giziew.org

የጌታ ዳግም ምፅዓት

ጌታ የሚመጣው በድብቅ ሳይሆን በግልጽ፤ ዓለም ሁሉ እያየው ነው። በድብቅ የሚሆን መነጠቅም ሆነ መሰል ተግባር የለም።
Share on facebook
Share
Share on twitter
Tweet
Share on telegram
Telegram
Share on whatsapp
WhatsApp
Share on email
Email
Share on print
Print

ጌታችንና መድኃኒታችን የዚህ ምድር ሥራውን አጠናቅቆ ወደ ሰማይ ሲያርግ ለደቀመዛሙርት የሰጣቸው አንድ ታላቅ ተስፋ ተመልሶ እንደሚመጣና እርሱ ወዳለበት እነርሱንም እንደሚወስዳቸው ነበር። “ታላቁ ተስፋ” በማለት ሐዋሪያው ጳውሎስ የሚጠቅሰው ይህ የጌታችን መመለስ፤ በዘመናት ሁሉ የክርስቶስ ተከታዮች ራሳቸውን ለሰይፍና ለስለት አሳልፈው እስኪሰጡ ድረስ በእምነት እንዲዘልቁ ያደረጋቸው ነው።

ከጌታችን ዳግም ምፅዓት ጋር በተያያዘ የሚከናወኑ ታላላቅ ተግባራት እንደሚኖሩ መጽሐፍ ቅዱሳችን ይነግረናል። ጌታ የሚመጣው በድብቅ ሳይሆን በግልጽ፤ ዓለም ሁሉ እያየው ነው። በድብቅ የሚሆን መነጠቅም ሆነ መሰል ተግባር የለም። እግሩ ምድርን አይረግጥም፤ ነገርግን ጌታችንን አምነው የሞቱ አዲስ አካል ለብሰው ከመቃብር ይነሳሉ፤ በኃጢአታቸው የሞቱ እዚያው ባሉበት በመቃብር ይቆያሉ፤ በሕይወት ያለን ደግሞ አዲስ አካል በቅጽበት በመልበስ እንለወጣለን። በህይወት ያሉ ኃጥአን በጌታችን የክብር ብርሃን ይሞታሉ። ከሞት የተነሱትና በህይወት እያለን የተለወጥነው ጌታን ለመቀበል በአየር እንነጠቃለን፤ ከዚያም በመላዕክት ታጅበን ወደ ሰማይ ከጌታችንና መድኃኒታችን ጋር እንሄዳለን። በዚያም ለአንድ ሺህ ዓመት እንቆያለን።

በምድር ላይ ግን ኃጥአን በአምላክ ክብር ብርሃን ከሞቱ በኋላ የሚቀሩት ሰይጣንና አጋንንት ለአንድ ሺህ ዓመት በምድር ይታሰራሉ። ሺሁ ዓመት ሲፈጸም ሰይጣንና መላዕክቱ ከእስራታቸው ይፈታሉ፤ በመቃብር የሚገኙት ኃጥአን ይነሳሉ፤ አዲሲቷ የሩሳሌም ወደ ምድር ትወርዳለች፤ በውስጧም ለሺህ ዓመት ከጌታችን ጋር በሰማይ የነበሩት ጻድቃን ከአምላካቸው ጋር ሆነው ይመጣሉ። ሰይጣንና ሠራዊቱ ከሞት ከተነሱት ኃጥአን ጋር በመሆን አዲሲቱን የሩሳሌም ለመውረር ለጦርነት ይዘጋጃሉ፤ እሣት ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወርዳ ትበላቸዋለች። ከዚያም ጌታችን ይችን ምድር በእሣት ያጸዳታል፤ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ይፈጥራል፤ እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከዚያ ወዲያ ሞት አይኖርም፣ ጻድቃን ከአምላካቸው ጋር በምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ። ይህ ባዶ ተስፋ ወይም ተረት ተረት ሳይሆን የታመነና የተረጋገጠ እውነታ ነው።

ይህ ከጌታችን ዳግም ምፅዓት እስከ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር መፈጠር ድረስ የሚሆን ትዕይንት ሲሆን ከዚህ በመቀጠል በጥያቄና መልስ በቅደም ተከተል የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎችን በመጥቀስ በዝርዝር እንዳስሰዋለን። በዳግም ምፅዓት እንጀምር፤

1. ስለ ጌታችንና መድኃኒታችን ዳግም መመለስ ምን ያህል እርግጠኛ መሆን እንችላለን?

“ክርስቶስ … ሁለተኛ ጊዜም ይገለጣል” (ዕብ. 9፡28) “ሄጄም ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ … ከእኔ ጋር እንድትሆኑ ልወስዳችሁ ዳግመኛ እመጣለሁ” (ዮሐ.14፡3)። በተጨማሪ ማቴዎስ 26፡64 ይመልከቱ። ክርስቶስ በከብቶች ግርግም በመወለድ የመጀመሪያውን ትንቢት እንደፈጸመ ሁሉ ይህንንም ራሱ የተናገረውን ትንቢት ይፈጽማል ብለን ልናምነው እንችላለን።

2. ጌታችንና መድኃኒታችን በምን መልኩ ነው የሚመለሰው?

“ይህን ካለ በኋላ እያዩት ወደ ላይ ዐረገ፤ ደመናም ከዐይናቸው ሰወረችው። እርሱም በሚሄድበት ጊዜ ትኵር ብለው ወደ ሰማይ ሲመለከቱ፣ እነሆ፤ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች ድንገት አጠገባቸው ቆሙ፤ እንዲህም አሏቸው፤ “እናንት የገሊላ ሰዎች ሆይ፤ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ እዚህ የቆማችሁት ለምንድን ነው? ይህ ከእናንተ ዘንድ ወደ ሰማይ ሲያርግ ያያችሁት ኢየሱስ፣ ልክ ወደ ሰማይ ሲወጣ እንዳያችሁት በዚሁ ሁኔታ ይመለሳል” (ሐዋ. 1፡9-11)። “በዚህ ጊዜ … የሰው ልጅም በሰማይ ደመና ሆኖ በኀይልና በታላቅ ክብር ሲመጣ ያዩታል” (ማቴ. 24፡30)። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚመሰክርልን ከሆነ ክርስቶስ የሚመለሰው ልክ እንደአካሄዱ ነው። ይህም ማለት ከሞት ከተነሳ በኋላ ወደ ሰማይ ሲያርግ በሄደው መልክ እየታየ፣ እየተሰማ፣ በገሃድ፣ በአካል ይመለሳል። ይህም ማለት በምሥጢር ወይም በምትሃት መልኩ ሳይሆን አንድ የሚዳሰስና የሚታይ አካል ያለው ሆኖ ነው የሚመጣው (ሉቃ.24፡36-43፣ 50-51)።

3. ክርስቶስ ሲመጣ ለሁሉም ነው የሚታየው ወይስ ለተወሰኑ ጥቂቶች ብቻ?

“እነሆ፤ በደመና ይመጣል፤ … ዐይን ሁሉ ያየዋል” (ራዕይ 1፡7)። “መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ ምዕራብ ድረስ እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅ አመጣጥም እንደዚሁ ይሆናል” (ማቴ. 24፡27)። “ጌታ ራሱ በታላቅ ትእዛዝበመላእክት አለቃ ድምፅበእግዚአብሔር የመለከት ድምፅ ከሰማይ ይወርዳልና። በክርስቶስ የሞቱትም አስቀድመው ይነሣሉ” (1ተሰ. 4፡16)። በጥቅሱ እንደተገለጸው መብረቅ በሚወጣበት ጊዜ ሁሉም ሰው እንደሚያየውና ከማንም ሰው መሰወር እንደማይችል ሁሉ የአምላካችንም ዳግም መምጣት እንዲሁ ከአድማስ እስከ አድማስ ሁሉም ሰው የሚያየው ትዕይንት ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ በ1ተሰሎንቄ 4፡16 ከላይ የተጠቀሰውን ሰዎች በተሳሳተ መንገድ “በድብቅ መነጠቅ” (ጻድቃን በምሥጢር ከዚህች ምድር ይሰወራሉ) ለሚል ትምህርት ሲያውሉት ይደመጣሉ። ሆኖም በደንብ ካስተዋልነው በመጽሐፍ ቅዱስ ካሉት ጥቅሶች ሁሉ ይህ ብቻ ነው በርካታ ድምጾች የሚሰሙበት። ስለዚህ ዳግም ምፅዓት ምሳሌያዊ፣ ወይም በምሥጢር የሚሆን ፀጥተኛ ኹነት፣ ወይም በልቤ ተከስቷል የምንለው አይደለም። ጌታችን ዓይን ሁሉ እያየው በገሃድ ነው የሚመጣው!

4. ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ አብረውት የሚመጡት እነማን ናቸው? ለምንድር ነው የሚመጡት?

“የሰው ልጅ ከመላአክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ፣ በክብሩ ዙፋን ላይ ይቀመጣል” (ማቲ. 25፡31)።“መላእክቱንም ከታላቅ የመለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፤ እነርሱም ምርጦቹን ከአራቱም ነፋሳት፣ ከሰማያት ከአንዱ ዳርቻ ወደ ሌላው ዳርቻ ይሰበስባሉ” ማቲ. 24፡31።

5. ጌታችን ወደዚህ ምድር የሚመጣበት ዓላማ ምንድንነው?

“እነሆ፤ ቶሎ እመጣለሁ፤ ዋጋዬ በእኔ ዘንድ አለ፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍለዋለሁ” (ራይዕ 22፡12)። “ሄጄም ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ እኔ ባለሁበት እናንተም ከእኔ ጋር እንድትሆኑ ልወስዳችሁ ዳግመኛ እመጣለሁ” (ዮሐ. 14፡3)።

6. በዳግም ምፅዓት ወቅት ጻድቃን ምን ይሆናሉ?

“ጌታ ራሱ በታላቅ ትእዛዝ፣ በመላእክት አለቃ ድምፅና በእግዚአብሔር የመለከት ድምፅ ከሰማይ ይወርዳልና። በክርስቶስ የሞቱትም አስቀድመው ይነሣሉ። ከዚያም በኋላ እኛ የቀረነው፣ በሕይወትም የምንኖረው ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ በዚህም መሠረት ለዘላለም ከጌታ ጋር እንሆናለን” (1ተሰ. 4፡16-17)። “እነሆ፤ … ሁላችንም እንለወጣለን፤ … መለከት ይነፋል፤ ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና” (1ቆሮ. 15፡51-53)። “እኛ ግን አገራችን በሰማይ ነው፤…ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በናፍቆት እንጠባበቃለን፤ እርሱም ሁሉን ለራሱ ባስገዛበት ኀይል፣ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል”(ፊሊ. 3፡20)።

በህይወት ሳሉ ክርስቶስን ሲከተሉ ቆይተው የሞቱ በዳግም ምፅዓት ወቅት ፍጹም የሆነ፣ የማይሞትና የማይበሰብስ አካል ለብሰው በትንሣኤ ሙታን ይነሳሉ። በህይወት ያሉ ጻድቃን ደግሞ ከሞት የተነሱት እንደለበሱት አዲስ አካል በመልበስ ጌታን በአየር ለመቀበል ሁሉም አብረው ይነጠቃሉ። ማስተዋል የሚገባን ጉዳይ፤ ክርስቶስ ሲመጣ እግሩ መሬት አይረግጥም፤ ጻድቃን እርሱን ለመገናኘት በጥቅሱ እንደተመለከተው “በአየር ላይ” ነው የሚነጠቁት። ስለዚህ “ክርስቶስ መጥቷል” እየተባለ በሃሰት ነቢያት ሲነገር የምንሰማው ትምህርት (ማቲ. 24፡23-27) ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ሊቀርብለት የማይችል ነው።

7. ክርስቶስ ሲመጣ ኃጥኣንስ ምን ይሆናሉ?

“… በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉዎችን ይገድላል” (ኢሳ. 11፡4)። “በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር የተገደሉት ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር በሁሉ ስፍራ ተረፍርፈው ይታያሉ” (ኤር. 25፡33)። ክርስቶስ ሲመጣ ከኃጢአት ጋር አንላቀቅም ብለው በራሳቸው መንገድ ሲሄዱ የነበሩ በጌታችንና መድኃኒታችን የክብር ብርሃን ይጠፋሉ።

8. የክርስቶስ ዳግም መመለስ በምድራችን ላይ ምን ያስከትላል?

“ከዚያም መብረቅ፣ ድምፅ፣ ነጐድጓድና ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ሰው በምድር ላይ ከተፈጠረ ጀምሮ እንዲህ ያለ ታላቅ የምድር መናወጥ ታይቶ አይታወቅም፤ … ደሴቶች ሁሉ ሸሹ፤ ተራሮችም ሊገኙ አልቻሉም” (ራዕይ 16፡18፣20)። “ተመለከትሁ፤ እነሆም፣ ፍሬያማው ምድር በረሓ ሆነ፤ ከተሞቹ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት፣ ከብርቱ ቍጣው የተነሣ ፈራረሱ” (ኤር. 4፡26)። “እነሆ፤ እግዚአብሔር ምድርን ባድማ ያደርጋታል፤ ፈጽሞ ያጠፋታል፤ … ምድር ፈጽሞ ባድማ ትሆናለች” (ኢሳ. 24፡1፣3።

9. መጽሐፍ ቅዱስ ዳግም ምፅዓት ቅርብ ስለ መሆኑን ዘርዘር ያለ መረጃ ይሰጥ ይሆን?

መልሱ አዎ ነው! ጌታችን ራሱ እንዲህ ብሏል፤ “እንደዚሁም እነዚህን ሁሉ ስታዩ፣ እርሱ በደጅ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ” (ማቲ. 24፡33)። ይህንን ካለ በኋላ ከዕርገቱ ጀምሮ እስከ ዳግም መምጣቱ የሚሆኑትን ምልክቶች አስመልክቶ የሚከተለውን በዝርዝር ተናገረ፤ …

ሀ) የየሩሳሌም መፍረስ፤

ትንቢት፤ “ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተክቦ የምታዩት፣ ሳይፈርስ እንዲህ እንዳለ የሚቀር አንድ ድንጋይ እንኳ አይኖርም፤ … በዚያን ጊዜ በይሁዳ የሚገኙ ወደ ተራራዎች ይሽሹ” (ማቲ. 242፣16)።

ፍጻሜው፤ የሩሳሌም በሮማዊው የጦር ጄኔራል ታይተስ በ70ዓም ፈረሰች።

ለ) ፀሐይ ጨለመች፤

ትንቢት፤ “ወዲያውኑ ከእነዚያ ከመከራው ቀናት በኋላ፣ ‘ፀሓይ ትጨልማለች፤” (ማቲ. 24፡29)።

ፍጻሜው፤ ይህ ትንቢት እኤአ በሜይ 19፣1780 ዓም ምድራችን በጨለማ የተወረረች ጊዜ የተከሰተ ነው። ስለ ሁኔታው አንድ የዓይን ዕማኝ ሲናገር፤ “የሜይ 19፣ 1780ው ዕለት ታሪካዊ ቀን ነበር፤ (ፀሐይ በመጨለሟ ምክንያት የምሽት ሰዓት ሳይደርስ) በበርካታ ቤቶች ሻማዎች በርተው ነበር፤ ዶሮዎች ወደማረፊያቸው ሲሄዱ ወፎች ልክ በመደበኛ ቀን እንደሚሆን ፀጥ ብለው ነበር፤ … በወቅቱ ሚዛን ደፍቶ የነበረው አጠቃላይ አመለካከት የፍርድ ቀን ደርሷል የሚል ነበር” ምንጭ Connecticut Historical Collections, compiled by John Warner Barber (2nd ed. New Haven: Durrie & Peck and J.W. Barber, 1836) p. 403)

