን በትጋት በማጥናት፣ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ከስህተት መጠበቅ እንችላለን። “የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስን ይመልሳል፤ የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው፤ ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል። የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው፥ ልብንም ደስ ያሰኛል፤ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፥ ዓይንንም ያበራል። የእግዚአብሔር ፍርሃት ንጹሕ ነው፤ ለዘላለም ይኖራል፤ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነትና ቅንነት በአንድነት ነው። ከወርቅና ከክቡር ዕንቍ ይልቅ ይወደዳል፤ ከማርና ከማር ወለላም ይጣፍጣል። ባሪያህ ደግሞ ይጠብቀዋል፤ በመጠበቁም እጅግ ይጠቀማል” (መዝ. 19፡7-12)።

“እርሱም (ጌታ ኢየሱስ) በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት”።

“ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ”።

ጥበበሥላሴ መንግሥቱ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *