ባለንበት ዘመን በተለይ በክርስትናው ዓለም ስለቤተመቅደስ አገልግሎትና ከዚያ ጋር ስለተያያዙ በርካታ እውነታዎች ሲነገር ብዙ አይደመጥም። እንዲያውም ብዙዎች ቤተመቅደሱና አብሮት ያለው ሥርዓት ለአይሁዶች እንዲድኑበት የተሠጠ የዱሮ ሥርዓት ነው በማለት አሁን ምንም ጥቅም እንደሌለው አድርገው ይወስዱታል። ይህ ደግሞ እግዚአብሔር ሰውን የሚያድንበት መንገድ በየጊዜው የሚለዋውጥ ወይም እንደ ሰው ከስህተቱ የሚማርና የሚያሻሽል አምላክ ተደርጎ እንዲወሰድ የሚያደርገው ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችን ግን እግዚአብሔር የማይለዋወጥ፣ አሠራሩም ከቀድሞው ጀምሮ ሁልጊዜ ተመሳሳይ እንደሆነና ስለሰው ልጆች መዳን ዓለም ሣይፈጠር በፊት አስቀድሞ ያሰበበት መሆኑን ያስተምራል (ዘኁ. 23፡19፤ ዕብ. 13፡8፤ ያዕ. 1፡17፤ ራዕይ 13፡8)። እንዲህ ከሆነ ታዲያ የቤተመቅደስ አገልግሎትና በዚያ ውስጥ የተካተቱት የሚያስተምሩን ምንድነው? ዛሬስ ሥርዓቱን የማናካሂደው ለምንድን ነው? የሚሉትንና መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት በዚህ ክፍል ለመዳሰስ እንሞክራን።
1. እግዚአብሔር ለምንድነው ቤተመቅደስ ሥሩልኝ በማለት ሙሴን ያዘዘው?
“በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ” (ዘጸ. 25፡8)። እግዚአብሔር ቤተመቅደሱን የመሥራት ትዕዛዝ የሰጠው ለሙሴ ነበር። ይህም የሆነበት ምክንያት ከልጆቹ ፈጽሞ መለየት የማይወደው የሰማይ አምላክ ማደሪያ በመፈለጉ ነበር፤ በመሆኑም የተለየ ማደሪያ ወይም ቤተመቅደስ እንዲሠሩለት ሙሴን ጠየቀው።
የመጀመሪያው ቤተመቅደስ ግርማ ሞገስ የተጎናጸፈና በድንኳን መልክ የተሠራው ሲሆን መዋቅሩም 4.5ሜትር በ 13.5ሜትር ነበር። ግድግዳዎቹ እርስበርሳቸው እንዲጋጠሙ ከተደረጉ የሳንቃ እንጨት ድርድር የተሠራና በወርቅ የተለበጠ ነበር (ዘፀ. 26፡15-19፤ 29)። ጣሪያው ደግሞ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፣ ከፍየል ጠጒር፣ ከአውራ በግ ቆዳና ከአቆስጣ ቁርበት የተሠራ ነበር (ዘጸ. 26፡1፣7-14)። ይህ “የምስክሩ ድንኳን” ተብሎ የሚጠራው ተንቀሳቃሽ ቤተመቅደስ “ቅዱስ” እና “ቅድስተ ቅዱሳን” የተባሉ ሁለት ክፍሎች ነበሩት። እነዚህን ክፍሎች አንድ ወፈር ያለ መጋረጃ የሚከፍላቸው ሲሆን “አደባባይ” ተብሎ የሚጠራው መስዋዕት የሚቀርብበት የውጪው ቦታ 23ሜትር በ46ሜትር ነበር (ዘጸ. 27፡18)። ቤተመቅደሱን አጥር ሆኖ የሚከልል ከጥሩ በፍታ የተሠራ 23ሜትር በ 46ሜትር የመጋረጃ አጥር ነበር።
2. እግዚአብሔር ከቤተመቅደሱ እንድንማር የሚፈልገው ምንድነው?