ሐ) “ጨረቃ ወደ ደም ተለወጠች”፤

ትንቢት፤ “ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ ፀሓይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ወደ ደም ትለወጣለች” (ኢዮኤል 2፡31)።

ፍጻሜው፤ ቀኑ በጨለመበትና ከላይ በተጠቀሰው ቀን በሜይ 19፣1780 ጨረቃም ደም መስላ እንደነበር ተመዝግቧል። “ጨረቃዋ ሙሉ ነበረች፤ ስትታይም ደም ትመስል ነበር” (Milo Bostick, Stone’s History of Massachusetts)

መ) ከዋክብት ከሰማይ ወደቁ፤

ትንቢት፤ “ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ” (ማቲ. 24፡29)።

ፍጻሜው፤ እኤአ በኖቬምበር 13፤ 1833 ዓም ምሽት ከዋክብት እንደዶፍ ስለመውረዳቸው የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ። እንዲያውም ፀሐይ ጠልቃ ምሽቱ በበረታበት ጊዜ ይወርድ የነበረው የከዋክብት መጠን ሰማዩን ከማብራቱ የተነሳ ጋዜጣ በጨለማ ማንበብ የሚያስችል ነበር ተብሎለታል። ይህ ሁኔታ ሰዎችን ከማስደንገጡ የተነሳ የዓለም ፍጻሜ ነው በማለት እንዲያስቡ ያደረጋቸው ሲሆን አንድ ጸሐፊ ክስተቱን አስመልክቶ ሲናገር፤ “በግምት ለአራት ሰዓታት ያህል ሰማዩ ደምቆ ይታይ ነበር” ብሏል (Peter A. Millman, “The Falling of the Stars,” The Telescope, 7 (May-June, 1940) 57.)

ሠ) ክርስቶስ በደመና ይመጣል፤

ትንቢት፤ “በዚህ ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ላይ ይታያል፤ የምድር ወገኖች ሁሉ ያለቅሳሉ፤ የሰው ልጅም በሰማይ ደመና ሆኖ በኀይልና በታላቅ ክብር ሲመጣ ያዩታል” (ማቲ.24፡30)።

ፍጻሜው፤ እነዚህ ከላይ ያየናቸው በሙሉ አሁን ካለንበት ዘመን በፊት እንደተፈጸሙ ሁሉ አሁን የቀረው የጌታችንና መድኃኒታችን በክብር መገለጥ ነው። ከእነዚህ ምልክቶች እስካሁን ድረስ የዓለም ፍጻሜ ሆኖ ክርስቶስ ያልመጣበት ምክንያት ብዙዎች ሲያፌዙ እንደሚሉት ስለማይመጣ ሳይሆን አፍቃሪውና ርኅሩኁ አምላካችን ሰዎች ወደ ንሰሐ እንዲመጡ እየታገሰ በመሆኑ ነው። ነገርግን ይህ ትዕግስት ዘላለማዊ አይደለም፤ መጨረሻ አለው። “አንዳንድ ሰዎች የዘገየ እንደሚመስላቸው ጌታ የተስፋ ቃሉን ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን ማንም እንዳይጠፋ ፈልጎ፣ ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ ስለ እናንተ ይታገሣል። የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ ይመጣል፤ በዚያች ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በእሳት ይጠፋል፤ ምድርና በእርሷም ላይ ያለ ነገር ሁሉ ይቃጠላል።” 2ጴጥ.3፡9፣10) ወገን ለዚያ ቀን ተዘጋጅተሃል?

10. ጊዜው መቅረቡን፣ የምድር ፍጻሜ መዳረሱን እንዴት እናውቃለን? መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩት ሰዎች በምን መልኩ ነው የገለጻቸው?