“አቤቱ፥ መንገድህ በመቅደስ ውስጥ ነው፤ እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው?” (መዝ. 77፡13)። የእግዚአብሔር አሠራር፣ ማለትም የመዳን ዕቅድ፣ በምድራዊ ቤተመቅደስ ተገልጧል። የቤተመቅደሱ አገልግሎትና በውስጡ ያሉት የአገልግሎት ዕቃዎች እግዚአብሔር ስለ መዳናችን ዕቅድ ሂደቱን እንድናስተውል፣ የእርሱን አሠራር እንድንረዳ፣ በሚታይና ስዕላዊ በሆነ መልኩ ያስተማረበት ተምሣሌያዊ ማስተማሪያ ዘዴ ነው። ይህንን በጥንቃቄ የተሰጠ አገልግሎት ለመረዳት በትጋት ማጥናት የግድ ይላል።
3. ሙሴ ቤተመቅደሱን ለመገንባት ዕቅዱን (ንድፉን) ከየት አገኘ?
“ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት። … እንግዲህ በምድር ቢኖርስ፥ እንደ ሕግ መባን የሚያቀርቡት ስላሉ፥ ካህን እንኳ ባልሆነም፤ እነርሱም ሙሴ ድንኳኒቱን ሊሠራ ሳለ እንደ ተረዳ፥ ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሚሆነውን ያገለግላሉ። በተራራው እንደተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ ብሎት ነበርና” (ዕብ. 8፡1፣2፣4፣5)። እግዚአብሔር ራሱ ነበር ለሙሴ የሥራ ዝርዝሩንና የአሠራሩን ንድፍ (ዲዛይን) የሰጠው። ሙሴ በምድር እንዲሠራ የተነገረው ቤተመቅደስ እግዚአብሔር በተራራው ላይ ባሳየው ንድፍ መሠረት ነበር። ስለዚህ ከተገለጸለት እንዳይዛነፍ “ተጠንቀቅ” ተብሎ ነበር የተነገረው። የቤተመቅደሱን ኪነህንጻ በጥቅሉ ካየነው አደባባይ፣ ቅዱስ እና ቅድስተ ቅዱሳን የሚባሉ ሦስት ክፍሎች አሉት።
4. በቤተመቅደሱ አደባባይ የነበሩት ዕቃዎች ምን ምን ነበሩ?
ሀ. መሠዊያው፡- የእንስሳት መስዋዕት የሚቀርብበት ወደ ቅጥሩ ልክ ሲገባ የሚገኝ ነው (ዘፀ. 27፡1-8)። ይህ መሰዊያ የክርስቶስ መስቀል ተምሣሌት ነው። በዚያ ላይ መስዋዕት የሚሆኑት እንስሳት ደግሞ የኢየሱስን ፍፁም መስዋዕትነት የሚያመላክቱ ናቸው (ዮሐ. 1፡29)።
ለ. የመታጠቢያው ሳህን፡- ወደ ቤተመቅደሱ መግቢያ በርና በመሰዊያው መሀል የሚገኝ ከናስ የተሠራ ትልቅ የመታጠቢያ ሰሃን ነው። ይህም ካህናት ወደ ቤተመቅደሱ የሚገባ መስዋዕት ከማቅረባቸው በፊት እጃቸውን፣ እግራቸውን የሚታጠቡበት ነው (ዘፀ. 30፡17-21፣ 38፣8)። ውሃው ከኃጢያት የመንጻትንና አዲስ ውልደትን (ዳግም መወለድን) የሚያመለክት ነው (ቲቶ. 3፡5)።
5. በቅዱሱ ክፍል የነበሩት ዕቃዎች ምን ምን ነበሩ?
ሀ. የገጽ ኅብስት ገበታ (ዘፀ. 25፡23-30)፤ ኅብስቱ የሕይወት እንጀራ የሆነው የኢየሱስ ተምሣሌት ነው (ዮሐ. 6፡5)።
ለ. ባለሰባት ቅርንጫፍ መቅረዝ (ዘፀ. 25፡31-40)፤ ይህም እንዲሁ የዓለም ብርሃን የሆነው የኢየሱስ ተምሣሌት ነው (ዮሐ. 9፡5፣ 1፡9)። ዘይቱ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የሚያመለክት ነው (ዘካ. 4፡1-6፣ ራዕይ 4፡5)።
ሐ. የዕጣን መሠዊያ (ዘፀ. 30፡7፣8)፤ ይህ ደግሞ የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ አምላኩ የሚያቀርበው ፀሎት ተምሳሌት ነው (ራዕይ 5፡8)።
6. በቅዱስተ ቅዱሳን ክፍል የሚገኘው ዕቃ ምን ነበር?
የቃል ኪዳኑ ታቦት፣ በቅድስተ ቅዱሳን የሚገኘው ብቸኛ ዕቃ ይህ ነበር (ዘፀ. 25፡ 10-22)። ከግራር እንጨት ተሠርቶ በወርቅ የተለበጠ ነበር፣ ከሣጥኑ ግራና ቀኝ በሙሉ ወርቅ የተሠሩ የመላዕክት ቅርጽ ነበሩት። በእነዚህ መላዕክት መካከል እግዚአብሔር በቤተመቅደሱ መገኘቱ የሚታይበት የስርየት (የምህረት) መክደኛው ነበር (ዘፀ. 25፡17-22)። ይህም በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር ዙፋን ተምሣሌት ነው (መዝ. 80፡1)።
7. በታቦቱ ውስጥ ያለው ምንድን ነው?
በታቦቱ ውስጥ የሚገኘው በድንጋይ ጽላት ላይ እግዚአብሔር በራሱ እጅ የጻፈው ዐሥርቱ ትዕዛዛት ነው። ይህም የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁልጊዜ ሊታዘዘው የሚገባው የእግዚአብሔር ቃል ነው (ራዕይ 14፡12፤ ዘዳ. 10፡4፣5)። በመላዕክቱ መካከል የሚገኘው የስርየት (የምኅረት) መክደኛ የሚባለው ደግሞ የእግዚአብሔር ሕዝብ ኃጢአቱን እስከተናዘዘና እስከተወው ድረስ በካህኑ አማካኝነት በምኅረት መክደኛው ላይ በሚረጨው ደም አሁንም ምኅረት ሊሰጠው እንደሚችል የሚያሳይ ነው (ምሣ. 28፡13፤ ዘሌ. 16፡15፣16)። የሚረጨው የእንስሳት ደም ለብዙዎች ኃጢያት ሥርየት የፈሰሰው የኢየሱስ ደም ምሣሌ ነው (ማቴ. 26፡28፣ ዕብ. 9፡22)።
8. በቤተመቅደሱ አገልግሎት ለምንድን ነው የእንስሳት መስዋዕት የሚቀርበው?
“እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፥ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም” (ዕብ. 9፡22)። “ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” (ማቴ. 26፡28)።
የእንስሳት መስዋዕት ማድረግ ያስፈለገው ደም ሳይፈስ ስርየት (የኃጢያት ይቅርታ) እንደሌለ ሰዎች እንዲያስተውሉ ነው። በጣም አስደንጋጭ የሆነው እውነታ ደግሞ የኃጢያት ዋጋ ሞት መሆኑ ነው (ሮሜ 6፡23)። ሁላችንም ኃጢያት ስለሠራን ሁላችንም ሞት ይገባናል። አዳምና ሔዋን ኃጢያት በሠሩ ጊዜ ክርስቶስ ፍጹም የሆነውን ሕይወቱን መስዋዕት በማድረግ ለሰዎች ሁሉ የሞትን ጽዋ ለመጠጣት ራሱን ባያቀርብ ኖሮ ወዲያውኑ በሞቱ ነበር (ዮሐ. 3፡16፣ ራዕይ 13፡8)። ኃጢያት ከገባ በኋላ እግዚአብሔር ኃጢአተኛውን የእንስሳ መስዋዕት እንዲያቀርብ ጠየቀ (ዘፍ. 4፡3-7)። ይህም የተፈጸመው ኃጢያተኛው በራሱ እጅ እንስሳውን ሲያርደው ሆነ (ዘሌ. 1፡4፣5)። ድርጊቱ እጅግ ዘግናኝና በደም የመጨማለቅ ሁነት መሆኑ የዘላለም ሞት የሚያስከትለው ኃጢያት ውጤት ምን እንደሆነ ለኃጢያተኛው በማሳየት እንዲሁም የአዳኝ አስፈላጊነት ምን ያህል እንደሆነ በማይረሣ መልኩ አእምሮው ላይ እንዲታተም አምላክ ያደረገው ሥርዓት ነው። ያለ አዳኝ ማንም የመዳን ተስፋ የለውም። በዚህ እንስሳት በሚታረዱበት የመስዋዕት ሥርዓት እግዚአብሔር እንዴት የራሱን ልጅ ለኃጢያት ስርየት ይሞት ዘንድ እንደሚሰጥ አስተማረበት (1ቆሮ. 15፡3)።
ጌታ ክርስቶስ አዳኝ ብቻ ሣይሆን በእኛ ምትክ የሚሞትም ነው (ዕብ. 9፡28)። መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን በተመለከተ ጊዜ “እነሆ የዓለምን ኃጢያት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” (ዮሐ. 1፡29) ብሏል። በብሉይ ኪዳን ጊዜ የነበሩት የክርስቶስን መስቀል በመጠባባቅ ቀራንዮን በተስፋ ይመለከቱ ነበር። እኛ ደግሞ የመዳናችንን መረጋገጥ በመረዳት ወደ ኋላ መለስ ብለን ቀራንዮን እናያለን። መስቀሉ የሁለቱ መካከልና ብቸኛ የመዳኛ መንገድ ነው፤ ምክንያቱም ለመዳን ሌላ መንገድ የለም (ሐዋ. 4፡12)።
9. በቤተመቅደሱ አገልግሎት እንዴት ነበር መስዋዕቱን የሚያቀርቡት? ትርጉሙስ ምንድን ነው?
“የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ በሚቀርበው እንስሳ ራስ ላይም እጁን ይጫን፤ ይህም ያስተሰርይለት ዘንድ በምትኩ ተቀባይነት ያገኛል። … በመሠዊያውም አጠገብ በሰሜን ወገን በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል” (ዘሌ. 1፡4፣11)። ኃጢያተኛው የሚሰዋውን እንስሳ በአደባባዩ በር ሲያመጣ ካህኑ ቢላና ሳህን ይሰጠዋል። ኃጢያተኛውም እጁን በእንስሳው ራስ ላይ በማድረግ ኃጢያቱን ይናዘዛል። ይህም ከኃጢያተኛው ወደ እንስሳው ኃጢያትን የማስተላለፍ ተምሣሌት ነው። በዚህ ጊዜ ኃጢያተኛው ንጹህ ሆኖ እንስሳው ተጠያቂ በደለኛ ሆኖ ይቆጠራል። አሁን በምሣሌያዊ አነጋገር እንስሳው በደለኛ ስለሆነ የኃጢያትን ዋጋ መክፈል አለበት፤ ይህም ሞት ነው። ስለዚህ ኃጢያተኛው በገዛ እጁ እንስሳውን በማረድ የእርሡን ኃጢያት ንጹህና ምንም በማያውቀውን እንሰሳ ላይ በመጫን ይገድለዋል። ይህንን አሰቃቂ ድርጊት በመፈጸም ኃጢያተኛው የእርሱ ኃጢአት እንዴት ንጹሁን መሲሕ እንደሚገድል በተግባር በዓይኑ እያየ ይማራል።
10. በመላው ሕዝብ ስም የእንስሳ መስዋዕት ሲቀርብ በሚፈሰው ደም ካህኑ ምንድነው የሚያደርገው? ምንንስ ያመላክታል?
“የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣል። ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመጋረጃው ፊት ለፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል” (ዘሌ. 4፡16፣17)። መስዋዕት ለህዝቡ (ለጉባኤው) ሁሉ ሲቀርብ የመድኃኒዓለም ተምሳሌት የሆነው ካህኑ ደሙን ወደ መቅደሱ በመውሰድ ቅዱሱንና ቅድስት ቅዱሣኑን በሚከፍለው መጋረጃ ላይ ይረጨዋል (ዕብ. 3፡1)። ስለዚህ በምሣሌያዊ አሠራር የህዝቡ ኃጢያት ከህዝቡ ወደ ቤተ መቅደሱ ተላለፈ ማለት ነው። ይህ ካህኑ የሚፈጽመው የደም አገልግሎት ክርስቶስ ስለ እኛ በሰማይ የሚያደርገውን አገልግሎት አስቀድሞ አመላካች ነው። ክርስቶስ በመስቀል ላይ የመስዋዕትነቱን ሞት ከሞተ በኋላ በትንሣኤ በመነሳት ሊቀካህናችን በመሆን ደሙን ይዞ ወደ ሰማያዊው ቤተመቅደስ ገብቷል (ዕብ. 9፡11፣12)። በምድር ባለው ቤተመቅደስ በካህኑ አማካኝነት የሚፈጸመው ይህ የደም አገልግሎት ጌታችንና መድኃኒታችን በሰማይ ቤተመቅደስ በእኛ የኃጢአት መዝገብ ላይ ደሙን በማድረግ የተናዘዝንባቸው ኃጢአቶች በሙሉ ይቅር መባላቸውን የሚያረጋግጥበት አገልግሎት ተምሳሌት ነው (1ዮሐ. 1፤9)።
11. ከቤተመቅደሱ አገልግሎት አንጻር ጌታችን ክርስቶስ የሚጠቀስባቸው ሁለት ዋና አገልግሎት የትኞቹ ናቸው? እነዚህ አገልግሎቶች እኛን የሚጠቅሙት እንዴት ነው?
“ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዷልና” (1ቆሮ. 5፡7)። “እንግዲህ ወደ ሰማያት ያረገ ታላቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፣ እምነታችንን አጥብቀን እንያዝ። በድካማችን የማይራራልን ሊቀ ካህናት የለንምና፤ ነገር ግን እንደ እኛ በማንኛውም ነገር የተፈተነ ሊቀ ካህናት አለን፤ ይሁን እንጂ ምንም ኀጢአት አልሠራም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበልና በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ፣ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ” (ዕብ. 4፡14-16)።
በሰማያዊው ቤተመቅደስ አገልግሎት ጌታችንና መድኃኒታችን የኃጢያታችን መስዋዕትና ሊቀካህናችን በመሆን ያገለግለናል። የእኛ ምትክና የመስዋዕት በግ በመሆንና በሰማይ የማያቋርጥ የክህንነት አገልግሎት በማድረግ ኢየሱስ ሁለት አስደናቂ ተግባራትን ለኛ ይፈፅማል።
ሀ. ያለፈው ኃጢያታችን በሙሉ ይቅር የተባለበትና አዲስ ፍጥረት የምንባልበትን ሙሉ ለሙሉ የህይወት ለውጥ በመስጠት፤ (ዮሐ. 3፡3-6፣ ሮሜ 3፡25)፤
ለ. አሁንም ሆነ ወደፊትም በጽድቅ ለመኖር የምንችልበትን ኃይል በመስጠት፤ (ቲቶ 2፡14፣ ፊሊ. 2፡13)፤
እነዚህ ሁለት አስደናቂ ተዓምራት አንድን ሰው ፃድቅ የሚያደርጉት ናቸው፤ ይህም ደግሞ በአንድ ሰውና በእግዚአብሔር መካከል ትክክለኛው ወዳጅነት ሲኖር የሚከሰት ነው፤ ጽድቅ ማለትም ትርጉሙ ይኸው ነው – ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ወዳጅነት መመሥረት። ማንም ሰው በራሱ ሥራ (በራሱ ጥረት) በምንም መልኩ ፃድቅ የሚሆንበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም። ምክንያቱም ጽድቅ ኢየሱስ ብቻ ሊፈጽመው በሚችል ተዓምር የሚገኝ ስለሆነ ነው (የሐዋ. 4፡12)። አንድ ግለሰብ ፅድቅን የሚያገኘው ራሱ መፈፀም የማይችለውን አዳኙ እንዲፈፅምለት ሲያምን ብቻ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱሳችን “በእምነት መፅደቅ (ፅድቅ በእምነት)” በማለት የሚጠራው ይህንኑ ነው። መድኃኒዓለምን የህይወታችን ጌታ እንዲሆን ስንጠይቀው የሚያስፈልገውን ተዓምር በህይወታችን እንዲፈፅም ከርሱ ጋር ሙሉ በሙሉ እየተባበርን መሆናችንን እናሳያለን። ይህ ለእኛና በእኛ ውስጥ በክርስቶስ የሚፈፀመው ተዓምር ብቻ ነው እውነተኛ ጽድቅ የሚባለው። ከዚህ ውጪ ያለው ሁሉ የማስመሰል ሥራ ነው።
12. አንዴ ፀድቀናል ብለን “ጌታ ሆይ” እያልን መኖር ሰማይ አያደርሰንም?