ሀ) ጦርነትና የጦርነት ወሬ፤ “ስለ ጦርነትና ስለ ሕዝብ ዐመፅ ስትሰሙ አትደንግጡ፤ ይህ አስቀድሞ መሆን የሚገባው ነውና፤ መጨረሻው ግን ወዲያውኑ አይሆንም” (ሉቃስ 21፡9)።

) ሁከት፣ ብጥብጥ፣ ጭንቀትና ፍርሃት፤ “በምድር ላይ ያሉ ሕዝቦች ይጨነቃሉ፤ ይታወካሉም፤ የሰማያት ኀይላት ስለሚናወጡ፣ ሰዎች በፍርሀትና በዓለም ላይ ምን ይመጣ ይሆን እያሉ በመጠባበቅ ይዝላሉ” (ሉቃስ 21፡25፣26)።

) በሁሉም መስክ የዕውቀት መብዛት፤ “ብዙዎች ወዲያ ወዲህ ይራወጣሉ፤ ዕውቀትም ይበዛል” (ዳን. 12፡4)።

መ) የዘባቾች መበራከትና ለእውነት ግዴለሽ መሆን፤ “በመጨረሻው ዘመን የራሳቸውን ክፉ ምኞት የሚከተሉ ዘባቾች እየዘበቱ ይመጣሉ” (1ጴጥ. 3፡3)። “ምክንያቱም ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞቶቻቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ። እውነትን ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ዘወር ይላሉ” (2ጢሞ. 4፡3፣4)። ዘመኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይልቅ ሌሎች የገነኑበት ሆኗል።

) የሞራል መላሸቅና መንፈሣዊ ክሽፈት፤ “ነገር ግን በመጨረሻው ዘመን … ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ ከንቱዎች፣ በትዕቢት የተወጠሩ፣ … ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል። ከእነዚህ ራቅ” (2ጢሞ. 3፡1-5)።

ረ) ሰዎች ራሳቸውን በማስደሰት ብቻ የሚኖሩ ይሆናሉ፤ “ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉና” (2ጢሞ.3፡4)። ንዋየፍቅር የዘመናችን መለያ ሆኗል፤ ዝርፊያ የችሎታ መለኪያ ሆኗል፤ ዘራፊዎች “ዘጋ” ተብለው እንደ ብርቱ ሠራተኛ ይደነቃሉ፤ ነውር ጨዋነት ሆኗል። በየትኛውም መልኩ ቢሆን በዘመናችን በሚዲያ በተለይም በኢንተርኔት የሚተላለፉ መልዕክቶችን በመከታተል ብቻ የሚባክነው ጊዜ ለግምት የሚዳግት ነው። ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ በተለይ በፌስቡክ ሰዎች ስለራሳቸው ፎቶና ሌሎች ጉዳዮችን በመለጠፍና ምስጋናዎችን በመቀበል እንዲሁም የቀጥታ መልዕክቶችን በቪዲዮ በመልቀቅ የሚያባክኑት ጊዜ ወዳጅነትን የሚያፈርስ፣ ትዳርን የሚናጋ ደረጃ ላይ ደርሷል። በውጪው ዓለምም ሆነ በአገራችን ማቆሚያ በሌለው ሁኔታ ስለታዋቂ የሙዚቃና የፊልም ሰዎች ዕለታዊ ህይወት እንዲሁም ስፖርታዊ ጉዳዮችን በማኅበራዊ ሚዲያና መሰል አውታሮች በመከታተል ብቻ እጅግ በርካታ ጊዜ ይባክናል። የዚያኑ ያህል ሰዎች ለመንፈሣዊ ጉዳዮች፣ ለእግዚአብሔር ቃል ጥናት፣ ለፀሎት፣ ለመንፈሣዊ አገልግሎቶች፣ ወዘተ “ጊዜ የለኝም” ሲሉ ይደመጣሉ።

) ሕገወጥነት፣ የወንጀል መበራከት፣ የክፋትና የዐመፅ መጨመር፤ “ክፋት ስለሚገን የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል” (ማቲ.24፡12)፤ “ክፉዎችና አታላዮች ግን እየሳቱና እያሳቱ፣ በክፋትም ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ” (2ጢሞ.3፡13)። “ምድር በደም መፋሰስ፣ ከተማዪቱም በዐመፅ ተሞልታለችና” (ሕዝ.7፡23)።

) የተፈጥሮ አደጋ መበራከት፤ “ታላቅ የመሬት መናወጥ ይሆናል፤ ራብና ቸነፈር በተለያየ ስፍራ ይከሠታል፤ … ከባሕሩና ከሞገድ ድምፅ የተነሣ፣ በምድር ላይ ያሉ ሕዝቦች ይጨነቃሉ፤ ይታወካሉም” (ሉቃስ 21፡11፣25)።

ቀ) ወንጌል በየቦታው ይሰበካል፤ “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” (ማቲ.24፡14)።

በ) ከመንፈሣዊነት ይልቅ የመናፍስት ጠሪነት ልምምድ መበራከት፤ “በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች እምነትን ክደው አታላይ መናፍስትንና የአጋንንትን ትምህርት እንደሚከተሉ መንፈስ በግልጥ ይናገራል” (1ጢሞ.4፡1)።“እነርሱም ምልክቶች የሚያደርጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸው” (ራዕይ 16፡14)። ዛሬ በዓለማችን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ከመመራት ይልቅ ፊታቸውን ወደ ጥንቆላ፣ ባሕላዊ አምልኮ፣ መናፍስት ጠሪነት፣ በቡና ወይም በካርታ የመጠንቆልን፣ አዋቂ ጋር መሄድ፣ ከሳይኪክ ጋር መማከር፣ ዕለታዊ ኮከብ ቆጠራ (ሆሮሰኮፕ) በመመልከት፣ ወዘተ ዕለታዊ ኑሯቸውን እየመሩ ይገኛሉ። በክርስትናውም ዓለም ቢሆን ከጥንቆላ ያልተለየ የአጋንንት አሠራር በክርስትና ስም ሲደረግ ይታያል፤ የወንጌል አገልጋዮች ናቸው የተባሉ ግለሰቦች፤ “ሐዋሪያ”፣ “ነቢይ”፣ “ነቢይት” ወዘተ የሚሉ ማዕረጎችን ለራሳቸው እየሰጡና በብልጽግና ወንጌል ብዙዎችን ቀቢጸተስፋ እየሞሉ ለራሳቸው የተንደላቀቀ ኑሮ የሚኖሩ ጥቂቶች አይደሉም። “ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው! ለአፌም ከማር ወለላ ይልቅ ጣዕም አለው” (መዝ.19፡103) በሚለው የእግዚአብሔር ቃል ምክት ዓለማዊነት፣ ስግብግብነት፣ ውሸት፣ ወዘተ ይሰበካል። ይህ በሃይማኖትና በመጽሐፍ ቅዱስ ስም የሚደረግ ውንብድና ለበርካታ አጭበርባሪዎች የገንዘብ ማካባቻ ቀላል መንገድ የከፈተ ሲሆን ብዙዎችን ግን በሃሰት መንገድ ወደሞት እየመራ ነው። ሃሰተኛ ፈውሶች፣ ሃሰተኛ ተዓምራት፣ ወዘተ በሚደረግባቸውና ከውጭው ዓለም በተኮረጀ ስልት ሰዎችን በመሬት ላይ በመዘረር ክብራቸውን በሚነካ መልኩ የሚፈጸመው ተግባር የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጽሞ የማያደርገውና በመጽሐፍ ቅዱስም አንዳች ድጋፍ የሌለው ነው። “ነቢይ ነኝ” የሚሉትም በመጽሐፍ ቅዱስ ተመርምረው የነቢይነትን ፈተና ማለፍ ይገባቸዋል። ራሳቸውን በፈለጉት ስም የሚጠሩት ታየኝ፣ ተመለከትሁ፣ ተገለጠልኝ፣ በራዕይ ነበርሁ፣ … የሚሉት ሳይሆን የአምላካችን ቃል ብቻውን ለዘላለም ይኖራል፤ “ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” ኢሳ. 40፡8። 

ተ) በሠራተኞች ላይ የሚፈጸም ግፍ መጨመር፤ “ልብ በሉ፤ እርሻችሁን ሲያጭዱ ለዋሉ ሠራተኞች ያልከፈላችሁት ደመወዝ በእናንተ ላይ ይጮኻል፤ የአጫጆቹም ጩኸት ሁሉን ቻይ ወደ ሆነው ጌታ ጆሮ ደርሶአል።..እናንተም እንዲሁ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፤ ምክንያቱም የጌታ መምጫ ተቃርቦአል”(ያዕ. 5፡4)

11. የጌታ ዳግም መመለስ ምን ያህል ቀርቧል?