“በሰማይ ያለውን ያባቴን ፈቃድ ሳይፈጽም ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም። በዚያ ቀን ብዙዎች፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህ አጋንንት አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ታምራት አላደረግንምን?’ ይሉኛል። በዚያ ጊዜ፣ ‘ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንት ክፉዎች፤ ከእኔ ራቁ’ ብዬ በግልጽ እነግራቸዋለሁ” (ማቴ.7፡21-23)። ጌታችን እዚህ ጥቅስ ላይ እንደተናገረው የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸም ያስፈልገናል። በዘመነ ብሉይ አንድ ሰው ኃጢያት ሲሠራ አንድ ጠቦት በግ ቤተመቅደሱ ድረስ ይዞ በመምጣት ኃጢያቱን ተናዝዞ ሲያርደው ላደረሰው ጥፋት ማዘኑን የሚያሳይበትና ከልቡ ጌታ ሕይወቱን እንዲመራ የሚፈልግ መሆኑን የሚናገርበት መንገድ ነው። ባለንበት ዘመን እንስሳትን ባናቀርብም ራሳችንን በየዕለቱ በመስቀሉ ላይ መሰዋት አለብን (1ቆሮ. 15፡31)። ክርስቲያን የክርስቶስን ምሳሌነት መከተል አለበት (1ጴጥ. 2፡21)። ይህ ሲሆን እጅግ ኃያል የሆነው የጌታችን ደም እኛን ጻድቅ የማድረግ ተዓምራቱን ይሠራል (ዕብ. 13፡12)፤ ይህ የሚሆነው ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ህይወታችንን እንዲቆጣጠር በፈቃደኝነት ስንሰጠውና አንዳንድ ጊዜ መንገዱ አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳን በሚመራን ሁሉ ስንከተለው ነው።
13. የሥርየት ቀን የሚባለው ምንድን ነው?
ሀ. በእስራኤል በዓመት አንድ ጊዜ እጅግ የተለየ ቀን ፍርድ ሥርዓት ይከናወን ነበር፤ ይህም የሥርየት ቀን ይባላል (ዘሌ. 23፡27)። በዚህ ቀን ሁሉም ሰው ኃጢያቱን እንዲናዘዝ ይጠበቅበታል። ይህንን ለመፈፀም እምቢ ያለ ለዘላለም ከእስራኤል ጉባዔ ይወገድ ነበር (ዘሌ. 23፡29)።
ለ. በዕለቱ ሁለት ፍየሎች ይመረጣሉ፤ አንዱ ጌታን የሚወክል ሲሆን ሁለተኛው የአዛዜል (የሚለቀቅ) ፍየል የሚባል ነበር። የጌታ ፍየል ተብሎ የተለየው ለህዝቡ የኃጢያት መስዋዕት በመሆን ይቀርባል (ዘሌ. 16፡9)። ሊቀካህኑም ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ በመግባት “የጌታ” የተባለውን ፍየል ደም በታቦቱ ላይ ባለው ሥርየት መክደኛ ላይ ይረጫል (ዘሌ. 16፡14)። ሊቀ ካህኑ በምኅረት መክደኛው ላይ የሚታየውን የእግዚአብሔርን ክብር ለመገናኘት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚገባው በዓመት አንዴ በዚህ የተለየ በተባለ የሥርየት ቀን ብቻ ነበር ።
ጉዳዩን ጠቅለል ባለ ሁኔታ ስናጤነው፤ በየዕለቱ ኑሯቸው እስራኤላውያን ለሚሠሩት ኃጢአት የሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ መስዋዕቱን የሚያርደው ራሱ ኃጢአተኛው እጁን በመስዋዕቱ ራስ ላይ በመጫን ሲሆን ይህም የእርሱን ኃጢአት ወደ እንስሳው እንዲተላለፍ ያደርጋል፤ የታረደውን እንስሳ ደም ካህኑ ወደ ቤተመቅደሱ ይዞ በመግባት ቅዱሱንና ቅድስተ ቅዱሳኑን በሚከፍለው መጋረጃ ላይ ይረጨዋል፤ ይህ ሒደት የግለሰቡን ኃጢአት ከእንስሳው ወደ ቤተመቅደሱ እንዲተላለፍ ያደርጋል፤ ይህ ሥርዓት በየዕለቱ ዓመቱን በሙሉ ሲከናወን ቆይቶ የሥርየት ቀን በሚባለው ዕለት ወደ ቤተመቅደሱ ሲተላለፍ የነበረው ኃጢአት የሚነጻበት ቀን ይሆናል፤ የዚያን ዕለት ሥነሥርዓት የሚያከናውነው ሊቀካህኑ ሲሆን በመጀመሪያ ለራሱና ለቤተሰቡ መስዋዕት በማቅረብ ራሱን ንጹህ ያደርጋል፤ ከዚያም “ለጌታ” የተባለውን ፍየል በማረድ በደሙ ዓመቱን በሙሉ በቤተመቅደሱ የተጠራቀመውን ኃጢአት ያነጻል፤ ይህ “ለጌታ” የተባለው ፍየል እጅ ተጭኖ ኃጢአት የሚናዘዙበት አይደለም፤ ስለዚህ ደሙ ወደ ቤተመቅደሱ ዓመቱን በሙሉ ሲተላለፍ የነበረውን ኃጢአት ለማንጻት የሚውል ነው፤ ሊቀካህኑ “የጌታ” በተባለው ፍየል ደም የቤተመቅደሱን ኃጢአት በሙሉ ሲያነጻ ኃጢአቱ በሙሉ ከቤተመቅደሱ ወደ እርሱ ይተላለፋል፤ በዚህ ወቅት ቤተመቅደሱ ሲነጻ ሊቀካህኑ ደግሞ ዓመቱን በሙሉ በቤተመቅደሱ የተከማቸውን ኃጢአት የሚሸከም ይሆናል፤ ከዚያም እርሱ የተሸከመውን ኃጢአት ከቤተመቅደሱ ይዞ በመውጣት ለሚለቀቅ ወይም የአዛዜል በተባለው ፍየል ላይ ይጭንበታል፤ ፍየሉም ወደ በረሃ ተወስዶ ይለቀቃል (ዘሌ. 16፡16፣ 20-22)። በዚህ ሁኔታ ዓመቱን በሙሉ የተጠራቀመው ኃጢአት ይነጻል፤ መጋረጃውም ይቀየራል፤ ባዲሱ ዓመት በየዕለቱ የሚደረገው የኃጢአት መስዋዕት ይቀጥላል።
14. እንደ ሌሎቹ የቤተመቅደስ ሥርዓቶች የሥርየት ቀን በመዳን ሂደት ውስጥ የሚያመላክተው ምንድነው?
“እንግዲህ በሰማያት ያሉትን የሚመስለው ነገር በዚህ ሊነፃ እንጂ በሰማያት ያሉት ራሳቸው ከእርሱ ይልቅ በሚበልጥ መስዋዕት ሊነጹ የግድ ነበር” (ዕብ. 9፡23)። በምድራዊው ቤተመቅደስ ይካሄድ የነበረው የሥርየት ቀን አገልግሎት በሰማይ በእውነተኛው ሊቀካህን በመድኃኒዓለም የሚካሄድና ኃጢያትን የማስወገድ ሥራ የሚያመለክት ነው። በዚህ ወቅት አምላካቸውን ለዘላለም ለማገልገል በመምረጥ ስማቸው በህይወት መዝገብ የተፃፉትን ክርስቶስ ውሣኔያቸውን በማጽናት በደሙ ያትምበታል። ይህ ሥርዓት የተለየ ቀን በመሆን ለእስራኤላውያን የፍርድ ቀን እንደነበር የምድር ነዋሪዎችን በተመለከተ አሁን በሰማይ የሚከናወነው ሥርዓትም የዚህችን ምድር የመንጻት ሁኔታ የሚያመላክት የፍርድ አሠራር ይሆናል። በእስራኤላውያን ዘመን በዓመት አንዴ ከሚካሄደው የሥርየት ቀን ሥርዓት በመነሳት ታማኙ ሊቀ ካህናችን ክርስቶስ በፈሰሰው ደሙ አማካኝነት በሰማይ የሚማልድልንና ኃጢያታችን ሁሉ የሚያስወገድ መሆኑን እንድናምን ይጠብቀናል። የመጨረሻው የሥርየት ቀን ወደ መጨረሻው የፍርድ ቀን ያመራል፤ የኃጢያትም ጉዳይ በእያንዳንዱ ግለሰብ ሕይወት ጭምር ውሳኔ ያገኛል። ውሳኔውም ወደ ሕይወት ወይም ወደ ሞት ይሆናል።
15. ዛሬ የቤተ መቅደስ ሥርዓት የማናካሂደው ለምንድን ነው?
“እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፤ አካሉ ግን ክርስቶስ ነው” (ቆላ. 2፤17)። “እንግዲህ በሰማያት ያሉትን የሚመስለው ነገር በዚህ ሊነፃ እንጂ በሰማያት ያሉት ራሳቸው ከእርሱ ይልቅ በሚበልጥ መሥዋዕት ሊነጹ የግድ ነበረ፤ ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች የእውነተኛይቱ ምሣሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባምና ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርሷ ወደ ሰማይ ገባ” (ዕብ. 9፡23-28)።
በእስራኤላውያን የቤተመቅደስ ሥርዓት በዝርዝር እንደተመለከተነው መዳንን አስመልክቶ የሚካሄዱት ሥርዓቶች በሙሉ ጌታችንና መድኃኒታችን በምሥጢረ ሥጋዌ ተገልጾ በዚህ ምድር በመስዋዕትነት ከሚፈጽመው ጀምሮ በሰማይ ዕርገቱ የሚቀጥለውና እስከ ዳግም ምፅዓቱ የሚዘልቅ ነው። ስለሆነም የምድሩ ቤተመቅደስ አገልግሎት በሙሉ መሲሕ ክርስቶስን አመላካች ጥላ ነበር እንጂ ዋናው (እውነተኛው) አልነበረም። ክርስቶስ ወደዚህ ምድር መጥቶ በቤተመቅደሱ የእግዚአብሔር ዕቅድ አመላካች የሆነውን ተግባር ሁሉ ከፈጸመ በኋላ ያንኑ ሥርዓት መልሶ ማድረግ ጌታችን ወደዚህ ምድር መጥቶ የከፈለውን መስዋዕት አለመቀበል ነው። ከዚህ በተጨማሪም በክርስቶስ በሥጋ ተገልጾ ያጠናቀቀውንና የፈጸመውን ሥርዓት በአሁኑ ጊዜ በመከተል “እንደገና ይፈፅማል” ብለን ያንኑ ሥርዓት መጠበቅ አስፈላጊነት የለውም። ነገር ግን ሥርዓቱን በማጥናት የመዳንን ምሥጢርና አስደናቂነት አስመልክቶ ጥልቅ ትምህርት ማግኘት እንችላለን።
የተወደዱ አንባቢ፤ መጽሐፍ ቅዱሳችን በክርስቶስ አማካኝነት ስላገኘነው የፅድቅ ተስፋዎች የሚከተለውን ይላል፡- መድኃኒዓለም ያለፉትን ኃጢአቶቻችን ሁሉ ይቅር በማለት ከበደል ሁሉ ንፁህ ያደርገናል (ኢሳ.44፡22፤ 1ዮሐ.1፡9)፤ ስንፈጠር ወደነበረን ክብር በመመለስ የእርሱን “መልክ” እንድንመስል ያደርገናል (ሮሜ8፡29)፤ ጌታችንና መድኃኒታችን የፅድቅን ነገር ሁሉ እንድንመኝና እንድንፈጽም የምንችልበትን ኃይል ይሰጠናል (ፊሊ.2፡13)፤ እግዚአብሔርን የሚያስደስቱ ነገሮችን ብቻ እንድናደርግ በተዓምራዊ ኃይሉ ያስችለናል (ዕብ.13፡20፣21፤ ዮሐ.15፡11)፤ እርሱ አንዳች በኃጢአት ያልጎደፈ ህይወት በመኖር የፈፀመውን ፅድቅ ለእኛ በመቁጠር ከዘላለም ሞት ኩነኔ ነጻ አውጥቶናል (2ቆሮ.5፡21)፤ እስከ ዳግም ምፅዓቱ ደግሞ “ነውር የሌለን” አድርጎ ሊያኖረን ይችላል (ፊሊ.1፡6፤ ይሁዳ 24)። እነዚህን አስደናቂና የታመኑ ተስፋዎች እንዲቀበሉ ጥሪ ለሚያደርግልዎት አምላክ የሚሰጡት ምላሽ ምንድነው?
ቅንብር፤ ዘውዱ ሰብለወርቅ