“ከበለስ ዛፍ ይህን ትምህርት ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፣ ቅጠሏ ሲያቈጠቍጥ፣ ያን ጊዜ በጋ እንደ ተቃረበ ታውቃላችሁ። እንደዚሁም እነዚህን ሁሉ ስታዩ፣ እርሱ በደጅ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ።” (ማቲ. 24፡32)።

12. በዘመናችን ሰይጣን ስለ ክርስቶስ ዳግም መመለስ ብዙ የሃሰት ድንቆችና ተዓምራት በማሰራጨት ሚሊዮኖችን እያሳተ ይገኛል፤ ላለመታለላችን ዋስትናችን ምንድነው?

“እነርሱም ምልክቶች የሚያደርጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸው” (ራዕይ 16፡14)። “ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻል የተመረጡትን ለማሳት ሲሉ ታላላቅ ምልክቶችንና ታምራትን ያደርጋሉ” (ማቲ.24፡24)። “ወደ ሕጉና ወደ ምስክር ቃሉ ሂዱ! እነርሱም እንዲህ ያለውን ቃል ባይናገሩ የንጋት ብርሃን አይበራላቸውም” (ኢሳ. 8፡20)።

በሼፕኸርድ ቡሺሪ ስብሰባ ላይ ካሜራው መልአክ አብሮ ቀረጸ ሲባል  

በዘመናችን እንደሚታየው ሰይጣን ለተወሰኑት ክርስቶስ አስቀድሞ መጥቷል በማለት እያታለላቸው የሚገኝ ሲሆን ሌሎችን ደግሞ ክርስቶስ የሚመጣው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተጠቀሰው መልኩ አይደለም በማለት ሊያሳምን ይሞክራል። ስለ ሰይጣን ስልት ጌታችን ሲናገር “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ” (ማቲ.24፡4)። “እነሆ፤ አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ” (ማቲ.24፡25) በማለት መክሮናል። ለምሳሌ በምሥጢር ወይም በድንገት በበረሃ እንደማይገለጥ አስቀድሞ አስጠንቅቆናል (ማቲ.24፡26)።

13. ስለ አንድ ታላቅ አደጋ ክርስቶስ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል፤ ምንድነው?

“የሰው ልጅም ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣልና እናንተም እንደዚሁ ዝግጁ ሁኑ” (ማቲ.24፡44)። “እንግዲህ በገደብ የለሽ ሕይወት፣ በመጠጥ ብዛትና ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝልና ያ ቀን እንደ ወጥመድ ድንገት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ” (ሉቃ.21፡34)። “ልክ በኖኅ ዘመን እንደሆነው የሰው ልጅ መምጣትም እንደዚሁ ይሆናል” (ማቲ.24፡37)

በኖህ ዘመን የነበሩ ሰዎች የጥፋት ውሃ እንደሚመጣ፣ ምድር በጎርፍና በኃይለኛ ዝናብ እንደምትጠፋ ቢነገራቸውም ችላ በማለት በጥፋት ውሃ እንዳለቁ ሁሉ እኛም በኑሮ ጉዳዮች ተጠምደን፣ በዓለማዊ ኑሮ ደስታን በመፈለግና ራሳችንን ማስደሰት ብቻ ትኩረታችን ሆኖ የክርስቶስ መምጣት በድንገት እንዳይሆንብን በትጋት መጠበቅ አለብን።

ስለዚህ ለመዘጋጀትና ራስን ለእግዚአብሔር የመስጠት ቀኑ ዛሬ፣ አሁን ነው። ተዘጋጅተዋል?

ቅንብር፤ ጥበበሥላሴ መንግሥቱ


Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *